የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከነሐሴ 23 - ነሐሴ 29

10ኛ ትምህርት

Aug 29 - Sep 04
የሚያጓጓ የተሳትፎ ዘዴሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት ጥናት የሚነበብ: ዘፍ. 1:1፣ 2፣ 26፤ዘፀ. 18:21–25፤ 1 ቆሮ. 12:12– 25;ሐዋ. 16:11–15፣ 40፤ሐዋ 4:31፤ሐዋ 12:12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ‹‹ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤›› ”(ማቴዎስ 9:37, 38)

በ ተለምዶ፥ “ድር ቢያብር አንበሣ ያስር” ይባላል። ልብ ካልነው፥ ይህ ዕውነትነት አለው። በየቀኑ ልምምድ የሚያደርጉት ለብቻዎ ቢሆን ኖሮ ከሚኖርዎት መነሳሳት ይልቅ ከሌሎች ጋር በቡድን ቢሆኑ የበለጠ ጉጉት እንደሚኖርዎት አስተውለው ያውቃሉ? ብዙ ሰዎች የጤና ቡድን፣ የጂምናዚየም፣ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎችን ይመዘገባሉ፥ ምክንያታቸው ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው ልምምድ የሚያደርጉ ከሆነ ምናልባት ይበልጥ እንቅስቃሴያቸው ደስታ እንደሚፈጥርላቸው ስለሚያስቡ ነው። በተመሣሣይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔርም ለእኛ ኅብረትን ፈጥሮልናል። እኛ አፈጣጠራችን ማህበራዊ ኑሮ እንድንኖር ነው፣ ደግሞም ለአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በምሣሌ እንደምንወስደው ሁሉ በህይወታችን በርካታ አጋጣሚዎችም እንደዚያው ናቸው፥ ድጋፍ የሚያደርግ ማህበራዊ ስርዓት ሲኖር ውጤታማነታችን ይበልጥ ይሆናል። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ደግሞ ይበልጥ ዕውነት ሆኖ ይገኛል።

መጽሐፍ ቅዱስን በሞላ ስንመለከት፥ ትንንሽ ቡድኖች ዕምነታችንን ለማጠንከር፣ ስለቃሉ ያለንን ዕውቀት ለመጨመር፣ የጸሎት ህይወታችንን ለማጠንከር፣ እንዲሁም ለምስክርነት እኛን ለማስታጠቅ እግዚአብሔር ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል አነስተኛ ቡድኖች ይገኙበታል። አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በአነስተኛ የቡድን አገልግሎት ውስጥ ተሳትፈዋል።ሙሴ የአነስተኛ ቡድኖች መሪ ነበር። ኢየሱስም የራሱ የሆኑ የደቀመዛሙርት አነስተኛ ቡድን መሠረተ፥ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስም በሮማውያን ምድር ጥቂት የወንጌል አጃቢዎችን በቡድን ይዞ ይጓዝ ነበር። በዚህ ሣምንት ጥናታችን፥ ስለ አነስተኛ ቡድኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመጣጥ ትኩረት እናደርጋለን፤ ደግሞም እርስዎ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን አጓጊ የሆነ ዘዴ እንፈበርካለን።

*የዚህን ሣምንት ትምህርት ለነሐሴ 30 2012 ሰንበት በማጥናት ይዘጋጁ።

ነሐሴ 24
Aug 30

አነስተኛ ቡድኖች: የእግዚአብሔር አሳብ ይቅደም


ዘፍጥረት 1:1፣ 2፣ 26፤ ዕብራውያን 1:1፣ 2፤እና ኤፌሶን 3:8፣ 9፤ ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች የእግዚአብሔርን አንድነት የሚገልጹልን እንዴት ነው?አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በፍጥረት ጊዜ ተሳትፈው ነበር። እያንዳንዳቸው የነበራቸው የተለያየ ተግባር የነበረ ቢሆንም፥ አንድነታቸው ግን ሳይነጣጠል ሥራቸውን ከውነዋል።አብ ዋናው ዲዛይን አውጪ፣ ታላቁ አርኪቴክት ነው። ዕቅዱንም ወኪሉ በሆነው በኢየሱስ በኩል ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ጋር በአንድነት በማጣመር ተግባራዊ አደረገው።እንዲህ ዓይነቱ ትልቅ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ድርጊት እኛ ልንደረዳው ከምንችለው በላይ ነው። እኛ የምናስተውለው እና ግልጽ የሚሆንልን ነገር ቢኖር ደግሞ የተፈጠረው ዓለም እና የከዋክብት ስፍር ዕውንነት ብቻ ሳይሆን፥ ሁሉን የፈጠረው ራሱ እግዚአብሄር መሆኑ ነው። (ሮሜ. 1:18–20 ላይ የሠፈረውን ይመልከቱ)።

