የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከሐምሌ 25 - ነሐሴ 1

6ኛ ትምህርት

Aug 01 - Aug 07
ያልተገደቡ አማራጮችሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት፡- 1ኛ ቆሮ 12÷12፣ ማቴ 3÷16-18፣ 1ኛ ቆሮ 12÷7፣ 1ኛ ቆሮ 1፡4-9፣ ማቴ 25÷14-30 ያንብቡ።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።” (1ኛ ቆሮ 12÷11)

እ ግዚአብሔር ለእርሱ እንድንመሰክር ይጠራናል (ሐዋ 1÷8፣ኢሳ 43÷10) ምስክርነት ጥቂቶች ብቻ የታደሉት የመንፈስ ስጦታ አይደለም። ምስክርነት እያንዳንዱን ክርስቲያን የሚመለከት መለኮታዊ ጥሪ ነው። ይህንን ጥሪ መፅሐፍ ቅዱስ በተለያየ መልክ ይገልፀዋል፤፤ “የአለም ብርሀን” (ማቴ 5÷10) “የክርስቶስ መልዕክተኞች” (1ኛ ቆሮ 5፡20) እንዲሁም “የንጉስ ካህናት” (1ኛ ጴጥ 2÷9) በማለት ይገልፀናል። ይህን ሀላፊነት እንድንወጣ የጠራን ጌታ እንዲሁ ለስራው ደግሞ ያስታጥቀናል። የመንፈስ ስጦታን ለእያንዳንዱ አማኝ ያድላል።

እግዚአብሔር ብቁ የሆኑትን አይደለም ሚጠራው። የጠራቸውን ብቁ ያደርጋቸዋል እንጂ። በተመሳሳይ ሁኔታ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ በነፃ ድነት ይሰጣቸዋል፤ የመንፈስ ስጦታንም እንዲሁ። እራሳችንን ለእግዚአብሔር ቀድሰን በምናስረክብበት ጊዜ ቁጥር ስፍር የሌላቸው እርሱን ማገልገል የምንችልባቸው አማራጮች አሉ። የራሱን ምርጫ ወደ ጎን ትቶ፤ ለጌታ ሙሉ በሙሉ የተቀደሰ ህይወት በመኖር ለመንፈስ ቅዱስ አሰራር በልቡ ቦታ የሚሰጥ ሰው ገደብ የሌለው ጥቅም ያገኛል።

በዚህ ሳምንት ጥናታችን በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አማካኝነት ስለምናገኛቸው ያልተገደቡ የአገልግሎት አማራጮች እንመለከታለን። ለ7ኛ ሰንበት ትምህርት ለመዘጋጀት የዚህ ሳምንት ትምህርት ያንብቡ።

ሐምሌ 26
Aug 2

6 ለአገልግሎት የተባበሩ፤ የተለያዩ የመንፈስ ስጦታዎች


ደቀመዝሙርት አንዳቸው ከአንዳቸው ምን ያህል የተለያዩ እንደሆኑ አስተውለው ያውቃሉ? አመጣጣቸው፣ ማንነታቸው፣ ተፈጥሮአቸው እና ስጦታቸው በእጅጉ የተለያየ ነበር። ይህ ግን ለቤተክርስትያን ተግዳሮት አልነበረም ይልቁንም ጥንካሬ ሆነ እንጂ። ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ ቁርጠኛ እና ሀቀኛ ነበር። በተቃራኒው ጴጥሮስ ደግሞ ለንግግር የሚቸኩል፣ ስሜታዊ እና ፈጣን ነበር ነገር ግን ተፈጥሮአዊ የአመራር ክህሎት ነበረው። ዮሐንስ ሩህሩህ ነበር ነገር ግን የተሰማውን ከመናገር ወደኃላ የማይል ነበር። እንድርያስ በማህበራዊ ህይወቱ ጠንካራ ነበር፤ ሌሎች የሚደርሱበት መንገድ የሚያሳስበው፤ ዙሪያ ገባውን የሚያስተውል ሰው ነበር። ቶማስ ጠያቂ ነበር አብዛኛውን ግዜም ተጠራጣሪ ነበር። እነዚህ ደቀመዛሙርት እያንዳንዳቸው የተለያየ ማንነት እና ስጦታ ቢኖራቸውም ለእርሱ ምስክር እንዲሆኑ እግዚአብሔር በሐይል ተጠቅሞባቸዋል።

