የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2020

ለእግዚአብሔር ወዳጆችን ማፍራት በተልዕኮ ውስጥ በመሳተፍ የሚገኝ ደስታ

መግቢያመደበኛ እትም

ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

እግዚአብሔር ወዳጆችን ማፍራት የእግዚአብሔርን ተልዕኮ በማካፈል የሚገኝ ደስታ አንዲት ሃሳብን ወደ ውስጣችን በማስረፅ በህይወታችን ላይ ጥልቅ የሆነ ለውጥ ያመጣንባቸው ጊዜያቶች አሉ። ከጥቂት አመታት በፊት የወንጌል አገልግሎት ስብሰባን ለማድረግ ከአንዳንድ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ተቀምጬ ነበር። ውይይታችን አቅጣጫውን ቀየረና ስለ እምነታችን፣ ስለ ምስክርነት እና ወንጌል ጉዳይ መነጋገር ጀመርን። አንዱ ወዳጄ ይህንን እሳቤ አንፀባረቀ “ተልዕኮ ቀዳሚው የእግዚአብሔር ሥራ ነው። የኛን ፕላኔት ለማዳን የሰማይን ሁሉ ሀብት ሥራ ላይ አዋለ። የኛ ሥራ ደግሞ የጠፉትን ለማዳን እርሱ ሥራውን በሚያከናውን ጊዜ በደስታ ከርሱ ጋር መተባበር ነው”። ከጫንቃዬ ላይ ከባድ ሸክም የተራገፈ ያክል ነበር የተሰማኝ። የጠፋውን አለም የማዳን ሥራ የእኔ አይደለም። የእግዚአብሔር እንጂ። የእኔ ሐላፊነት ደግሞ እርሱ የሠራውን ሥራ በመተባበር መሥራት ነው።

ተልዕኮ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ የተነገረው ሃሳብ በቃሉ ውስጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተገልጾልናል። ሰለሞን በዚህ መልኩ ገልጾታል “እርሱ (እግዚአብሔር) ዘላለማዊነትን በልቡ አስቀመጠ” (መክ. 3፡11)። አንድ ሰው ተወልዶ ወደዚህ ምድር ሲቀላቀል እግዚአብሔር በዛ ሰው ተፈጥሮ ውስጥ ዘላለም የመኖር ጥልቅ መሻትን አኖረ። አውግስቲን አንድ ጊዜ እንዲህ አለ “የተሰራነው ለአንተ ነው ልባችን ባንተ እረፍት እስካላገኘች ድረስ በሌላ እረፍት የላትም”። በዮሐንስ ወንጌል ገለፃ መሠረት ወደዚህ ምድር በውልደት ለመጡ ሰዎች ሁሉ ብርሃን የሆነው የሱስ ነው (ዮሐ. 1፡9)። እግዚአብሔር እያንዳንዳችን እርሱን እንድንናