የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከመስከረም 2–8

12ኛ ትምህርት

Sep 12 - Sep 18
ማካፈል የተገባው መልዕክትሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ጥናት የሚነበቡ:2 ጴጥ. 1:12፣ 16–21፤ራዕ. 19:11–18፤ ራዕ. 14:14– 20፤መክብብ 12:13፣ 14፤ራዕ. 14:6–12


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ‹‹ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤ በታላቅ ድምፅም፣ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” አለ።››(ዮሐንስ ራዕይ 14:6, 7, አ.መ.ት)

ክ ርስቶስ ሞት ለዓለም ሁሉ ነበር፤ማለትም፥እንዲደርስ የታሰበው የትም ይሁን መች ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ያለማዳላት እንዲዳረስ ነው። በመሆኑም፥ ወንጌል የሚነገረው ለሁሉም ዓይነት ቡድን፣ ባህል፣ እና ቅድመ ታሪክ ላላቸው ሰዎች ነው። የጎሳ ክፍፍሎችን ያጋጥማቸዋል። ኢየሱስ በህይወቱ፣ በሞቱ እና በትንሳዔው ከሲዖል ኃይላት እና ስልጣናት በላይ የመሆኑ ዜና ትልቅ የምስራች ነው። ወንጌል ማለት ስለ ኢየሱስ ብቻ የሚነገርበት ነው። እርሱ ለእኛ ሲል ሞተ፣ አሁን ደግሞ ለእኛ ሲል ይኖራል።ከኃጢዓት ቅጣት እና ጉልበት ሊያስለቅቀን አንድ ጊዜ መጥቶ ነበር፣ አሁን ደግሞ ዳግም ሲመጣ ከኃጢዓት መገኘትም ነጻ ሊያወጣን ነው።እኛ ልንሞት የሚገባንን ሞት ሞቶልን፥ እርሱ መኖር የሚገባውን ህይወት እንድንኖር አበቃን። በክርስቶስ እኛ ጸድቀናል፣ ተቀድሰናል ደግሞም አንድ ቀን እንከብራለን።

መጽሐፍ ቅዱስ በሁለቱ የኢየሱስ ምጻቶች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ ሊያድነን ነበር አሁን ሲመለስ ደግሞ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ የገዛውን ወደቤቱ ሊያደርስ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ፥ የዮሐንስ ራዕይ፥ የተጻፈው ዓለምን ለኢየሱስ ዳግም መመለስ በተለይ ለማዘጋጀት ነው። ለዚህ ትውልድ ደግሞ ይህ በጣም አስቸኳይ መልዕክት ነው። በዚህ ሣምንት ትምህርታችን፥ የራዕይ መጽሐፍን ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ካለው ተጽዕኖ አንጻር በዘመናዊው ማኅበረሰብ መካከል እናጠናለን። በአንድነት በመሆንም፥ በዚህ የመጨረሻ ዘመን መልዕክት የምንካፈለውን ለመጨረሻዋ ዘመን ቤተክርስቲያኑ የተሰጠውን ኢየሱስን ጥሪ እንደ አዲስ እንተዋወቃለን።