ትናንሽ ቡድኖች የእግዚአብሔር የመጀመሪያ አሳብ ነበሩ። ምንም እንኳን ስለ እግዚአብሔር ምስጢራዊ የሆኑ ፈርጆች በሚመለከት ተምሳሌቶችን ስንጠቀም ሁላችንም ልንጠነቀቅ የሚገባን ሆኖ ሣለ፥ እስቲ ላላ አድርገን አንድ አጋጣሚ እንውሰድ እና፥ አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በድነት ታሪክ ውስጥ የተቧደኑ አድርገን እንቁጠር።በአንድነት በመሆን የሰውን ዘር በመፍጠር እንዲሁም ከወደቀም በኋላ ለማዳን ተባብረው ሲሰሩ እናገኛቸዋለን።

በዮሐንስ 10:17፣ 18 የሚገኘውን ከሮሜ 8:11፤እና 1ኛ ቆሮንቶስ 15:15 ጋር እናነጻጽር እስቲ። የክርስቶስ ትንሣኤ በድነት ዕቅድ ውስጥ የአብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን ኅብር የሚያመለክተን እንዴት ነው?______

አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የሰውን ዘር ለመቤዠት ዓላማ በተለይ ‹‹ትንሽ ቡድን›› ሆነው ተቀናጁ። ‹‹በማይተመነው አምላክ ዘንድ የደህንነት ዕቅድ ከዘለዓለም ዘመናት በፊት ሲታሰብ የነበረ››—ኤለን ጀ. ኋይት፣ ፈንዳሜንታልስ ኦፍ ክርስቲያን ኤጁኬሽን ገጽ 186(በእንግሊዝኛው)።ለእግዚአብሔር አያሌ ሰዎችን ወደ ድነት ከማምጣት የበለጠ ጠቃሚ የሆነ ምንም ነገር የለም።

(1ኛጢሞ. 2:4፣ 2ኛ ጴጥ. 3:9) በትንንሽ ቡድኖች ውስጥ በዚህ ሣምንት እንደምናጠናው በርካታ ዓላማዎችን ማጨቅ የሚቻል ቢሆንም፥ ሁሉን የሚገዛው ትኩረታቸው መሆን ያለበት የጠፉትን ሰዎች ለኢየሱስ መማረክ ነው። ይህም ማለት፥ በትንንሽ ቡድኖች ሆነን ስንሰራ፥ ራሳችንን መርዳት ብቻ ሳይሆን ሌሎንም ጭምር እንደግፋለን። ይህም ማለት፥ የትንንሽ ቡድኖች የመጨረሻው ግብ ነፍሳትን መማረክ መሆን አለበት። በእግዚአብሔር የአንድነት ምስጢር ላይ እስቲ ጥቂት ያሰላስሉ። ለማስተዋል የሚከብድ ነው አይደል? የሆነ ሆኖ፥ ሙሉ በሙሉ የማንገነዘበውም ቢሆን እንኳ እምነታችንን እንጥልበታለን፣ እንታመነዋለንም አይደል? እንዲህ ዓይነቱ መርህ ከዕምነት ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው መርህ የሆነው ለምንድነው?

