የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከመስከረም 9–15

13ኛ ትምህርት

Sep 19 - Sep 25
የእምነት እርምጃችንሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ: ፊልጵ. 2:5–11፤ማቴ. 4:18– 20፤ሐዋ 9:3–6፣ 10–20፤ዮሐንስ 21:15–19፤1ኛ ዮሐንስ 3:16–18።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ራሱን ባዶ አደረገ፤›› (ፊልጵስዩስ 2:5–7, አ.መ.ት)

ሠ ማይ የነበረውን ታላቅ ክብር፥የመላዕክትን ስግደት፣ እና የአባቱን አብሮነት ትቶ መምጣት ሊታሰብ የማይችል መስዋዕትነት ነበር። ይሁንና፥ ኢየሱስ ግን ወደዚህች ምድር ስቃይ እና ሞት በመምጣት የአብን የፍቅር ባህርይ እየገለጠ፣ የሰውን ዘር ፍቅር ዳግም ሊገዛ እና ሰብዓዊውን ፍጥረት ሁሉ ሊቤዥ ወደደ። ‹‹የተቤዠንበትን ዋጋ እኛ ቤዛነት ያገኘኝ ከተቤዠን ጋር በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እስከምንቆም ድረስ በፍጹም ልንረዳው አንችልም። ያን ጊዜ ገና በለጋዎቹ ስሜቶቻችን ውስጥ የዘለዓለም ቤታችን ግርማ ሲፈነዳ፥ ኢየሱስ ይህንን ሁሉ የተወልን፣ ከሰማይ ደጆች ስደተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን የመጥፋት እና የዘልአለም ሞትን አደጋ እንኳን መጋፈጡ ለእኛ ሲል መሆኑ ይታወሰናል። በዚያን ጊዜም አክሊሎቻችንን ከራሳችን አውርደን በእግሮቹ ስር እየጣልን ‹‹…“የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ጥበብና ብርታት፣ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ሊቀበል ይገባዋል።›› እንላለን። ራዕ. 5:12.”— ኤለን ጂ. ኋይት, ዘ ዲዛየር ኦፍ ኤጅስ, p. 131.

ለእኛ ደህንነት ሲል ኢየሱስ የከፈለው መስዋዕትነት የሚሰላ አይደለም።እርሱ ለሚሰጠን ምሪት መልስ ስንሰጥ፣ የእርሱን ትዕዛዝ ስንቀበል፣ እንዲሁም የጠፉትን ሰዎች ወደእርሱ መንግስት ለመማረክ ስንተባበረው ሣለ፥ መስዋዕትነትን ይጠይቀናል።ምንም እንኳን መስዋዕቶቻችን በምንም መንገድ ቢሆን ከእርሱ ጋር የማይወዳደር ቢሆንም ቅሉ፥ ለእኛ ያደረገው ነፍሳትን የመማረክ አገልግሎት እንደዚሁ፥ ምን ያህል እንደተማመነብን ያሳያል። ምንም ወደማናውቀው ውሃ ውስጥ ዘልለን የመግባት ያህል ያልለመድነው ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ የሚመራን ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ጌታችን መስዋዕትነቶችን እንድንከፍል ጥሪ ያደርግልናል፥ ዳሩ ግን አያይዞ የሚሰጠን ደስታ ግን ከዚያ የላቀ ነው።

*የዚህን ሣምንት ትምህርት እያጠኑ ለመስከረም 16 ሰንበት ይዘጋጁ።

መስከረም 10
Sep 20

የኢየሱስ ራሱን መስዋዕት ያስደረገ ፍቅር


ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ የነበረው ያ አስተሳሰብ በእኛም እንዲሆን ዘንድ ያበረታታናል።ይህም እንግዲህ የሚያስደንቅ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል። የክርስቶስ አስተሳሰብ ምን ዓይነት ነበር?የእርሱን የአስተሳሰብ ሁኔታዎች የሚገዙት ምን ምን ነበሩ?የእርሱስ አስተሳሰብ ይዘቶች ምን ነበሩ? እስቲ ፊልጵስዩስ 2:5–11ን እናንብብ።

