የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከሐምሌ 18 - ሐምሌ 24

5ኛ ትምህርት

Jul 25 - Jul 31
በመንፈስ የተሞላ ምስክርነትሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት ፡- ዮሐ.15÷26፣27፣ ሐዋ.2÷41፣42፣ ሐዋ.8÷4 ዕብ.4÷12፣ ሐዋ.17÷33፣ 34 ፣ ሐዋ. 18÷8 ያንብቡ ።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።” (ሐዋ.4÷31)

ኢ የሱስ ክርስቶስ የቀደሙ አማኞችን “ወደ አለም ሁሉ ሔደው ወንጌል እንዲሰብኩ” (ማር 16÷15) ሲያዛቸው ከቶ የማይቻል ተልዕኮ መስሏቸው ሊሆን ይችላል። እንዴት ብለው ያንን ታላቅ ትዕዛዝ ይወጡታል? ቁጥራቸው ጥቂት ነበር። ሐብታቸውም የተመናመነ ነበር። በአብዛኛው ያልተማሩና ከተራው ማህበረሰብ የተውጣጡ ነበሩ። ነገር ግን ከተለመደው ውጪ ታላቅ ተልዕኮን እንዲወጡ የሚያስችላቸው ታላቅ አምላክ ነበራቸው። ኢየሱስም እንዲህ በማለት ተናገረ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (ሐዋ.1÷8) የመንፈስ ቅዱስ መሞላት ነበር የመስቀሉን እውነት አለምን በሚቀይር መልክ እንዲያስተላልፉ ሐይል የሆናቸው።

መንፈስ ቅዱስ ምስክርነታቸውን ውጤታማ አደረገው። በጥቂት አስርት አመታት ወንጌል አለምን አነቃነቀ። የሐዋርያት ስራ እነዚህ አማኞች “አለምን እንዳወኩ” (ሐዋ።17÷6) ይነግረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ወንጌል “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” እንደተሰበከ ይነግረናል። (ቆላ 1÷23) በዚህ ሳምንት ጥናታችን፤ምስክርነታችንን በማበርታት መንፈስ ቅዱስ የሚጫወተውን ሚና እንመለከታለን። ለስድስተኛው ሰንበት ትምህርት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ሐምሌ 19
Jul 26

9 እየሱስ እና የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ተስፋ


እየሱስ ደቀመዛሙርትን ትቶ ወደ ሰማይ በመመለሱ የተፈጠረባችውን ፍርሀት ያከመው የመንፈስ ቅዱስ መውረድን ተስፋ በመስጠት ነበር።”እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል።እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።”(ዮሐ።16፡7)አፅናኝ የሚለው ቃል በግሪክ ጰራቅሊጦስ ሲሆን እርዳታ ወይም ድጋፍ ለመስጠት አብሮ የሚሆንን ሰው የሚገልፅ ነው። የመንፈስ ቅዱስ አንዱ እና ዋንኛው ተግባር በምስክርነት ግዜ ከአማኞች አጠገብ አብሮ በመሆን ሀይልንና ምሪትን መስጠት ነው። ለእየሱስ በምንመሰክርበት ጊዜ ብቻችንን አይደለንም። እውነትን ሊሰሙ ወደሚወዱ ልበ-ቅኖች ሊመራን አብሮን ይሆናል። እኛ እነሱን ከማግኘታችን አስቀድሞ ልባቸውን ያዘጋጃል።አንደበታችንን መንፈስ ቅዱስ ይቆጣጠራል፤ የአድማጮችን ህሊና ይወቅሳል እንዲሁም ለጥሪው ምላሽ እንዲሰጡ ያበረታታቸዋል።

ዮሐ።15÷26-27 እና ዮሐ.16÷8 ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በምስክርነት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ስለሚኖረው ሚና ምን ይነግሩናል?መንፈስ ቅዱስ የሚመሰክረው ወይም ደግሞ የሚያብራራው ስለ እየሱስ ክርስቶስ ነው። የመንፈስ ቅዱስ የመጨረሻ ግብ ጥሪውን ሊቀበሉ የወደዱ ሰዎችን በሙሉ ወደ እየሱስ ክርስቶስ መምራት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ዋነኛ ተልዕኮ እየሱስን ማክበር ነው። ስለዚህም አማኞች ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክሩ ያነሳሳቸዋል። በዙሪያችን ላሉ ሰዎች መመስከር የምንችልበትን እድል እንድንመለከት አይናችንን በመክፈት እነርሱ ደግሞ የወንጌሉን መልዕክት እንዲቀበሉ ሁኔታውን ያመቻችላቸዋል። የዮሐንስ ወንጌል “አለምን ስለ ሐጥያት ይኮንናል” በማለት በግልፅ ያስቀምጣል።