ነሐሴ 25
Aug 31

ትንንሽ ቡድኖች ከቅዱሱ መጽሐፍ


መጽሐፍ ቅዱስ የትየለሌ ትንንሽ ቡድኖች በጸሎት፣ ኅብረት በማድረግ፣ እርስ በእርስ በመበረታታት፣ እና ለክርስቶስ በአንድነት በመትጋት እንደሰሩ በምሳሌነት ያቀርብልናል። እነዚህ ቡድኖችም ለእግዚአብሔር ሰዎች ኃላፊነቶቻቸውን እንዲያጋሩ እና የተለያዩ ተሰጥዖዎቻቸውን በሙላት እንዲጠቀሙ ዕድሎችን አስገኝቶላቸዋል።ይህም ማለት፥ አነስተኛ ቡድኖች ጌታ እኛን በሙላት የሚጠቀምበትን ዕድል ይፈጥሩልናል።

ዘጸዓት 18:21–25 ላይ ያለውን ያንብቡ። የሙሴ አማት ዮቶር በሙሴ ላይ ፋይዳ ያለውን ለውጥ እንዲፈጥር ያደረገውን ምን ዓይነት ምክር ሰጥቶ እናገኛለን? ይህ ዕቅድ በወሳኝነት ጥቅም የሚኖረው ለምንድነው?እያንዳንዱ በእስራኤል ሰፈር ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ፥ በአስር በአስር ከተጣመሩት መካከል የአንዱ ቡድን አባል በመሆን፥ ፈሪሐ እግዚአብሔር ባለው ሹም ይመራ ነበር። እነዚህ አነስተኛ ቡድኖች ችግሮችን መፍቻዎች ናቸው፣ ደግሞም ከዚያም ያለፉ ጭምር ነበሩ።ኅብረት ለማድረግ እና ችግሮች ሲኖሩ መከላከያ እንዲሁም የመንፈስ ህይወት ማጎልበቻ አጋጣሚዎችም ነበሩ።ለእስራኤላውያን እግዚአብሔር ያለው ዕቅድ ራዕይ የሚካፈልባቸው ስፍራዎች ነበሩ። በእንደ እነዚህ ዓይነት ቡድኖች ውስጥ፥ ሰዎች ምንም ዓይነት ችግር እየተጋፈጡ ቢሆን መፍትሔ ሊፈልጉላቸው እስከሚችሉ ድረስ ሊረዱ የሚያስችል የጠበቀ እና ክብካቤን የተሞላ ግንኙነት ለመመስረት ይችላሉ።አጠያያቂ የማይሆነው ነገር ያኔም ሆነ ዛሬ፥ ሰዎች የሚቸገሩት ሌሎች እርዳታ ሊያደርጉላቸው በሚችሉባቸው ነገሮች መሆኑ ነው። አነስተኛ ቡድኖችም የጋለ፣ ክብካቤን የተሞላ ኅብረት ለማድረግ እና በመንፈስ ለማደግ የሚችሉባቸው እና ችግር ፈቺ ዕድሎችን ያስገኛሉ።

አነስተኛ ቡድኖችን በተመለከተ ልምዱ ያላቸው እንደሚነግሩን ከሆነ በቡድን ለመግባት ዓይነተኛ የሚባለው መጠን ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ነው። ይህም መጠን ሙሴ እና ኢየሱስ የየራሳቸውን ቡድን ሲመሰርቱ የተጠቀሙበት ትክክለኛው መጠን ነው። በሉቃስ 6:12፣ 13፤ማቴዎስ 10:1፤እና ማርቆስ 3:13–15 ያለውን ያንብቡ። ደቀመዛሙርትን ሲጠራ እና የእርሱ አነስተኛ ቡድን አገልግሎት አካል ሲያደርጋቸው የፈለገው ሁለት ዕጥፍ ዓላማ ምን ነበር?ደቀመዛሙርትን ሲጠራ ኢየሱስ የፈለገው ዓላማ ለመንፈሳዊ እና ተግባራዊ ለሆነ ተልዕኮ ወደ ዓለም ለመላክ እነርሱን ለማዘጋጀት ነበር። ከእርሱ ጋር ኅብረትን በማድረግ፥ በጸጋ ማደግ ይችላሉ። በትንንሽ ቡድኖቻቸው በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ዐውድ፥ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ ይማራሉ። በየዕለቱም፥ ኢየሱስን በዙሪያው ላሉት የተቸገሩ ሰዎች ሲያገለግል በተመለከቱ ቁጥር፥ ከሚያዩት ነገር የየራሳቸውን ስጦታ እንዴት እንደሚጠቀሙ መማር ይችላሉ። ኢየሱስ የመሠረተው አነስተኛ ቡድን ዓላማው መንፈሳዊ ምግብ እንዲሁም መድረስ ጭምር ነበር።