እነዚህ ጥቅሶች ስለ ክርስቶስ አሳብ እና የእርሱን አጠቃላይ ህይወት ሲገዛ ስለነበረው ልማድ የሚመሩን እንዴት ነው?ለዘልዓለም ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነበር። ጳውሎስ ይህንን ዘላለማዊ ዕውነት እንዲህ ባሉ ቃላት ያስቀምጥልናል።‹‹እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤››(Phil. 2:6, አ.መ.ት.).በተርጓሚዎች “ባህርዩ” ተብሎ የተቀመጠው ቃል ከግሪክኛው ሞርፍ ከሚለው ቃል የመነጨ ነው።ይህም ማት የአንድ ነገር ስር መሠረት ማለት ነው።

ሁለት እኩል ዋጋ ያላቸውን ነገሮች የሚያጣምር ነው።ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ባይብል ኮሜንታሪ ይህንን ነገር እንዲህ ተብራርቶ እናገኛለን፡ ‹‹ይህ አገላለጽ ክርስቶስን ከአብ ጋር የሚያስተካክለው ሲሆን፥ ከሌሎች ኃይላት ሁሉ ልቆ እንዲቀመጥ ያደርገዋል። ጳውሎስም የክርስቶስን በፍቃደኝት ራሱን ማዋረድ በይበልጥ ቁንጽል አድርጎ ለመጥቀስ ይህንን ክፍል አጽንዖት ይሰጥበታል።››—7ኛ ዕትም ገጽ. 154 (ከእንግሊዝኛው) ስለ ዘለዓለማዊ ተፈጥሮው ስትናገር ኤለን ጀ. ኋይትእንዲህ ጨምራለች፡‹‹በክርስቶስ የምናየው ህይወት ያልተቀዳ፣ ያልተዋሰ፣ እና ያልተፈለፈለ ህይወት ነው።››—ዘ ዲዛየር ኦፍ ኤጅስ, ገጽ. 530 (ከእንግሊሊኛው) ኢየሱስ አምላክ ሆኖ ከዘመናት ሁሉ በፊት እንዳልነበረ፥ ‹‹ራሱን ባዶ አደረገ›› እዚህም ላይ ጥቅም ላይ የዋለው አገላለጽ ከግሪክኛ የተወሰደ ነው።

ቃል በቃል ‹‹ባዶ›› ተብሎ ተመልክቶ እናገኛለን። ኢየሱስ በገዛ ፍቃዱ በእግዚአብሔርነቱ ያለውን ዕድል እና ስልጣናት ሁሉ ጥሎ ‹‹ራሱን ባዶ›› በማድረግ፥ ለሰው ዘር ትሁት አገልጋይ ለመሆን የሰውን መልክ ያዘ። አገልጋይ ከመሆኑ የተነሣም፥ ስለ ፍቅር የተቀመጠውን የሰማይን ህግ ለመላው ዩኒቨርስ በመግለጥ፥ በሒደትም በመስቀል ላይ ታላቁን የፍቅር ተግባር ፈጽሞ አሳየ። የእኛን ህይወት ለዘለዓለም ለመቤዠት ሲል የራሱን ህይወት ተወ። የኢየሱስ አስተሳሰብ ጭብጡ ያለው ራስን መስዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ላይ ነው።ኢየሱስን መከተል ማለት እርሱ ባፈቀረበት መንገድ እኛም ማፍቀር፣ እርሱ ባገለገለበት መንገድ እኛም ማገልገል፣ እርሱ እንደመሰከረ እኛም መመስከር ማለት ነው።ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እኛን ከራስ ወዳድ ትጋታችን ባዶ እንዲያደርገን ስንፈቅድለት፥ የሚያስከፍለን የሆነ ነገር ይኖራል። ኢየሱስ ያለውን ነገር ሁሉ ከፍሎበታል። ዳሩ ግን፥፣ ቅዱስ ቃሉ ስለ ኢየሱስ እንደሚነግረን፥ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤››(ፊሊ. 2:9, አ.መ.ት.).

ሠማይን የምናገኝ ከሆነ በምድር ላይ የምንከፍለው ማንኛውም መስዋዕትነት ይከፈል። በጉዟችን መስዋዕት መክፈል የማይቀር ነገር ሆኖ ሣለ፥ የአገልግሎቱ ሐሴት ዛሬ ላይ ስናየው ሚዛን ይደፋል፤ በዘለዓለም ህይወታችን ሁሉ የምንደሰትበት ከክርስቶስ ጋር የመኖር ሐሴት ደግሞ የከፈልነውን መስዋዕትነት በዚህ ያለውን ምንም የማይፈይድ ያህል ያደርገዋል። ለክርስቶስ ሲሉ የራስዎን ነገር የካዱበት ጊዜ ዕውነት እንናገር እና መች ነው? ስለ ክርስትና ህይወትዎ ከዚህ መልስዎ በመነሳት ምን ሚዛን ያወጣሉ?