*የዚህን ሣምንት ትምህርት በማጥናት ለመስከረም 9 ሰንበት ይዘጋጁ።

መስከረም 3
Sep 13

ጴጥሮስ የዘመኑ መልዕክት


በደህንነት ታሪክ ውስጥ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ስለሚመጣው ነገር እንዲዘጋጁ ለህዝቡ በትንቢት ቃል ልዩ መልዕክት አዘጋጅቶ መላክ አላቋረጠም ነበር። እግዚአብሔር ዱብ እዳ አይወድም(ኢሳ. 46:9, 10)ነብያትን በመላክ እና ፍርድ ከመሆኑ አስቀድሞ መልዕክቱን በመግለጥ የራሱን ሕዝቦች ለመጻዒው ያዘጋጃል።(አሞፅ 3:7)የውሃ ጥፋት ከመሆኑ አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት፣ ኖህን በመጠቀም የውሃ ጥፋት በመምጣት ላይ መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት እግዚአብሔር ላከ። በግብጽ ደግሞ፥ ሰባት የጥጋብ ዓመታት አልፈው ከዚያ ለርሃብ እንዲዘጋጁ እግዚአብሔር ዮሴፍን አስነሳላቸው። በአይሁድ የሚገኙ ነብያት ደግሞ በባቢሎናውያን እጅ ኢየሩሳሌም ልትወድም እንደሆነ ለእስራኤላውያን መሪዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። መጥምቁ ዮሐንስም ቢሆን ለኢየሱስ የመጀመሪያው ምጻት ህዝቡ እንዲዘጋጅ የንሰሐ መልዕክትን ይዞ ቀርቦ ነበር።

እስቲ 2ኛ ጴጥ.1:12ን እናንብብ። ለትውልድ እግዚአብሔር የሰጠውን መልዕክት ለመግለጽ ጴጥሮስ የሚጠቀመው ምን አይነት አገላለጽ ነው?በ2ኛ ጴጥ 1:16–21 ያለውን ያንብቡ፤ ጴጥሮስ እና ደቀመዛሙርት ያወጁት የዘመኑ መልዕክት ምን ነበር?በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት የምናገኘው ዘለዓለማዊ ጠቀሜታ ያለው መልዕክት ክርስቶስ መጥቷል የሚለው ነበር። በመስቀል ላይ ክርስቶስ ባደረገው መስዋዕትነት የአብ ፍቅር ተገልጧል። ምንም እንኳን፥ ‹‹የኃጢዓት ዋጋ ሞት›› ቢሆን፥ በክርስቶስ በኩል ዘለዓለማዊ ህይወት ተረጋግጦልናል። በዕምነት መቀበል የእኛ ምርጫ ነው። (ሮሜ. 3:23፣ሮሜ. 6:23፣ኤፌ. 2:8)ይህ በኢየሱስ ያገኘነው የደህንነት መልዕክት ከቶ የማያረጅ ነው። ለየትኛውም ትውልድ ቢሆን የዘመኑ መልዕክት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ፥ የዮሐንስ ራዕይ፥ ኢየሱስን እንዲሁም የእርሱን ዘለዓለማዊ ደህንነት በመጨረሻው ዘመን ዐውድ ውስጥ በማድረግ፥ ለእርሱ ዳግም ምጻት ሰዎችን የሚያዘጋጅ አድርጎ ያቀርበዋል። የሰዎችን ልማድ ሐሰተኝነት እንዲሁም ራስን ማዕከል ያደረገውን ሃይማኖታዊነት ያጋልጣል። ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ድረስም፥ በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ የምናገኘው ኢየሱስ ስለሰው ዘር ሲል ያደረገውን ተግባር ነው።

ኢየሱስ የአብ ምግባር የታመነ ምስክር ነው።እርሱ ‹‹የምድር ነገስታት ገዢ›› ነው፤ ደግሞም ‹‹የወደደን ከኃጢታችንም በደሙ ያጠበን፥ አምላኩን እና አባቱን እንድናገለግልም መንግስት እና ካህናት ያደረገን›› እርሱ ነው። (ራዕ. 1:1–6፣አ.መ.ት ይመልከቱ) የራዕይ መጽሐፍ ዋና ዓላማው ኢየሱስ እና ለእርሱ ዳግም ምጸት የእርሱን ህዝብ ለማዘጋጀት የሰጠውን የመጨረሻ ዘመን መልዕክት የያዘ ነው። የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍን ሲያስቡ፥ ወደ ህሊናዎ የሚመጣው ምንድር ነው? የእርስዎ አሳብ ከኢየሱስ ይልቅ በይበልጥ ስለ አውሬዎች እና ስለ ትንቢታዊ ምልክቶች ነውን? እነዚህን ትንቢቶች በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ ኢየሱስ የሰጠን ለምን ይመስልዎታል? እነዚህስ ስለ ሰብዓዊ ዘር እርሱ ያለውን የፍቅር ዕቅድ የሚገልጡልን እንዴት ነው?

