የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከነሐሴ 9 - ነሐሴ 15

8ኛ ትምህርት

Aug 15 - Aug 21
እንደ ኢየሱስ ማገልገልሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ: ማቴ. 5:13፣ 14፤ፊልጵ. 2:15፤ማር. 12:34፤ኤፌ. 4:15፤ማቴ. 4:23–25፤ማቴ. 25:31–46።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ‹‹ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው።(ማቴዎስ 9:36)

ኢ የሱስ በፍጹም ልቡ ለሰዎች ይራራ ነበር። ከራሱ ይልቅ ስለ ሌሎች ጥቅም እና ጭንቀት ያስብ ነበር።ህይወቱን ለተመለከተው፥ በሌሎች ሰዎች ላይ ማዕከል ያደረገ ነበር። አገልግሎቱም ቢሆን የፍቅር መሰጠትን ያንጸባርቅ ነበር። እርሱም በዙሪያው የሚገኙትን ሁሉ ሰዎች አካላዊ፣ አዕምሯዊ እንዲሁም የስሜት ፍላጎት ያሟላላቸው ከመሆኑ የተነሣ፥ እርሱ ለሚያስምረው መንፈሳዊ ዕውነት ልባቸውን ክፈት አድርገው ነበር። ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ የታወሩትን ሲያበራ፣ መስማት ለተሳናቸው ጆሯቸውን ሲከፍት፣ ከአጋንነት እስራት ነጻ ሲያወጣ፣ የተራቡትን ሲመግብ፣ እና ለተቸገሩት ሲራራ፥ ብዙ ልቦች ተነክተው ህይወታቸው ለመለወጥ በቅቷል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ሰዎች የእርሱን ልባዊ የሆነ የያገባኛል ስሜት በማየታቸው፥ እርሱ ለሚያስተምረው መንፈሳዊ ዕውነት ክፍት በመሆናቸው ነው። ‹‹የክርስቶስን ዘዴ ብቻ በመጠቀም ነው ሰዎችን በተሳካ ሁኔታ ለመድረስ የምንችለው። መድሃኒዓለም የእነርሱን መልካምነት እየተመኘ ከሰዎች ጋር ተቀላቀለ። ምን ያህል ርህራሄ በልቡ እንዳለ አሳያቸው፣ የሚፈልጉትን አገልግሎት አቀረበላቸው፣ ልባቸውን እንዲጥሉበት አስተማመናቸው። ከዚያም ተቤዣቸው።

›› ‘ፎሎው ሚ.”— ኤለን ጂ. ኋይት ዘ ሚኒስትሪ ኦፍ ሂሊንግ፣ ገጽ. 143(በእንግሊዝኛው) ይህች ዓለም የእርሱን አዋጅ እንድትሰማ የሚያስፈልጋትን ያህል እንዲሁ የምስራቹን በተግባር ልታይ እንደሚገባት ጭምር ኢየሱስ ተገንዝቦ ነበር። ለሌሎች ለማገልገል ቁርጠኛ የሆነ ክርስቶስን የመሠለ የምስክርነት ህይወት ከአፋችን ስለሚወጣው ንግግር ትልቅ የሆነ ምስክርነት ያለው ሲሆን ለምናሳየው ምስክርነትም ተዓማኒነትን ያስገኝልናል። የዚህን ሣምንት ትምህርት እያጠኑ ለነሐሴ 16 2012 ለሰንበት ይዘጋጁ።

