የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከነሐሴ 2 - ነሐሴ 8

7ኛ ትምህርት

Aug 08 - Aug 14
ቃሉን ማካፈልሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ: መዝ. 119:105፤ኤር. 23:29፤ዕብ. 1:1–3፣ 2 ጢሞ. 3:14–17፣1 ዮሐ 1:7–9፣መክብብ. 3:1፣ 2 ጢሞ. 4:2።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡“ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”(ኢሳ.55:11)

ም ስክርነት ስንወጣ፥ ንግግራችን ኢየሱስን ይወክላል. ዳሩ ግን፥ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የምናውቀው ምን ነገር ይኖራል? ዕርግጡን እናውራና፥ ቅዱስ ቃሉ የሌለን እንደሆነ ስለ ታላቁ ተጋድሎ፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ስለ ጌታችን ውልደት፣ ህይወት፣ አገልግሎት፣ ሞት፣ ትንሣዔ እና ዳግም ምጻት ምን ዕውቀት ሊኖረን ይችላል?

ተፈጥሮ ስለ እግዚአብሔር ኃያልነት እና ስልጣን የሚያወራው ነገር ቢኖርም፥ ስለ ድነት ዕቅድ ግን የሚገልጽልን ነገር የለም። ኢየሱስ፥ በመንፈስ ቅዱስ አካል ለብሶ፥ ‹‹ለሰው ሁለ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር›› (ዮሐ. 1:9) የሆነ ሆኖ፥ መለኮታዊውን ዕውነት የሚያብራራልን የእግዚአብሔር ቃል ካልኖረን፥ ለልባችን መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን መገለጥ የተገደበ ይሆናል።የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል፥ ህያው ቃል የሆነው የኢየሱስ ንጹህ እና ሙሉ መገለጫ ነው።

ምንም እንኳን የኃይማኖት መሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል ያጠኑ ቢሆንም፥አያሌዎች ግን ዋነኛውን መልዕክት ስተዋል። ኢየሱስ እንዲህ አለ ‹‹በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው።››(ዮሐ. 5:39) በትክክል ስንረዳው፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው የትኛውም ነገር የኢየሱስን ባህርይ ውበት የሚያንጸባርቅ ነው።የእግዚአብሔርን ቃል ስንካፈል ደግሞ፥ ዋነኛው ግባችን እኛ ትክክል ሆነን ሌላኛው ሰው መሳሳቱን ለማሳየት ሳይሆን፥ በእያንዳንዱ የምናካፍለው የዕውነት ፈርጅ ውስጥ ኢየሱስን መግለጥ መሆን አለበት። *የዚህን ሣምንት ትምህርት አንብበው ለነሐሴ 9 2012 ሰንበት ይዘጋጁ።

ነሐሴ 3
Aug 09

የእግዚአብሔር ቃል ማሳያዎች


እስቲ መዝ. 119:105፣ኤር. 23:29፣ሉቃ. 8:11፣ እና ማቴ. 4:4ን ያንብቡ። በእነዚህ ምንባቦች ከተመለከቱት ማሳያዎች ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋሉት አምስቱ ምን ምን ናቸው? እነዚህ አምስት ማሳያዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲወክሉ የተመረጡት ለምን ይመስልዎታል?በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ የተመለከቱት ልዩ ልዩ ምልክቶች የእግዚአብሔርን ቃል ዋነኛ የሆኑ ተግባራት የሚያመለክቱ ናቸው።ቃሉን ከሌሎች ጋር መካፈል፥ ህይወትን ፍንትው አድርጎ ከሚያሳይ ብርሃን ጋር አንድ ነው። ኢየሱስ፥ “የዓለም ብርሃን” እንደመሆኑ፥ ስለ እግዚአብሔር ምንነት ስለ ባህርይው ያላቸውን ያለማስተዋል ጨለማ ጥሶ ያልፋል።በአለማስተዋል የጨለሙ ህሊናዎች፥ ከእግዚአብሔር ቃል የተነሣ በመንፈስ ቅዱስ ብርሃናማ ይሆናሉ። ኤርሚያስ እንደሚናገረው ከሆነ፥ የእግዚአብሔር ቃል እንደ መዶሻ እና እንደ እሳት ነው። ይህም በህይወታችን ውስጥ ያለውን የኃጢዓት ዕድፍ ሁሉ ያቃጥላል ደግሞም ደንዳናውን ልባችንን ይሰብራል። ሰዎች በቅዱስ ቃሉ ውስጥ የኢየሱስን ክብር እንዲያዩ ስንረዳቸው ሣለ፥ የደነደኑ ልቦቻቸው ይሰበራሉ፥ ደግሞም የፍቅሩ እሳት የራስወዳድነትን፣ የስግብግብነትን፣ የክፉ ምኞትን እና የእኔነትን ዕድፍ ሁሉ ያቃጥላል።

የእግዚአብሔር ቃል በዘር ተመስሏል። አንድ ዘር ዓይነተኛ የሆነ መገለጫው ቢኖር ህይወት የሚመነጭበት መሆኑ ነው።ዘሮች ለመብቀል ጊዜ ይወስድባቸዋል።ሁሉም ዘሮች በአንድ ዓይነት ጊዜ እኩል አይበቅሉም።ደግሞም ሁሉም ተክሎች በተመሣሣይ ሁኔታ እኩል አያድጉም።ነገር ግን ነገሮች መልካም እስከሆኑ ድረስ፥በዘሩ ውስጥ ያለው ህይወት አፈሩን ሰንጥቆ አዲስ ህይወት በመሆን ጸድቆ ይወጣል።የእግዚአብሔርን ቃል ዘር በሌሎች ልብ እና ህሊና ውስጥ በምንዘራበት ጊዜ፥ውጤቱን ሁልጊዜም ወዲያውኑ ላናይ እንችላለን፤ ዳሩግን ዝም ያለች ብትመስልም ይህች ዘር እያደገች ነው፥ እናም በእግዚአብሔር በራሱ ጊዜ፥ ምናልባት ለመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ምላሽ ይሰጡና፥ ለእግዚአብሔር መንግስት መኸር ሆነው ይገባሉ።

ኢየሱስ የእርሱን ቃል እንደ ህይወት እንጀራ አድርጎ በምሳሌ አስቀምጧል። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ደግሞ፥ መልካም ከሆነ የእንጀራ ጉርሻ እኩል እርካታን የሚያስገኙልን ነገሮች ጥቂት ናቸው። የእግዚአብሔር ቃል የነፍሳችንን ርሃብ የሚያጠግብ እና የውስጥ መንፈሳዊ ጥማታችንን የሚያረካልን ነገር ነው።ከቃሉ ውስጥ የተገባልንን ቃልኪዳኖች ለሌሎች በሚያካፍሉበት ጊዜ ይህም ቃል ኢየሱስ መሆኑን እነርሱ እንዲገነዘቡ ስለሚያስችሏቸው፥ ህይወታቸው በእርሱ መልካምነት ይለወጣል፣ በፍቅሩ ይማረካል፣ በጸጋው ይደመማል፣ በመገኘቱም ይረካል። አንዴ እንደገና፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ለማወቅ ስለምንችላቸው ዕውነታዎች እስቲ እናሰላስል። ለእኛ ትምህርት ስለሚሆነን ነገር ምን ያህል ዋጋ ልንሰጠው እንደሚገባን ይህ ምን ያስተምረናል?

ነሐሴ 4
Aug 10

የእግዚአብሔር ቃል የመፍጠር ጉልበት


በዕብራውያን 1:1–3፤ ዕብራውያን 4:12 እና መዝሙረ ዳዊት 33:6-9 የሰፈረውን እስቲ ያመሳክሩ። እነዚህ ምንባቦች ስለ እግዚአብሔር ቃል ኃይል ምን ነገሮችን ይነግሩናል?የእግዚአብሔር ቃል ህያው ቃል ነው።ይሁን ያላቸውን ነገሮች የማሳካት ስልጣን በውስጡ የያዘ ነው።ሰብዓዊ የሆኑ ቃላት ሊናገሩ የሚችሉት ሆነው ስላለፉት ነገሮች ነው፤ ዳሩ ግን፥ እግዚአብሔር ሲናገር ሊሆን ያለውን ነገር ይናገራል፣ ከዚያም በቃሉ ጉልበት እነዚህን ይፈጥራቸዋል። የእግዚአብሔር ቃል መፍጠር የሚችል ቃል ነው።ከእርሱ አፍ የሚወጣው የሚደመጥ ቃል ይሁንልኝ ያለውን ነገር ሁሉ መፍጠር የሚያስችል ጉልበት ያለው ነው።