መስከረም 4
Sep 14

የራዕይ መጽሐፍ የመጨረሻ ዘመን ትኩረት


የወንጌላት ተቀዳሚው ማዕከል የክርስቶስ የመጀመሪያው ምጻት ላይ ነው። ስለ እርሱ መወለድ፣ ስለ እርሱ ህይወት፣ ስለ እርሱ አገልግሎት እና ስለ እርሱ ሞትና ትንሳዔ ይተርካሉ። ምንም እንኳን ስለ እርሱ ዳግም ምጻት የሚናገሩም ቢሆን፥ የእነዚህ ዋነኛው ትኩረት ይህ አልነበረም። የዮሐንስ ራዕይ ዋነኛው ትኩረት ግን፥ ለዘመናት የከረመው የምዕተ ዓመታት ግጭት ጡዘት ጫፍ ላይ ነው።እያንዳንዱ አበይት የሆኑ ትንቢቶች የሚጠናቀቁት በጌታችን ግርማዊ ዳግም መመለስ ነው።

ራዕይ 1:7፣ራዕ 11:15፣ራዕይ 14:14–20፣እና ራዕይ 19:11–18ን እናንብብ። በእነዚህ እያንዳንዳቸው ምንባቦች ውስጥ ምን ተመሣሣይ የሆነ ማጠቃለያ ሊያገኙ ቻሉ?በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ከመጀመሪያው ምዕራፍ አንስቶ እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ድረስ፥የኢየሱስ ምጻት የእያንዳንዱ ትንቢት ጡዘት ጫፍ ነበር።‹‹የታረደው በግ››(ራዕ. 5:12፣አ.መ.ት.). የነገስታት ንጉስ እና የጌቶች ጌታ ሆኖ ይመለሳል፤ (ራዕ. 19:16) የእርሱን ሕዝቦች ሲያሳድዱ እና ሲጨቁኑ የነበሩትን ጠላቶች ሁሉ ድል ይነሳል። (ራዕ. 17:14)ከዚህ ኃጢዓት ቅዠት በመገላገል ወደ ባለግርማው ቤታቸው ይወስዳቸዋል። በመልካም እና በክፉው መካከል ያለው ትልቁ ተጋድሎ ይጠናቀቃል። ምድር አዲስ ትሆለች፤ በዚህም ከጌታቸው ጋር አብረው ለዘለዓለም ይኖራሉ። (ራዕ. 21:1–4).

በራዕይ መጽሐፍ 22:7 (እንዲሁም ቁጥር 12፣ 17 እና 20ን ይመልከቱ)፥ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” (አ.መ.ት)። ከዚህ የተነሣ፥ የኢየሱስ የመጨረሻው ጥሪ የሰው ዘር የሆነ ሁሉ ለፍቅሩ ምላሽ እንዲሰጥ፣ ጸጋውን እንዲቀበል እና የእርሱን ዕውነት በመከተል በቅርብ ለሚሆነው የእርሱ ዳግም ምጻት እንዲዘጋጁ ነው።በራዕይ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ፥ የኢየሱስን ጥሪ እናገኛለን፡ ‹‹መንፈስና ሙሽራዪቱ፣ “ና” ይላሉ፤ የሚሰማም፣ “ና” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ።››(ራዕ. 22:17, አ.መ.ት.).

ጌታችን ሁላችንንም ዘለዓለማዊ የሆነ ህይወት ከእርሱ ለማግኘት እንድንሻ ይጋብዘናል። ከዚያም በማስከተል ደግሞ የደህንነት መልዕክቱን የተቀበሉ ሁሉ፥ የእርሱን ፍቅር ሌሎችም እንዲቀበሉ በመጋበዝ ከእርሱ ጋር አብረ እየሰሩ የእርሱን ዳግም ምጻት በጉጉት እንዲጠባበቁ ግብዣውን ያስተላልፋል። ዓለምን በቅርብ ለሚሆነው የእርሱ ዳግም ምጻት ለማዘጋጀት የእርሱን መልዕክት እንድናስተላልፍ ተልዕኮ ሰጥቶ ሰድዶናል። ከኢየሱስ ጋር አብሮ በመሆን ለዓለም በሚሰድደው ተልዕኮ ከመሳተፍ የበለጠ ሽልማት የለም።ከክርስቶስ ጋር በመሆን በመጨረሻዎቹ ቀናት የደህንነት ዕቅድ ውስጥ ትብብር ከማድረግ ጋር የሚወዳደር የሚያረካ ነገርም የለም።

