የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከነሐሴ 30 - መስከረም 1

11ኛ ትምህርት

Sep 05 - Sep 11
የኢየሱስን ታሪክ ማካፈልሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ትምህርት የሚነበቡ:ኤፌ. 2:1–101፣ዮሐንስ 4:7–11፣ማርቆስ 5:1– 20፣ዕብ. 10:19–22፣ገላ. 2:20፣ 1ኛቆሮ. 1:30፤


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡‹‹በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ እናንተ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤›› (1ኛ ዮሐንስ 5:13፣አ.መ.ት.).

በ ቀደሙት ትምህርቶች ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ ከተቀደሰ ሕይወት በበለጠ ስለ ወንጌል ጉልበት በአርኪ ሁኔታ ሊገልጽ የሚችል ምንም ነገር የለም። አንዳንድ ሰዎች ስለ እርስዎ ስነ መለኮታዊ አተያይ ክርክር ሊገጥሙ ይችሉ ይሆናል። በተለያዩ አስተምህሮዎች ላይ ክርክር ይኖራቸው ይሆናል። ስለ ቅዱስ ቃሉ ያለዎትን ግንዛቤ ጥያቄ ውስጥ ሊከትቱት የሚችሉ ቢሆንም፥ ኢየሱስ ለእርስዎ ምን ማለት እንደሆነ እና ለእርስዎ ያደረገልዎትን ነገር ግን ሊጠራጠሩ የሚችሉት እምብዛም ነው።

ምስክርነት ማለት ስለኢየሱስ የምናውቀውን ነገር ማካፈል ነው። ለእኛ እርሱ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ለእኛ ያደረገልንን ነገር እንዲያውቁ ለሌሎች ማሳወቅ ማለት ነው።እኛ የምናምነው ነገር ዕውነት መሆኑን በማረጋገጥ እና የሌሎችን ዕምነት ስህተት ማውጣት ላይ ብቻ ትኩረታችንን አድርገን ምስክርነት የምናከናውን ከሆነ፥ ጠንካራ የሆነ ባላንጣ ነው የሚገጥመን።ምናልባት ስለ ኢየሱስ ያለን የእኛ ምስክርነት በጸጋው ከተለወጠ፣ በፍቅሩ ከተማረከ እና በዕውነቱ ከተደመመ ልባችን የሚመነጭ እንደሆነ፥ ሌሎችም በዚያው ልክ ይህ ዕውነት ምን ያህል ህይወታችንን እንደለወጠው በማየት ወደ መደነቅ ይመጣሉ። ልዩነቶችን ሁሉ የሚፈጥረው በተለወጠ ህይወት ዐውድ የሚቀርብ ዕውነት ነው።

ክርስቶስ የእያንዳንዱ አስተምህሮ ማዕከል ሲሆን፥ እና እያንዳንዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የእርሱን ባህርይ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ቅዱስ ቃሉን የምናካፍላቸው ሁሉ የእርሱን ቃል ለመቀበል ሰፊ ዕድል ይኖራቸዋል። *የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለመስከረም 2/2012 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጳጉሜ 1
Sep 06

ኢየሱስ: የምስክርነታችን ሁሉ መሠረት


ክርስቲያን እንደመሆናችን፥በየግላችን የምንናገረው ታሪክ አለን፥ ይህም ታሪክ ኢየሱስ እንዴት አድርጎ ህይወታችንን እንደለወጠው እንዲሁም ለእኛ ምን እንዳደረገልን የሚተርክ ነው። ኤፌሶን 2:1–1 ያለውን እናንብብ። ክርስቶስን ከማወቃችን አስቀድሞ ምን ዓይነት መልክ ነበረን? ክርስቶስን መቀበላችንን ተከትሎስ ለእኛ የሆነልን ነገር ምንድነው? ሀ. ክርስቶስን ሳናውቀው በፊት(ኤፌ. 2:1–3)ለ. ክርስቶስን ካወቅነው በኋላ (ኤፌ. 2:4–10)አስደናቂ ለውጥ እኮ ነው! ክርስቶስን ሳናውቀው አስቀድሞ፥ እኛ ሁላችንም ‹‹በኃጢታችን እና በበደላችን ምክንያት ሙታን›› ሆነን፣ ‹‹የዓለምን ክፉ መንገድ›› የምንከተል ‹‹የስጋችንን ምኞት እያረካን›› እና ‹‹እንደሌሎቹም የቁጣ ልጆች ነበርን።››(አ.መ.ት.). ቀለል ባለ መንገድ ለማስቀመጥ፥ ክርስቶስን ከማወቃችን አስቀድሞ፥ በህይወታችን ከንቱ፣ የምንቅበዘበዝና የጠፋን ሰዎች ነበርን።