መስከረም 11
Sep 21

የቁርጠኝነት ጥሪ


እስቲ በምናብዎ ራስዎን በጴጥሮስ እና በዮሐንስ ቦታ ያድርጉት። ውብዋ የገሊላ ጸሐይ በጠዋት የማለዳውን ጭጋጋማ አየር እየሰነጠቀችው በመፈንጠቅ ላይ ነች።የእርስዎ አሳብ ሁሉ አንድ ነገር ላይ ነው፡ ዓሳ መያዝ፥ በጣም ብዙ ዓሳ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የማስገር አጋጣሚዎች ሁሉ በመልካም እየተከናወኑ በመሆኑ፥ ሌላ ቀን ደግሞ ይመጣና በጥሩ ሁኔታ እንደሚያሰግሩ እርስዎ ተስፋ እያደረጉ ነው። በማስከተል ገና በማለዳ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሲመጣ ይመለከቱታል። ህይወትዎ በሙሉ ሌላ ታሪክ ውስጥ ሊገባ ከጫፍ መድረሱን ግን ገና አላስተዋሉም። ከእንግዲህ ዳግም እንደድሮው መሆን የለም።

እስቲ ማቴዎስ 4:18–20 ላይ ያለውን እናንብብ። ጴጥሮስ እና ዮሐንስ እንደዚህ ዓይነት ፈጣን የሆነ ቁርጠኝነት በማሳየት ክርስቶስን ለመከተል ፍቃደኛ የሆኑት ለምን ይመስልዎታል? በዚህ ጥቅስ ከምናገኘው የትኛው ክፍል ነው ዓሳን ከማስገር ወደተሻለ ዓላማ እንዲመጡ ጥሪ ያደረገላቸው?ከዮሀንስ ወንጌል እንደምናገኘው፥ ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ እነዚህ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚያውቁት ነገር እንደነበረ ነው፤ የሆነ ሆኖ፥ ለእርሱ በሙላት ቁርጠኛ አልሆኑም ነበር። ሆኖም፥ስለ ክርስቶስ የምናየው መለኮታዊ የሆነ ምግባር አለ፥ ከገጽታው፣ ከቃላቱ እና ከድርጊቱ የሚፈልቀው የሆነ ነገር ብቻ ለእነዚህ ገሊላውያን ዓሳ አስጋሪዎች ወደ መለኮታዊ ጥሪ እየጋበዛቸው መሆኑን የሚያመለክት ነገር ነበረ። እነርሱ ጀልባዎቻቸውን፣ የዕለት ጉርሳቸውን እና የለመዱትን አከባቢ ትተው እንዲከተሉት ያደረጋቸው ምክንያት ለላቀ ዓላማ የቀረበላቸው ጥሪ ስለተሰማቸው ነው።እነዚህ ተራ የሚባሉ ዓሳ አስጋሪዎች እጅግ ለላቀ ዓላማ የተጠሩ መሆናቸውን ተገነዘቡ። ዛሬ ላይ እግዚአብሔር ሙያችንን እንድንተው እየጠራን ላይሆን ቢችልም፥ የላቀ ለሆነ ዓላማ ግን እየጠራዎት ነው - ይህም ማለት ደግሞ፥ የእርሱን ፍቅር እንድናካፍል እና የእርሱን ዕውነት ለስሙ ክብር እንድንመሰክር ዘንድ ነው።

እስቲ ማቴዎስ፥ ቀራጩን በማቴዎስ 9:9 በተተረከበት መንገድ እናስበው። በጣም የሚደነቅ የሆነ ምን ነገር ከዚህ ምንባብ እናገኛለን?በሮማውያን ዘመን የነበሩት ግብር ሰብሳቢዎች በአብዛኛው በዝባዦች የነበሩ የተሰጣቸውን የሹመት ስልጣን ተራውን ህዝብ ለመጨቆን የሚጠቀሙ ነበሩ። በመላው እስራኤል ውስጥ ከሚጠሉ እና ከሚወገዙ ገጸ ባህርያት መካከል ይገኙበታል። በክርስቶስ ጥሪ፥ ‹‹ተከተለኝ›› ሲባሉ ስናይ፥ ማቴዎስ ኢየሱስን እንዳደመጠው እና በልቡ እርሱን ሊከተለው ሲመኝ እንደነበረ እንድንገምት ያደርገናል።ጥሪው ሲመጣለት ዝግጁ ነበር።ክርስቶስ እርሱን ሊቀበለው የሚችል በመሆኑ እና ከደቀመዛሙርቱ መካከል እንዲሆን ሊጋብዘው በመቻሉ ተገርሞ ነበር።