በዘፍጥረት 1 ላይ ባየነው የፍጥረት ታሪክ ውስጥ፥ ‹‹እግዚአብሔርም አለ፥ ›› የሚሉት አገላለጾች በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ውለው እናገኛቸዋለን። (ዘፍ. 1:3, 6, 11, 14, 20, 24, 26, 29) ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚወጡት ይሁኑልኝ የሚላቸው ቃላት እርሱ በተናገረበት ጊዜ ላይ ደረቁን ምድር እንዲታይ፣ ሐመልማሉ እንዲጸድቅ፣ አበቦች እንዲፈኩ፣ ፍሬዎች እንዲቋጠሩ እና እንስሳት እንዲታዩ እስኪያደርጉ ድረስ ጉልበት ያላቸው ነበሩ። በዘፍጥረት 1 ላይ ጥቅም ላይ ከዋሉት መካከል የእግዚአብሔርን የፈጠራ ተግባር ሲገልጽ የምናገኘው አንድ ዕብራይስጥኛ ቃል አለ። ይህም ባራ ተብሎ የሚነበብ ቃል ነው። ከአመሰራረቱ ስናየው፥ ይህ ቃል ያገለገለው ከምንም ላይ ተነስቶ እግዚአብሔር አንድን ነገር መፍጠሩን ለማመልከትነው። ይህ ግስ ጥቅም ላይ የዋለው እግዚአብሔር ብቻ የዐረፍተነገሩ ባለቤት በሆነባቸው አጋጣሚዎች ነው። ይህም ማለት፥ ባራ ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው ማለት ሲሆን፥ ይህንንም የሚያደርገው በሚናገራቸው ቃላቶቹ አማካይነት ነው።

እግዚአብሔር በቃሉ ጉልበት ዓለምን ይፈጥራል ብቻ ሳይሆን፥በቃሉ አማካይነት ይህንን ያጸናል ደግሞም ያስቀጥለዋል። በእግዚአብሔር ንግግር ውስጥ ያለው ይኸው ጉልበት በተጻፈው ቃሉ ውስጥም ይገኛል። በፍጥረት ጊዜ በስራ ላይ የነበረው ይኸው መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ቃሉ በተጻፈበት ጊዜ ላይም በስራ ላይ ነበር።መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብብበት ጊዜ ወይም ለሌሎችም ስናካፈል እንዲሁ ይገኛል። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ህይወትን የሚዘራ፣ ህይወትን የሚለውጥ የሚፈጥር የእግዚአብሔር ቃል ጉልበት አለ። “ዓለማትን እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የፈጣሪ ጉልበት የእግዚአብሔር ቃል ነው።ይህም ቃል ኃይልን በማካፈል፤ ህይወትን ይዘራል።እያንዳንዱ ትዕዛዝ ቃልኪዳን አለበት፤ በፍቃደኝነት ከወሰድነው፣ ወደ ነፍሳችን ከተቀበልነው፥የማይተመነውን የእርሱን ህይወት ጭምር ይዞልን ይመጣል።

ተፈጥሮን ይለውጣል፣ በዚያውም ነፍስን በእግዚአብሔር አምሳል ዳግም ይፈጥራታል።”—ኤለን ጂ. ኋይት፤ ስነ-ትምህርት , ገጽ. 126. (በእንግሊዝኛው) እኛም፥ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያሉትን ቃልኪዳኖች በግላችን በምንጨብጥበት ጊዜ፥ህይወታችን ይለወጣል፤ ደግሞ እኛ ሌሎች እነዚህን አስደናቂ ቃልኪዳኖች እንዲጨብጡ ስንደግፋቸው፥ መንፈስ ቅዱስ የእነርሱንም ህይወት እንዲሁ ይለውጣል። በአይነ ህሊናችሁ ይህንን ሣሉ: እግዚአብሔር አለ እንዳለውም ሆነ። የዚህን ትርጕም እንዴት ነው የምንገነዘበው? ይህ የሚያስደንቅ ዕውነታ ስለ እርሱ ጉልበት የሚነግረን ምንድር ነው? ይህንንስ የመሠለ ዕውነት ስለ እግዚአብሔር የፈጠራ ጉልበት ማወቃችን ሊያጽናናን የሚገባው ለምንድነው?

