የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከሰኔ 27 - ሐምሌ 3

2ኛ ትምህርት

Jul 04 - Jul 10
ተወዳጅነት ያለው ምስክርት፦ የግል ምስክርነት ሀይልሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ፡- ማር.5፡15-20፤ ማር.16፡1-11፤ ሐዋ. 4፡1-20፤ 1ዮሐ.1፡1-3፤ ገላ.2፡20፤ ሐዋ.26፡1-32።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።” (ሐዋ 4፡20)

በ ግል ምስክርነት ውስጥ ያለ ያልተለመደ ሀይል አለ። ልቦቻችን በክርስቶስ ፍቅር ሲግሉ እና በፀጋው ስንለወጥ ስለርሱ ትርጉም ያለውን ንግግር መናገር ይቻለናል። የሱስ ለሌሎች ያደረገውን ነገር ማካፈል አንድ ነገር ነው። በግላችን ለኛ ያደረገውን ነገር ለሌሎች ማካፈል ደግሞ ሌላ ነገር ነው። የግል የህይወት ልምምድን ጉዳይ ተቃውሞ መከራከር አስቸጋሪ ነገር ነው። ሰዎች የእናንተን የስነ መለኮት እሳቤ ወይንም የጥቅስ አተረጓጎማችሁን አልያም በሃይማኖት ጉዳይ ላይ በማፌዝ ሊከራከሩ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ግለሰብ እንዲህ አለ “እኔ ተስፋ የለሽ ነበርኩ አሁን ግን ተስፋ ያለኝ ሰው ነኝ፤ በህሊና ወቀሳ የተሞላሁ ሰው ነበርኩ አሁን ግን ሰላም አለኝ፤ አላማ የለሽ ሰው ነበርኩ አሁን ግን አላማ ያለኝ ሰው ነኝ” ነገሮችን በጥርጣሬ አይን በሚያዩ ሰዎች ላይ እንኳን የወንጌል ሀይል ተፅዕኖ ያርፍባቸዋል።

ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ እንደሆነው ድንገተኛና ድራማዊ ክስተት የተለወጡ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን ግለሰቡ ውድ የሆነውን ክርስቶስ በመረዳት እያደገ ይመጣል፣ አስደናቂ ስለሆነው ፀጋውም ጥልቅ የሆነ አድናቆት ይኖረዋል ከዛም በነፃ ስለተበረከተለት ድነት ታላቅ የሆነ ምስጋና ያመጣል። ክርስቶስ ህይወታችን ዳግም በትኩረት እንዲሞላ ያደርገዋል። አለማችን ለዘመናት ስትናፍቀውና ስትጓጓለት የነበረው ምስክርነት ይሄ ነው።

የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለሐምሌ 4 ሰንበት ይዘጋጁ።

ሰኔ 28
Jul 05

ያልተለመዱ ምስክርነቶች


ማር. 5፡15-20ን አንብቡ። የሱስ ይህን ሰው ከራሱ ጋር አቆይቶ አዲስ ስላገኘው እምነት ከማስተማር ይልቅ አስር ከተማ በሚባል አገር ለቤተሰቦቹ እና ወዳጆቹ እንዲመሰክር ያደረገው ለምን ይመስሎታል?ዴካ ፖሊስ “Deca polis” የሚለው ቃል የመጣው ከሁለት ቃላት ነው፤ ዴካ “Deca” ማለት አስር ማለት ሲሆን ፖሊስ “Polis” ማለት ደግሞ ከተሞች ማለት ነው። የአስር ከተማ “Decapolis” አካባቢ የሚገኘው በአንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ በገሊላ ባህር ዳርቻ አካባቢ የሚገኙ አስር ከተሞችን ያዘለ ነው። እነዚህ ከተሞች በጋራ የመግባቢያ ቋንቋና ባህል የተዛመዱ ናቸው። ይህ በአጋንንት የተያዘ ሰው በነዚህ ከተሞች ሁሉ በደንብ ይታወቃል። ባልተጠበቁ ድርጊቶቹ እና ወንጀል የመፈጸም ተግባሩ የተነሳ የሰዎችን ልብ በፍርሃት ያራደ ነበር፡ የሱስ በዚህ ሰው ልብ ውስጥ የተሻለ ነገር እንደሚያስፈልገው ተመለከተ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያሰቃየው ከነበረው አጋንንት በአስደናቂ ሁኔታ ነፃ አወጣው።