ነሐሴ 10
Aug 16

0 ኢየሱስ ለህዝቡ የነበረው አመለካከት


ኢየሱስ ሁልጊዜም ሌሎችን ይመለከት የነበረው በመልካም ጎናቸው ነው። በውስጣቸው ያለውን መልካምነት መዝዞ ያወጣ ነበር። በወቅቱ ከነበሩት የኃይማኖት መሪዎች ይደርስበት ከነበረው ወቀሳ አንዱ ‹‹ይህ ሰው ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል›› (ሉቃ 15:2 አ.መ.ት.) ነበር። እነርሱ ‹‹ርኩሳን›› ብለው ከሚያስቧቸው ጋር ኀብረትን በማድረጉ ላይ ችግር ነበረባቸው። የሃይማኖት አተያይ ከመሰብሰብ ይልቅ ለመበተን የሚያደላ ነበር። ኢየሱስ ስለራሱ ሲናገር፡ ‹‹ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።›› ብሎ ሲናገር በጣም ተገርመውበታል (ማቴ. 9:13)።

ጻፎች፣ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን የሚከተሉት ሃይማኖትን መከላከል ላይ መሠረት ያደረገ ነበር። በእነርሱ እምነት፥‹‹በሀጢዓት ላለመበከል ማድረግ የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ›› የሚል ነበረ። ኢየሱስ ደግሞ የሚያስተምረው ፍጹም የተገላቢጦሹን ነበር። በዓለም እባብ የተሞላ ጉድጓድ ውስጥ ዝፍቅ ብሎ ገባ እንጂ ሊሸሽ አልሞከረም። እርሱ ‹‹የዓለም ብርሃን›› (ዮሐ. 8:12) ነውና። ማቴዎስ 5:13፣ 14 ላይ የተጻፈውን ያንብቡ፤ የእርሱን ተከታዮች ለመመሰል ኢየሱስ የተጠቀማቸው ሁለት ማሳያዎች ምንድናቸው? እነዚህን ማሳያዎች በተለየ ሁኔታ ለመጠቀም የፈለገው ለምን ይመስልዎታል? ደግሞም በዮሐ. 1:9፣ዮሐ.12:46፣ፊልጵ. 2:15 የሚገኙትንም ያንብቡ።በጥንታዊቷ ዓለም ጨው በጣም ጠቃሚ ከሆኑ ሀብቶች መካከል አንዱ ነበር። እጅግ በጣም ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ስለሆነ፥ አንዳንድ ጊዜ ሮማውያን ባለምዋሎች በመገበያያነት ይጠቀሙበት ነበር። የትልቅ ባለጠግነት ምልክት ነበር። ምግብን ለማጣፈጥ እና ለማቆየትም ያገለግል ነበር። ኢየሱስም የጨውን ተምሳሌት ተጠቅሞ ለተከታዮቹ በማስተማሩ፥ ዕውነተኛ የሆነው የሐብት መለኪያ በዓለም ላይ ኃያል የሆኑ እና ባለጠጋ ሰዎች ያላቸው እንዳልሆነ እየነገራቸው ነበር። ዕውነተኛው የዓለም ሐብት ለእግዚአብሔር መንግስት ሲሉ ልዩነትን ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ ቁርጠኛ ክርስቲያኖች ናቸው። በፍቅር የሚያደርጉት ከራስ ወዳድነት የጸዳ ተግባር የዓለምን መልካምነት እና የከባቢውን ጣዕም ይጠብቃል።

ኢየሱስ የተጠቀመው ሁለተኛው ተምሳሌት (በማቴዎስ 5:14) የምናገኘው ሲሆን፥ ‹‹የዓለም ብርሐን›› ስለመሆን የሚያወራው ነው። ብርሃን ከጨለማ አይሸሽም። በጨለማ ይፈነጥቃል። ከጨለማ ተለይቶ አይወጣም። ጨለማውን ሰነጣጥቆ በማለፍ ጨለማውን ብርሃን ያደርጋል።የኢየሱስ ተከታዮች የዚህን ዓለም ጨለማ ሰነጣጥቀው በጎረቤቶቻቸው፣ በመንደራቸው፣ በአነስተኛ እና ትላልቅ ከተሞችም ጭምር በማለፍ በእግዚአብሔር ክብር እንዲያጥለቀልቁ ይጠበቅባቸዋል። ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 17:15–18 የተናገረውን አይተን፥ ከዓለም መለየትን እና ከዓለም የመጠንቀቅን አሳብ የምንገነዘበው እንዴት ነው? እነዚህ ነገሮች አንድ ናቸውን? ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሲጸልይ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን እንድትጠብቃቸው ብሎ የለመነው ምን ለማለት ፈልጎ ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ነሐሴ 11
Aug 17