አጋጣሚው ምንም ቢሆን ምን፥ እርስዎ በጥቂቶች ቡድን አባል የሆኑበትን እና እርስ በእርስ ተንከባካቢዎች በመሆን የጋራ ግብን ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ ስለነበረበት አጋጣሚ እስቲ ያስቡ። ከዚያ የተማሩት እና የጥቂቶችን ቡድን ደግሞ ከዕምነት ዐውድ አንጻር ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያስተዋሉት ምንድነው?

ነሐሴ 26
Sep 01

ለአገልግሎት መደራጀት


1ኛ ቆሮንቶስ 12:12–25 ላይ ያለውን ያንብቡ። በአነስተኛ ቡድኖች በመሆን በኅብረት ስለ መስራት በሚመለከት የሚደነቅ የሆነ ምስልን ከሰው ልጅ አካል የምናገኘው እንዴት ነው?ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ ስጦታዎች የሚኖራቸውን ጠቀሜታ ብቻ አይደለም የገለጸው፤ በማያያዝም እንዴት ሊደራጁ እንደሚችሉ ሞዴል ያቀርባል። መንፈሳዊ ስጦታዎችን በክርስቶስ አካል ዐውድ በማድረግ እንዴት እንደሚከናወንም ጭምር አብራርቶ አቅርቧል። የአንድን አካል ተፈጥሮ እና የሥራ ዘርፎች የሚመራመሩ አናቶሚ እና ፊዚዮሎጂ እንደሚያሳየን፥ የአንድ ሰው አካላት በተለያዩ እርስ በእርስ ተደጋጋፊ የሆኑ ስርዓቶች የተደራጁ መሆናቸውን ነው። ለምሣሌ፥ የምግብ አፈጫጨት፣ የልብ እና ደም ስሮች፣ የአተነፋፈስ እና የአጥንቶቻችን ሥርዓቶች ውስብስ ከሆኑ የአካላቶቻችን ስርዓቶች መካከል ይገኙበታል። መንፈሳዊ ስጦታዎችም እንደ አካላችን የተለያዩ ክፍሎች ናቸው።በስርዓቶች ወይም በቡድኖች እንዲደራጁ ሲደረጉ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ። ዕውነት ለመናገር፥ በበርካታ አጋጣሚዎች ለየብቻቸው ስራቸውን መስራት አይችሉም። አካላቶቻችን የሚሰሩትን በዘፈቀደ የሚያከናውኑ የተለያዩ አካላት ዕባጮች አይደሉም። እያንዳንዱ የአካላቶቻችን ተግባራት በጥብቅ የተገመዱ ሆነው የተደራጁ በመሆናቸው ወደ አንድ የጋራ ግብ በአንድነት ይመጣሉ።

ከዚህ ሁሉ በመነሳት መንፈሳዊ ስጦዎታቻችንን በተሸለ መንገድ ልንጠቀምባቸው ስለምንችልባቸው አካባቢዎች የምናገኘው አንድ ነገር አለ። እኛ ለብቻችን ሆነን በምንፍጨረጨርበት ጊዜ ተስፋ ለመቁረጥ ቀላል ነው፤ ዳሩ ግን ተመሣሣይ ፍላጎት እና ግብ ባላቸው አነስተኛ ቡድኖች አባል ስንሆን፥ ጥረቶቻችን ሁሉ ይበልጥ ስብስብ ያሉ እና በጣም የጎሉ ሆነው ልናገኛቸው እንችላለን። አነስተኛ ቡድኖች መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን መለማመድ የምንችልበትን ጥሩ የሆነ ከባቢ ይፈጥሩልናል፤ ደግሞም የአጥቢያ ምዕመኑ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ልብ ሆነው ሊገኙም ይችላሉ።