ደስታ የሚመስሉ ነገሮችን አከናውነን ይሆናል፥ ዳሩ እና የጎደለ የህይወታችን ዓላማ ይቆረቁረን ነበር። ወደ እንዲሁም የእርሱን ፍቅር መለማመዳችን ነው ልዩነቱ። የምር ህያዋን ሆነናል።እጅግ ‹‹በምህረቱ ባለጠጋ›› ግን፥ የነፍሳችን መቃተት ክርስቶስ በመምጣታችን፣ አሁን በክርስቶስ ስለሆንን ከመሆኑ እና ‹‹ከጸጋው ባለጠግነት›› የተነሣ፥ የድነትን ስጦታ ልናገኝ በቅተናል።እርሱም ሁላችንንም አቃንቶ ‹‹እግዚአብሔርም ከክርስቶስ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፤ ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው፤›› (አ.መ.ት.). በክርስቶስ አማካይነት፥ ህይወት አዲስ ትርጉም እና ዓዲስ ዓላማ አገኘች። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ አወጀው፡ ‹‹ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች።›› (ዮሐ 1:4 አ.መ.ት.)

ኤፌሶን 2:10ን ያንብቡ። መልካምን ማድረግ የክርስትና ዕምነት ማዕከሉ ስለመሆኑ ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ‹‹ሕግን በመፈጸም ሳይሆን›› በዕምነት ድነትን ስለማግኘታችን እያሰብን ይህንን አመለካከት እንዴት ልንገነዘብ እንችላለን? ሮሜ. 3:28?የሆነ ሰው ኢየሱስን እንዲያውቅ ሊረዳ በሚችል መልኩ በክርስቶስ ምክንያት ህይወትዎ የተለወጠው እንዴት ነው?

ጳጉሜ 2
Sep 07

የግል ምስክርነት የሚለውጥ ኃይል


ዮሐንስ እና ያዕቆብ፥ የዘብዴዎስ ልጆች አንደመሆናቸው፥ ‹‹የነጎድጓድ ልጆች›› ተብለው ይጠሩ ነበረ። (ማርቆስ 3:17, አ.መ.ት.) እንደውም፥ ይህንን ቅጽል ስም የሰጣቸው ኢየሱስ ራሱ ነበር። የዮሐንስን ተቀጣጣይነት የሚያሳየው አጋጣሚ የተፈጠረው ኢየሱስ እና ደቀመዛሙርት በሠማርያ አቋርጠው በሚሔዱበት ጊዜ ላይ ነበር።ማታ ላይ ለማደሪያ የሚሆን ቦታ ለመፈለግ ጥረት ሲያደርጉ፥ ሠማርያውያን በአይሁዶች ላይ ካላቸው ክፉ አመለካከት የተነሣ ተቃውሞ ገጠማቸው። በጣም የቆረቆዘ የሚባለው መስተንግዶ እንኳን ተነፈጋቸው።

ያዕቆብ እና ዮሐንስ ለዚህ ችግር የሚሆን መፍትሔ እንዳላቸው አሰቡ።‹‹ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት።››(ሉቃስ 9:54, አ.መ.ት.) ኢየሱስ ወንድማማቾቹን ስለገሳጻቸው በጸጥታ ያንን መንደር ለቅቀው ሄዱ። የኢየሱስ አማራጭ የፍቅር አማራጭ ነው እንጂ በግብግብ የሚያምን አይደለም። የኢየሱስ ፍቅር ባለበት ስፍራ፥ የዮሐንስ መዳፈር እና መቆጣት በአንዴ ተቀይሮ ወደ ፍቅር አዘል ቸርነት እና ርጋታ የተሞላ አፍረቃሪ ስሜት ተለወጠ።በመጀመሪያው የዮሐንስ መልዕክት ውስጥ፥ፍቅር የሚለው ቃል ወደ አርባ ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፤ በተለያዩ መልክ የተገለጸበት መንገድ ደግሞ ወደ 50 ጊዜ ይደርሳል።