በጥልቅ ልባችን ውስጥ በህይወታችን ከምናየው ለሚልቅ ነገር የመናፈቅ ስሜት አለ። እኛም እንደዚያው የላቀ፣ የከበረና ዓላማ ላልው ህይወት ናፍቆት ሊኖረን ይገባል። በዚህም የተነሣ፥ ክርስቶስ ለእኛም እንደማቴዎስ እንድንከተለው ጥሪ ያደርግልናል። ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ ሰዎች ምን ምን ወደኋላ እንደተው እስቲ ያስቡ። ለምን ነበር በስተመመጨረሻ የተገባ ሆኖ የምናገኘው?

መስከረም 12
Sep 22

ጳውሎስ: የተመረጠው የሸክላ ዕቃ


ጳውሎስ ክርስቶስን ሲቀበል፥ ህይወቱ በሙሉ የሚያስገርም ለውጥ አስተናገደ።ከክርስቶስ የተነሣ አዲስ የሆነ ዕጣ ፈንታ ሆነለት። ከለመደው የተመቸው ነገር እንዲወጣ በማድረግ አስቦ በማያውቀው መንገድ መራው። በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተነሣም፥ ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በሜድትራኒያን ዙሪያ ገባ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሲያውጅ ኖረ። የክርስትናን እና የዓለምን ታሪክ ሲለወጥ ምስክር ሆነ።

እስቲ ሐዋርያት ሥራ 9:3–6፣ 10–20 ላይ ያለውን እናንብብ። ከእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለጳውሎስ ህይወት ኢየሱስ መለኮታዊ የሆነ ዓላማ እንዳዘጋጀለት እንዴት ልናውቅ እንችላለን?ኢየሱስ አንዳንድ ጊዜ በጣም የማይጠበቁ ዕጩዎችን መርጦ ስሙን እንዲያውጁ ያደርጋል። እስቲ አጋንንት የነበረበትን ሰው፣ ሠማሪያዊቷን ሴት፣ ያቺን ሴተኛ አዳሪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢ፣ የገሊላ ዓሳ አስጋሪዎች፣ እንዲሁም አሁን ደግሞ እጅግ የከፋውን የክርስቲያኖች አሳዳጅ ያስቡ። እነዚህ ሁሉ በጸጋው ተለውጠው ከዚያም በልባቸው ሐሴት እንደተሞሉ ክርስቶስ በህይወታቸው ውስጥ የሠራውን ነገር ለማወጅ ተላኩ። ማናቸውም ቢሆኑ ታሪኩን ከመተረክ አልቦዘኑም። ክርስቶስ ለእነርሱ የሰራላቸው ሥራ እጅግ የሚያስደንቅ ከመሆኑ የተነሣ ከማካፈል በቀር ምንም ምርጫ አልነበራቸውም። ዝም ሊሉ አላስቻላቸውም።

በሐዋርያት ሥራ 28:28–31 እና 2ኛ ጢሞ 4:5–8 ድረስ ያለውን እስቲ ያመሳክሩ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የምናገኘው እና ጳውሎስ ህይወቱን በሙሉ ነፍሳትን በሚማርክ አገልግሎት አሳልፎ ለመስጠት የነበረውን ቁርጠኝነት ያለማሰለስ ስለማከናወኑ የሚያመለክት ምንድር ነው?በህይወቱ መጨረሻ ላይ፥በሮም የቁም እስር ላይ እንዳለ ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ማረጋገጫን ሰጠ፡ ‹‹ስለዚህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ እነርሱም ይሰሙታል።››(ሐዋ. 28:28፣አ.መ.ት.)ከመዛግብት እንደምናገኘው ከሆነ እርሱን የጎበኙትን ሁሉ ሲቀበል እና ቃሉን ሲሰብክላቸው ነበር። (ሐዋ. 28:30፣ 31)በህይወቱ መጨረሻ ላይ ለጢሞቴዎስ የወንጌላዊን ሥራ እንዲሰራ ሲያበረታታው ሣለ ጳውሎስ ስለራሱ ሊናገር የቻለው ብቸኛው ነገር፡ ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።››(2ኛጢሞ. 4:7፣አ.መ.ት.).