(ዮሐ 16÷8)። በሌላ አነጋገር ከእግዚአብሔር ምን ያህል እንደራቁ በማሳየት ንስሀ እንዲገቡ ልባቸውን ይኮረኩራል። ስለ ፅድቅም ደግሞ አለምን ይወቅሳል። መንፈስ ቅዱስ የሰራነውን ሐጥያት ገልፆ ማሳየት ብቻ ሳይሆን በፅድቅ እንድንመላለስም ደግሞ ያስተምረናል። ከእኛ የቆሸሸ ማንነት ከቶ የማይነፃፀር እና የራቀ ቅድስና ያለውን እየሱስን ያሳየናል። የመንፈስ ቅዱስ ስራ ምን ያህል ክፉዎች እንደሆንን ማሳየት ብቻ ሳይሆን፤ እየሱስ ደግሞ ምን ያህል መልካም፣ ሩህሩህ፣ አዛኝ እና አፍቃሪ እንደሆነ በማሳየት እሱን እንድንመስል መቅረፅ ነው።

በቀላሉ ምስክርነት ማለት እየሱስን ለማክበር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መተባበር ነው። በመንፈስ ሀይል እና ምሪት ውስጥ በመሆን ህይወታችንን ስለቀየረው ጌታ እንመሰክራለን። ነፍሳትን የማዳን ስራ በምንሰራበት ወቅት ፤ የልብ መለወጥን የምናመጣው እኛ ሳንሆን መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ማስታወስ ያለብን ለምንድነው?

ሐምሌ 20
Jul 27

0 በሐይል የተሞላች ቤተክርስቲያን


የሐዋርያት ስራ መፅሀፍ “የመንፈስ ቅዱስ ስራ” ተብሎ መጠቀሱ ትክክል ነው። አስደሳች የምስክርነት፣ የወንጌል ሰበካ እና የቤተ ክርስቲያን እድገት ገድልን የሚዘግብ መፅሀፍ ነው። የሐዋርያት ስራ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት ለክርስቶስ ቀንተው አለም ላይ ተፅዕኖ ስላሳደሩ ሰዎች የሚተርክ ነው። አስደናቂ የሆነ ውጤትን ማስገኘት የቻሉት ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ላይ በመደገፋቸው ነበር። የእነርሱ ህይወት ራሳቸውን አሳልፈው በሚሰጡ ወንዶች እና ሴቶች ልጆቹ በመጠቀም መንፈስ ቅዱስ ሊሰራ የሚችለው ስራ ማሳያ ነው።

የሐዋርያት ስራ 2÷41፣ 42፤ ሐዋ 4÷4 እና 31፣ ሐዋ 5÷14፣42 ፤ ሐዋ 6÷7 እና ሐዋ 16÷5ን ያንብቡ ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን ልብ የሚነካ ነገር አገኙ? የሐዋርያት መፅሀፍ ፀሀፊ የሆነው ሉቃስ እንደነዚህ አይነት ፈጣን እድገቶችን በመዘገብ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ምንድነው?ሉቃስ የሐዋርያት ስራ መፅሐፍን የፃፈበት አላማ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የሰራውን ስራ ለማጋራት ነው። በዚህ የመጀመሪያ ክፍለ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴን ለማሳየት የቁጥር መግለጫዎችን መጠቀሙንም ልብ ይበሉ። ይህም የተጠማቂያን ቁጥር ነው። በሐዋ.2÷41፣ በአንድ ቀን 3000 ሰዎች ስለመጠመቃቸው ይናገራል። በሐዋ.4፡4፤ አምስት ሺህ ሰዎች ፤ በሐዋ.5÷14 ላይ ደግሞ ብዙዎች እንደተጨመሩ ይዘግባል። እንደ ሊድያ፣ እንደ ፊሊጲሲውሱ ወይኒ ጠባቂ፣ የምዋርተኝነት መንፈስ እንደነበረባት ገረድ ወይም እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን የመንፈስ ቅዱስን ስራ ሉቃስ ተከታትሎ ይዘግባል። ዋናው ነጥብ ከእያንዳንዱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጉባኤ ውስጥ እየሱስ ሞቶለት የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ግለሰብ መኖሩ ነው።