በ1ኛ ዮሐንስ 1:1–4፣ 1ኛ ዮሐንስ 3:1፤ 1ኛ ዮሐንስ 4:7–11፤ እና በ1ኛ ዮሐንስ 5:1–5 የተመለከተውን ያንብቡ። ከዚህ ምንባብ ስለዮሐንስ ምስክርነት እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር ከነበረው መስተጋብር የተነሣ በህይወቱ ስለተፈጠረው ለውጥ የምናገኘው ምን ነገር አለ?ዘለዓለማዊ የሆነ እና ዩኒቨርስ ሁሉ የሚተዳደርበት መርኅ አለ።ኤለን ጀ. ኋይት ስለዚህ ስትናገር እንዲህ ብላለች፡ ‹‹ጉልበትን መጠቀም ከእግዚአብሔር መንግስት መርህ ጋር የሚጣረስ ነው፤ እርሱ የሚፈልገው አገልግሎት የፍቅር ነው፤ ፍቅር አዛዥ አይሻም፤ በጉልበት ወይም በስልጣንም አይንበረከክም። ፍቅርን የሚያነሳሳው ፍቅር ብቻ ነው።››—ዘ ዲዛየር ኦፍ ኤጅስ፣, ገጽ. 22 (በእንግሊዝኛው) ለክርስቶስ የተሰጠን ስንሆነ፥ የእርሱ ፍቅር በእኛ ውስጥ አልፎ ለሌሎች ይፈነጥቃል።

የክርስትና ትልቁ ምስክርነት የተለወጠ ህይወት ነው። ይህ ማለት ስህተት አንሰራም ደግሞም አንዳንድ ጊዜ ፍቅር ማስተላለፍ የማንችልበት እና እንደሚጠበቅብን ጸጋውን ማሳለፍ የማንችልበት ሁኔታ የለም ማለት አይደለም። ዳሩ ግን፥ ዓይነተኛ በሆነ ሁኔታ፥ የክርስቶስ ፍቅር ከእኛ ህይወት ፈልቆ በዙሪያችን ለሚገኙት እኛ በረከት እስከምንሆን ሊያበቃን የሚችልበት ዕድል አለ ማለት ነው። እርስዎ የክርስቶስን ፍቅር ለሌሎች እንዴት አድርገው በጥሩ ሁኔታ ሊያንጸባርቁ ችለዋል? መልስዎ ምን መዘዝ ሊኖረው እንደሚችልም ያስቡ።

ጳጉሜ 3
Sep 08

የኢየሱስን ታሪክ መተረክ


ኢየሱስ የላካቸው የመጀመሪያዎቹ ሚሲዮናውያን እነማን ነበሩ? ከደቀመዛሙርት መካከል አልነበሩም። የረዥም ጊዜ ተከታዮች ከነበሩት መካከልም አልነበሩም።የመጀመሪያዎቹ ልዑክ ሚሲዮናውያን የነበሩት ዕብድ ሰዎች፣ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አገሩን ሲያናውጡ የነበሩ እና በአጎራባች መንደሮችም ልብን የሚያርድ ስጋት የፈጠሩ የአጋንንት እስረኞች ነበሩ።

ከተፈጥሮ በላይ በሆነ የክፋት ኃይል፥ ከእነዚህ የአጋንንት እስረኞች አንዱ የታሰረበትን ሰንሰለት ይበጥስ ነበር የሚያስፈራ ድምጽ ያወጣ ነበር፤ ደግሞም የገዛ ስጋውን በስለት ይቆራርጥ ነበር። ከድምጻቸው የሚሰማው ሰቆቃ በነፍሳቸው ውስጥ ያለውን ሰቆቃ የሚያንጸባርቅ ነበር። (ማቴ. 8:28፣ 29፤ማርቆስ 5:1–5) ግን ኢየሱስን ሲገናኙ፥ህይወታቸው ተለወጠ። ከእንግዲህ እንደ ድሮው አይሆኑም።ኢየሱስ የሚያሰቃያቸውን አጋንንት ከአካላቸው በማስወጣት በአሳማዎች አስገብቶ ከገደሉ አፋፍ ወደ ባህር ውስጥ ጥልቅ ሰደዳቸው። (ማቴ. 8:32–34፤ማርቆስ 5:13፣ 14)