እኛ የተጠራንበት መንገድ ልክ እንደ ጳውሎስ ትዕይንት የተሞላ ባይሆንም፥ እግዚአብሔር ግን እያንዳንዳችንን ከእርሱ ጋር በመሆን ዓለምን በመለወጥ ሥራው ውስጥ እንድንተባበር እየጠራን ይገኛል። ምንም እንኳን ለዓመታት የለፋው ልፋት እያለም ቢሆን፥ (2ኛቆሮ. 11:25–30ን ይመልከቱ)፥ ጳውሎስ በጌታ ለተጠራበት ጥሩ ታማኝ ሆኖ ነው የዘለቀው። ይህ ቀድሞ የኢየሱስ አሳዳጅ የነበረ ሰው በጣም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ የክርስትና ዕምነት ዋቢ አማካሪ (ኢየሱስ ሳይቆጠር) ሊሆን የቻለበት ታሪክ ለጌታ ሥራ የራሱን ህይወት አሳልፎ ለሚሰጥ ሰው ህይወት ምን ዓይነት ነገር ሊያደርግ እንደሚችል ማሳያ ነው።

እርስዎን እንዲሰሩ እግዚአብሔር የሚጠራዎት በምን ጉዳይ ነው? እያደረጉትስ ነውን?

መስከረም 13
Sep 23

የፍቅር ጥያቄዎች


ፍቅር ሁልጊዜም በተግባር የሚገለጽ ነው።ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ለሚጠፋው የሰው ዘር የሆነ ነገር እንድናደርግ የሚያነሳሳን ነው። ጳውሎስ ይህንን በቆሮንቶስ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት በግልጽ አመልክቷል፡ ‹‹የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤..››(2 ቆሮ. 5:14፣አ.መ.ት )ክርስትና ከመጀመሪያውም መጥፎ ነገሮችን መተው እና በዚያም ደህንነትን ማግኘት አይደለም። ኢየሱስ በሰማይ የነበሩትን መጥፎ ልማዶቹን ‹‹በመተው›› አይደለም መጥቶ እኛን ያዳነን። መልካም የሆኑ ነገሮችን ትቶ ነበር በመምጣት እንድንድን ያስቻለን። የኢየሱስ ጥሪ ጊዜያችንን እና ያለንን ነገር ለሚፈልገው ዓላማ እንድንሰጠው ብቻ አይደለም፤ ጥሪው ህይወታችንን እንድንሰጠው ነው።

እየሱስ በገሊላ ባህር ዳርቻ ላይ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በማለዳ ሲገናኝ፥ የመለኮታዊ ፍቅርን ጥያቄዎች ብሩህ አድርጎ አስቀመጠው። በዮሐንስ 21:15–19 ያለውን ያንብቡ። ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ለጴጥሮስ ያቀረበለት ጥያቄ ምንድር ነው? ኢየሱስስ ይህንን ጥያቄ በተለይ ጴጥሮስን እንዲጠይቀው ያደረገው ምክንያት ምንድርነው?ጴጥሮስ ጌታን የካደው ሦስት ጊዜ ነበር፥ ደግሞም ኢየሱስ ከጴጥሮስ ከራሱ ከንፈር የፍቅርን ምላሽ የተቀበለው ሦስት ጊዜ ነበር። ደቀመዛሙርት በተገኙበት፥ ጴጥሮስ በመለኮታዊ ፍቅር ይቅርታ ያገኘ መሆኑን እና ኢየሱስ አሁንም ቢሆን ለዓላማው ሊጠቀምበት የሚፈልግበት ሥራ እንዳለው በማረጋገጥ የጴጥሮስን በራስ መተማመን እየገነባ ነበር።