የከተሜው ሰዎች የእርያ መንጋዎቹ በአጋንንት እንዲያዙ የሱስ እንዳደረገ እና እርያዎቹ ወደ ባህር ለመግባት ወደ ገደል እንደሮጡ ሲሰሙ ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ ወጡ። የማርቆስ ወንጌል እንደ ዘገበልን “ወደ ኢየሱስም መጡ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ፡፤” (ማር. 5፡15)። ይህ ሰው በድጋሚ በአካል፣ በአዕምሮ፣ በስሜትና በመንፈስ ሙሉ ሆነ። የወንጌል አስፈላጊነት በሀጢያት የተሰበረውን ማንነታቸውን በመመለስ ክርስቶስ ቀድሞ ለፈጠረው ምሉዕነት ማብቃት ነው።

በአጋንንት ተይዞ ነፃ ከወጣውና የራሱን ምስክርት ካካፈለው ሰው በተሻለ ሁኔታ ለነዚሀ አስር ከተሞችና አካባቢዎች ሊደርስ የሚችል ታዲያ ማነው? ኤለን ጂ ኃይትም በጥሩ ሁኔታ ገልጻዋለች” ስለ ክርስቶስ ስንመሰክር ያወቅነውን መናገር አለብን፤ እኛ ራሳችን ያየነውን፣ የሰማነውንና ያጣጣምነውን። የእርሱን ዱካ ደረጃ በደረጃ እየተከተልን ከቆየን እርሱ ሲመራን ስለነበረው መንገድ በትክክል የምንናገረው ነገር ይኖረናል። የእርሱን የተስፋ ቃላት እንዴት እንዳጣጣምንና እውነተኛውን የተስፋ ቃል እንዳገኘን እንናገራለን። ስለ ክርስቶስ ፀጋ ካወቅነው ነገር በመነሳት የምስክርነት ፍሬን እናፈራለን። ለሚጠፋው አለም ይሆን ዘንድ ጌታ የጠራን ለእንደዚህ አይነቱ ምስክርነት ነው” `The Desire of Ages, p.3 40። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በፀጋው ሰዎችን በመለወጥ በዚህ አለም ላይ ለውጥን ለማምጣት ያልተለመዱ የምስክርነት ሁኔታዎችን ይጠቀማል።

የእናንተ ታሪክ ምንድነው? ማለትም የተለወጣችሁበት የራሳችሁ ታሪክ ምን ይመስላል? ወደዚህ እምነት እንዴት እንደመጣችሁ ለሌሎች የምትነግሩት ምን ነገር አለ? ያልተለወጠ ሰው እናንተ ከምታካፍሉት የህይወት ልምምዳችሁ ምን ሊጠቀም ይችላል?

ሰኔ 29
Jul 06

የተነሳውን ክርስቶስ ማወጅ


እሁድ በማለዳ ነበር ሁለቱ ማርያሞች በጥድፊያ ወደ ክርስቶስ መቃብር ያቀኑት። የሄዱት ምንም ሊጠይቁት አልነበረም። በህይወት የሌለ ሰው ምን ሊሰጣቸው ይችላል? ለመጨረሻ ጊዜ እርሱን ያዩት አካሉ በደም ታጥቦ፣ ቆስሎና ደቆ ነው። የመስቀሉ ትዕይንት በአዕምሮአቸው ውስጥ በጥልቅ ተቀርጾ ነበር። አሁን ላይ ተግባሮቻቸውን እንዲሁ እያከናወኑ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ አስከሬኑን ሽቱ ለመቀባት ወደ መቃብሩ ሄዱ። የተስፋ መቁረጥ ጭጋግ ህይወታቸውን በሀዘን ጨለማ ዋጠው። የወደፊቱ ቀን ትንሽዬ የተስፋ ጭላንጭል ብቻ ያለበትና እርግጠኝነት የሌለበት ነው።

መቃብሩ ጋ ሲደርሱ ባዶ ሆኖ አገኙት። ይህንን የትንሳኤ ጠዋት ክስተት ማቴዎስ እንዲህ ዘግቦታል “መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደተናገረ ተነስቶአልና በዚህ የለም” (ማቴ 28፡ 5-6)። አሁን ሴቶቹ በደስታ ተጥለቀለቁ። በሀዘን ጭጋግ የተሞላው ደመና ከትንሳኤው ጠዋት በወጣው የጸሐይ ጮራ በኖ ጠፋ። የሀዘን ሌሊታቸው አበቃ። ደስታ ፊታቸው ላይ ተንፀባረቀ የሰቆቃ እንባቸው በሀሴት መዝሙሮች ተተካ።