ኤለን ጂ ኋይት የሚከተሉትን ቃላት በመናገር ስለ አነስተኛ ቡድኖች ዋጋ አጽንዖት ትሰጣለች፡ ‹‹ለክርስትና ጥረቶች መሠረት እንዲሆኑ አነስተኛ ህብረቶችን መመስረት ሊሳሳት ከማይችለው ከእርሱ ለእኔ የተሰጠኝ አሳብ ነበር። ብዛታቸው አያሌ የሆኑ በቤተክርስቲያን ቢኖሩ፥ አባላቶቹ በትንንሽ እንዲቧደኑ ይደረጉ፤ ከዚያም ለቤተክርስቲያን አባላት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ለማያምኑቱ የሚሰሩ ይሁኑ። በአንድ ስፍራ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ብቻ ዕውነቱን የሚያውቁ እንደሆነ፥ የሠራተኞች ባንድ ሆነው ይዋቀሩ። የጥምረታቸውን ህብር ሳይሰብሩ፥ በፍቅር እና አንድነት በመሣሣብ፥ እርስ በእርስ ወደፊት ለመጓዝ ይበረታቱ፣ ጥንካሬ እና ብርታትን ከሌላኛው ይገብዩ።

››”—ቴስቲሞኒስ ፎር ዘ ቸርች, ዕትም. 7፣ገጽ. 21፣ 22 (በእንግሊዝኛው) የአነስተኛ ቡድኖች አገልግሎት እያንዳንዱን የቤተክርስቲያን አባል በመንፈስ እንዲያድግ፣ የጋለ ኅብረትን እንዲለማመድ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የሰጠውን ስጦታ ለአገልግሎት እንዲጠቀም ለማድረግ የተቀባ አገልግሎት ነው። ከላይ ስለ ሰፈረው የኤለን ጂ. ኋይት ዐረፍተ ነገር እስቲ ጥቂት ያሰላስሉ።ሐረግ በሐረግ ይተንትኑት። ይህ መለኮታዊ ምክር በእርስዎ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል?

ነሐሴ 27
Sep 02

የአዲስ ኪዳን አነስተኛ ቡድኖች


የአዲስ ኪዳንዋ ቤተክርስቲያን ሀይለኛ ዕድገት ነበራት። በጥቂት አጭር አመታት ጊዜ ውስጥ፥ ከጥቂት የአማኞች አነስተኛ ቡድን በመነሳት ወደ አስር ሺህ አማኞች ለማደግ ቻሉ።የአማኞችን ፍልሰት እንዲጎላ እና ለዚህ ፈጣን ክስተት አስተዋጽዖ ያደረጉ በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። የኢየሱስ አገልግሎት ለወንጌሉ ዘርን የዘራ ሲሆን፣ አያሌዎንችም የደቀመዛሙርትን ስብከት እንዲቀበሉ አዘጋጅቷል። ክርስቶስ ወደ ሠማይ ማረጉን ተከትሎ፥ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በጴንጤቆስጤ ቀን በጸሎት ላይ ሣሉ በአማኝ ደቀመዛሙርት ላይ ወረደ። በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ለምናየው ፈጣን ዕድገት አስተዋጽዖ ከነበራቸው ጉዳዮች አንዱ በትንንሽ ቡድን የተዋቀረው አደረጃጀታቸው ነበር። አነስተኛ ቡድኖች ለውጥን ያመጣሉ።

በሐዋርያት ሥራ 18:1–5 እና ሐዋርያት ሥራ 20:1–4 የሚገኘውን ያንብቡ። ጳውሎስ በቅርበት አብሯቸው ይሰራ የነበሩትን ስም ሉቃስ መጥቀስ ያስፈልገው ለምን ይመስልዎታል?ጳውሎስ አብሯው ሲሰሩ የነበሩትን አንዳንዶችን ስም ሉቃስ መጥቀሱን ስናይ ያስገርማል። ለእርሱ እያንዳንዱ አስፈላጊ በሩ። ሁሉንም በስም ያውቃቸው ነበር። እርስ በእርስም በወንጌል ስርጭት አገልግሎታቸው ይደጋገፉ ነበር። ምንም እንኳን እርሱ የዘረዘራቸው ስሞች ብዛት አነስተኛ ቢሆንም፥ ከዚህ በመነሳት ምንም እንኳ አነስተኛ ቡድን ብንሆን እርስ በእርስ ቅርበት ማጎልበት፥ አስፈላጊ ስለመሆኑ ማስረጃ እናገኛለን።