በዮሐንስ 21:15–19 ያለውን ደግመው ያንብቡ፥ አሁን ግን ጴጥሮስ ፍቅሩን ለክርስቶስ እያረጋገጠ የመለሰለትን መልስ ሲሰጠው ኢየሱስ በሰጠው ምላሽ ላይ እናተኩራለን። በምላሹ ኢየሱስ ከእርሱ ሲጠይቀው የምናገኘው ምንድር ነው?መለኮታዊው ፍቅር ህያው ነው፣ አልተኛም። ዕውነተኛ ፍቅር ከሙቀት ስሜት የበለጠ ነው፣ ጥሩ አሳብ ብቻ የምንለው አይደለም። ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነው። ፍቅር ወደ ድርጊት እንድንሔድ ይገፋፋናል። ደግሞም በጠፋችው ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ከርታታ የእግዚአብሔርን ልጆች ፍለጋ እንድንወጣ ይመራናል። ኢየሱስ ሲናገር ለጴጥሮስ፥‹‹ጠቦቶቼን መግብ›› በማለቱ፥ ትዕዛዝ እና የሚያጽናና ማረጋገጫን በአንድነት የያዘ ነበር። ጌታው ለፍቅር ምላሽ የሚያሰጥ ጥሪ አድርጎለት፥ አያይዞም ምንም እንኳን ኢየሱስ በታሰረበት ጊዜ ላይ የሰራው ሥራ፥ ኢየሱስን እንደማያውቀው መካድ ብቻ ሳይሆን እየተሳደበ እስከሚክድ ድረስ ልክ ክርስቶስ ታደርጋለህ ብሎ እንደነገረው ያደረገው ለጴጥሮስ የዕውነት የሚያሳፍረው ነገር የነበረ ቢሆንም፥ እርሱ ግን ለእርሱ የሚሰራለት ሌላ ስራ እንዳለው ጴጥሮስን አበረታታው።

ነጥቡ ምንድነው? እርስዎም በከርታታነት ጌታን አስቀይመውት ይሆን ይሆናል። ከአንድ ጊዜ በላይ በድርጊትዎ እርሱን ክደውት ሊሆን ይችላል። መልካሙ ዜና ግን ጸጋው አሁንም ድረስ ለእኛ መሆኑ እና እግዚአብሔር ገና ተስፋ ያልቆረጠብን መሆኑ ነው።በእርሱ ስራ ውስጥ፣ እኛ ፍቃደኛ እስከሆንን ድረስ፥ አሁንም ቦታ አለን። ልክ ጴጥሮስ እንዳደረገው፥ እርስዎስ ጌታን ‹‹ክደው›› ያውቃሉ? ምናልባት ከሆነ፥ ከዚህ ታሪክ፥ የጴጥሮስ ክህደት ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስ ዘንድ ለጴጥሮስ የተነገሩት ቃላት፥ ለእርስዎ የሚነግሩዎት ነገር ምንድር ነው?

መስከረም 14
Sep 24

የፍቅር ግዴታ


በጴጥሮስ እና በኢየሱስ መካከል የነበረው ንግግር ሲደመደም፥ እነዚህ ሁለት ሰዎች በባህሩ ዳርቻ ላይ ሲራመዱ እናያቸዋለን። ማዕበሉ እየመጣ ዳርቻውን እየመታ ሲመለስ፥ ኢየሱስ የደቀመዝሙርነትን ዋጋ ለጴጥሮስ ሲያስረዳው ነበር። የኢየሱስን ጥሪ ተቀብሎ ‹‹በጎቼን መግብ›› እንዳለው የሚያደርግ ከሆነ የሚያጋጥመውን ነገር ጴጥሮስ እንዲያውቅለት ኢየሱስ ይፈልግ ነበር።

በዮሐንስ 21:18፣ 19 ያለውን እናንብብ። ስለ ደቀመዝሙርነት ዋጋ ኢየሱስ ለጴጥሮስ የነገረው ነገር ምንድር ነው? ኢየሱስ በዚህ የህይወቱ ነጥብ ላይ ለጴጥሮስ የሚያስደነግጠውን ነገር የገለጠለት ለምን ይመስልዎታል?በእነዚህ ቃላት አማካይነት፥ ክርስቶስ አንድ ቀን ጴጥሮስ የሚያጋጥመውን ሰማዕትነት እየተነበየለት ነበር። እጆቹን ዘርግቶ በመስቀል ላይ መሰቀል ይጠብቀዋል። በዚህ ራዕይ ውስጥ፥ ክርስቶስ ምርጫን ለጴጥሮስ ሰጠው። የህይወትን ትልቁን ሐሴት፡ ለእግዚአብሔር መንግስት የተማረኩ ነፍሳትን የማየትን ዕድል። በጴንጤቆስጤ ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ወደ ክርስቶስ ሊመጡ ነው ያሉት። በኢየሱስ ስም ተዓምራትን እያደረገ ገና በአያሌ ሺዎች ፊት እርሱን ሊያከብረው ነው። ከክርስቶስ ጋር በእርሱ ተልዕኮ ውስጥ ህብረት የማድረግ ዘለዓለማዊ ሐሴት ሊጠግብ ገና ይቀረዋል። ይህ ሁሉ ዕድል ግን ያለዋጋ አይገኝም። መስዋዕትነትን፥ የመጨረሻውን መስዋዕትነት መክፈልን ይጠይቀዋል። ጴጥሮስ ምንም የጋረደው ነገር ሳይሆን በገሃድ ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ ነው የተጠየቀው። ለጴጥሮስ አሁን በዓለም ላይ ያለውን የኢየሱስ ተልዕኮ እንዳይቀላቀል የሚበዛበት ምንም ዓይነት መስዋዕትነት የለውም ነበር።