አዎን እንድንበዛ እንፈልጋለን ቢሆንም ግን፤ ምስክርነት በአብዛኛው የአንድ ለአንድ ጥረት ውጤት ነው። የአዲስ ኪዳን ቤ/ክ እድገትን ለማፋጠን ፤ አዳዲስ አብያተ-ክርስቲያናት ተተክለዋል። የጥንቷ ቤተክርስቲያን በፍጥነት ካደገችበት ምክንያቶች አንዱ አዳዲስ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ከእርስዋ ስር እየወጡ ይመሰረቱ ስለነበር ነው። ዛሬም ቢሆን ለእኛ እንዴት ያለ ታላቅ ትምህርት ነው። የአዲስ ኪዳን ቤተክርስትያን ዋንኛ ትኩረት ተልዕኮዋ ላይ ነበር። በአጥቢያ ቤ/ክ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዋንኛ ማዕከል ታላቁ ተልዕኮ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 21
Jul 28

1 መንፈስ ቅዱስ እና ምስክርነት


በመላው የሐዋርያት መፅሀፍ መንፈስ ቅዱስ በሐይል ተገልጧል። አማኞች በተለያየ መንገድ ስለ ጌታ በሚመሰክሩበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አግዟቸዋል እንዲሁም አማኞችን በመጠቀም ሌሎችን አገልግሏል። በከባባድ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው በመመስከራቸው የደረሰባቸውን ተግዳሮትና ፈተና እንዲቋቋሙ ብርታት ሆኗቸዋል። ወደ ልበ-ቅን እውነት ፈላጊዎችም መርቷቸዋል። ወደ አንድ አላማ ከማምራታቸው ቀደም ብሎ የከተማውን ነዋሪዎች ልብ የማዘጋጀት ስራ ይሰራ ነበር። ከቶውንም ያላሰቡትን በሮች ይከፍትላቸው ነበር አንደበቶቻቸውንና ድርጊቶቻቸውንም ያበረታ ነበር።

የሐዋ 7÷55 ፣ ሐዋ 8÷29፤ ሐዋ 11÷15፣ ሐዋ 15÷28-29 እና ሐዋ 16÷6-10ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለምስክርነት የወጡ ደቀመዛሙርትን በምን መልኩ ነው ያገዘው? ወይም መንፈስ ቅዱስ በጥቅሶቹ ውስጥ ምን አይነት ሚና ነበረው?በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት በእውነትም አስደናቂ ነበር። ከላይ የተጠቀሱት መንፈስ ቅዱስ ከሰራቸው ስራዎች መሀል ለማሳያ ያክል የቀረቡ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። አቅላቸውን ስተው እና በጭካኔ ተሞልተው በድንጋይ በሚወግሩት ሰዎች ፊት እስጢፋኖስ ስለጌታው እንዲመሰክር አበረታው። ተዓምራዊ በሆነ መልክ ፊሊጶስን ተፅዕኖ ፈጣሪ እና እውነት ፈላጊ ወደ ሆነ ኢትዮጵያዊ መርቶ የአፍሪካ አህጉር በሯን ለወንጌል እንድትከፍት አደረጋት።

አህዛብ አማኞችም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደሚቀበሉ ለጴጥሮስ የማረጋገጫ ምልክት ሰጠው። በመገረዝ ጉዳይ ዙሪያ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ልትከፈል ጫፍ በደረሰችበት ወቅት ቤተክርስቲያንን ወደ አንድነት ሲያመጣ በሐዋርያው ጳውሎስ በኩል መላው የአውሮጳ አህጉር ለወንጌል የተከፈተ እንዲሆን አድርጓል። በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ንቁ ስራ እንደነበረ በዛሬዋ ቤተክርስቲያንም ሊሰራ ነቅቶ እየጠበቀ ነው። ሊያበረታን፣ ሊያጠነክረን፣ ሊያስተምረንና ሊመራን፣ አንድ ሊያደርገን እና የአለማችን ታላቅ ተልዕኮ ወደ ሆነው ሰዎችን ወደ ክርስቶስ እና ወደ እውነቱ ወ ደመምራት ሊያመጣን ይፈልጋል።

