የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከነሐሴ 16 - ነሐሴ 22

9ኛ ትምህርት

Aug 22 - Aug 28
ድል አድራጊ ስሜትን ማጎልበትሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ትምህርት የሚጠኑ:ዮሐንስ 4:27–30፣ 39–42፤ማቴ. 15:21–28፤2 ተሰ.. 1:1–4፤ሮሜ. 15:7፤ኤፌ. 4:32፤1 ጴጥ. 3:15።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡‹‹ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤››(1 ጴጥ 3:15, አ.መ.ት.).

ይ በልጥ የኢየሱስን ህይወት ባጠናን ቁጥር፥ እርሱ እንዴት አድርጎ ሰዎችን እንደተቀበለ እና እንዳበረታታ በማየት እንገረማለን። ምንም እንኳን በጊዜው ለነበሩት የኃይማኖት መሪዎች የሚቆረቁራቸውን ነቀፋ የነቀፋቸው ቢሆንም፥ ከኃጢዓት ጋር ትግል የገጠሙትን፣ የበደል መቅሰፍት የመታቸውን፣ እና ተስፋ ቢስ በሚያደርግ ኩነኔ ውስጥ የሚገኙትን በደስታ ነበር የተቀበለው። እርሱ ጸጋውን የሰጠው ለእነርሱ ነበር። ምህረቱም እጅግ ለከፉት ኃጢዓተኞች ድረስ ርቆ የተዘረጋ ነበር። የእርሱ ይቅርታ ጥልቀት ከኃጢዓታቸውም በላይ ልቆ የማይለካ ጥልቅ ነው። ለፍቅሩም ወሰን የለውም።

ኢየሱስ ምንም ዓይነት የኩራት ወይም የበላይነት ነገር አላሳየም። እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠረ፣ ግን በኃጢዓት እንደወደቀ እና እርሱም ሊያድነው እንደመጣለት አድርጎ ነበር የሚመለከት የነበረው። ከእርሱ ፍቅር የሚያመልጥ ማንም የለም። የእርሱ ጸጋ እስከማይደርስበት ድረስ ዝቅ ብሎ የወደቀ የለም።ለተገናኛቸው ሁሉ የሚገባቸውን ያህል የሰብዓዊነት ክብር በማሳየት ያስተናግድ ነበር።እርሱ በሰዎች ዕምነት ስለነበረው ወደ መንግስቱ ለማምጣት ተጽዕኖ ሲፈጥር ነበር። ህይወታቸውም በእርሱ መገኘት እንዲለወጥ ያደረገው ለእነርሱ እጅግ ግድ ይለው ስለነበረ ነው። እነርሱም እንዲሆኑ የፈለገባቸውን ያህል ደርሰው ተገኙ።

በዚህ ሣምንት ትምህርት፥ ለሰዎች ኢየሱስ ያለውን አመለካከት ጠለቅ ብለን በመመልከት፥ እነዚህን መርሆዎች እኛ በራሳችን እንዴት እንደምንተገብራቸው እንመራመራለን። *የዚህን ሣምንት ትምህርት ለነሐሴ 22/ 2012 ሰንበት በማጥናት ይዘጋጁ።

ነሐሴ 17
Aug 23

7 የወንጌል አቀባበል


በዮሐንስ 4:27–30፣ 39–42 ያለውን ያንብቡ። ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ኢየሱስ ያደረገው ንግግር ሁሉም ዓይነት ሰዎች፥ ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ጭምር፥ ለወንጌል ክፍት ስለመሆናቸው ዕውነታውን የሚያሳየው እንዴት ነው?ደቀመዛሙርት ለወንጌል ልባቸውን የከፈቱ ሰዎች ይገኛሉ ብለው ከሚጠብቋቸው ዝርዝር የማይገባው ስፍራ ሠማርያ ነበር።ሠማርያውያን ከአስተምህሮ እና ከአምልኮ ጋር በተገናኘ ከአይሁዶች ጋር የማያቋረጥ ተቃርኖ ውስጥ ነበሩ። ይህ ባላንጣነት ደግሞ ለአስርት ዓመታት የቆየ ነበር። ሠማርያውያን በኢየሩሳሌም በሚገነባው መቅደስ ስራ ላይ ለመሳተፍ ይፈልጉ ነበር፥ ግን በዙሪያቸው ካሉት አህዛብ ባህል ጋር ያላቸው የተጣመረ ቁርኝት እንዲሁም ከተደባለቀው ዕውነታቸው የተነሣ እንቢተኛ ሆነውበታል። ከዚህም የተነሣ፥ ሠማርያውያን በገሪዚም ተራራ ላይ መቅደስን ሠሩ። ደቀመዛሙርትም ቢሆኑ ወንጌልን ለማወጅ የማይመች ያልለማ መሬት አድርገው ሠማርያን ዘልለው ያልፉ ነበር።