ነሐሴ 5
Aug 11

የእግዚአብሔርን ቃል የማጥናት ጥቅሞች


የእግዚአብሔርን ቃል ከማጥናት የምናገኛቸው አያሌ ጥቅሞች አሉ።ሐዋርያው ጴጥሮስ በቅዱስ ቃሉ እንደሚነግረን፥ ‹‹የመለኮት ባህርይ ተካፋዮች›› (2ኛ ጴጥ. 1፡4) እንሆናለን። ያዕቆብ ሲናገር ደግሞ፥ ‹‹…ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል …›› (ያዕ 1:21)ሲል ይናገራል።ጳውሎስ ደግሞ ሲጨምር ‹‹…እንዲሁም ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል…››(ሐዋ 20:32) ብሏል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማው መቤዠት ነው። ኢየሱስን በቅዱስ ቃሉ ሁሉ ውስጥ ስናይ፥ እንለወጣለን።እርሱን በራሱ ቃል ውስጥ ስንመለከተው፥ልክ እንደ እርሱ እንሆናለን (2ቆሮ. 3:18)።

“በምድራዊ ትምህርት እንዲሁም በመንፈሳዊ ተፈጥሮ ህግም ጭምር በምናባችን በማየት ለመለወጥ እንበቃለን።አዕምሮ እንዲረጋ በተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ ራሱን በሒደት ማመሳሰል ይችላል።”—ኤለን ጂ. ኋይት፤ ዘ ግሬት ኮንትሮቨርሲገጽ. 555 (እንግሊዝኛው) 2ኛ ጢሞቴዎስ 3:14–17 እና ዮሐንስ 17:14–17 ጥቅሶችን ያንብቡ። የእግዚአብሔርን ቃል ከማንበብ ምን ተጨማሪ ጥቅሞችን እናገኛለን?ለብላቴና ወዳጁ ጢሞቴዎስ በጻፈው መልዕክት፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ቅዱስ ቃሉን በመታመን እንዲይዝ እና መንፈስ ያለበትን ቃል ማጥናት የሚያስገኘውን ጥቅም እንዲያካፍል ሲያሳስበው እናገኘዋለን። ጳውሎስ እንደሚያስበው ከሆነ፥ መፅሐፍ ቅዱስ ‹‹ለማስተማር…ይጠቅማል።››ዕውነትን እየገለጠ ስህተትን ያጋልጣል።የእግዚአብሔርን ዕቅድም ለሰው ዘር በሙሉ አጉልቶ ያሳያል።ኃጢዓትን ይኮንናል፣ የሳተውን አስተሳሰባችንን ያቀናል፤እንዲሁም በጽድቅ መንገድ ይመራናል።

ቅዱስ ቃሉ የክርስቶስን ጽድቅ ይገልጣል። ከገዛ ኃጢዓተኛ ማንነታችን አዘቅት ወደራሱ ጽድቅ ውበት መርቶ ያወጣናል። የኢየሱስን ያልተቆጠበ ፍቅር ከእኛ እኔነት የተሞላ ማንነት ጋር ስናወዳድር፥ በመደነቅ እንሞላለን። የእርሱን ፍቅር እና ክብካቤ ጥልቀት ከቅዱስ ቃሉ ስንገነዘብ ሣለ ህይወታችን ይለወጣል። የእርሱን ቃል ለሌሎች በምናካፍልበት ጊዜ፥ እነርሱም ደግሞ በሙላት ይለወጣሉ።ኢየሱስን በቃሉ ውስጥ መግለጥ በመቻላችን፥ እኛም እንደ እርሱ እንሆናለን። የምስክርነት ዓላማ እኛ ስለምናስበው ወይም እኛ ስለምናምነው ነገር አይደለም። ሁሉ ነገሩ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለውን ዘለዓለማዊ ዕውነት ማካፈል ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የእኛን ህይወት በበረከት ሲያጥለቀልቀው፥ ለሌሎችም እንዲሁ እንዴት በረከት ሊሆንላቸው እንደሚችል ምስክርነት ሊኖረን ይችላል።

እርስዎ በግልዎ ተግዳሮት ያጋጠመዎትን ጊዜ እና የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎ ጥንካሬ የፈጠረልዎትን አጋጣሚ እስቲ ያስቡ። ከዚያ አጋጣሚ ምን ትምህርት ወስደዋል?