በማርቆስ 5:1–17 ያለውን ያንብቡ። በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን ተፈጠረ፥ የከተማውስ ሰዎች የሆነውን ለማየት ሲመጡ ምን ገጠማቸው?አጋንንት የነበረባቸው ሰዎች በክርስቶስ ጉልበት የተለወጡ አዲስ ሰዎች ሆነው ነበር። የከተማው ነዋሪዎች ሰዎቹን ሲያገኛቸው፥ በኢየሱስ እግር አጠገበው ቁጭ ብለው፣ ከጌታ አፍ የሚወጣውን እያንዳንዱን ቃል አያደመጡ ነበር።የማቴዎስ ወንጌል ነጻ የወጡት ሁለት አጋንንት ያለባቸው ሰዎች መሆናቸውን ሲናገር፥ የማርቆስ ወንጌል ላይ የምናገኘው ትኩረቱን ከሁለቱ በአንዱ ላይ በማድረግ ሲተርክ ነው። ዋናው ነጥብ ግን፥ ኢየሱስ አካላቸውን፣ አዕምሯቸውን፣ ስሜታቸውን እና መንፈሳቸውን ጭምር ያደሰላቸው መሆኑ ነው።

በማርቆስ 5:18–20 የተጠቀሰውን እስቲ ያንብቡ። እንደሚመስለው፥ እነዚህ የተቀየሩ አጋንንት የነበረባቸው ሰዎች፥ አዳዲስ አማኞች እንደመሆናቸው፥ ከኢየሱስ ጋር ለመቆየት ፈልገው ነበር፤ ዳሩ ግን ኢየሱስ ምን እንዲያደርጉ ሰደዳቸው?‹‹ለጥቂት ጊዜያት፥ የክርስቶስን ትምህርት ለመስማት ዕድሉን ያገኙት እነዚህ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከለአፉ ከወጣው ከጆሯቸው ያመለጠ አንድም የስብከቱ ቃል አልነበረም። ከክርስቶስ ጋር የነበሩት ደቀመዛሙርት ለማድረግ እንደቻሉት ህዝቡን ለማዘዝ አልቻሉም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ መሲህ ስለመሆኑ ማስረጃውን በማንነታቸው ያሳዩ ነበር። እነርሱ የሚያውቁት ምን እንደሆነ፣ እነርሱ ራሳቸው ያዩትን፣ የሰሙትን እና የነካቸውን የክርስቶስን ጉልበት ምንነት ሊናገሩ ይችሉ ነበር። በእግዚአብሔር ጸጋ የተነካ ልብ ያለው ማንም ቢሆን ሊያደርግ የሚችለው ይህንኑ ነው።››—ኤለን ጂ. ኋይትዘ ዲዛየር ኦፍ ኤጅስ, ገጽ. 340 (በእንግሊዝኛው)ከእነርሱ ምስክርነት የተነሣ ዴካፖሊስ የምትባለው አስሩ ከተሞች በገሊላ ባህር ዳርቻ ላይ የኢየሱስን ትምህርት ለመቀበል ተዘጋጀች። የግል ምስክርነት አቅም እስከዚህ ድረስ ነው።