1ኛ ቆሮ 12÷12-13፣ 18-22 ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የክርስቶስ አካል በሆነው ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰዎች ስላላቸው የተለያየ ስጦታ አስፈላጊነት ምን እናስተውላለን?እግዚአብሔር የተለያየ አመጣጥ፣ ክህሎት እና ብቃት ያላቸውን ሰዎች ወስዶ ለአገልግሎት የሚያበቃቸውን የመንፈስ ስጦታ በመስጠት ይደሰታል። የክርስቶስ ብልቶች ሁሉም አንድ አይነት የሆኑ ተመሳሳይ ሰዎች አይደሉም። ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውም አይሆኑም። ቤተክርስትያን በክርስቶስ እና በቃሉ ፍቅር ተዋህደው፤ ይህን ፍቅር እና እውነት ለአለም ለማጋራት የቆረጡ የተለያየ ስጦታ ያላቸው ሰዎች፤የተጋጋለ እንቅስቃሴ ውጤት ነች። (ሮሜ 12÷4 1ኛ ቆሮ 12÷12)።

የክርስቶስ አካላት የተለያየ ስጦታ አላቸው፤ እያንዳንዱ ትልቅ ዋጋ ያለው ሲሆን፤ ሁሉም ለክርስቶስ አካላት ጤናማ እንቅስቃሴ ወሳኝ ናቸው። አይን፣ ጆሮ እና አፍንጫ የተለያየ አገልግሎት ኖሯቸው ለሰው አስፈላጊ እንደሆኑ፣ ሁሉም ስጦታዎች አስፈላጊ ናቸው። (1ኛ ቆሮ 12÷21-22) የሰውነት አካሎቻችሁን ስትመለከቱ ትናንሽ አካላት ሳይቀሩ ወሳኝ ሚና አላቸው። የአይን ሽፋሽፍቶችን ያስተውሉ። ሲታዩ ጠቃሚ ማይመስሉት የአይን ሽፋሽፍቶቻችን ባይኖሩን የአቧራ ብናኞች ዕይታችንን ይጋርዱብናል፤ ከዚህ የተነሳ ታክሞ ሊድን የማይችል ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል። ምናልባትም ያን ያህል አስፈላጊ የማይመስለው የቤተክርስቲያን አባል ወሳኝ የሆነ የክርስቶስ አካል እና የመንፈስ ስጦታ የተቸረው ነው። እነዚህን ስጦታዎች ለእግዚአብሔር ስናውላቸው እያንዳንዳችን ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንችላለን።3

ምንም እንኳን ልዩ ክህሎት ያሎት ቢሆንም እርሶ ማድረግ የማይችሉት ሌሎች አባላት ማድረግ የሚችሏቸው ነገሮች ምንድናቸው? ይህ እንዴት በተገቢው ስፍራችን እንድንገኝ ያደርገናል?

ሐምሌ 27
Aug 3

7 የሁሉም በጎ ስጦታዎች ሰጪ


1ቆሮ 12÷11፣ 18፣ ኤፌ 4÷7፣8፣ እና ያዕ 1÷17 ላይ እንደተጠቀሰው የሁሉም ስጦታዎች ምንጭ እግዚአብሔር ነው፤ “ፍፁም በረከት ሁሉ” ከእርሱ ይወርዳል። ስለዚህ ከማንነታችን ጋር የሚስማሙ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሰጥቶን የእርሱን ሀሳብ እንድናገለግል እና ስሙን ለማክበር እንደሚጠቀምብን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ማር 13÷34 እና 1ቆሮ 12÷11 ያንብቡ። እግዚአብሔር ለማን ነው የመንፈስ ስጦታዎች የሚሰጠው?መፅሐፍ ቅዱስ በግልፅ እንዳስቀመጠው እያንዳንዳችን ለሌሎች ወንጌል የማካፈል ልዩ የቤት ስራ አለን። በማር 13÷24 በእየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው፤ ቤቱን ጥሎ በሔደ ግዜ ለባሮቹ ቤቱን እንዲጠብቁ አዘዛቸው፤ ለእያንዳንዱ የሚሆን ሥራም ሰጥቷቸዋል። እያንዳንዱ ግለሰብ ሥራ ተሰጥቶታል፤ ይህንን የተጠሩለትን ስራ መፈፀም እንዲችሉ እግዚአብሔር ለሁሉ የመንፈስ ስጦታ ይሰጣል። ህይወታችንን ለክርስቶስ አሳልፈን ሰጥተን በጥምቀት የእርሱ አካል የሆነችው የቤተክርስቲያን አካል ሆነን በምንቀላቀልበት ጊዜ ይህንን አካል እንድናገለግል እና ለአለም እንድንመሰክር መንፈስ ቅዱስ ስጦታ ይሰጠናል።