ለደቀመዛሙርት ያልታያቸው ነገር ለኢየሱስ ታይቶት ነበር፡ ክፍት የሆነው ልባቸው።ዮሐንስ በውሃው ጉድጓድ አጠገብ የነበረችውን ሴት የተረከበት መንገድ ሲጀምር እነዚህን ሦስት ቃላት ይጠቀማል፡ ‹‹ጌታም ይህን እንዳወቀ ይሁዳን ለቆ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ።በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት።›› (ዮሐ. 4:3-4) በዚያ ባልተለመደ ስፍራ የተዘጋጀ ልብ እንደሚኖር መንፈስ ቅዱስ ስላሳመነው ኢየሱስ በሰማርያ አልፎ መሔድ ‹‹ግድ ሆነበት።›› ዓይኖቻችን በመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ቅባት ሲቀቡ፥ ሌሎች የማይቻሉ ነገሮችን በሚያዩባቸው አጋጣሚዎች እንኳን የሚቻሉ ነገሮችን እናያለን።ሌሎች ምድረ በዳ በሚያዩባቸው ቦታዎች እንኳን ለእግዚአብሔር መንግስት የለመለመን መኸር እናያለን። ሐዋርያት ሥራ 8:4፣ 5፣ 14ን ያንብቡ።ኢየሱስ በሰማርያ የፈጸመው አገልግሎት የመጨረሻ ውጤት ምን ሆነ?ደቀመዛሙርትም ቢሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ዕድሉን እንኳን ለሠማርያውያን ሳይሰጧቸው በሠማርያ በኩል አቋርጠው ያልፉ ነበር። ኢየሱስ ግን ለእነርሱ ያልታያቸውን ነገር አየ።መንፈስ ቅዱስ በአንዲት ሴት ልብ ውስጥ ተቀባይነትን እንዳስቀመጠ ኢየሱስ ተገነዘበ። አስደናቂ የሆነው የእርስዋ መለወጥ በከተማዋ ባሉት ሰዎች ሁሉ ላይ ተጽዕኖን ፈጠረ። ከምስክርነታችን ወዲያውኑ ምላሽ አናገኝም ይሆናል፥ ዳሩ ግን ለመቀበል በተዘጋጁ ልቦች ውስጥ ዘሮችን ስንዘራ ሣለ፥ አንድ ቀን ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆኑ መኸር ሆነው ይገኛሉ።

የቃላቶቻችንን ተጽዕኖ እና የሌሎች ድርጊት ውጤት፥ መልካም ይሁን ክፉ፥ በእርግጠኝነት ለማወቅ አንችልም። ስለዚህ፥ ሌሎች ባሉበት ስለምንናገረው እና ስለምናደርገው ድርጊት ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድነው?

ነሐሴ 18
Aug 24

8 የአመለካከት ማስተካከያ


ብዙ ጊዜ አመለካከታችን በሌሎች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር አቅማችን ላይ የራሱ ጫና አለው። ግልፍተኛ፣ ነቃፊ እና ባዕድነት የሚታይበት አመለካከት ካሳየን ሰዎችን ከእኛ እንዲሸሹ እናደርጋለን፤ ምንም እንኳን ለመመስከር የሚችሉ ቢሆን፥ እርስዎ የሚናገሩት ቃል፥ የቱንም ያህል ዕውነትን የተሞላ ቢሆን፥ ተቀባይነት ለማግኘት ዕድሉ በጣም ያነሰ ነው።