ማስታወስ ያለብን በጥንቷ ቤ/ክ እና በሐዋርያት ዘመን እንደነበረው ዛሬም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ ንቁ እና በስራ ላይ መሆኑን ነው። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕይወታችን እንዲገለጥ ክፍት እና ምቹ እንድንሆን ዕለት በዕለት ማድረግ የሚገባን ነገር ምንድነው? እኛን በመጠቀም እና በእኛ ውስጥ አልፎ እንዲሰራ የምናስችለው ምን አይነት ምርጫዎችን በመምረጥ ነው?

ሐምሌ 22
Jul 29

2 መንፈስ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔር ቃል እና ምስክርነት


የአዲስ ኪዳን ቤ/ክ ምስክርነት ማዕከል ያደረገው የእግዚአብሔርን ቃል ነበር። ጴጥሮስ በጴንጠቆስጤ ቀን ባደረገው ስብከት ክርስቶስ መሲህ መሆኑን ለማረጋገጥ በርካታ የብሉይ ኪዳን መፅሐፍትን ጠቅሷል። እስጢፋኖስም እየሞተ የመሰከረው ምስክርነት በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰ የእስራኤል ታሪክ ነበር። ጴጥሮስ“እግዚአብሔር ቃሉን በክርስቶስ እየሱስ ለእስራኤል ልጆች እንደላከው” በሐዋ 10÷36 ላይ ይናገራል። ከዛም ለቆርነሌዎስ የትንሳኤውን ታሪክ አካፈለው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ የመሲሁን ምፃት በተመለከተ በብሉይ ኪዳን የተተነበየ ታላላቅ ትንቢቶችን ይጠቅሳል። ፊሊጶስ ደግሞ ለኢትዮጵያዊው እውቀት ፈላጊ በኢሳይያስ 53 ላይ የተጠቀሰውን ትንቢት አስፈላጊነት አስረዳው። በሁሉም አጋጣሚዎች ፤ ደቀ-መዛሙርት የራሳቸውን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ነበር ያወጁት። በመንፈስ የተመራ የቃሉ መረዳት የአገልግሎታቸው መሰረት ነበር።

ሐዋ 4÷4፣ 31፤ ሐዋ 8÷4 ሐዋ 13÷48፣ 49፣ ሐዋ 17÷2፣ ሐዋ 18÷24 ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በመንፈስ ቅዱስ፣ በእግዚአብሔር ቃል እና በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ምስክርነት መሐል ስለነበረው ቁርኝት ምን ያስተምሩናል።ቅዱሳን መፅሐፍትን እንዲፅፉ ሰዎችን የመራው ያው መንፈስ በቃሉ ውስጥ አልፎ የሰዎችን ህይወት የመለወጥ ስራን ይሰራል። መፅሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ህያው ቃል በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ህይወት- ሰጪ ሐይል አለ። 2ኛ ጴጥ 1÷21 እና ዕብ 4÷12ን ይንብቡ። የእግዚአብሔር ቃል የሰዎችን ህይወት የመለወጥ ከፍተኛ ሐይል የኖረው ለምንድነው?“አለማትን ካለመኖር ወደ መኖር የጠራቸው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለው የመፍጠር ሀይል ነው። ይህ ቃል ሐይል አለው፤ ሕይወት ይሰጣል። እያንዳንዱ ትዕዛዝ ተስፋ አለው፤ በደስታ ተቀብለው፤ ከሕይወትዎ ጋር ካዋሀዱት ዘለዓለማዊውን ሕይወት ይሰጣል። የተፈጥሮን ሕግ ቀልብሶ የሰውን ልብ እንደገና በእግዚአብሔር አምሳል ይፈጥራል። “(Ellen G. White, Education p.126). መፅሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ያለ ከፍተኛ ሰዎችን የመለወጥ ሐይል ያለው ቅዱስ ቃሉ እንዲፃፍ ሰዎችን ያነሳሳቸው ያው መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በምናነብበት ግዜ የመለወጥን መንፈስ ስለሚያሳድርብን ነው።