ጳጉሜ 4
Sep 09

በማረጋገጥ መመስከር


1ኛ ዮሐንስ 5:11–13፤ዕብራውያን 10:19–22፤እና 1ኛ ቆሮንቶስ 15:1፣ 2፤ ከቅዱስ ቃሉ የምናገኘው እና በእርግጠኝነት በክርስቶስ ስለመዳናችን እንድንመሰክር የሚያስችለንን ምን የዘለዓለም ህይወት ማረጋገጫ እናገኛለን?በኢየሱስ ደህንነት ስለማግኘታችን የግል የሆነ እርግጠኝነት ከሌለን፥ ለሌሎች ለማካፈልም የማይቻል ነገር ነው።እኛ ለራሳችን ያልኖረንን ነገር ለሌሎች ለማካፈል አንችልም። ያለማቋረጥ ግራ በመጋባት ውስጥ የሚኖሩ፣ ለመዳን የሚበቃ ነገር ያላቸው እንደሆነ የሚጠራጠሩ ክርስቲያኖች አሉ።አንድ ብልህ የሆነ አዛውንት መምህር አንድ ጊዜ እንዲህ አለ፡ ‹‹ራሴን አይና፥ ምንም ልድን የምችልበት መንገድ እንደሌለ ይሰማኛል። ከዚያም ቀና ብዬ ኢየሱስን ሳየው፥ ልጠፋ የምችልበት ምንም መንገድ እንደሌለ ይሰማኛል።››በዘመናት መካከል የኢየሱስ ድምጽ ያለምንም ማንገራገር እኛ ዘንድ ይደርሳል እንዲህ ሲል፡‹‹እናንት የምድር ዳርቻ ሁሉ፣እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።›› (ኢሳ. 45:22). ጌታችን በነጻ በሰጠን ደህንነት እያንዳንዳችን እንድንደሰት ይፈልጋል።

በእርሱ ጸጋ መጽደቅ ማለት እና የኃጢዓት በደለኝነት ከሚፈጥርብን ኩነኔ ነጻ መሆን ምን ማለት እንደሆነ እንድንለማመድ ይናፍቃል።በሮሜ 5 ስለሚገኘው ነገር ጳውሎስ እንደሚናገረው፡ ‹‹እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን››(ሮሜ 5:1፣አ.መ.ት.).በተጨማሪም አስረግጦ ይህንን ይለናል፡ (ሮሜ. 8:1፣አ.መ.ት.) ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ ሌላ ማረጋገጫ ይሰጠናል፡ ‹‹ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።››(1ኛዮሐንስ 5:12፣አ.መ.ት)

በእምነት ኢየሱስን እስከተቀበልን፥ ደግሞም እርሱ በእኛ ልብ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ካደረ፥ ዛሬውኑ የዘላለም ህይወት ስጦታ ተሰጥቶናል። ይህ ማለት ግን የእግዚአብሔርን ጸጋ እና በክርስቶስ ደህንነት ያገኘ ሰው ከዚያ ወዲያ አይጠፋም ማለት አይደለም። (2ኛጴጥ. 2:18–22፤ዕብ. 3:6፤ራዕ. 3:5) ከእርሱ ለመሸሽ ሁልጊዜም ነጻነት አለን፤ ዳሩ ግን፥ የእርሱን ፍቅር አንዴ ከቀመስነው፣ እና የመስዋዕትነቱ ጥልቀት ምን ያህል እደሆነ ከተገነዘብን፥ ይህንን ያህል ከሚያፈቅረን ከእርሱ ለመሸሸ መምረጥ በፍጹም የለብንም። በየዕለቱ ለእኛ በኢየሱስ የተሰጠንን ጸጋ ለመካፈል እድሎችን እንፈልጋለን እንጂ።

በኢየሱስ ስላገኘነው ደህንነት ማረጋገጫ አለዎትን? ከሆነ ደግሞ፥ መሠረትዎ ምን ላይ ነው? ይህን የመሠለ ማረጋገጫስ ለምን ኖረዎት? ከየትስ ይገኛል? በሌላ አባባል፥ እርግጠኛ ካልሆኑ፥ እርግጠኝነት ያሳጣዎት ምንድር ነው? ማረጋገጫ እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ?

ጳጉሜ 5
Sep 10

ልንመሰክር የሚገባን ነገር


‹‹ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።››(ገላ. 2:20). ክርስቶስን ስንቀበል መስዋዕትነት መኖሩ የግድ ነው።እኛ አሳልፈን እንድንሰጥ የሚጠብቅብን ነገሮች አሉ።ኢየሱስ እርሱን ለመከተል ካስፈለገ የምናደርገውን በግልጽ አስቀምጧል፡ ‹‹ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤›› (ሉቃስ 9:23፣አ.መ.ት.). በመስቀል ላይ መሞት የሚያሳምም አሟሟት ነው። እኛም ህይወታችንን ለክርስቶስ ጥሪ አሳልፈን ስንሰጥ እና ከነኃጢዓቱ ‹‹አሮጌው ሰው›› ሲሰቀል(ሮሜ. 6:6ን ይመልከቱ)፥ህመሙ ከባድ ነው። አንዳንድ ጊዜ የምናፈቅረውን ፍላጎታችንን እና ስር የሰደደ ልማዳችንን መክዳት ከባድ ቢሆንም፥ ሽልማቱ ከህመሙ ስለሚልቅ አይወዳደርም።