እያንዳንዱ የቡድኑ ሰዎች በሌሎች ዘንድ ካለው የተለየ የሆነ ስጦታዎች እንዳሏቸው ግልጽ ነው። የመጡበት ቅድመ ታሪክ የተለያየ ነበረ።ነገሮችን የሚያዩባቸው መንገዶችም አንድ ዓይነት አይደሉም፤ ዳሩ ግን እያንዳንዳቸው ዓላማቸውን ክርስቶስን አድርገው የሚያበረክቱት ረብ ያለው አስተዋጽዖ ነበረ። የተለያዩ ስጦታዎች፣ ቅድመ ታሪክ እና ልምዶች ያሏቸው መሆናቸው፥ ለቤተክርስቲያን ዕድገት አስተዋጽዖ አበረከተ።እያንዳንዳቸውም ከየግላቸው ቅድመ ታሪክ በመነሳት እና ከኢየሱስ ጋር ከነበራቸው የግል ልምምድ ለክርስቶስ ተልዕኮ አስተዋጽዖ አበከርክተዋል።

በሐዋርያት ሥራ 16:11–15፣ 40 እናሐዋርያት ሥራ 12:11፣ 12 የሰፈረውን እርስ በእርስ ያስተያዩ። ሊዲያ እንደተለወጠች ወዲያውኑ ለጳውሎስ ያቀረበችው ግብዣ ምን ነበር? ጳውሎስ እና ጴጥሮስም ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ የሔዱት ወዴት ነበር?በአዲስ ኪዳን አማኞች በቤት ውስጥ ስብሰባዎችን የሚያደርጉት እምብዛም ነው። የክርስቲያኖች ቤቶች የተጽዕኖ ማዕከላት እንዲሁም የአነስተኛ ቡድኖች አገልግሎት ልብ ሆነዋል። በቤትዎ ውስጥ የአነስተኛ ቡድን አገልግሎት ለመጀመር ወይም ከወዳጅዎ ጋር በመጣመር የአነስተኛ ቡድን አገልግሎት በዚያ ግለሰብ ቤት ለመጀመር አስበው ያውቃሉ? የአነስተኛ ቡድን አባልነት ያለዎት ከሆነ ደግሞ፥ ስለ ጠቀሜታዎቹ ከሰንበት ትምህርት ክፍለ ጊዜ ተካፋዮች ጋር ሊያጋሩ የሚችሉትን ነገር እስቲ ያሰላስሉ።

ነሐሴ 28
Sep 03

የአነስተኛ ቡድን እንቅስቃሴዎች


አነስተኛ ቡድኖችእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ለማሳደግ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ናቸው። ሰዎች የጋራ ችግሮቻችውን የሚነጋገሩባቸው እና ጭንቀቶቻቸውን የሚገልጹባቸው ‹‹ማምለጫዎች›› ናቸው። እንክብካቤን በተሞላ ግንኙነት ዐውድ መንፈሳዊ ዕድገትን የመፍጠር ዕድል አላቸው። በርካታ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎቸ በተለምዶ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሔድ ይልቅ መጀመሪያ ላይ በትንንሽ ቡድኖች በመሆን በቤት ውስጥ ሲሳተፉ ምቾት ይሰማቸዋል።

ሐዋርያት ሥራ 4:31፣ሐዋርያት ሥራ 12:12 እና ሐዋርያት ሥራ 20:17–19፣ 27–32 ላይ የሰፈረውን ያንብቡ።. በነዚህ የአዲስ ኪዳን ቡድኖች ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ይዘቶች ይዘርዝሩ። እነዚህ ቡድኖች የተሳተፉባቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ምን ምን ናቸው?ቀደምት ክርስቲያኖች ለሌሎች ምልጃን ለማቅረብ፣ ስለጋራ ጭንቀቶቻቸው ለመጸለይ፣ የጋለ ኅብረትን ለመካፈል፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት፣ ለአገልግሎት ለመታጠቅ፣ ከሐሰተኛ መምህራን እርስ በእርስ ለመጠባበቅ፣ እና በጋራ በወንጌል ስርጭት ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ሲሉ በአንድነት ይገናኙ ነበር። አነስተኛ ቡድኖች ልዩነት ይፈጥራሉ። ሰዎች ለአገልግሎት ስጦታዎቻቸውን ሲያስተባብሩ፥ ለወንጌል ስርጭት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ ትኩረት ሲያደርጉ፥ በጌታ እጅ ያሉ ታላቅ መሣሪያዎች ይሆናሉ።