ለሌሎች ቃሉን በምናካፍልበት ወቅት ደግሞ ይኸው መንፈስ ቅዱስ በቃሉ በኩል ሕይወታቸውን የመለወጥ ስራ ይሰራል። እግዚአብሔር የእኛን ሳይሆን የራሱን ቃል ለማክበር ነው ቃል የገባው። ሐይል ያለው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንጂ በሰዎች ግምት ውስጥ አይደለም።

ሐምሌ 23
Jul 30

3 ህይወትን የሚቀይር የመንፈስ ቅዱስ ሐይል


የሐዋርያት መፅሐፍ በጥልቀት ሲጠና እግዚአብሔር በመንፈሱ በሰዎች ህይወት ውስጥ የሚሰራውን ድንቅ ያሳየናል። የሐዋርያት ስራ ወንጌል ልክ ባልሆኑ ባህላዊ አስተሳሰቦች እና ልማዶች ላይ ዘላቂ እና ስር-ነቀል ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ እንዲሁም የክርስቶስን ፀጋ እና እውነት በማስተማር ድል የሚቀዳጅ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ተግባራዊ ምሳሌ ነው። መንፈስ ቅዱስ የትም ድረስ ወርዶ ሰዎችን ያገኛቸዋል ፤ እዛው ግን አይተዋቸውም። በመገኘቱ ይለወጣሉ፤ ህይወታቸውም ይታደሳል።

ሐዋ 16÷11-15፣23-24 ፣ ሐዋ 17÷33፣ 34 እና ሐዋ 18÷8 ን ያንብቡ። እነዚህ በመፅሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከምናገኛቸው ጌታን የመቀበል ታሪኮች ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህ የተለያዩ ታሪኮች የእግዚአብሔር ሐይል ከየትኛውም ባህል እና ማንነት የመጡ ሰዎችን የመለወጥ አቅም እንዳለው የሚያሳየን እንዴት ነው?______

የሰዎቹ ብዝሐነት እንዴት የሚያስገርም ነው። ሊድያ ባለፀጋ የአይሁድ ነጋዴ ነበረች፣ የፊሊጲሲዎሱ ወይኒ ጠባቂ በመሐከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኝ የመንግስት ሰራተኛ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች መድረስ ይችላል። ወንዶች ሆኑ ሴቶች፣ ባለፀጋ ሆኑ ድሆች ፣ የተማሩ ሆኑ ያልተማሩ መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም መለወጥ ይችላል። የመጨረሻዎቹ ሁሉቱ ገፀባህሪያትም እንዲሁ አስደናቂ ናቸው። ሐዋ 17÷34 የኦርዮስ ፋጐሱን ዲዮናስዮስ መለወጥ ያስረዳናል። የአቴና አሪዮስ ፋጎሳውያን በፍርድ ቤት የሚፈርዱ የዳኞች ማህበር ናቸው። እጅግ የተከበሩ እና ወሳኝ የግሪክ ማህበረሰብ አባላት ነበሩ።

በመንፈስ ቅዱስ ሐይል፤ የሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎት የማህበረሰቡ ከፍተኛ መደብ አባላትን ሳይቀር ደረሰ። ቀርስጶስ (ሐዋ 18÷8) የአይሁድ ምኩራብ አለቃ ነበር። የአይሁድ ብሉይ ኪዳን አስተምህሮ የጠለቀ እውቀት የነበረው ሰው ነበር፤ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ ያንንም አልፎ ህይወቱን ቀየረው። እነዚህ የታሪክ ማጣቀሻዎች የእግዚአብሔርን ቃል እያካፈልን ስለ ክርስቶስ በምንመሰክርበት ጊዜ ከየትኛውም አመጣጥ ፣ ባህል፣ ትምህርት እና እምነት የተገኙም ቢሆን፤ በሰዎቹ ህይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አስደናቂ ነገሮችን የማድረግ ሐይል እንዳለው ነው።