ክርስቶስ በቶሎ ይመጣልን? ዮሐንስ እነዚህን ቃላት ከጻፈ 2,000 ዓመታት አልፎታል። ነገር ግን፥ የሞቱ ሰዎች አሁን ስላሉበት ሁኔታ ያለንን ግንዛቤ ከግምት ካስገባን፥ ለእያንዳንዳችን በሚኖረን በግል ገጠመኞች የክርስቶስ ዳግም ምጻት ማለት ከሞት ቀጥሎ ወዲያውኑ የሚያጋጥመን ክስተት መሆኑ ለምን ይሆን?ይህንንስ ዕውነታ መረዳታችን ክርስቶስ ምን ያህል በቶሎ እየመጣ እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?

መስከረም 5
Sep 15

የራዕይ መጽሐፍ የመጨረሻው ዘመን መልዕክት


የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ መሐል ለመሐል ሲሰነጠቅ ምዕራፍ 14 ላይ ያርፋል።በዚህ ምዕራፍ ደግሞ በሰው ዘር ታሪክ የመጨረሻ ቀናት ላይ ለሚኖሩ የእግዚአብሔር ሰዎች በጣም ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ይህም በመጨረሻውም ዘመን ለሰው ዘር የሚሰጠውን የእግዚአብሔር መልዕክት ይተርካል። ይህ የመጨረሻ ዘመን መልዕክት ደግሞ ለእግዚአብሔር ህዝቦች እና ለሰው ዘር በአጠቃላይ ወሳኝነት አለው። እስቲ በራዕይ 14:14–20 ያለውን እናንብብ። የጌታችንን መመለስ የሚስልልን ምን ዓይነት ተምሣሌት እናገኛለን?የመከሩ ተምሣሌት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የክርስቶስን መመለስ ለማመልከት ነው።(ማቴ. 13:37–43፣ማርቆስ 4:29)በዮሐንስ ራዕይ 14 ላይም፥ የደረሰውን መከር የመሰብሰብ ምሳሌው የሚያመለክተው የጻድቃንን ቤዛ ሲሆን፥ የበሰለው ዘለላ መታጨድ ደግሞ የሚያመለክተው የርኩሳንን መወገድ ነው።ራዕይ 14:6–12 ላይ ደግሞ ወንዶች እና ሴቶች ለምድር የመጨረሻው መከር እንዲዘጋጁ የተሰጠውን አስቸኳይ መልዕክት እናገኛለን።

ራዕይ 14:6፣ 7ን ያንብቡ፤በእነዚህ ሁለቱ ቁጥሮች ውስጥ የሚገኘው መልእክት ይዘት ምንድነው? እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን ማንነታችንን እንድንገነዘብ የሚረዱንስ እንዴት ነው?በራዕይ ምዕራፍ 14 ላይ የምናገኘው የመጀመሪያው መልዓክ መልዕክት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ለህይወታቸው ዓላማ እንዲኖራቸው ጥሪ የሚያቀርብ ነው። ለሁሉም ይቅርታን የሚሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌል ያሳያል። ሁላችንንም ደግሞ ከኃጢዓት በደል በማንጻት ባለድሎች እንድንሆን ጉልበት ይሰጠናል። ከዚህ መልዕክት ክርስቶስ እኛን ስለ መፍጠሩ እና ስለ ማዳኑ በማየት ለራሳችን ያለንን ግምት ማጎልበት እንችላለን። አንድ ቀን የፍትህ መጓደል ሁሉ ያበቃና የእግዚአብሔር የመጨረሻ ፍርድ እንደሚሰጥ ያመላክታል። ደግሞም ርኩሰት ሁሉ ለዘለዓለም እንደማይቆይ የሚገልጥልን በመሆኑ የሚያስደስት የምስራች ነው።