ነሐሴ 6
Aug 12

የእግዚአብሔርን ቃል መተግበር


የሆነ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያሉ ከሦስት መቶ በላይ ቃልኪዳኖችን ቆጥሮ ነበር። እነዚህ ቃልኪዳኖች እያንዳንዳቸው ‹‹በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ››(ኤፌ. 3፡20) ከሚችለው ከእግዚአብሔር ልብ የሚመነጩ ናቸው። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳኖች ለእያንዳንዳችን የሚገባልን የእርሱ ውዴታ ግዴታዎች ናቸው። እነዚህን ቃልኪዳኖች በዕምነት ስንጠማጠማቸው እና ለሌሎችም ሰዎች እንዲሁ እንዲጠማጠሟቸው ስናስተምር ሣለ፥ በረከት ከዓርያም ወደ ህይወታችን ይፈስሳል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ዓይነቱ መለኮታዊ ዕውነታ በሮሜ 8 እንዲህ ሲል አጽንዖት ይሰጥበታል፡ ‹‹ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?›› (ሮሜ. 8:32)። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን ቃልኪዳን ግለጽ ሲያደርገው ደግሞ ‹‹በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል።›› (2 ጴጥ. 1:3)። በመስቀል ላይ በሞተው በክርስቶስ እንዲሁም በሰይጣን እና በኃይላቶቹ እንዲሁም በገሐነም ስልጣናት ላይ ባገኘው ድል ምክንያት፥ በፈሪሃ እግዚእብሔር መንፈሳዊ ህይወት እንድንኖር የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ አዘጋጅቶልናል። መሠረታዊ፣ አካላዊ የሆነውን ፍላጎታችንን ለማሟላትም ጭምር ቃል ገብቶልናል።

እስቲ 1 ዮሐንስ 1:7–9 እና ፊልጵስዩስ 4:13፤19ን አነጻጽሯቸው። ምንም እንኳን እነዚህ ቃል ኪዳኖች እርግጥ የተለያዩ ቢሆኑም ቅሉ፥ ስለ እግዚአብሔር ባህርይ የሚነግሩን ነገር ምንድነው? እነዚህ ቃልኪዳኖች በእርስዎ ህይወት ላይ ያመጡት ተጽዕኖ ምንድን ነው?በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ያነበብናቸው ቃልኪዳኖች የሚያወሩልን ለየት ስለሚል፣ ግን በእግዚአብሔር ምስል ውስጥ ካስገባነው በጣም ተመሣሣይ ስለሆነ ነገር ነው። ስለ እግዚአብሔር የፍቅር ይቅርታ፣ የማይገደብ ጉልበት እንዲሁም ለእኛ መሠረታዊ ፍላጎቶች ደንታ እንደሚሰጠው ይገልጹልናል። እግዚእሔር ለእኛ እጅግ ግድ የሚለው እንደሆነ ትልቅ የሆነ ማስተማመኛ ነው።

ዕብራውያን 3:19፤4:1–3 እና ማቴዎስ 13:58ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ዕምነት ምን ያህል እንደሚያስፈልገን የሚነግሩን ነገር ምን ይሆን?በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ አያሌ አስደናቂ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳኖችን እናገኛለን፤ ደግሞም ከእግዚአብሔር ቃል ያገኘናቸውን ቃል ኪዳኖች በዕምነት ስንጠማጠም እና የተናገረው ክርስቶስ በመሆኑ ስናምንባቸው፥በእነዚህ ቃልኪዳኖች የታመቁት በረከቶች የእኛ ይሆኑልናል። በህይወታችን በቃሉ ውስጥ ያስቀመጠው ቃልኪዳን ዕውን እንዳይሆን ጋሬጣ የሆነው፥ በእግዚአብሔር ችሎታ ላይ ዕምነት የማንጥል በመሆናችን ነው። በዚህ ሣምንት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያሉትን የሚደግፉ የተስፋ ቃሎች የሚፈልግ አንድ ሰው ዘንድ እንዲመራዎት ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ።