በ1903 ዓ.ም እ.ኤ.አ ኤለን ጂዋይት የተሰጠውን መክሊት ለአገልግሎት እንዲጠቀምበት አንድ ሰውን ለማበረታት ደብዳቤ ፅፉ ነበር። “ሁላችንም የእግዚአብሔ ር ቤተሰብ ነን። መጠኑ ሊለያይ ቢችልም ተጠያቂ የምንሆንባቸው እግዚአብሔር የሰጠን መክሊቶች አሉን። መክሊቶቻችን ብዙ ቢሆኑ ወይም ጥቂት እግዚአብሔርን ለማገልገል ልንጠቀምባቸው እና ሌሎችንም በተሰጣቸው መክሊት ተጠቅመው ለሚያቀርቡት አገልግሎት እውቅና መስጠት አለብን።

“የትኛውንም አካላዊ፣ አዕምሮአዊ ወይም መንፈሳዊ አቅም መናቅ የለብንም።“የካቲት፣1903። ሐዋ 10÷36-38፣ ማቴ 3÷16-18፣ ሐዋ 2÷38-42 ያንብቡ እነዚህ ጥቅሶች በጥምቀት ወቅት ስለ መንፈስ ቅዱስ ምን አይነት ተስፋ እንዳለ ያስተምሩናል?ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ግዜ ለቀጣይ አገልግሎት ብቁ የሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደተቀበለ እያንዳንዳችን በጥምቀት ወቅት መንፈስ ቅዱስን እንደምንቀበል ተስፋ ተሰጥቶናል። ቃሉን አክብሮ ለቤተክርስቲያን እና ለአለም በረከት እንድንሆን የመንፈስ ስጦታዎች እንደሚሰጠን እርግጠኛ እንድንሆንለት ይፈልጋል።

ሐምሌ 28
Aug 4

8 የመንፈስ ስጦታዎች አላማ


1ቆሮ 12÷7 እና ኤፌ 4÷11-16ን አንብቡ። እግዚአብሔር የመንፈስ ስጦታዎችን የሚሰጥበት ምክንያት ምንድነው? የነዚህ ስጦታዎች አላማ ምንድነው?የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በርካታ አላማ አላቸው። ስጦታዎቹ የሚሰጡት ቤተክርስትያን የእርሱን አገልግሎት ከፍፃሜ እንድታደርስ ለማስቻል ነው። ለአለም ላይ ያላትን ተልዕኮ ከግብ የምታደርስ በአንድነት የቆመች ቤተክርስቲያንን እንዲፈጥሩ ታልመው ነው ስጦታዎቹ የሚሰጡን። እንደ ማገልገል፣ መስበክ፣ ማስተማር፣ ማበረታታት፣ እና መስጠት ያሉ የመንፈስ ስጦታዎችን ለቤተክርስትያን እንደተሰጠ የመፅሐፍ ቅዱስ ፀሀፍያን ፅፈዋል። እንግዳን ስለ መቀበል፣ ምህረት ስለ ማድረግ፣ ስለ እርዳታ፣ እና ስለ ደስተኛነት ስጦታዎችም ይነግሩናል። ሮሜ 12 እና 1ቆሮ 12 ላይ እነዚህ ስጦታዎች ከሞላ ጎደል ተጠቅሰዋል።