‹‹የተለየ በሆነ መንገድ፥ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ጠባቂዎች እና መንገዱን አብሪዎች ሆነው በምድር ላይ ተሰይመዋል። ለእነርሱ የተሰጠው ዓደራ ለጠፊው ዓለም የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ ማስተላለፍ ነው። ደግሞም የእግዚአብሔር ቃል የሚያስደንቅ ብርሐን በእነርሱ ላይ በርቷል። እጅግ በጣም ትልቅ ፋይዳ ያለውን ስራ ተቀብለዋል - የአንደኛውን፣ ሁለተኛውን እና ሦስተኛውን መልዓክ መልዕክት ማወጅ። በዚህ ልክ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ሌላ ሥራ የለም። የእነርሱን ትኩረት ሊወስድ የሚችል ሌላ ነገር እንዲኖር መፍቀድ የለባቸውም።››—ኤለን. ጂ. ኋይት, ኢቫንጀሊዝም፣ገጽ. 119፣ 120.

እንደ ቤተክርስቲያን ስናስብ፥ ደግሞም ከዚያም ባለፈ፥ እንደ ግለሰብ፥ እነዚህን ቃላት ወደ ልባችን የምናዘልቃቸው እንዴት ይሆን?

መስከረም 6
Sep 16

የእግዚአብሔርን መልዕክት ይበልጥ በሙላት መገንዘብ


በራዕይ መጽሐፍ የምናገኘው የመጨረሻው ዘመን መልዕክት ኢየሱስን የሰውን ዘር ሁሉ በሚያድን የጸጋው ሙላት ይቀርጽልናል። (ራዕ. 14:6) የእግዚአብሔርን ፍርድ በማሰብ፥ የእርሱን ትዕዛዛት እንድናከብር፣ እንዲሁም የእርሱን ሕግ እንድንከተል በምናደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን እንድንፈራ ወይም አክብሮትን እንድናሳይ በትህትና የቀረበ ጥሪ ነው። (ራዕ. 14:7). እግዚአብሔርን መፍራት ማለት የአስተሳሰባችን ጉዳይ ነው። ደግሞም እግዚአብሔርን በሚያስደሰስት ሁኔታ ለመኖር እና በምናስበው ነገር ሁሉ እርሱን እንድናስቀድም የቀረበ ጥሪ ነው። ፈሪሓ እግዚአብሔር የተሞላ ህይወት እንድንመራ የሚያደርገን አስተሳሰብ ነው። (ምሣ. 3:7፣ሐዋ. 9:31፣ 1ኛ ጴጥ. 2:17) ይህ መልእክት በተጨማሪም፥ ለእግዚአብሔር ‹‹ክብርን›› እንድንሰጥም ይጋብዘናል። ለእግዚአብሔር ክብርን መስጠት ማለት በህይወታችን ከምናደርገው ነገር ጋር የተገናኘ ነው።

እስቲ መክብብ 12:13፣ 14 እና 1ኛቆሮንቶስ 6:19፣ 20ን እናንብብ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔርን መፍራትን እና ለእርሱ ክብርን መስጠትን በምን መንገድ ይተረጉሙልናል?በዚህ ግብረገብ በዘቀጠበት ዘመን፥በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከራሳቸው በቀር ለማንም ግድ የማይላቸው በበዙበት ጊዜ ላይ፥ ይህ የፍርድ ሰዓት መልዕክት መሰጠቱ ስለድርጊቶቻችን ኃላፊነት የምንወስድ መሆኑን አመላካች ነው። ለእግዚአብሔር አክብሮት በማሳየት፣ እግዚአብሔርን በመታዘዝ እና በፍርድ መካከል የአስተሳስብ ግንኙነት አለ። መታዘዝ ማለት ከኢየሱስ ጋር ያለን የመዳን ግንኙነት ውጤት ነው። የእርሱ ጽድቅ ብቻ ነው ፍርዱን እንድናልፍ የሚያበቃን፤ ደግሞም በእርሱ ጽድቅ የተነሣ ደህንነት የተረጋገጠልን እንሆናለን። በእርሱ ጽድቅም እንደዚሁ ለእርሱ ክብር በምናደርገው ነገር ሁሉ እንኖራለን።