ስናነጻጽረው፥ አወንታዊ አመለካከት እና ዕምነት በሌሎች ላይ ሲኖረን እነርሱን ወደ እኛ ይስባል።የወዳጅነት ቁርኝትን ይፈጥራል። ኢየሱስ ይህንን መርህ ያስቀመጠበት ዘዴ ውብ ነው፥ እንዲህ ብሎ ነበር፡ ‹‹ከእንግዲህ አገልጋዮች አልላችሁም፤ አገልጋይ ጌታው የሚሠራውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጽሁላችሁ ወዳጆች ብያችኋለሁ።›› (ዮሐ. 15:15) ወዳጆች ድክመት እና ስህተት ቢኖርም እንኳን እርስ በእርስ ይረዳዳሉ ደግሞም ደስታ እና ሐዘንንም በነጻነት ይካፈላሉ። ማቴዎስ 15:21–28 እና ማርቆስ 14:6–9 ላይ የተጻፉትን ያንብቡ።

እነዚህ ጽሑፎች በጣም በሰፊው የተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ስለሚገኙ ሴቶች ያብራሩልናል።ኢየሱስም ለአንደኛዋ በጣም ግልፍተኛ ሲመስል በሌላዋ ዘንድ ደግሞ እርጋታ ይታይበታል። ከዚህ ምንባብ ላይ ኢየሱስ በሰፊ ጸጋው እያንዳንዳቸውን ለመድረስ ስለመሞከሩ እና ዕምነታቸውን እየገነባው እንደነበረ በምን ምልክት እናውቃለን?በማቴዎስ ወንጌል 15 ላይ የምናገኛት ሴት ከነዓናዊት ናት። ኢየሱስ በመጀመሪያ ላይ ጥያቄዋን ሆን ብሎ እንቢ ሲላት፥ ተግታ በጠየቀችው ቁጥር ዕምነትዋ እንዲጎለብት ነበር። በሒደትም የፈለገችውን አድርጎላት በማስከተልም በይሁዳ ምድር የሚገኝ የትኛውም የኃይማኖት መሪ ለአንዲት ምስኪን ከነዓናዊት የማይናገረውን አስደናቂ ዐረፍተ ነገር ተናገረ። በይፋ እንዲህ አለ፡ ‹‹አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው …›› (ማቴ. 15:28)።የትኛውም የኃይማኖት መሪ ሊሰጠው ከሚችለው የሚበልጥ ትልቅ አድናቆትን ሰጣት።እንደው የእርስዋ ልብ ምን ያህል እንደተደሰተ እና ህይወትዋስ ምን ያህል እንደተለወጠ ለመሳል ይሞክራሉ?

የኢየሱስን እግር ውድ በሆነ ሽቶ የቀባችው ሴት መልካም ስም ያልነበራት አይሁዳዊት ሴት ነበረች፥ ብዙ ጊዜ ኃጢዓትን የምትሰራ እና ክፉኛ የወደቀች ሴት ብትሆንም፥ ይቅር የተባለች፣ የተለወጠች እና እንደገና አዲስነትን ያገኘች ነበረች። ሌሎች እርስዋን በኮነኗት ጊዜ፥ ኢየሱስ አድናቆቱን በመግለጽ ድርጊትዋን ተቀበለው።እንደውም እንዲህ አወጀላት፡ ‹‹ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።››(ማር. 14:9)።

ከላይ ባነበብናቸው ሁለት ታሪኮች ውስጥ፥ የአዎንታዊ ድል አድራጊ ስሜት ጠቃሚ ፈርጆች ምን ምን ናቸው? ለምስክርነት ብቻ ሳይሆን፥ በህይወትዎ አጠቃላይ እንዲጠቀሙበት እርስዎ የሚያስፈልግዎት የባህርይ ማስተካከያ ምን ዓይነት ነው?