በሌሎች ላይ ህይወትን የሚቀይር ተጽዕኖ የፈጠሩ ጉልበታም ምስክርነቶች ትኩረታቸውን የሚያደርጉት ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልን ነገር ላይ ነው እንጂ፣ እኛ ለእርሱ ስንል ስለተውነው ነገር አይደለም።ትኩረታቸው የሆነው በእርሱ መስዋዕትነት ላይ እንጂ እኛ ‹‹መስዋዕትነት›› እያልን በምንጠቅሰው የራሳችን ነገር አይደለም። ምክንያቱም ክርስቶስ በመኖሩ ለእኛ የሚጠቅመንን ነገር እንድንተውለት አይጠይቀንምና። የሆነ ሆኖ፥ የክርስትናን ታሪክ ካየነው ለክርስቶስ ሲሉ አያሌ መስዋዕትነቶችን በመክፈል ታሪኮች የተሞላ ነው። እነዚህ ሰዎች ደህንነት እያገኙ፣ ወይም የፈጸሙት ድርጊት ምንም ያህል ከራስ ወዳድነት ጽዱ እና ሰማዕትነት ቢሆንም እንኳን፥ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ውለታ የሚቆጥሩት አይደለም።ይልቁንም፥ በአብዛኛዎቹ አጋጣሚዎች እንደምናየው፥ ክርስቶስ ለእነርሱ ያደረገውን ሲገነዘቡ፥ እነዚህ ወንዶች እና ሴቶች ሁሉንም ነገር፥ ለህይወታቸው እግዚአብሔር ባቀረበው ጥሪ መሰረት በመሰዊያው ላይ አስቀመጡ እንጂ።

በዮሐንስ 1:12፣ዮሐንስ 10:10፣ዮሐንስ 14:27፣እና 1ኛ ቆሮንቶስ 1:30 ያለውን ያንብቡ። የእኛ ምስክርነት ሁልጊዜም ክርስቶስ ለእኛ ባደረገልን ነገር ላይ የተመረኮዘ ነው። ከላይ በቀረቡት ጥቀሶች ውስጥ ከተጠቀሱት የእርሱ ጸጋዎች ጥቂቱን እስቲ ይዘርዝሩ።ከላይ ከቀረበው ጥቅስ በመነሳት፥ ክርስቶስ ለህይወትዎ ያደረገውን ነገር እስቲ ያስቡ። በህይወትዎ ዘመን ሁሉ የተሰጡ አገልጋይ ሆነው አልፈው፣ ወይም ምናልባትም የሚያስደንቅ የሆነ መለወጥ አጋጥሞዎት ሊሆንም ይችላል።ለእርስዎ ኢየሱስ ምን ያህል መልካም እንደሆነልዎት እና ከእርሱ ስላገኙት ዓላማ፣ ሠላም፣ እና ሐሴት ያሰላስሉ።እርሱ በህይወትዎ ባለፉበት ከባድ አጋጣሚ እንዴት ያለ ብርታት ሆኖ እንዳሳለፈዎት ጊዜያቶቹን ያስቡ።

ለክርስቶስ ሲሉ ምን ዓይነት መስዋዕትነትን ለማድረግ ተጠርተው ያውቃሉ? ለሌሎች በረከት ሊሆን በሚችል ሁኔታ ከአጋጣሚዎችዎ የተማሩት ምን ነገር አለ?