ማር.16፡1-11ን አንብቡ። ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ ማርያም ስታውቅ ምን ምላሽ ሰጠች?ማርያም የተነሳውን ክርስቶስን ከተገናኘች በኋላ ይህንን ታሪክ ለመናገር ሮጠች። መልካም ዜና የሚያጋሩት ስለሆነ ዝም መሰኘት አልቻለችም። ክርስቶስ ህያው ነው! መቃበሩም ባዶ ነው አለም ደግሞ ይህንን ማወቅ አለበት። በህይወት ጎዳናችን ላይ እኛም የተነሳውን የሱስ ካገኘን በኋላ ይህ መልካም ዜና ከሌሎች ጋር ሊካፈሉት የተገባ በመሆኑ ታሪኩን ለመንገር መሮጥ አለብን።

በነዛ ሁሉ ጊዜያት የሱስ ምን ሊሆን እንደሚችል፤ እንደሚሞትና ከዛም እንደሚነሳ ለመረጣቸው ደቀ መዛሙርት የነገራቸው ቢሆንም የማርያምን ምስክርነት ግን ሊቀበሉ አልወደዱም፡- “እነርሱም ሕያው እንደሆነ ለእርስዋም እንደታያት ሲሰሙ አላመኑም።” (ማር.16፡11)። የየሱስ የራሱ ደቀመዛሙርት ወድያው ስላላመኑ ሌሎች ወዲያው የኛን ቃል ባይቀበሉ በዚህ ልንደነቅ አይገባም። ለመጨረሻ ጊዜ በምስክርነትዎ እፍረት የተሰማዎ መቼ ነው? እንዴት ምላሸ ሰጡ ከዚህ ልምምድስ ምን ተማሩ?

ሰኔ 30
Jul 07

የተለወጡ ህይወቶች ልዩነትን ያመጣሉ


“ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደተናገሩ ባዩ ጊዜ፣ መጽሐፍትን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደሆኑ አስተውለው አደነቁ። ከየሱስ ጋርም እንደነበሩ አወቁአቸው” (ሐዋ 4፡13)። የአዲስ ኪዳንዋ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት እያደገች ሄደች። በጴንጤቆስጤ ቀን 3000 ሰዎች ተጠመቁ (ሐዋ. 2፡41) ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ተጨመሩ (ሐዋ.4፡4)። ወዲያውም ባለሥልጣናቱ ምን እየተካሄደ እንዳለ አወቁ። እነዚህ የአዲስ ኪዳን አማኞች ከክርስቶስ ጋር ነበሩ። ህይወታቸው ተለውጧል። በፀጋው ስለተለወጡ ዝም ማለት አልተቻላቸውም።

ሐዋ.4፡1-20ን አንብቡ። እዚህ ስፍራ ላይ ምን ሆነ? አለቆች ጴጥሮስና ዮሐንስን ዝም ለማሰኘት ሲሞክሩ ምን ተፈጠረ? ምን ምላሽ ነበር የሰጡት?______እነዚህ አማኞች በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ስለሆኑ ታሪካቸውን መናገር አለባቸው። ጴጥሮስ፣ ጮሆ የሚናገረው አሳ አጥማጅ በእግዚአብሔር ፀጋ ተለውጧል። ያዕቆብ እና ዮሐንስ የነጎድጓድ ልጆች የተባሉትና ቁጣቸውን መቆጣጠር የሚቸግራቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፀጋ ተለውጠዋል። ደቀ መዛሙርት እና የቀደመችው ቤተክርስትያን አባላት እያንዳንዳቸው ዝም የማያሰኛቸውና ሊናገሩት የሚችሉት የራሳቸው ታሪክ አላቸው። ኤለን ጂ ኋይት “ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ” በሚለው መጽሐፏ ላይ የተናገረችውን ወሳኝ ንግግር እስቲ ያስተውሉ “በየሱስ ያገኘውን የከበረ ወዳጅነት ለሰዎች ለማሳውቅ በልቡ የሚሻ ሁሉ ሳይዘገይ ወደ ክርስቶስ ይቀርባል። የሚያድነው እና የሚቀድሰው እውነት በልቡ ውስጥ ተዘግቶ ሊቀር አይችልምና።”