በተፈጥሮአዊ ክህሎቶቻችን እና በመንፈስ ስጦታዎቻችን መሀል ስላለው ግንኙነት እያሰቡ ሊሆን ይችላል። መንፈሳዊ ስጦታዎች በቤተክርስትያን እና በአለም ላይ ላለው ልዩ አገልግሎት አማኞችን ለማስታጠቅ መለኮት የሚያድላቸው ብቃቶች ናቸው። እነዚህ ስጦታዎች በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው ለክርስቶስ አገልግሎት የዋሉ ተፈጥሮአዊ ክህሎቶችንም ያካትታሉ። ሁሉንም ተፈጥሮአዊ ክህሎቶችን የሰጠን እግዚአብሔር ነው፤ ነገር ግን ሁሉንም ለክርስቶስ አገልግሎት ላንጠቀምባቸው እንችላለን።

“የመንፈስ ስጦታዎች በምሳሌው ላይ የተጠቀሱት መክሊቶች ብቻ አይደሉም። ተፈጥሮአዊ ሆኑ መንፈሳዊ፣ የተማርናቸው ሆኑ የታደልናቸው፣ ሁሉንም ስጦታዎች ያካትታል። ሁሉንም ለክርስቶስ አገልግሎት መጠቀም አለብን። የእርሱ ደቀመዝሙር ስንሆን የሆነውን እና ያለንን ጠቅልለን ለእርሱ አሳልፈን እንሰጣለን። እነዚህን ለእርሱ የሰጠናቸውን ስጦታዎች ለሰዎች በረከት ለእርሱ ደግሞ ክብር እንዲሆኑ አጥርቶ እና አክብሮ ይመልስልናል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ሐዋርያት፣ ነብያት፣ ወንጌል ሰባኪዎች እና የቤተክርስትያን ሽማግሌዎች ሌሎች አባላትን እንዲያበረቱና እንዲያስታጥቋቸው ለአገልግሎት ተሹመዋል። (ኤፌ 4÷11-12)። የሁሉም የቤተ ክርስትያን አመራር ስራ ምዕመናን መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን ለይተው የክርስቶስን አካል ለመገንባት እንዲጠቀሙበት ማስተማር እና ማገዝ ነው። ለቤተክርስትያን በረከት መሆን የሚችል በግል ወይም በስራ ጉዳይ የሚጠቀሙበት ተፈጥሮአዊ ክህሎት ምንድነው?

ሐምሌ 29
Aug 5

9 ስጦታዎቻችንን መለየት


1ኛ ቆሮ 1÷4 ን ከ 2ኛ ቆሮ 1÷20-22 ጋር ያነፃፅሩ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ተስፋ በተለይም ደግሞ ከዳግም ምጻቱ ጋር ተያይዞ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ምን ይነግሩናል?እግዚአብሔር የእርሱ ቤተክርስትያን ከክርስቶስ ዳግም ምጻት አስቀድሞ ሁሉንም የመንፈስ ስጦታዎች እንደምታንፀባርቅ ቃል ገብቷል። ቃሉንም ከቶ አያጥፍም። የተሰጡንን ስጦታዎች እንድናስተውል ለልባችን ሹክ የሚለን የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሰጥቶናል። ስጦታዎችን የሚሰጠን እግዚአብሔር ሲሆን በመንፈሱ በኩል ደግሞ የሰጠንን ይገልፅልናል።

ሉቃ 11÷13፣ ያዕ 1÷5፣ማቴ 7÷7 ያንብቡ። እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ለማወቅ ከፈለግን ማድረግ የሚገባን ነገር ምንድነው?እራሳችንን ለጌታ አሳልፈን ከሰጠን በኋላ የሰጠንን ስጦታዎች እንድናስተውላቸው እንዲረዳን ስንጠይቀው ስጦታዎቻችንን እናገኛቸዋለን። ከመመፃደቅ እራሳችንን አርቀን ዋናው ጉዳያችን እሱን ማገልገል በሚሆንበት ጊዜ፤ የእርሱ መንፈስ ለእኛ ባዘጋጃቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች ያስደንቀናል።