1 የኢየሱስ መስተንግዶ


ኢየሱስ እንደግብ የያዘው በሰዎች ውስጥ ያለው መልካም ነገር ማጉላትን ነበር።ሁኔታዎች ባልተለመደ ሁኔታ ፈታኝ በነበሩ ጊዜ እንኳን፥ ምላሹ ጸጋ የተላበሰ ነበር። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ‹‹ ከአንደበቱ በሚወጣ የጸጋ ቃል እየተገረሙ፣›› (ሉቃ 4:22) ሰዎቹ ይሰሙት እንደነበረ ይመሰክርልናል። ሰዎችን ይቀርብ የነበረበት ዘዴ ትጥቅን የሚያስፈታ ነበር። በጸጋን የተሞሉት ንግግሮቹን በሰሙ ሁሉ ዘንድ በልባቸው ውስጥ ትክክለኛውን ህብረዜማ ይፈጥር ነበር።

በማቴዎስ 8:5–10 እና ማርቆስ 12:34 ያለውን ያንብቡ፤ለሁለት ያልተለመዱ ሰዎች፥ ሮማዊው መቶ አለቃ እና ለአይሁድ ጸሓፊ ኢየሱስ የተናገራቸው ተስፋን ያዘሉ ቃላት ምንድናቸው?ለሮማዊው ኢየሱስ የተናገረው ወታደራዊ የሆነ ዐረፍተ ነገር የሚያነሳሳ ነው። በእስራኤል ዘንድ እንኳን እንዲህ ዓይነት እምነት እንዳላገኘ ኢየሱስ ሲናገር ይህ ዓይነት ቅጥር የጦር መኮንን ምን ሊሰማው እንደሚችል በህሊናችሁ ሣሉት። ኢየሱስ ‹‹አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም›› ብሎ ሲናገር የአይሁድ ጸሓፊው ምን ሊሰማው እንደሚችል እስቲ አስቡ። በሰዎች ውስጥ ያለውን መልካምነት ማውጣት ኢየሱስ ይችልበታል። ሰዎች ለወንጌል ልባቸውን እንዲከፍቱ ለማድረግ አድናቆትን ከመቸር እኩል ጉልበት ያላቸው ነገሮች ጥቂት ናቸው። በዙሪያዎ የሚገኙ ሰዎችን መልካም ነገራቸውን በማየት እንደሚያደንቋቸው እስቲ ይንገሯቸው። ኢሳይያስ 42:3፤ቆላስይስ 4:5፣ 6፤ እንዲሁም ኤፌሶን 4:15 ያመሳክሯቸው።

ከሌሎች ጋር ስለ ዕምነታችን እና ከእነርሱ ጋር ስላለን ግንኙነት ለመካፈል ከእነዚህ ጥቅሶች የምናገኘው ወሳኝ የሆነ መርኅ ምንድነው?ቃላቶቻችን የሚያበረታቱን እና በጸጋ የተሞሉ ሲሆኑ፥በሌሎች ህይወት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ አወንታዊ ነው። ኢየሱስ ‹‹የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም›› ደግሞም ‹‹የሚጤስ ጧፍን አያጠፋም›› ብሎ ትንቢታዊ የሆነን ቃል ኢሳይያስ ሲመሰክር እናገኘዋለን። በሌላ አባባል፥ ኢየሱስ ርህሩህ ከመሆኑ የተነሣ ያለአግባብ ማንንም ወደ ዕምነት ገና የመጣውን ሆነ ሊሰብርም ሆነ በልባቸው የዕምነት ጭላንጭል ያላቸውን ሊያጠፋ አይጨክንም።

እኛ መናገር የፈለግነው ነገር እኛ ከምንናገርበት መንገድ እኩል፥ እንዲያውም ከዚያ በበለጠ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድነው? ‹‹ዕውነቱ ይኸው ነው፥ የፈለገ ይቀበል፣ ያልፈለገ የራሱ ጉዳይ›› ስለሚለው ዐረፍተ ነገር የእርስዎ ምላሽ ምንድነው? በዚህ ዕውነት በሆነ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ችግሩ ምን ላይ ነው?