የሃይማኖት መሪዎች ቁጥር 16 ላይ ምን እንደተናገሩ እስቲ ተመልከቱ። የተሰራውን ተአምር እውነትነት በገሃድ አውቀዋል፤ የተፈወሰው ሰው ፊት ለፊታቸው ቆሞ አይተውታልና። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አስተሳሰባቸውን ለመቀየር አልወደዱም። ምንም እንኳን ይህን የመሰለ እንቢተኝነት ቢገጥማቸውም ጴጥሮስና ዮሐንስ ከመመስከር ወደኋላ አላፈገፈጉም።

ክርስቶስን በማወቅና ክርስቶስን ለሌሎች በማካፈል መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው? በግላችን ክርስቶስን ማወቃችን ስለ እርሱ ለመመስከር እንድንችል የሚጠቅመን እንዴት አድርጎ ነው?

ሐምሌ 1
Jul 08

ልምዶቻችንን ማካፈል


ሐዋ.26 ላይ ጳውሎስ በንጉስ አግሪጳ ፊት እንደ እስረኛ ሆኖ ሲቀርብ እናገኘዋለን። በዚህ ስፍራ ላይ ጳውሎስ ለንጉሱ በቀጥታ የተናገረው ስለ ራሱ የግል ምስክርነት ነው፤ የእየሱስ ተከታዮችን እንዴት ሲያሳድድ እንደነበር ብቻ ሳይሆን ከዛ በኋላ ህይወቱ ተለውጦ የየሱስ ምስክር እንደሆነ እና ስለ ሙታን ትንሳኤ የተስፋ ቃል ጭምር ነው (ሐዋ.26፡8)።

ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ሲለወጥ ጌታችን እንዲህ ተናገረው “ነገር ግን ተነሳና በእግርህ ቁም ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቻለሁና።” (ሐዋ.26፡16) እምነታችንነ ማካፈል ሁልጊዜም ቢሆን በሃይል የተሞላ የህይወት ልምምድ ነው። ክርስቶስ ባለፈው ህይወታችን ያደረገውን ታሪክ፣ በዛሬ ህይወታችን እያደረገ ስላለው ታሪክ እና በወደፊት ህይወታችን ሊፈፅም ስላለው ነገር መናገራችን ነው።

ምስክርነት ፈፅሞ ስለኛ ጉዳይ አይደለም። ሁልጊዜም ስለርሱ ነው። እርሱ ሀጢያታችንን ይቅር የሚል፣ በሽታችንን የሚፈውስ፣ አፍቃሪ በሆነ ርህራሄው የሚሸልመን እና በመልካም ነገር የሚያረካን አምላክ ነው (መዝ.103፡3-5)። ምስክርነት ማለት በእኛ ታሪክ ውስጥ ያየነውን የእርሱን አስገራሚ ፀጋ ማካፈል ነው። በግላችን ከአምላክ አስደናቂ ፀጋ ጋር የተገናኘነው በምስክርነት ነው። 1ዮሐ.1፡1-3ን አንብቡና ከገላ.2፡20 ጋር አነፃፅሩ። ምን አይነት ተመሳሳይነትን አስተዋላችሁ? የዮሐንስ ልምምድ ከጳውሎስ ጋር የተመሳሰለው እንዴት አድርጎ ነው?ምንም እንኳን ዮሐንስ እና ጳውሎስ የተለያየ የህይወት ልምድ ቢኖራቸውም ሁለቱም ግን በግላቸው ከየሱስ ጋር ተገናኝተዋል። ከየሱስ ጋር ያላቸው ልምምድ ደግሞ የሆነ ጊዜ ላይ ብቻ ሆኖ ያለፈና ያበቃ ጉዳይ አይደለም። በየእለት ህይወታቸው እየተለማመዱት የቀጠለ የፍቅሩ ሃሴት እና በእውነቱ ብርሃን የመራመዳቸው ሂደት ነው።