መንፈስ ቅዱስ ማንን መድረስ ማንን ደግሞ አልፎ መሔድ እንደሚችል መገመት አንችልም ፤ መገመትም የለብንም። የኛ ስራ ወደ ህይወታችን ለመጡ ነፍሳት ሁሉ መመስከር ነው። የተቀረውን ጌታ ያከናውናል። የክርስቶስ ሞት አለምአቀፋዊ ነው። ማለትም ለሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር የተደረገ መስዋዕትነት ነው። ይህ ወሳኝ የሆነ እውነት ማንም ሰው ከድነት ተስፋ ውጪ እንዳልሆነ የሚያስረዳን እንዴት ነው?

ሐምሌ 24
Jul 31

4

ተጨማሪ ሐሳብ


የኤለን ጂ ዋይትን Acts of Apostles” የሚል መፅሐፍ “The gift of the spirit” የሚል ምዕራፍ ገፅ 47-56 ያንብቡ። በድነት እቅዱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብ እና ከእየሱስ ክርስቶስ ጋር ይተባበራል። ለምስክርነት በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፤ ሰዎችን በማዳን ተግባር እርሱን እየተባበርነው ነው። የምንመሰክርበትን ዕድል ይከፍትልናል። በእግዚአብሔር ቃል በኩል እውነትን በመግለጥ የሰዎችን አዕምሮ ያበራል።ያሰሩንን የአስተሳሰብ ብዥታዎችን ቀንበር ሰብሮ ነፃ ያወጣናል፣ የጠራ የእውነት መረዳት እንዳይኖረን በሚጋርዱን የባህል ማነቆዎች ላይ ድል ያቀዳጀናል። እንዲሁም ካሰሩን ክፉ የልማድ ትብታቦች ፈቶ ያወጣናል።

ለእየሱስ በምንመሰክርበት ጊዜ ፤ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እየተባበርን መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። እኛ እዛ ከመድረሳችን በፊት እርሱ የሰዎችን ልብ ለወንጌል በማዘጋጀት ስራ ላይ ተጠምዶ ነው የቆየው። በበጎነት በምናደርጋቸው ተግባራት፣ በምናካፍላቸው ምስክርነቶች፣ በምናስጠናቸው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ በምናድላቸው ትራክቶች እና ፅሁፎች ወይም በምንሳተፍባቸው የወንጌል ጥረቶች የሰዎችን ልብ ሊያነቃቃ አብሮን ይሆናል። ያንን ግለሰብ ጥለን ከሔድን በኋላም ወደ ድነት የሚያደርሰውን መረጃ እያቀበለ ስራውን ይቀጥላል።


የመወያያ ጥያቄዎች1.ከሰንበት ትምህርት ክፍል አባላቶቻችሁ ጋር በእናንተ ምስክርነት አልፎ መንፈስ ቅዱስ በሐይል ሲሰራ ያስተዋላችሁበትን አጋጣሚ ያካፍሉ።

2.እምነትዎን የማካፈል ፍርሐት ወይም መጨናነቅ ገጥሞት ያውቃል? የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎትን መረዳት ይህንን ፍርሀት ሊቀንስ የሚችለው በምን መልክ ነው?

3.በዚህ ሳምንት ጥናታችን በምስክርነት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ስለሚያከናውናቸው “ተግባራት” ተመልክተናል። ከዚህ ውጪ በምስክርነት ወቅት መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚያግዝባቸውን መንገዶች ያብራሩ። ነፍሳትን ለማዳን የምስክርነት ስራ ለመስራት መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚያስታጥቀን እንዴት ነው?

4.ትምህርቱ መፅሐፍ ቅዱስ የምስክርነታችን ማዕከል እንደሆነ ይናገራል። ለመሆኑ መፅሐፍ ቅዱስ የእምነታችን እና የምስክርነታችን ቁልፍ ቦታ የያዘበት ምክንያት ምንድነው? በመፅሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑ እየተናገሩ፤ ነገር ግን በስውር፤ ያለውን ስልጣን እና መልዕክት ከሚያንኳስሱ ሰዎች ወጥመድ ማምለጥ የምንችለው እንዴት ነው?