ነሐሴ 12
Aug 18

2 የኢየሱስ የፈውስ አገልግሎት፡ ክፍል 1


ጌታችን ወንጌልን የሠራበት መንገድ ከንግግር እና ከተጠቀለሉ ምስላዊ ስብከቶች ያለፈ ነው፤ እንደኑሮ የካበተ እና ድርጊትን የተሞላ ነው። በየዕለቱ የተለያየ ዓይነት ፍላጎት፣ የአካላዊ፣ የአዕምሮ፣ የስሜት እና የመንፈስ ጥያቄዎች ካላቸው ሰዎች ጋር በትከሻ እየተጋፋን እናልፋለን። ክርስቶስ ደግሞ ለሰዎች ብቸኝነት፣ ሐዘን፣ የልብ ጭንቀት ግድ የሚለን መሆናችንን እንዲሁም በደስታቸው፣ በተስፋቸው እና በህልማቸውም ትኩረት ሰጥተን መደሰታችንን ስናሳይ ሣለ፥ ክርስቶስ በእኛ በኩል ሆኖ እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን ሊደርስ ይፈልጋል።

ኢየሱስ ለሰዎች ጥልቅ ፍላጎቶች ደርሶ ለማገልገል እንዲችል የሚታየውን የተጋለጠውን ፍላጎታቸውን ያገለግል ነበር። የሚታይ ፍላጎት የምንለው በራሳቸው ሊፈቱት እንደማይቻላቸው አድርገው የሚሰማቸውን የህይወታቸው አንዱን ፈርጅ ማለት ነው።ለምሣሌ ሲጃራ ማጤስ ለማቆም፣ ክብደት ለመቀነስ፣ የተሻለ አመጋገም ለመልመድ፣ ወይም ጭንቀት ለመተው ያላቸው ፍላጎት ሊሆን ይችላል። የምግብ፣ የመኖሪያ፣ ወይም የህክምና ክብካቤ ፍላጎትም ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ስለ ትዳር ወይም ስለ ቤተሰብ ምክር የማግኘት ፍላጎትም ሊሆን ይችላል። ከሁሉ የሚበልጠው ፍላጎት ግን፥ከእግዚአብሔር ጋር ላላቸው የግል ግንኙነት እናም ለህይወታቸው ዘለዓለማዊ ረብ እንዲኖረው ማስቻል የሰው ልጆች የሚፈልጉት ዋናው ነገር ነው።በተበላሸው ዓለም ሣሉ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው ከሁሉ ትልቁ ፍላጎት።