“ደቀመዛሙርት በእምነት እና በፀሎት ራሳቸውን ለእርሱ ስራ አሳልፈው እስኪሰጡ ድረስ የመንፈስ ቅዱስ መሞላት አልተቀበሉም ነበር። ያንን ባደረጉ ጊዜ ግን የሰማይ በረከቶች በሙሉ በተለየ መልክ ለክርስቶስ ተከታዮች ተላልፈው ተሰጡ . . . እነዚህ ስጦታዎች በክርስቶስ በኩል የኛ ሆነዋል። ነገር ግን የመቀበላችን ጉዳይ የሚወሰነው የእግዚአብሔርን መንፈስ በምናስተናግድበት ሁኔታ ነው።“ (Ellen G. White, christ object lesson p.327)

መንፈሳዊ ስጦታዎች (1ቆሮ 12÷4-6) እርሱን በስኬት እንድናገለግል የሚሰጡን ችሎታዎች ናቸው። ቤተክርስትያን እነዚህ ስጦታዎቻችንን የምንጠቀምባቸው ስፍራዎች ሲሆኑ፤ አገልግሎቶቻችን ደግሞ እነዚህን ስጦታዎቻችንን የምንገልፅባቸው መንገዶች ናቸው። መንፈሳዊ ስጦታዎች ሙሉ በሙሉ በልፅገው እና ጎልብተው አይመጡም። መንፈስ ቅዱስ ለተለየ አገልግሎት ሲያነሳሳን፤ ለሰዎች ወንጌልን ወጥቶ በማድረስ፣ ስጦታዎቻችንን እንድንገልፅ መፀለይ አለብን።

የመንፈስ ስጦታ ምንድነው? በተለይም እነዚህ ስጦታዎች ለጌታ አገልግሎት የበለጠ ማሳደግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ሐምሌ 30
Aug 6

0 ስጦታዎችን ማሳደግ


በማቴ 25:14–30 የተጠቀሰውን የመክሊት ሰጪ ሰው ታሪክ ያንብቡ። በዚህ ታሪክ ውስጥ በዋናነት የተንፀባረቀው ትምህርት ምንድነው? የመጀመሪያዎቹ ሁለት አገልጋዮች ተመስግነው የመጨረሻው የተረገመው ለምንድነው? ይህ ታሪክ መክሊቶቻችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን የሚያስተምረን እንዴት ነው? በተለይም ማቴ 25፡29 ን ልብ ይበሉ።ያ ሰው ለአገልጋዮቹ እንደየአቅማቸው ነበር መክሊት የሰጣቸው።(ማቴ 25፡15) እያንዳንዱ ሰው የተለያየ መጠን ነበር የተቀበለው። አንዱ አምስት፣ሌላው ሁለት ሌላው አንድ። እያንዳንዱ አገልጋይ የተሰጠውን መክሊት በምን መልክ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለበት የሚወስነው እራሱ ነበር። እዚህ ጋ መስተዋል ያለበት ወሳኝ ነጥብ የተሰጣቸው መክሊት የራሳቸው እንዳልሆነ ነው። መክሊቶቹ በሀላፊነት የሾማቸው ሰው ንብረት ናቸው።

የመክሊቶቹ ባለቤት ማን ብዙ መክሊት ማን ትንሽ መክሊት ተሰጥቶታል የሚለው ጥያቄ አይደለም የሚያሳስበው። የሱ ጭንቀት በተሰጣቸው መክሊት ምን ሰሩበት የሚለው ነው። ጳውሎስ በ 2ኛ ቆሮ 8፡12 ላይ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል። “በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።” እግዚአብሔር ግድ የሚለው ምን ያህል አለን የሚለው ሳይሆን ባለን ምን አረግንበት የሚለው ነው። እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሁለት አገልጋዮች ስለታማኝነታቸው አመሰገናቸው።

መክሊታቸውን በመጠቀማቸውም በዛላቸው። ያ ክፉ አገልጋይ ግን የተሰጠውን መክሊት ባለመጠቀሙ አልበዛለትም። “የአገልጋይነት መንፈስ ከእግዚአብሔር እና ከሰዎች ጋር የሚያዛምደን ገመድ ነው።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 326. ያ ክፉ አገልጋይ ይህንን የማገልገል ዕድል አባክኖ በስተመጨረሻም ማገልገል የሚችልበትን መክሊት እራሱ ተነጠቀ። እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ለስሙ ክብር በምንጠቀምበት ጊዜ ይበዛሉ፣ እንዲሁም ያድጋሉ። እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች እንዴት ነው መለየት የምንችነው? ለእርሱ አገልግሎት ሊጠቀመን ያቀደበትን መንገድ እንዲያሳውቀን በትህትና መፀለይ አለብን። ሲናገረን ደግሞ ወዲያው ተግባር ላይ ማዋል ይኖርብናል። በምንጠቀምባቸው ወቅት ስጦታዎቻችን ያድጋሉ። በአገልግሎታችንም እንረካለን።