መለወጥ ታዲያ ያለፈውን ነገር ብቻ የሚያካትት ነውን? ዋናው ጉዳይ የባለፈው ህይወታቸው የመለወጥ ልምምድ ብቻ ነው ብለው ለሚያስቡ ሰዎች እንዲህ ብላ ተናግራለች “ሃይማኖትን አንድ ወቅት ላይ አውቀውት ስላለፉ በየቀኑ መለወጥ አላስፈለጋቸውም ነገር ግን እያንዳንዳችን በየእለቱ መለወጥ ግድ ይለናል” Manuscript Release, vol. 4, p. 46:: ያለፈው የህይወት ልምምድዎ ምንም አይነት ቢሆን፣ በሃይል የተሞላና አስደናቂ ቢሆን በየእለቱ ከጌታ ጋር በመገናኘት የእርሱን እውነተኛነት፣ መልካምነት እና ሃይል የመረዳት አስፈላጊነት ምን ያክል ነው? በሰንበት ቀን ምላሽዎን ይዘው ወደ ውይይት ቡድንዎ ይምጡ።

ሐምሌ 2
Jul 09

የግል ምስክርነት ሀይል


በአግሪጳ ፊት የቀረበውን ጳውሎስን በድጋሚ እንመልከት እስቲ። በሄሮድስ ፊት የቀረበው ሃዋርያው ጳውሎስ አይሁዳዊ አርበኛ የሆነና በአይሁድ ነገስታት የመጨረሻው መስመር ላይ የነበረ ግለሰብ ነው። አግሪጳ አይሁድ ነኝ ይላል ነገር ግን በልቡ ሮማዊ ነበር። (የSDA Bible Commentary, vol. 6. P. 436ን ተመልከቱ)። በእድሜው የገፋው ሚሲዮናዊ የሆነው ሐዋሪያ በአያሌ ጉዞ የተዳከመ እና በመልካምና በክፉ መካከል በነበረው ትግል የቆሰለ ሰው ነው። እዚህ ጋ ሲቆም ግን ልቡ በእግዚአብሔር ፍቅር ተሞልቶ እና በአምላክ በጎነት ፊቱ ፈክቶ ነበር። በህይወቱ ምንም ነገር ቢከሰት፣ ምንም ያክል ስደት፣ መከራ ቢያጋጥመው እግዚአብሔር መልካም ነው ብሎ ማወጅ ይችላል።

አግሪጳ ሰዎችን በመልካም እይታ የማያይ፣ ተጠራጣሪ፣ ልበ ደንዳና እና ቅንነት ለሰፈነበት ስርአት ቸልተኛ የሆነ ሰው ነው። በተቃራው ጳውሎስ ደግሞ በእምነት የተሞላ፣ ለእውነት የተሰጠ እና ጽድቅን በመጠበቅ ታማኝ የሆነ ሰው ነው። በሁለቱ ሰዎች መካከል ላለው ንፅፅር ከዚህ በላይ መረጃ ሊሰጠን አይችልም። ክስ ሲቀርብ ሳለ ጳውሎስ ለመናገር ከአግሪጳ ፈቃድን ጠየቀ።

ሐዋ.26፡1-32ን አንብቡ። ጳውሎስ ለአግሪጳ የመሰከረው እንዴት ነበር? ከተናገራቸው ቃላት የምንማረው ምን ነገር አለ?ሩህሩህነት ልቦችን ሲከፍት ጨካኝ ባህሪ ደግሞ ልቦችን ይዘጋል። እዚህ ጋ ጳውሎስ ለአግሪጳ በሚያስነድቅ ሁኔታ ደግ ሆኖ ነበር። ሲጠራው ሳለ እንዲህ አለው “የአይሁድን ስርአት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና” (ሐዋ.26፡3)። ከዛም በዚህ መግቢያ በር የራሱን የንግግር ጉዳይ አቀረበ።

በሐዋ.26፡12-18 የጳውሎስን የመለወጥ ታሪክ አንብቡ ከዛም በሐዋ.26፡26-28 ላይ ሁኔታው እንዴት በአግሪጳ ላይ ተፅዕኖን እንደፈጠረበት በጥንቃቄ ተመልከቱ። አግሪጳ በዚህ መንገድ ምላሽ የሰጠው ለምን ይመስላችኋል? በጳውሎስ ምስክርነት ውስጥ ያስደነቀው ነገር ምንድነው?በጳውሎስ ምስክርነት ውስጥ የሱስ እንዴት ህይወቱን እንደለወጠው መጥቀሱ እግዚአብሄር የለሽ በሆነው ንጉስ ላይ የፈጠረው ሃያል የሆነ ተፅዕኖ ነበረው። ከተለወጠ ህይወት በላይ ውጤታማ የሆነ ምስክርነት የለም። በእውነተኛ ልብ የተቀየረ ሰው ህይወት ምስክርነት በሌሎች ላይ አስደናቂ ተጽዕኖን ይፈጥራል። እግዚአብሔር የለሽ የሆኑ ነገስታት እንኳን በፀጋው ህይወታቸውን በተቀየሩ ሰዎች በኩል ውስጣቸው ተነቃንቋል። እንደ ጳውሎስ ያለ አስገራሚ ታሪክ ባይኖረንም እንኳን በፀጋው ሁላችንም የሱስን ማወቅ እና በደሙ መዋጀት ምን ማለት እንደሆነ ልንነግራቸው እንችላለን።