በማቴ 9፡1-7 ያለውን የሽባውን ሰው ታሪክ እንዲሁም በማቴዎስ 5፡ 25-34 ያለችውን ደም የሚፈሳት ሴት ታሪክ ያንብቡ። በእነዚህ ሁለቱም ታሪኮች ውስጥ ኢየሱስ አካላዊ ፈውስን ትልቅ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅ ፍላጎት ጋር ስለማስተሳሰሩ ምን ምልክቶችን እናገኛለን?ኢየሱስ ያቀርብ የነበረው አገልግሎት አካላዊ እና ስሜታዊ ከሆነው ፈውስ እጅግ የበለጠ ነበር። ኢየሱስ ይመኝ የነበረው ከኃጢዓት ስንጥቅ የተነሣ የፈራረሰው ነገር ሙሉ በሙሉ መፈወሱን እንዲያዩ ነበር። ለክርስቶስ፥ አካላዊ የሆነው ፈውስ ኖሮ መንፈሳዊ ፈውስ ባይገኝ ጎዶሎ ነበር። የእግዚአብሔር ፍቅር የአንድን ግለሰብ አካላዊ እና ስሜታዊ የሆነ ጤንነት እንድንጠብቅ በውስጣችን ፍላጎት ከፈጠረልን፥ በዚያውም ልክ ለዚያ ግለሰብ መንፈሳዊ የሆነ ደህንነት ጭምር እንድንመኝ የሚያነሳሳን ሲሆን በዚህም የተነሣ እርሱ ወይም እርሷ በዚህም ሆነ በወዲያኛው እሰከ ዘለዓለም ድረስ ሙሉ የሆነ ህይወት መኖር ይችላል፤ ትችላለች ማለት ነው።

እንደምናውቀው፥ ኢየሱስ የፈወሳቸውም ሰዎች ቢሆኑ በጊዜያቸው ሞተዋል። ስለዚህ ዕውነተኛው ፍላጎት፥ ከምንም ነገር በላይ፥ መንፈሳዊ ነው ማለት አይደል? የእኛ ቤተክርስቲያን ለሰዎች ፍላጎት ትኩረት በማድረግ በማህበረሰባችን ውስጥ የእውነት ግድ እንደሚለን ለማሳየት የምትችልበት ምን ምን ዘዴዎች ይኖራሉ? በእርስዎ ማህበረሰብ ውስጥ ስላሉ ሰዎች እስቲ ያስቡ፤ የእርስዎ ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሰዎች ህይወት ላይ ለመፍጠር የሞከረችው ለውጥ ምን ዓይነት ነው?

ነሐሴ 13
Aug 19

3 የኢየሱስ የፈውስ አገልግሎት: ክፍል 2


በማቴዎስ 4:23–25 እና ማቴዎስ 9:35 ያለውን ያንብቡ። የክርስቶስ አገልግሎትን የመሰረቱ ሦስት ፈርጅ ያላቸው ምን ምን አይነት አካሔዶች ጥቅም ላይ ውለዋል? የሰዎችን ፍላጎት ያሟላውስ እንዴት ነበር፣ ደግሞስ በህይወታቸው ላይ የነበረው ተጽዕኖስ ምን ዓይነት ነበር?ኢየሱስም በአገልግሎቱ ውስጥ የትምህርት፣ የስብከት እና የፈውስ ሦስት እጥፍ የሆነ አገልግሎት አጠቃልሎ ነበር። ዘለዓለማዊ የሆኑ መርኆዎችን ሲያካፍለን፥ ሁላችንም እንደዚያው ትርጉም እና ኣላማ ያለው ህይወት እንድንመራ ነው።እንዲህ ብሏልና፡ ‹‹…እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።” (ዮሐ. 10:10)። ከእርሱ አገልግሎት የተትረፈረፈ ጸጋ ተገልጦልናል። ደግሞም፥ ዛሬም ሆነ እስከ ዘለዓለም እጅግ የተትረፈረፈ ህይወት እንዲኖረን ሊያስችለን ነው የመጣው።