በራዕይ 14:7፣ራዕይ 4:11፣ዘፍጥረት 2:1–3 እና ዘፀዓት 20:8– 11 ያለውን ያንብቡ። እግዚአብሔርን በዕውነት የማምለክ መሠረቱ ምንድነው፣ ደግሞስ ሰንበት ይህንን ግንዛቤያችንን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?ሰይጣን የአምልኮ ማዕከሉ መሆኑን ስላየ ሰንበት ላይ በቀጥታ ጥቃት አድርሶበታል። ክርስቶስ ፈጣሪ መሆኑን በማጉላት ‹‹ሰማይን እና ምድርን ለፈጠረው›› እንዲሰግዱ በየትም ስፍራ ለሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች ጥሪውን ያስተላልፋል። (ራዕ. 14:7, አ.መ.ት) በዝግመተ ለውጥ ዘመን ላለነው በተለይ ይመጥነናል። እኛን ለፈጠረን እና በእርሱ ዕውነተኛ ዋጋችንን እንድናውቅ ላደረገን ለኢየሱስ እንድንሰግድ ጥሪ ያቀርብልናል።

እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ስለመሆኑ፥ እንዲሁም በዚህ የተሣ እርሱ ብቻ ስግደት የሚገባው መሆኑን በማሳሰብ ረገድ ሰንበት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እስቲ ያስቡ።የሆነ ሆኖ፥ ከእግዚአብሔር ትዕዛዛት፣ ከህይወታችን አንድ ሰባተኛውን በየሣምንቱ በመስጠት እርሱ ፈጣሪያችንን እንድናስብበት ከታዘዝንበት ይልቅ በጣም ጠቃሚ የሆነ ከዚህ የበለጠ ምን ትምህርት እናገኛለን?

መስከረም 7
Sep 17

የእግዚአብሔር የመጨረሻ ጥሪ


በራዕይ 14:8፣ራዕይ 17:3–6፣እና ራዕይ 18:1–4 የሚገኘውን ያንብቡ፤ ከእነዚህ ጥቅሶች በመነሳት ስለ መንፈሳዊቷ ባቢሎን ምን ትምህርት እናገኛለን?______በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ውስጥ፥‹‹ባቢሎን›› የሚለው አገላለጽ የሚወክለው በሰብዓዊ ሥራ ላይ የተመረኮዘውን የሐሰት ሃይማኖት ስርዓት እና የሐሰት አስተምህሮዎች ነው። ይህም የሰውን ዘር እና የየራሳቸውን ጽድቅ ከኢየሱስ እና ከኃጢዓት አልባ ህይወቱ በላይ ያሞግሳል። ደግሞም ሰብዓዊ የሆኑ የሀይማኖት መምህራንን ትምህርት ከእግዚአብሔር ትዕዛዛት በላይ ያስቀምጣል። ባቢሎን የጣዖት አምልኮ፣ የጸሀይ ስግደት እና ነፍስ ስላለመሞትዋ የሚናገረው የተሳሳተ ትምህርት የተማከለባት ናት። ይህ ሐሰተኛ የሆነ የሃይማኖት ስርዓት በበርካታ የባቢሎን የሃይማኖት ልማዶች ውስጥ በመጣመራቸው በስግደትም ውስጥ ተካትተዋል።በጥፋት አፋፍ ላይ ለምትገኘው ባቢሎን የመጣው የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን መልዕክትም ከኢየሱስ እና ከእርሱ ጽድቅ የመነጨ መልዕክት ነው። የሰማይን ጥሪ ሲያስተጋባ ሣለ እንዲህ ይላል፡ ‹‹…“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! … ሕዝቤ ሆይ፤….ከእርሷ ውጡ፤›› (ራዕ. 18:2, 4) የክርስቶስን መልዕክት በሙላት እንዲያሞግሱ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶችን እግዚአብሔር አስነስቷል። ኢየሱስን ማሞገስ ማለት እርሱ ያስተማረውን ነገር ሁሉ ከፍ አድርጎ ማሳየት ነው። ደግሞም ‹‹መንገድ፣ ዕውነት እና ህይወት›› የሆነውን እርሱን ማወጅ ጭምር ነው። (ዮሐ 14:6) ከኢየሱስ ዕውነት ጋር በማስተያየት የባቢሎንን ስህተቶች ያጋልጣል።