በ1ኛ ዮሐንስ 3:16–18 ላይ ያለውን ያንብቡ። ፍቅርን እንደ ግንጥል ጌጥ ከሚሆን በማለት ዮሐንስ የሚያቀርብልን አማራጭ ምንድር ነው? ዮሐንስ የፍቅርን ትልቁን መስዋዕትነት እንዴት አድርጎ ነው የገለጸው?ለዘለዓለም ህይወት ብለን፥ ካደረግነው ምንም ቢሆን መስዋዕትነት አይመስልም። የጊዜ እና የጥረት መስዋዕትነታችን፥ ህይወታችንን እንደ መዋዕለ ንዋይ ስናፈስስ፥ ተትረፍርፎ እንደተመለሰልን ያስታውቃል።ፍቅርን በተግባር እንደማሳየት፣ ፍላጎትን ወደቁርጠኝነት እንደማሳደግ ያለ ምንምሐሴት የለም። ለክርስቶስ አምባሳደሮች በመሆን ለምስክርነት በአገልግሎት ውስጥ በመሰጠት ለመውጣት ምንም ነገር ሳይተበትበን ለመለኮታዊው ፍቅር ምላሽ ስንሰጥ፥ የህይወታችንን ዓላማ በማሳካት ትልቁን የህይወትን ሐሴት እናጣጥማለን። ኢየሱስ በቀላሉ እንዳስቀመጠልን፡‹‹እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ።››(ዮሐንስ13:17፣አ.መ.ት.)የህይወት ትልቁ ሐሴት እና የማያልቀው ደስታ የሚመጣው እግዚአብሔርን በምንኖረው ህይወት እና ለዓለም የእርሱን ፍቅርና ዕውነት በማካፈል የመኖራችንን ትርጉም ማሳካት ከመቻል የሚገኝ ነው።

ስለ ዘለዓለም ለመገንዘብ ከባድ የሆነ ነገር ነው፥ በተለይም ከጊዜ የምናውቀው ቅንጣት የማትሞላውን ብቻ ሲሆን።ዳሩ ግን፥ በሚችሉት አቅም ሁሉ እስቲ ዘለዓለም የተባለውን ነገር በህሊናዎ ይሳሉ፥ ዘለዓለማዊ የሆነ መልካም ህይወት በዚህ ከሚኖረን ምንም ነገር ይበልጣል- ደግሞም በዚያው ልክ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ የሚኖረን ነገር ምንም ቢሆን በኢየሱስ ካለን ዘለዓለማዊ ህይወት ተስፋ እንድንጎድል በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም።

መስከረም 15
Sep 25


ተጨማሪ ሐሳብ


‹‹በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ የበላይ አመራር ያላቸው ሁሉ ለእያንዳንዱ አባል በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ የተወሰነውን ክፍል ወስደው ለመተግበር የሚችሉበትን ዕድል እንዲሁም ዘዴዎች መፍጠር አለባቸው። በቀደምት ጊዜያት በተደጋጋሚ ይህ ሳይደረግ ቀርቷል። ዕቅዶች በግልጽ ሳይቀመጡ እና በሙላት ሳይፈጸሙ ቀርተው የሁሉም መክሊት በንቃት ተግባር ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል። ከዚህ የተነሣ የጠፋውን ነገር መጠን የሚገነዘቡ ጥቂቶችም ቢሆኑ አሉ።