እስቲ በማርቆስ 1:32–39 ያለውን እናንብብ። ኢየሱስ ቀኑን ሙሉ ሲፈውስ እና አጋንንትን ሲያስወጣ ዋለ። በቀጣዩ ማለዳ የጸሎት ጊዜ ከወሰደ በኋላ፥ አያሌ ሰዎች አሁንም ፈውስን ፈልገው ሲቀርቡ፥ ወደሌላ ከተማ ሔደ። እነርሱን ለምን አልፈወሰም? በቁጥር 3 እና 39 ላይ እርሱ ለዚህ ያስቀመጠውን ምክንያት ልብ ይሏል፤ይህ ታሪክ ዕምቅ መረጃ የያዘ ነው። እንደ ትላንትና አያሌ ሰዎችን ሲፈውስ ቆይቶ፥ በቀጣዩ ቀን ኢየሱሰ ሕዝቡ፥ ያውም እየፈለጉት እና መፈወስ የሚያስፈልጋቸው ብዙ እያሉ፥ ትቷቸው ሔደ። ወደ ዓለም የመጣበት ምክንያት ለወንጌል መሆኑን በራሱ ማብራሪያ አሳወቃቸው። ኢየሱስ አንድ የሚደነቅ ተዓምራትን ፈጻሚ ብቻ አልነበረም። እርሱ ሰውን ለመቤዠት ተልዕኮ ተሰጥቶት የመጣ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር እንጂ። ሰዎችን ከአካላዊ ህመማቸው በመፈወስ ብቻ ሊረካ አልቻለም። ሰዎች እርሱ ያመጣላቸውን ዘለዓለማዊ የሆነ ህይወት እንዲያገኙ ይመኝላቸው ነበር።

ወደ ምድር የመጣበት ምክንያት ምን እንደሆነ በእነዚህ ቃላት አስደግፎ ተናግሯል፡ ‹‹ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።›› (ሉቃ 19:10) እያንዳንዱ የፈውስ ድርጊት የእግዚአብሔርን ባህርይ ለመግለጥ፣ ከስቃይ ለመገላገል እና ለዘለዓለም ህይወት ማግኛ አጋጣሚ እንዲሆን የተጠቀመበት ዕድል ነበር። እርስዎ ድህነት ያጠቃዎት ወይም ታማሚ ቢሆኑ ኢየሱስ የሚሰጠውን የተትረፈረፈ ህይወት ለመኖር የሚቻልዎት ነውን? ኢየሱስ ከአካላዊ ፈውስ የጠለቀ ነገርን ለሰዎች ሰጥቷቸዋልን? ለሰዎች አካላዊ እና የስሜት ፍላጎቶች እያገለገልን ሣለ፥ በምን ተግባራዊ መንገዶች በመንፈሳዊ ዕውነታዎችም ሰዎችን መምራት እንችል ይሆን?

ነሐሴ 14
Aug 20

4 ለኢየሱስ ግድ የሚለው ነገር


በማቴዎስ 24 ላይ ከኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር አያይዞ እንዲሁም ስለእርሱ ዳግም ምጻት ቀናት በሚመለከት ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸውን መልዕክት ተከትሎ በምዕራፍ 25 ላይ ባለው የመጨረሻው ዘመን ተምሳሌት እናገኛለን። እነዚህ ተምሳሌቶች ዳግም ምጻቱን ለሚጠብቁ ሰዎች የሱስ ግድ የሚሰጠውን የባህርይ ጥራት የሚያሳዩ ናቸው።። የአስርቱ ቆነጃጀት ታሪክ ዕውነተኛ፣ ፍጹም፣ መንፈስን የተሞላ የሆነን ህይወት ጠቃሚነት የሚያሳይ ነው።የአስሩ መክሊቶች ታሪክ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የሰጠንን ስጦታ በታማኝነት የመጠቀምን ጠቃሚነት አጽንዖት ይሰጣል። የበግ እና ፍየሎቹ ምሳሌ ደግሞ ዕውነተኛ የሆነ ክርስትና በእያንዳንዱ ቀን ወደህይወታችን ለሚያመጣቸው ሰዎች ፍላጎት በዕውነተኛ ልብ ማገልገል እንደሚያስፈልግ ይገልጽልናል።