ማቴዎስ 9:37፣ 38ን ያንብቡ። ስለመከሩ ኢየሱስ ምን አለ፥ ደግሞስ ለችግሩ ያስቀመጠው መፍትሔ ምን ነበር?ደቀመዛሙርት ይታያቸው የነበረው ወንጌል ሊስፋፋ የሚችልበት ዕድል የሳሳ መሆኑ ነበር፤ ዳሩ ግን ኢየሱስ ትልቅ የሆነ ዕድል ታየው። ‹‹መከሩ ብዙ ነው›› በማለት መልካሙን ዜና ነገራቸው፥ በማስከተልም ያለውን ችግር ገለጸላቸው‹‹የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው›› (ማቴ. 9:37, አ.መ.ት) ለዚህ ደግሞ ክርስቶስ ያቀረበው መፍትሔ ‹‹የመከሩ ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞን እንዲልክ›› መለመን ነበር። (ማቴ. 9:38, አ.መ.ት.) አነስተኛ ቡድኖች ለክርስቶስ ጸሎት ምላሾች ሲሆኑ ለክርስቶስ መከር የሠራተኞችን ቁጥር በብዙ ዕጥፍ ያሳድጋሉ።

የሁሉም አነስተኛ ቡድኖች ትኩረት ምስክርነት እና አገልግሎት ነው። የአነስተኛ ቡድኖች አገልግሎት ወደ ውጭ መሆኑ ቀርቶ ወደ ውስጥ መሆን ሲጀምር ብዙም ሳይርቅ ይከስማል። ምናልባት አነስተኛ ቡድኖች አገልግሎታቸው ለራሳቸው ቢሆን እና ከምክክር ቡድን ያላለፉ ቢሆኑ፥ ዓላማው ጨንግፎ የመኖሩ መሠረታዊውን ምክንያት ያጣል። አነስተኛ ቡድኖች መኖራቸው ሰዎችን ወደ ኢየሱስ መምራት፣ በኢየሱስ ላይ ያላቸውን ዕምነት መመገብ፣ እንዲሁም ለኢየሱስ እንዲመሰክሩ ማስታጠቅ ነው።

ምናልባት እግዚአብሔር በቤትዎ ውስጥ የአነስተኛ ቡድን እንዲጀመር ጥሪ እያደረገ ሊሆን ይችል ይሆን? እግዚአብሔር ምን እንዲያደርጉ ግፊት እያሳደረብዎት እንደሆነ ለማወቅ ለምን መጸለይ አይጀምሩም? በህይወትዎ እጅግ በጣም ሽልማትን የሚያስገኘው ጊዜ ሊገለጥ ጫፍ ላይ ሊሆኑም ይችላሉ እኮ።

ነሐሴ 29
Sep 04


ተጨማሪ ሐሳብ


ከዓመታት በፊት፥ ከአህጉሪቱ አበይት ከተሞች ውጭ የምትገኝ አነስተኛ የአውሮፓ ቤተክርስቲያን ለጌታ አንድ ፋይዳ ያለውን ነገር ለማድረግ ወሰነች። ቤተክርስቲያኒቱ አዝጋሚ ነበረች። ለዓመታት ማንም አልተጠመቀም ነበር። ይህ ልማድ የቀጠለ እንደሆነ፥ ቤተክርስቲያኒቱ ዕጣ ፈንታዋ እስከዚህም ነበር። መጋቢው እና ቤተክርስቲያኒቱ በቅንነት ጸልየው ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ በጥንቃቄ ማሰብ ጀመሩ።