‹‹በእግዚአብሔር ጉዳይ ላይ አመራር የያዙ፥ እንደ መልካም ጀነራሎች በመሆን፥ በሚኬድበት አቅጣጫ ላይ ስለሚደረጉ እርምጃዎች ዕቅዶችን ማውጣት አለባቸው። በዕቅዳቸውም ውስጥ በተራ አባላት አማካይነት ለወዳጆቻቸው እና ለጎረቤቶቻቸው መከናወን የሚችሉ ልዩ ትምህርቶችን ሊሰጧቸው ይገባል። የቤተክርስቲያናችን አባላት የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች ለስራ እስካልተሰባሰቡ እና ኃይላቸውን አሰባስበው ከአገልጋዮች እና የቤተክርስቲያን ሹሞች ጋር እስካልተባበሩ ድረስ በምድር ያስቀመጠው የእግዚአብሔር ስራ ወደ ፍጻሜ አይመጣም።

‹‹የኃጢዓተኖች ደህንነት ከልብ የሆነ የግል ጥረትን ይጠይቃል። የህይወትን ቃል ልናመለክታቸው፣ ወደ እኛ እስኪመጡ ድረስ ላንጠብቅ ይገባል።ደግሞ፥ በትጋት ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ ለወንዶች እና ለሴቶች ይህንን ማነሳሻ እንደተናገርኩ ይቆጠር! አሁን የተሰጠን ጊዜ በጣም አጭር ነው። በዘለዓለማዊው ዓለም ጠርዝ ላይ ቆመናል። የሚባክን ጊዜ የለንም። እያንዳንዱ አጋጣሚ ወርቃማ ነው። ደግሞም ራስን ለማገለገል ብቻ ተጠቅመን ለማሳለፍ የሚያሳሳ ነው። እግዚአብሔርን በፍቅር እየፈለጋችሁ የእርሱ ታማኝ ሰራተኞች ሆናችሁ በማሳው ውስጥ ለመሰማራት ወገባችሁን የታጠቃችሁ እነማን ናችሁ?

‹‹በእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ውስጥ መክሊት አለ፥፣ ይህም ትክክለኛውን ስፍራ ሲያገኝ፣፥ ለዚህ ሥራ ትልቅ እገዛ እንዲያደርግ ሊጎለብት የሚችል ነው። አሁን ላይ አብያተክርስቲያናትን ለማቅናት የሚፈለገው ነገር በቤተክርስቲያን ውስጥ መክሊቶችን ለማሰልጠን እና ለማጎልበት በብልህ ሰራተኞች የሚከናወን መልካም ተግባር ነው- ይህ መክሊት ለጌታችን አገልግሎት እንዲውል ትምህርት ሊሰጥበት ይገባል።››—ኤለን ጀ. ኋይት፣ቴስቲሞኒሰስ ፎር ዘ ቸርች፣ 9ኛ ዕትም፣ገጽ. 116፣ 117 (ከእንግሊዝኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች1.ከላይ የተጠቀሰው የኤለን ጂ ኋይት ጥቅስ ዋነኛው አሳብ ምንድነው? በእርስዎ የግል ምስክርነት እና በቤተክርስቲያን የወንጌል ጥረት ላይ ምን ተጽዕኖ ይፈጥራል?

2.ዕውነተኛ ፍቅር ሁልጊዜ የሚገለጠው እንዴት ነው? ዕውነተኛ የሚባል ፍቅር የማይነካካቸው አሳሳች የሆኑ የፍቅር ዓይነቶች ምንድር ናቸው?

3.በጥናት ክፍለ ጊዜ፥ ለጌታ ሲሉ ሰዎች ስላደረጉት መስዋዕትነት ተነጋገሩ፥ ህይወትን ማጣትን ጨምሮ ማለት ነው። ከእነዚህ ታሪኮች ምን ልንማር እንችላለን?

4.በእሁዱ ጥናት መጨረሻ ላይ ለቀረበው ለክርስቶስ ሲሉ ምን መስዋዕት አድርገው እንደሚያውቁ ለተጠየቁበተ ጥያቄ የእርስዎ ምላሽ ምን እንደነበር ያስታውሱ።´ዕውነት ለመናገር፥ እርስዎ ምን መስዋዕት አድርገዋል? ለምንስ ያንን አደረጉ? ይገባ ነበርን? ክርስቲያን ላልሆነ ሰው ያደረጉትን ነገር እና ምክንያቱን በተመለከተ እንዴትስ ያብራሩታል?


የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ

የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ

ማሳሰቢያ

የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡ እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