በማቴዎስ 25:31–46 ያለውን እስቲ እናንብብ። ኢየሱስ ዕውነተኛን ክርስትና በምን መንገድ ነው የገለፀው? ይህ ምንባብ የሚጠቅሰውን የአገልግሎት ፈርጆች ይዘርዝሩ።ምንም እንኳን ይህ ምሣሌ የሚናገረው የሰዎችን ዕውነተኛ የሆነ አካላዊ ፍላጎት ቢሆንም - ታሪኩ ቸል ልንለው የማይገባ ሆኖ ሣለ - ከዚህ የላቀ ነገር ሊኖር የሚችልበት ዕድል ይኖር ይሆን? እርካታ ለማግኘት የሚመኙ ሰዎች የነፍሳት የተሰወረ ርሐብ እና ጥማታቸው ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 6:35፣ ዮሐ. 4:13፣ 14)። እኛ ሁላችን በክርስቶስ ትክክለኛ ማንነታችንን ለማግኘት የምንናፍቅ ተቅበዝባዦች ነን። (ኤፌ. 2:12፣ 13፣ 19)። በእርሱ ጽድቅ እስክንሸፈን ድረስ በመንፈስ እንደተራቆትን ነው። (ራዕ. 3:18፤ራዕ. 19:7፣ 8)።

የብሉይ ኪዳን ነብያት የሰውን ዘር ሁኔታ ሲገልጹ ተስፋ እንደታጣበት ድውይ አድርገው ነው። (ኢሳ. 1:5፣ኤር. 30:12–15)። የኃጢዓት ህመም ለሞት የሚዳርግ ቢሆንም መድሃኒቱንም ነብያቱ አመልክተውናል። ‹‹አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤>>ይላል እግዚአብሔር።››(ኤር 30:17)። ለህይወታችን የሚያሰጋውን የነፍስ ህመም የሚፈውሰው ኢየሱስ ነው።

የበጎቹን እና የፍየሎቹን ምሳሌ ስናይ በዙሪያችን ያሉትን አካላዊ ፍላጎቶች እንድናሟላም ጭምር ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ቢሆንም፥ ከዚህም የበለጠ ነገር ደግሞ አለው። ይህም የነፍሳትን የውስጥ ፍላጎት የሚያሟላው የክርስቶስ ታሪክ ነው፥ ደግሞም ከእርሱ ጋር በአገልግሎቱ በመካፈል በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ ለማገልገል የቀረበ ጥሪ ጭምር ነው።የሌሎችን አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አዕምሯዊ እና የመንፈስ ፍላጎታቸውን ቸል ብለን ራሳችንን ማዕከል ያደረገ ህይወት ብቻ መኖር ዘለዓለማዊ ጥፋት ሲደርስ ዝም እንደ ማለት ነው። በምሣሌዎቹ እንደምናየው፥ ከራሳቸው ለሚልቀው ነገር ህይወታቸውን የሰጡ ሰዎች በጌታቸው ምስጋና ሲቀርብላቸው እና ወደዘለዓለም ህይወትም እንዲገቡ ሲጋበዙ ሣለ፥ በራስ ወዳድነት የራሳቸውን ጉዳይ ብቻ ሲፈልጉ እና የሌሎችን ፍላጎቶች ቸል ያሉት ሰዎች ደግሞ በጌታቸው ተኮንነው እናገኛቸዋለን።

ነሐሴ 15
Aug 21

5

ተጨማሪ ሐሳብ


‹‹ብዙዎች በእግዚአብሔር እያመኑ ሣለ በሰው ላይ ግን ዕምነት የላቸውም።ነገር ግን የርህራሄ እና የእርዳታ ድርጊቶችን ያደንቃሉ። ምድራዊ ምስጋና እና ካሳዎችን ወደ ቤታችን የሚያመጣ ነገር ሳይኖር፥ የታመሙትን ስንንከባከብ፣ የተራቡትን ስንመግብ፣ የታረዙትን ስናለብስ፣ ያዘኑትን ስናጽናና እና መልዕክተኛ ብቻ በመሆን በዝግታ ፍቅር እና አክብሮት ሁሉ ወደሚገባው ወደአንዱ ስንመራቸው ሣለ ይህንን ተመልክተው ልባቸው ይነካል። አመስጋኝነት ይበቅላል። ዕምነት ይቀጣጠላል። እግዚአብሔር ለእነርሱም ግድ እንደሚለው ይመለክታሉ፤ በዚህም የተነሣ የእርሱ ቃል ሲከፈትም ለመስማት ዝግጁ ሆነው ይገኛሉ።›› ኤለንጀ. ኋይት, ዘ ሚኒስትሪ ኦፍ ሂሊንግ፣ገጽ 145 (በእንግሊዝኛው)