ነሐሴ 19
Aug 25

9 ዕውነትን በፍቅር መናገር


ወዳጅነት ብቻውን ሰዎችን ለክርስቶስ አይማርክም።በርካታ ወዳጆች፣ አብረናቸው መሆን የሚያስደስተን እና ከእኛ ጋር አብረው መሆን የሚወድዱ ሊኖሩን ቢችሉም፥ ምናልባት ለእኛ ኢየሱስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም እንዴት ህይወታችንን እንደለወጠው ብንነግራቸው ወዳጅነታችንም የዘለዓለማዊ ህይወት ለውጥን ሊያስገኝ ይችላል። እርግጥ ነው፥ እኛን በአጠገባቸው ማድረጋቸው ሊያስደስታቸውም ቢችል፥ እግዚአብሔር ደግሞ እኛን የጠራን ለሌሎች መዝናኛ ብቻ እንድንሆን አይደለም።ወዳጅነት ብቻውን ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ባያመጣም፥ ባዕድነት በራሱ ሰዎችን ከክርስቶስ ያሸሻል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣›› (ኤፌ. 4:15) እንድናስተምር አሳስቦናል። ወዳጅነትና መልካም የሆነው ጥምረት የሚገነባው ከሰዎች ጋር በምንችለው አቅም ሁሉ የምንስማማ ሲሆን፣ ተቀባይነትን ስናሳይ፣ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ አድናቆታችንን ስናሳይ ነው። እስቲ ስለ ሰዎች ከክፋታቸው ይልቅ መልካምነታቸውን አጉልተን ማየትን ልምድ እናድርግ። 2ኛተሰሎንቄ 1:1–4 ላይ ያለውን እናንብቡ። ጳውሎስ የተሰሎንቄ ሰዎችን የሚያደንቅላቸውን ጥቂት ቀጥተኛ ነገሮች እስቲ እንዘርዝር።በሌሎች ላይ የሚያዩትን ክፉ ነገር በመሰርሰር የሚደሰቱ አንዳንድ ሰዎች አሉ። የሆነ ሰው በትክክል ያልሰራውን ነገር ነቅሶ ማውጣት ሐሴትን ያስገኝላቸዋል፤ ምክንያት ባይኖራቸው እንኳን ይህንን ማድረጋቸው ከሌላው የተሻሉ ሆነው እንዲሰማቸው ስለሚያደርጋቸው ይመስላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። እርሱ ያገለገለባቸውን አብያተ ክርስቲያናት ክፉ ነገር ያይባቸው ነበር። እርግጥ ለመናገር፥ ስህተትን የማይቀበል የነበረ ሲሆን፥ ኃጢዓትንም በግልጽ ይኮንን ነበር ቢሆንም፥ ትኩረቱ የነበረው የገነባውን ቤተክርስቲያን በማጎልበት ላይ ነበር። ይህንን ያደርግ የነበረበት አንደኛው ዘዴ እነርሱ ትክክለኛ የሆኑባቸውን አጋጣሚዎች በማጉላት ነበር። ኤለን ጂ ኋይት ስለ አወንታዊ የሆኑ ግንኙነቶች የተናገረችው ዐረፍተ ነገር በጣም የሚደነቅ ነው። ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ዝቅ ብናደርግ፥ እና ቸር እንዲሁም ትሁት እና ገር ልብ ያለን ርህሩሆች ብንሆን ኖሮ፥ አሁን ላይ አንድ ብቻ ለቆመለት ዕውነት የሚቆሙ አንድ መቶ የተለወጡ ሰዎች ይኖሩ ነበር።››—የቤተክርስቲያን ምክሮች፣ዕትም 9፣ ገጽ 189 (በእንግሊዝኛው)

ከላይ ስለቀረበው ዐረፍተ ነገር እስቲ ጊዜ ወስደው ያሰላስሉ። ቤተክርስቲያን ምናልባት ቸር፣ ትሁት፣ ገር ልብ ያላቸው፣ እና ርህሩህነት ከልባቸው የሚፈልቅባቸው አባላት ቢኖሯት ምን መልክ ይኖራታል? እንዲህ ዓይነትዋ ቤተክርስቲያን ምን ትመስል ነበር? እስቲ ወደራስዎ ልብ ይመልከቱ እና በዚህ ረገድ እርስዎ ሊያስተካክሉት የሚችሉት ነገር ይኖር ይሆን?