ስለ ምሳሌው እስቲ ያሰላስሉ ፤በራስዎ ህይወት ላይም ተግባራዊ ያድርጉት። እግዚአብሔር በሰጠዎት ስጦታ ምን አይነት ተግባር እየፈፀሙ እንዳለ አንዳች ትምህርት ይሰጥዎ ይሆን? ያለዎት ነገር በሙሉ የእግዚአብሔር መሆኑን ያስተውሉ።

ነሐሴ 1
Aug 07


ተጨማሪ ሐሳብ


ኤለን ጂ.ኋይት፤Christ object lessons ላይ የፃፈችውን “መክሊቶች” የሚለውን ምዕራፍ ያንብቡ። p. 325-365. ስለ መንፈሳዊ ስጦታ መፅሀፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን በትክክል ስንረዳ ቤተክርስቲያን ወደ አንድነት ታመራለች። እያንዳንዳችን ዋጋ ያለን እና አስፈላጊ የክርስቶስ አካል ብልቶች መሆናችንን ማስተዋል ወደ አንድነት የሚመራ እሳቤ ነው። የክርስቶስ ተልዕኮን ለማሳካት እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አባል አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ አባል ለአገልግሎት እንዲውል የተሰጠው ስጦታ አለ።

“እያንዳንዱ ሰው ለጌታ የሚሰራው ስራ አለ። ለእያንዳንዱ አገልጋይ ደግሞ የተሰጠው ልዩ ስጦታ ወይም መክሊት አለው። ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አቅሙ አንድ፤ሁለት ፣ ወይም አምስት መክሊት ተሰጥቶታል። እያንዳንዱ አገልጋይ በሀላፊነት የተሰጠውን ስራ እንደሚወጣ እምነት ተጥሎበታል፤ ባለን አቅም መጠን እንደምናገለግል እምነት ተጥሎብናል። ስጦታዎችን በማከፋፈል ረገድ ፤ እግዚአብሔር አድሎ የለበትም። ለአገልጋዮቹ እንደየአቅማቸው ነው የሰጣቸው፤ ያንኑ ያህል ምላሽ ደግሞ ይጠበቅባቸዋል።“ Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 2, p. 282.

እነዚህ ስጦታዎች የተሰጡት ለእራሳችን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር እንዲውሉ ነው። ስጦታዎቹ የተሰጡበት ጥንስስ እና መነሻ የእርሱን ስም ማክበር ነው።


የመወያያ ጥያቄዎች1.እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ እንዳለ ጠለቅ ብለው ጊዜ ወስደው ያሰላስሉ። ይህ ለአጥቢያ ቤተክርስትያንዎ ምን አይነት ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው? ይህ አስተሳሰብ ሁሉንም አባል በአገልግሎት በማሰለፍ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?

2.ለሰንበት ትምህርት ክፍልዎ አባላት የሌሎች አባላት ስጦታ እንዴት እንደባረኮት ያጋሩ። የራስዎን መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዴት እንዳገኙ ያካፍሏቸው፡፤ መንፈሳዊ ስጦታዎ ምን ምንድናቸው? ሌሎችንስ ለመባረክ በምን መልኩ እየተጠቀሙባቸው ነው?

3.ይህ ትምህርት ስጦታዎቻችን የሚያድጉት ስንጠቀምባቸው እንደሆነ አስተምሮናል። ዞር ብለው ህይወትዎን ይመልከቱ። ለስሙ ክብር ስለተጠቀሙበት ያደገልዎ መክሊት አለ? በተመሳሳይ ሁኔታ በሐሙሱ ክፍል መጨረሻ ላይ ያለውን ጥያቄ ድጋሚ እራስዎን ይጠይቁ፤ እግዚአብሔር በሰጥዎ ስጦታ ምን ያህል ታማኝ ነዎት?