አዲስ ኪዳንን ማጥናት ሲቀጥሉ፥ አነስተኛ ቡድን ያለው አገልግሎት ለመመስረት ወሰኑ። ዘጠኝ ተራ አባላት ከጉባዔው ራዕዩን አንግበው ተነሱ። በአንድነት ለመጸለይ እና የአነስተኛ ቡድን አገልግሎታቸውን በተዋጣ ሁኔታ እንዴት ማዋቀር እንደሚችሉ ለማጥናት ራሳቸውን ሰጡ። ብዙም ሳይቆይ እያንዳንዱ የየራሳቸውን ቤት የወንጌል ማዕከል ለማድረግ ወሰኑ። ቡድኑም ስጦታዎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ለመጠቀም ተማሩ። የጸሎት እና የመስተንግዶ አገልግሎቶችን አስጀመሩ።ከማህበረሰቡ ጋር ወዳጅነትን መሠረቱ። ለቤተሶቻቸው፣ ወዳጆቻቸው እና ለቀድሞ አድቬንቲስቶች የቸርነት ድርጊቶችን ማቅረብ ቀጠሉ። አነስተኛው የመሪዎች ቡድን በዘጠኝ ቤቶች በመሆን አርባ እንግዶች በተገኙበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ።

እንዴት አድርጎ መንፈስ ቅዱስ ሲሰራ እንደነበረ ሲያዩ ተገረሙ። በሒደትም ከአርባው መካከል አስራ ሰባቱ ተጠመቁ።የዚያች አነስተኛ፣ ዘገምተኛ ቤተክርስቲያን ምስክርነት እንግዲህ፥ አነስተኛ ቡድኖች ታላቅ የሆነ ልዩነት ፈጣሪነት እንዳላቸው ነው። በርካታ የቤተክርስቲያን አባላትን በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ ከማሳተፊያ ዘዴዎች መካከል እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ዘዴ አንዱ ይሄ ነው።


የመወያያ ጥያቄዎች1.በውይይት ጊዜ፥ በሐሙስ ጥናት የተመለከቱት የአነስተኛ ቡድኖችን አስፈላጊ የሆነ ይዘት በተጨማሪነት ተወያዩ። አንድ አነስተኛ ቡድን በምን ዓይነት እንቅስቃሴ ላይ ሊሰማራ ይችላል? አንድ አነስተኛ ቡድን ልዩ ስጦታ ያላቸውን ስጦታቸውን ከዚህ ቀድሞ ከነበራቸው በሚልቅ መንገድ እንዲጠቀሙበት ሊያደርግ የሚችልባቸው መንገዶች ምን ምን ናቸው?

2.አነስተኛ ቡድኖች ወደ ውስጥ ሳይሆን ወደ ውጭ ትኩረቱን ያደረገ ተልዕኮ ሊኖራቸው የሚያስፈልገው ለምንድነው? ይህም ማለት፥ አንድ ቡድን አባላቶቹን ምንም ያህል እንዲፋፉ ቢደግፍ እንኳን፥ ወንጌልን ማሰራጨት ማእከላዊ ዓላማው ሆኖ መቀጠል ያለበት ለምንድነው? ደግሞስ ለምን፥ አንድ አነስተኛ ቡድን ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን አካል ጋረ እንደተጣመረ መቆየት ያስፈልገዋል? ለምንስ ይህ በጣም አስፈላጊ ሆነ?

3.በተሳካ ሁኔታ ለመስራት ያልቻለ እና በሒደትም የከሰመ አነስተኛ ቡድን አባል ሆነው ያውቃሉ? እስቲ ይህ ሊፈጠር የቻለበትን ምክንያት ብለው የሚየስቡትን ያወያዩ፤

4.ከላይ ስለተመለከተው ታሪክ፣ በአውሮፓ ውስጥ በአነስተኛ ቡድን አገልግሎት ስለተፈጠረው ነገር እስቲ ያስቡ።ይህ በጣም የተሳካለት ለምን ይመስልዎታል? በብዙ መልኩ ቀላል የሚመስል ግን በጣም ውጤታማ የሆነ የሰሩት ሥራ ምን ነበር? ደግሞስ ቤት አከባቢ ከሚገኘው ‹‹የማያሰጋ›› ቦታ ሆኖ መሥራት በቤተክርስቲያን ህንጻ ውስጥ ከመጠቀም ይልቅ የወንጌል ስርጭትን ለአጎራባች ወይም ለማህበረሰቡ ለማዳረስ ውጤታማ የሚሆነው ለምንድነው?