ነሐሴ 20
Aug 26

የተቀባይነት መሠረት


በሮሜ 5:7 እና ኤፌሶን 4:32 የሰፈረውን ያንብቡ። ሁሉን መቀበል የሚባለውን መሠረት እንዴት ትገለጹታላችሁ? ተቀባይነት የሚታይበት አመለካከት በምን ይመሠረታል?በእነዚህ ሁለት ምንባቦች ጳውሎስ አንዱ ለአንዱ ማሳየት ያለበትን ቅቡልነት እንደመሠረት አድርጎ ያቀርብልናል።ክርስቶስ እያንዳንዳችንን በይቅርታ የተቀበለን ሆኖ ሣለ፥ እርስ በእርስ ይቅርታ ለማድረግ እና ለመቀባበል እንቢተኛ ልንሆን እንችላለን? እርግጥ ለመናገር፥ ኢየሱስ የተቀበለን በመሆኑ ብቻ ነው እርስ በእርስ ልንቀባበል የምንችለው፥ ሌሎች እንከኖቻችን እያሉም ቢሆን እንኳን። ይህ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል በጥልቀት አስቡበት። ስለራሳችሁ እና ስለአንዳንድ ያደረጋችኋቸው እንዲሁም አሁን ድረስ ትግል ስለሆኑባችሁ ነገሮችም አስቡ፥ ምናልባትም ሌሎች ቢያውቋቸው ሊያስደነግጡ የሚችሉ እርስዎ ብቻ የሚያውቋቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

እና ግን ምን ሆነ? ሌሎች የማያውቁትን ነገሮችዎን የሚያውቀው ክርስቶስ በዕምነት ተቀበለዎት። አዎን፥ እርሱ ሁሉንም ያውቃል፣ ሆኖም ግን፥ ይቀበልዎታል፤ እርስዎ መልካምነትዎ ስለበዛ ሳይሆን፥ ከራሱ የተነሣ። እናስ ታዲያ፥ ለሌሎች የምናሳየው አመለካከት ምን መሆን አለበት? አንዳንዶች ለመገንዘብ የሚቸገሩት እሳቤ እዚህ ላይ ይገኛል። ከሙሉ ልብ መቀበል የሚባለው ሰዎችን ከነማንነታቸው መቀበል ነው፤ ኃጢዓተኛ ልማድ እያላቸውም ቢሆን እንኳን፥ ሰዎች በእግዚአብሔር አምሳያ የተፈጠሩ ናቸውና። ክርስቶስ ለእኛ የሞተልን ‹‹ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ›› ሞቶልናልና ‹‹የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣›› ሌሎችንም ይቅር ማለት እና መቀበል እንችላለን። ለእኛ ያሳየው ፍቅር ለሌሎች የምናሳየው ተቀባይነት እና ይቅርታ ሁነኛው መሠረት ነው። (ሮሜ. 5:6–10)።

ዳሩ ግን፣ አንድ ጊዜ ቅቡልነት ያለበት፣ እንክብካቤ የተሞላ ግንኙነት ከተመሠረተ፥ ሌላኛውን ግለሰብ በፍቅር የቅዱስ ቃሉ ዕውነት መጋፈጥ ሁልጊዜ አስፈላጊ ነው። ይህንን ሳናደርግ ብንቀር ያለማፍቀር ያክል ነው። ወዳጆች እስከሆንን ድረስ፥ ህይወትን የሚለውጥ፣ ዘለዓለማዊ ህይወትን ከወዳጆቻችን ጋር ለመጋራትም ግድ ሊለን ይገባል። የኢየሱስ አስተያየት ‹‹ደስ ያላችሁን አድርጉ፣ እኔ እንደሆነ እቀበላችኋለሁ›› የሚል አይደለም።ይልቁንም የእርሱ አመለካከት የነበረው፥‹‹የሰራችሁት ነገር ምንም ቢሆን ምን፥ ይቅር ለማለት እና ለመለወጥ የሚያስችል ጉልበት ለመስጠት ፍቃደኛ ነኝ።›› የሚል ነው።

በክርስቶስ መንፈስ በትህትና የሚቀርብ መንፈሳዊ የሆነ ዕውነት በፍቅር አመለካከት እስከሆነ ድረስ ልቦችን ይረታል እንዲሁም ህይወትን ይቀይራል። የአንድን ግለሰበብ ኃጢዓተኛ ባህርይ ሳንቀበል ግለሰቡን ብቻ መቀበል የምንችለው እንዴት ነው? ኃጢዓትን ሳንታገስ እና ሳናበረታታ አንድን ሰው መቀበል ምንችለው እንዴት ነው?