ነሐሴ 7
Aug 13

ቃሉን ማካፈል


የምስራች ከሆነ መበሰር አለበት። አንድ የምስራች በጣም ልብዎን ያሞቀበትን የህይወትዎን ጊዜ እስቲ መለስ ብለው ያስቡ። ለመጋባት ዕጮኛ የያዙበት፣ ልጅ የወለዱበት፣ አዲስ ሥራ የተቀጠሩበት፣ ወይም አዲስ መኪና ወይ ቤት የገዙበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። በጣም ከመደስትዎ የተነሣ ለሌሎች ለመንገር ጓግተው የነበረበት ጊዜ ነው። ደስታን ለሌሎች ማጋራት በጣም አስደናቂ ቢሆንም፥ ለዩኒቨርስ በአጠቃላይ ምርጥ የሚባለው የምስራች የኢየሱስ ታሪክ ነው።በእርሱ ቃል ውስጥ በክርስቶስ በኩል ስላገኘነው ድነት አዳዲስ መረዳቶችን ስናገኝ ሣለ፥ ልባችን በሐሴት ስለሚጥለቀለቅ፥ ለሌላ ሰው ለመንገር እንጓጓለን። ሐዋርያት የሚሰብኩትን ስብከት የኃይማኖት መሪዎች ሊያስቆሟቸው ሲታገሉ በነበረ ጊዜ፥ ጴጥሮስ እንዲህ አወጀ፡ ‹‹እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።›› (ሐዋ. 4:20)።

“የሚያድነው እና የሚያጸድቀው ዕውነት በልቡ ውስጥ ዝም እንደማያሰኘው እና ከክርስቶስ ጋር ያለውን የሚደነቅ ወዳጅነት ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል የተጸነሰ ፍላጎት በልቡ እንዳለው ሰው ማንም ቢሆን ወደ ክርስቶስ በፍጥነት ሊመጣ አይችልም። ምናልባት እኛ የክርስቶስን ጽድቅ ተጎናጽፈን፥ በውስጣችን በሚኖረው መንፈስ የተሞላን እንደሆነ፥ በዝምታ ልንቀመጥ አይቻለንም።”—ኤለን ጂ. ኋይት፤ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ, ገጽ. 78. (በእንግሊዝኛው)

በሮሜ መጽሐፍ 1:14–16 ላይ ጳውሎስ እንዲህ ጽፏል፡‹‹ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ፣ ዕዳ አለብኝ፤በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው።በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው።›› ሐዋርያው ጳውሎስ ስለተለወጠበት ታሪክ ለመናገር ምንም ሙከራ አላደረገም። ልቡን ያጥለቀለቀው በኢየሱስ ያገኘው ሐሴት ነው። ለእርሱ የምስራች ማለት የሚበሰር ነገር በመሆኑ፥ ዝም ሊያሰኘው አልቻለም።

የእግዚአብሔርን ቃል ስለማካፈል በተመለከተ በኢሳይያስ 50:4፣መክብብ 3:1 እና 2ጤሞቴዎስ 4:2 የምናገኘው መሠረታዊ መርህ ምንድነው?ህይወታችንን ለክርስቶስ እና ለእርሱ አገልግሎት አሳልፈን ስንሰጥ፣ ‹‹በጊዜው›› ወይም በትክክለኛው ሰዓት ላይ እርሱ ለከፈታቸው ልቦች የምንናገርበትን በር ይከፍትልናል። እኛ በምናደርጋቸው ምስክርነቶች ሁሉ፥ሦስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆዎችን በህሊናችን መያዝ አለብን፤ ምን እንናገር፣ እንዴት እንናገር፣ እንዲሁም መች እንናገር የሚለው ነው።

በጥቂቱ ከእነማን ጋር ለመገናኘት ዕድል አለ? ደግሞስ ለእነርሱ በተሻለ መንገድ እንዴት ሊመሰክሩላቸው ይችላሉ?