በራዕይ 14:7፣ 9–11፤ ያለውን እናንብብ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጎልተው የምናገኘው የአምልኮ/ስግደት ዓላማ ምን ምን ናቸው?በዮሐንስ ራዕይ 14 ላይ ሁለት የስግደት ድርጊቶችን ተብራርተው እናገኛለን - ለሁሉ ፈጣሪ የሚቀርበው ስግደት እና ደግሞ ለአርዌው የሚቀርብ ስግደት። እነዚህ ሁለት የስግደት ድርጊቶች ማዕከላቸውን የሚያደርጉት ደግሞ በእግዚአብሔር የአምልኮ ቀን፥ ዕውነተኛው ሰንበት፣ እንዲሁም በመተኪያው ወይም ማሳሳቻ ሰንበት ላይ ነው።ሰንበት በፈጠረን፣ በቤዛችን እና በሚመጣው ንጉስ በክርስቶስ፣ ላይ ያለንን ዕረፍት፣ የተረጋገጠ ደህንነት እና መተማመኛ ማሳያ ነው። ማሳሳቻው ዕለት ደግሞ የሚያሳየው በሰብዓዊ ምክንያታዊነት እና በሰው ሰራሽ ህጎች የሚተካውን ሰብዓዊነት እና ስህተት ነው።

በራዕይ 14:12 ያለውን ያንብቡ፤ በተለይም አስቀድሞ ስለመጣው ነገር በሚመለከት ይህ ጥቅስ የሚያወራው ስለምን ነው? ጸጋ እና ሕጉ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ተገልጠው የምናገኛቸው እንዴት ነው? ደግሞስ ከዚህ በመነሳት ሕጉ እና ጻጋው የወንጌል የማይነጣጠሉ ፈርጆች ስለመሆናቸው የምንረዳው እንዴት ነው?

መስከረም 8
Sep 18


ተጨማሪ ሐሳብ


‹‹እግዚአብሔር የጥንትዋን እስራኤል እንደ ጠራት ሁሉ ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን ጥሪ አለው፥ በምድር ላይ መብራት ሆና እንድትቆም። የአንደኛውን፣ የሁለተኛውን እና የሦስተኛውን መልአክ መልዕክት ሃያል ሰይፍ ተጠቅሞ ወደ ተቀደሰው ማንነቱ እንድታቀርባቸው ዘንድ ከሌሎች አብያተክርስቲያናት እና ከዓለም ለይቷታል። ለዘመኑ የሚሆኑ የትንቢትን ታላቅ ዕውነታዎች በመስጠት የእርሱን ሕግ ማስቀመጫ ዕቃዎች አድርጓቸዋል። ለቀደምት እስራኤላውያን ያስቀመጠላቸውን ቅዱሳን መገልገያ ዕቃዎች ተመስለው፥ ለዓለም እንዲነገሩ የተቀመጡ ቅዱሳን ዐደራዎች ናቸው።