ነሐሴ 21
Aug 27

በፍቅር የተነገረ ዕውነት


ኢየሱስ ‹‹ለመወደድ ሲል›› ዕውነትን መናገርን ቸል አላለም፤ ምክንያቱም ፍቅር እንዲህ አያደርግም። ፍቅር ማለት ሁልጊዜም መልካምን ነገር ለሌላው የሚመኝ ነው። በዕውነት እና በፍቅር መካከል ተቃርኖ የለም። ዕውነት በፍቅር እና በቸርነት ሲነገር የፍቅር መገለጫ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር። ‹‹“መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ›› (ዮሐ 14:6)። መዳኛ ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ነው(ሐዋ 4:12)። የእርሱ ጸጋ ድነትን ሰጥቶ የእርሱን ዕውነት እንድናውቅ እና በእርሱ ህይወት እንድንኖር አድርጎናል።ዕውነት ያለፍቅር ግትር ወዳለ ሕጋዊነት ይመራል፥ ይህም መንፈሳዊ ህይወትን የሚተናነቅ ነገር ነው። ደግሞ ያለ ዕውነት ‹‹ፍቅር›› ብቻ ማለት ደግሞ ፋይዳ ቢስ የሆነ አጉል ታጋሽ የሆነ ስሜታዊነትን ስለሚያስከትል፥ ሰዎችን በግራ መጋባት ማዕበል እንዲዋዥቁ ያደርጋል። በፍቅር የተነገረ ዕውነት ግን ፍጹም የሆነ ክርስቲያናዊ ህይወትን የሚያላብስ ግልጽ አቅጣጫን፣ ዓላማን እና መተማመኛን ያላብሳል።

በ 1ኛ ጴጥሮስ 3:15፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4:2፤እና ቲቶ 3:4፣ 5 የተጻፈውን እናንብብ። በእነዚህ ጥቅሶች ከሰፈሩት መግለጫዎች የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውነት እና በትሁት ቅቡል መንፈስ የተንጠለጠለ ሚዛን ምንድነው?የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከዕውነት በላይ ፍቅርን አጉልተው አናገኛቸውም። በጣም ውብ በሆነ መንገድ ፍቅርን ከዕውነት፣ ከጸጋ እና ከሕግ፣ ርህራሄ እና ታማኝነት ጋር ደባልቀውት እናያለን። ጴጥሮስ አማኝ ወዳጆቹን ሲያስጠነቅቅ እንዲህ አለ፡ ‹‹ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤›› (1 ጴጥ. 3:15)።በሌላ አባባል፥ የምናምነው ነገር ምን እንደሆነ፣ ለምን እንዳመንነው ማወቅ፣ እና ምን እንዳመንን እና ለምን እንዳመንን ለማብራራትም የምንችል መሆን አለብን። ይህ ማለት ለሁሉም ነገር መልስ ሊኖረን ይገባል ወይም ሌሎችን ስለእኛ ዕምነት እንዲሸነፉ ማድረግ መቻል አለብን ማለት አይደለም። ይልቁንም ‹‹በትህትና እና በአክብሮት›› ማለትም ትህትና በማሳየት እና የያዝነው ነገር ምን ያህል ዋጋ ያለው እንደሆነ በመገንዘብ፥ ዕምነታችንን ማብራራት እና መጠበቅ አለብን ማለት ነው።

ጳውሎስ ለታዳጊው የእርሱ ተተኪ የመከረው ምክር ደግሞ፡ ‹‹ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።›› (2 ጢሞ 4:2 አ.መ.ት.) ለቲቶ ደግሞ፥ ዳግም የተወለዱትን ሁሉ የእግዚአብሔር ቸርነት እና ፍቅር ብቻ ሊያድናቸው እንደቻለ ያሳስበዋል (ቲቶ 3:5)። እኛም ብንሆን፥ ዕውነትን ማቅረብ ያለብን በትህትና እና በአክብሮት ፍቅርን ተሞልተን ሊሆን ይገባል። ጌታችን ደግሞ የመጨረሻውን ዘመን መልዕክት ያለ ክርስቶስ እየሞተ ለሚገኘው ዓለም ቅቡል በሆነ አመለካከት ለማዳረስ አብረነው እንድንቆም ይጠራናል።

ምናልባት አንድ ሰው ቀርቦ፥ ‹‹ለምን ክርስቲያን ሆንሽ/ሆንክ?›› ብሎ ቢጠይቅዎት ምላሽዎ እንዴት ይሆናል፣ ደግሞስ ለምን?