መስከረም 1
Sep 11


ተጨማሪ ሐሳብ


ማርቆስ 5:25–34ን ያንብቡ ‹‹ክርስቶስን በቅርብ ርቀት እየተከተለ ሲባዝን የነበረው ህዝብ ህይወት ሰጪ የሆነ ጉልበት አልተገለጠለትም፤ ዳሩ ግን፥ ይህች የምትሰቃይ ሴት እጆችዋን ዘርግታ በነካችው ጊዜ፥ ሙሉ እንደምትሆን አምና ነበረና፥ መዳንዋ ተሰማት። ለመንፈሳዊ ነገሮችን እንደዚያው ነው።በተራ መንገድ ስለሃይማኖት ማውራት፣ ያለ ነፍስ ጥማት እና ህያው ዕምነት መጸለይ ፋይዳ ቢስ ነው። ክርስቶስን መድኃኒዓለም ነው ብሎ ብቻ የሚቀበል ልዝብ የሆነ ዕምነት ይዘን፣ ለነፍስ ፈውስ ልናመጣ አንችልም። ወደ ደህንነት የሚያመጣ ዕምነት ማለት ለዕውነት በዕውቀት ላይ ብቻ የሚጠጋጋ አስተሳሰብ አይደለም። … ስለ ክርስቶስ ማመን ብቻውን በቂ አይደለም፥ በእርሱ ልናምንበት ጭምር ግድ ይለናል። ለጥቅማችን የሚሆን ብቸኛው ዕምነት እርሱን እንደግል አዳኝ አድርጎ የሚቀበል፣ እና የእርሱን ባህርይ ለማንነታችን የሚያላብስ ሲሆን ነው። …

‹‹እርሱ ታማኝ ስለመሆኑ መመስከራችን ሠማያዊ የሆነ ክርስቶስን ለዓለም የምንገልጥበት የተመረጠ ውክልና ነው። በጥንት ዘመን ቅዱሳን ሰዎች የተገለጠውን የእርሱን ጻጋ ቦታ ልንሰጠው ይገባል፤ ዳሩ ግን ይበልጡን ውጤታማ የሚሆነው የራሳችንን ልምድ ስንመሰክር ነው።በእኛ ውስጥ የሚሰራው ኃይል መለኮታዊ መሆኑን በምንገልጥበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር ምስክሮች ነን።እያንዳንዱ ግለሰብ ከሌሎች የተለየ የሆነ ህይወት አለው፤ ደግም በተለየ መንገድ ከእነርሱ ወጣ ያለ ልምድም ይኖረዋል። እግዚአብሔር የሚመኘው በየራሳችን ማንነት የሚመሰከር ሆኖ የእርሱ ምስጋና ወዳላይ እንዲያርግ ነው።እነዚህ ወርቃማ የሆኑ የእርሱን ጸጋ የሚያመሰግኑ አድናቆቶች፥ ክርስቶስን በሚመስል ህይወት ሲታጀቡ፥ለነፍሳት መዳን ጉልበት የሚሆን የማይደናቀፍ ጉልበት አላቸው።”—ኤለን ጀ. ኋይት, ዘ ዲዛየር ኦፍ ኤጅስ, ገጽ. 347 (በእንግሊዝኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች1.ማራኪ የሆነ ምስክርነት ምን ምን የያዘ ነው? ጳውሎስ በአግሪጳ ፊት የሰጠውን ምስክርነት በሐዋርያት ሥራ 26:1–23 ላይ ያንበቡ። የእርሱ ምስክርነት መሠረት ምን ነበር?

2.በግላችን ክርስቶስ ስላደረገልን ነገር መመስከራችን እጅግ ጉልበታም የሚሆነው ለምን ይመስልዎታል? ‹‹እሺ፣ ይህ በእርስዎ ህይወት ተፈጠረ፣ ግን እኔ እንደዚህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ የማያውቅ ቢሆንስ?››ብሎ ለሚጠይቅዎት እንዴት አድርገው ምላሽ ይሰጣሉ? እኔ ኢየሱስን ለምን መከተል እንደሚኖርብኝ በሚመለከት ለማስተማር ከራስዎ ልምድ በመነሳት ማስተማር መቻል ያለብዎት ለምንድነው?

3.ለማያምኑ ሰዎች የራስዎን ምስክርነት በሚሰጡበት ጊዜ ላይ መጠንቀቅ ከሚኖርብዎት ነገሮች አንዳንዶቹ ምን ምን ናቸው? 4.ስለ ደህንንትዎ መረጋገጥ በሚያወሳው ጥያቄ ላይ እስቲ ጥቂት ያሰላስሉ፤ የክርስትና ልምምድ አስፈላጊው ክፍል ይህ የሚሆነው ለምንድነው? በጣም ሳንኩራራ ግን ደግሞ በተመሣሣይ ሁኔታ ስለራሳችን መዳን እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?