ነሐሴ 8
Aug 14


ተጨማሪ ሐሳብ


ከኤለን ጂ. ኋይት ጽሑፎች “እግዚአብሔርን መረዳት” ገጽ 87 –91, የሚለውን “ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ” ከሚለው መጽሐፍ፤ “ባይብል ሪዲንግስ ዊዝ ፋሚሊስ” ገጽ 192–193, የሚለውን ርዕስ ከጎስፕል ወርከርስ መጽሐፍ እና “ባይብል ወርክ ቴክኒክስ” በሚል ርዕስ ገጽ. 481–486, ኢቫንጀሊዝም ከሚለው መጽሐፍ ያንብቡ።

እግዚአብሔር በየአጋጣሚው በልባችን ላይ ሥራውን አላቆመም። ምናልባት እግዚአብሔር በየት በኩል እየሰራ እንደሆነ ለመገንዘብ መንፈሳዊ ዝንባሌ ቢኖረን፥ ከሌሎች ጋር የእርሱን ቃል ለመካፈል የሚሰጡንን ዕድሎች ሁሉ በተከታታይ መመልከት እንችላለን።የልቦቻችንን መደብ እግዚአብሔር ሲያዘጋጅ ሣለ፥የወንጌልን ዘር የመዝራት ዕድል እናገኛለን። የኒቆዲሞስን፣ በውሃው ጉድጓድ አጠገብ የነበረችውን ሴት፣ የደም መፍሰስ ችግር የነበረባትን ሴት፣ በመስቀል ላይ የነበረውን ወንበዴ፣ ሮማዊውን መቶ አለቃ፣ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ሰዎችን ልብ ገና ኢየሱስ ሳይገናኛቸው በፊት ነበር መንፈስ ቅዱስ ያዘጋጀው። የህይወት አጋጣሚዎቻቸው እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ አቀባበላቸው ምንም ዓይነት ቢሆን፥ ሁሉም የክርስቶስን መልዕክት ለመቀበል የተዘጋጁ ነበሩ።

አብረናቸው እንድንጻልይ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃልኪዳኑን የመካፈል፣ ወይም አንድ ዓይነት ጽሑፍ ለመስጠት ይፈቅዱልን እንደሆነ ሰዎችን ለመጠየቅ የሆነ ዓይነት የማንገራገር ነገር ተፈጥሮብናል።ሁሌ በሚባል ሁኔታ ከሌላ ሰው ጋር ስለ ዕምነታችን ለማካፈል የተገፋፋን ሲመስለን፥ ይህንን ግፊት በውስጣችን የፈጠረው መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ እና የእኛን ምስክርነት ይህ ሰው እንዲቀበለው ያዘጋጀው ስለሆነ ነው።


የመወያያ ጥያቄዎች1.አንድ ሰው በሆነ ጉዳይ ላይ ክፉኛ በደለኝነት ተሰምቶት ቢመጣ እና ከእግዚአብሔር ይቅርታን የሚፈልግ ቢሆን፥ እርስዎ ለእርሱ የሚሰጡት ምክር ምን ይሆናል፣ ደግሞስ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ያካፍሉታል? ከበደልነት እና ከእግዚአብሔር የይቅርታ ጉልበት ጋር በተያያዘ በህይወትዎ የተለማመዱት ልምድ ምን ይመስላል?

2.አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ህይወታችን የሚያመጣው እነርሱ ዕውነቱን እንዲያውቁ የሚጓጓላቸው በመሆኑ ነው። እንዴት አድርገን ስለ እግዚአብሔር ምሪት ቶሎ ምላሽ መስጠት እንችላለን?

3.እስቲ ጥቂት ጊዜ በመስጠት በእግዚአብሔር ኃይል እና በፍጥረት ታሪክ እንዲሁም በፍጥረት ራሱ በተገለጠው የእግዚአብሔር ጉልበት ላይ በማሰላሰል ያሳልፉ። ዩኒቨርስ የሚባለው እጅግ ትልቅ ከመሆኑ እና ከመግዘፉ የተነሣ ዩኒቨርስ የሚባለውን እሳቤ ለመጨበጥ በጣም ያዳግተናል። ደግሞም ይህንን የፈጠረው እግዚአብሔር ከፈጠረው በላይ ትልቅ ነው ብለን እስቲ እናሰላስል። እኛ የምናገለግለው አምላክ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ማወቃችን እንዴት አድርጎ ምቾት ይፈጥርልናል? ደግሞም ኃያልነቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያፈቅር አምላክ ነው። ስለ እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች በማወቃችን የምናገኘው ትልቅ ተስፋ ምንድነው? ደግሞስ ይህንን ዕውቀት ተጠቅመን ለሌሎች ስለ እርሱ ለመመስከር የምንችለው እንዴት ነው?