ነሐሴ 22
Aug 28


ተጨማሪ ሐሳብ


‹‹ክርስቶስ የመልካም እረኛ ትህትና፣ የወላጅ ፍቅር እና አቻ የሌለው የአፍቃሪ መድኅን ጻጋን ማንነቱ አድርጎ እናገኘዋለን። በማራኪ አገላለጽ የሚያቀርብልን በረከቱን ነው። እነዚህን በረከቶቹን በማወጅ ብቻ አይረካም፣ ይልቁንም የራሳችን ለማድረግ እንድንጓጓ በሚያደርግ እጅግ ማራኪ በሆነ መንገድ ያደርሰናል።እንግዲህ፥ አገልጋዮቹም እንዲሁ የዚህን የማይነገር ስጦታ ግርማ ባለጠግነት ሊያዳርሱ ይጠበቅባቸዋል። አስተምህሮዎችን በከንቱ መደጋገሙ ልፋት ሆኖ የሚቀር ሆኖ ሣለ፥ ከክርስቶስ የምናገኘው የሚደነቅ ፍቅር ልቦችን ያቀልጣል ያስገዛልም። ‹‹አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ይላል አምላካችሁ።

አንተ ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር፤ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትነግር፣ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጩኽ።ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤ለይሁዳም ከተሞች፣“እነሆ፤ አምላካችሁ!” በል።እነሆ፤ ልዑል እግዚአብሔር በኀይል ይመጣል፤ክንዱ ስለ እርሱ ይገዛል።እነሆ፤ ዋጋው ከእርሱ ጋር ነው፤የሚከፍለውም ብድራት አብሮት አለ።መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።›› ኢሳይያስ 40:1፣ 9–11”—ኤለን ጂ. ኋይት, የዘመናት ምኞት, ገጽ. 826, 827 (ከእንግሊዝኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች1.አለመታደል ሆኖ፥ አንዳንድ ሰዎች ግን የሌሎችን ውድቀት በማሳበቅ ደስታን ለራሳቸው ሊያመጡ ይጥራሉ፤ በዚሁ ዓይት የአስተሳሰብ ማጥ ውስጥ እንዳንገባ እንዴት አድርገን ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን?

2.እስቲ ይህንን ሁኔታ ያስቡ፡ አንድ ወዳጅዎ ከቀብር ሲመለስ እንዲህ ብሎ ሲናገሩት ሰሙ እንበል። ‹‹አክስቴ አሁን ከሰማይ ሆና ስለምታየኝ ደስ ይለኛል። በጣም ደስ የሚል ስሜት ይሰጠኛል።›› እስካሁን በዚህ ሣምንት ባጠናነው መርህ ተመርኩዘን ምላሽዎ እንዴት ይሆናል? በሌላ አባባል፥ ሙታን አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን ቢሆንም ምን፥ በዚህ ሰዓት ላይ ስለሙታን ማስተማር ጊዜው ትክክል የማይሆነው ለምንድነው?

3.ከዚህ በታች የሰፈረውን ዐረፍተ ነገር ለሌሎች በምናደርገው ምስክርነት ዕይታ ተወያዩበት ‹‹ክፋትን ብቻ ተመራምሮ ነቅሶ ማውጣት በነቃሹ ውስጥ ክፋትን ያጎለብታል። በሌሎች ጥፋት ላይ ቤት ስንሰራ እኛነታችንም ወደዚያው ምስል ይለወጣል። ይልቁንም የኢየሱስ ነጸብራቅ ብንሆን፥ የእርሱን ፍቅር እና የባህርይ ፍጽምና በመላበስ፥ ወደእርሱ ምስል እንለወጣለን። በእኛ ፊት ያስቀመጠልንን የላቀ ምስል በማሰላሰል፥ ንጹህ እና ቅዱስ ወደሆነ ከባቢ አየር፣ ያውም ወደ እግዚአብሔር መገኘት እናርጋለን። መኖሪያችንን በዚያ ስናደርግ ደግሞ ከእኛ ጋር የተነካኩትን ሁሉ የሚያጋግል ብርሐን ከውስጣችን ይፈነጥቃል።››—ኤለን ጂ. ኋይት, ጎስፕል ወርከርስ፣ገጽ. 479 (ከእንግሊዝኛው)