‹‹የዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 14 ላይ ያሉት ሦስቱ መላዕክት የእግዚአብሔርን መልዕክት ብርሃን የሚቀበሉ እና የእርሱ ወኪል በመሆን በዓለም ወርድ እና ርዝመት ሁሉ ይህንን ማስጠንቀቂያ ለማሰማት የሚላኩትን ሰዎች የሚወክሉ ናቸው። ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዲህ ሲል አወጀ፡‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ›ማቴዎስ 5:14. መስቀሉን ለሚቀበል ለእያንዳንዱ ነፍስ፥ የቀራንዮው መስቀል ‹‹የነፍስዎ ዋጋ እነሆ›› የሚል ይመስላል። ‹‹እንዲህም አላቸው፤“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤››ማርቆስ 16:15.ምንም ዓይነት ሥራ ቢሆን ይህንን ሊያደናቅፍ አይገባም። ለዘመናችን እጅግ ጠቃሚው ሥራ ይህ ነው፤ አድማሱም ጊዜ የማይገድበው ነው። ተከታዮቹን የሚነዳቸው ጉልበት፥ ለሰው ዘር ሁሉ ቤዛ ይሆናቸው ዘንድ ባቀረበው መስዋዕትነት ውስጥ ኢየሱስ ያሳየው ፍቅር ነው።

‹‹ክርስቶስ እያንዳንዱን ለእርሱ ራሱን የሰጠውን ሰብዓዊ አቋም ሁሉ በደስታ ይቀበላል። ደግሞም፥ ስጋ የለበሰውን ፍቅር ምስጢር ለዓለም ለማስተጋባት ይችል ዘንድ፥ ከመለኮታዊው ጋር ሰብዓዊውን ወደ ህብረት ያመጣዋል። ወሬው ስለዚህ ይሁን፣ የጸሎትም ርዕስ ይኸው ይሁን፣ መዝሙርም በዚሁ ይዘመር፣ ዓለም በዚህ የዕውነት መልዕክት ተጥለቅልቃ እስከዳርቻዎቿ ይሙላት።>>—ኤለን ጀ. ኋይት, ካውንስልስ ፎር ዘ ቸርች፣ገጽ. 58, 59. (በእንግሊዝኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች1.በራዕይ ምዕራፍ 14 ላይ የምናገኘው የሦስቱ መላዕክት መልዕክት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትን ቤተክርስቲያን ምንነት የሚያመላክተው እንዴት ነው?

2.እስቲ ስለ ሰንበት እና ሰንበት ስለሚወክለው ነገር ጠቀሜታ ጥቂት ያሰላስሉ፤ በዚህ ሣምንት ካየነው በመነሳት፥በውስጡ የያዘው መልዕክት በዋናነት ከህይወታችን ላይ አንድ ሰባተኛውን በመመደብ እርሱን የእኛ ፈጣሪ እና የእኛ ቤዛ አድርገን እንድናስበው የሚጠይቅ የእግዚእብሔርን ትዕዛዝ የያዘ ነው። ደግሞም፥ ወደ አንድ ቅዱስ ተራራ ወይም ወደ አንድ ቅዱስ ከተማ የግድ ለአምልኮ መሔድ አይኖርብንም።በሰዓት እጅግ አያሌ ማይሎችን እየበረረ (የምድር ወገብ አከባቢ ላይ ሲለካ) ሰንበት በየሳምንቱ ወደእኛ ይመጣል። ይህንን ዕውነት ማወቃችንስ የቀኑን እንዲሁም የሚወክለውን ነገር ፋይዳ እንድንገነዘብ የሚያደርገን እንዴት ነው?

3.የባቢሎንን መውደቅ ወይም የአርዌውን ምልክት እሳቤ ከልብ ሊያሳምን በሚችል ሁኔታ ለሌላ ሰው ሊያብራሩ የሚችሉት እንዴት ነው? በሌላ አባባል፥ ምንም እንኳን የፈለግነውን ጥረት አድርገን አንዳንድ ሰዎች ሊቀየሙን የሚችሉ ቢሆንም ቅሉ፥ ዕውነትን በተቻለን መጠን ለሌሎች በማያስቀይም መንገድ ልናቀርብ የምንችለው እንዴት ነው?