ኢየሱስ ያሳየን ከራስ ወዳድነት የጸዳ አገልግሎት ልቦችን የሚሰብር፣ አሉባልታን የሚሰብር፣ እንዲሁም ለወንጌል ቅቡልነትን የሚፈጥር ነው።ቤተክርስቲያን በሁሉም ስፍራ ፍላጎቶችን በፍቅር የምታሟላ የክርስቶስ አካል ናት። ክርስቶስ ወደህብረተሰቡ መካከል የሚሰድደን በእርሱ ስም ልዩነትን እንድንፈጥር ነው። ምንም እንኳን በእርግጥ በዓለም ስለመበከል ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ብንሆንም ቅሉ፥ (ደግሞም ለቤተክርስቲያናችን ዕውን እና ትልቅ አደጋ ቢሆኑም) ሰዎችን ባሉበት ቦታ ላይ ስለ መድረስ እና እነርሱ ሊሆኑ ወደሚገባቸው ስፍራ እንዲመጡ ለሚፈልጋቸው እግዚአብሔር ጥቅም እንዲውሉ ስለ ማድረግ ልንማር ይገባናል።


የመወያያ ጥያቄዎች1.ርህራሄን የተሞላው የክርስቶስ አገልግሎት አሉባልታን በመናድ ሰዎችን ለመንፈሳዊ ዕውነታዎች ክፍት እንዲሆኑ ለማድረግ የቻለው ለምን ይመስልዎታል? የእኛ ምስክርነት ኢየሱስ እንዳደረገው ከራስ ተኮርነት የጸዳ መሆኑ የሚታይ ቢሆን ኖሮ ለሰዎች ምስክርነት ስንሰጥ ምን ያህል ውጤታማ ልንሆን እንደምንችል እስቲ በህሊናችሁ ሣሉት።

2.አንድ ዕውነተኛ፣ ትክከለኛ እና እንደውም አስፈላጊ የሆነን ነገር የተናገሩበትን - ግን ደግሞ በስህተት የተናገሩበትን ጊዜ ያስቡ፥ ማለትም በድምጸትዎ ወይም አቀራረብዎ ሊሆን ይችላል። ከዚያ አጋጣሚ ዳግም የማታደርጉትን ምን ተምራችሁ አለፋችሁበት ለምሣሌ ከመናገር ወይም ከመሣሠሉት ነገሮች አስቀድሞ እስከሚረግቡ ድረስ ጥቂት ስለመጠበቅ የሚረዳ ነገር ምን አገኙ?

3.ከህመማቸው የተፈወሱ እንደውም ከሞት የተነሱቱ ሁሉ ጊዜያቸውን ጠብቀው መሞታቸውን አሰላስሉ። በዙሪያችን ለሚገኙት የወንጌል ስርጨት ተግባር ስናከናውን ሣለ እንዴት ማድረግ እንደሚገባን ይህ የሚነግረን ነገር ምንድነው?

4.አሁን ላይ እያደረጋችሁት ያልሆነ ግን በማህበረሰባችሁ ውስጥ የሚያስፈልግ ምን ዓይነት አገልግሎት ቤተክርስቲያንዎ ልታስጀምር ትችላለች?

5.እኛም የሚታይ ፍላጎታቸውን በመድረስ ለሚፈልጉት መንፈሳዊ ዕድሎችን ልንፈጥር የምንችለው እንዴት ነው?