ሐምሌ 3
Jul 10


ተጨማሪ ሐሳብ


Read Ellen g. White, `Almost Thou Persudest me` pp. 433-438, in the Acts of the Apostles. የክርስቲያን ህይወት አስፈላጊነቱ ከየሱስ ጋር ያለንን ሙሉ እና የበለጸገ ግንኙነት ለሌሎች ለማካፈል መናፈቅ ነው። ትክክለኛ አስተምህሮ አስፈላጊ ቢሆንም በፀጋ የተለወጠ እና በፍቅር የተቀየረን ህይወት ሊተካ አይችልም። ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ ስትል ግልፅ አድርጋ አስቀምጣዋለች። “አዳኙ በአለማዊነት እና ራስ ወዳድነት ክበብ የደነደኑ ልቦችን እንደማያቀልጥ ወይም እንደማይሰብር ያለጥርጥር ያውቃል። ወንጌል ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ደቀ መዛሙርቱ እውነተኛ ህይወት በሆነው በህያው የየሱስ እውቀት ልቦች ሲግሉና ከንፈሮች አንደበተ ርቱዕ ሆነው የሰማያዊ ስጦታን ሲቀበሉ እንደሆነ ያውቃል።” The acts of the Apostles, p.31። በዘመናት ምኞት መጽሐፍ ላይ ይህንን ሃይል የተሞላበትን ንግግር ታክላለች። ድግግሞሽ የሞላባቸው አስተምህሮዎች ምንም ማድረግ ባይችሉም የክርስቶስ አስደናቂ ፍቅር ግን ልቦችን ያቀልጣል በቁጥጥር ስርም ያውላቸዋል” Page 826።

የግል ምስክርነትን መስጠት ከእግዚአብሔር ቃል ላይ ያገኙትን እውነት ሌሎችን ለማሳመን መጣር እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ አሉ። የእግዚአብሔርን የእውነት ቃል ማካፈል ወሳኝና አበረታች ነገር ቢሆንም የግል ምስክርነታችን ከዚህ ባለፈ በዘላለም ሕይወት በየሱስ በነፃ ተሰጥቶን ስላገኘናቸው ከህሊና ወቀሳ ነጻ መሆን፣ ሰላም፣ ምህረት፣ ይቅርታ፣ ጥንካሬ፣ ተስፋ እና ደስታ የሚነገር ነው።


የመወያያ ጥያቄዎች1.የግል ምስክርነት በሌሎች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በኩል ሃይለኛ የሆነው ለምንድነው? የሌሎች ምስክርነቶች እንዴት አድርጎ በእርስዎ የህይወት ልምምድ ላይ ተፅዕኖ ፈጠረብዎ?

2.በረቡዕ መጨረሻ ለተጠየቀው ጥያቄ ያለዎትን ምላሽ በውይይት ቡድኖች ውስጥ ይወያዩ። በየእለቱ ከየሱስ ጋር ያለን ልምምድ ለምስክርነታችን ብቻ ሳይሆን ለግል እምነታችን ወሳኝ የሆነው ለምንድነው?

3.እርግጥ ነው በሃይል የተሞላ ምስክርነት ውጤታማ ምስክርነት ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያሳይ ሕይወት የምስክርነታችን ወሳኝ ክፍል የሆነው ለምንድነው?

4.የግልዎን ምስክርነት ለውይይት ቡድንዎ ያጋሩ። አስታውሱ የምታጋሩት ክርስቶስ ለእናንተ ያደረገውን ነገር እና ዛሬ እርሱ ለእናንተ ምን ማለት እንደሆነ ነው። የሱስ በህይወትዎ ውስጥ ምን ልዩነት አምጥቷል?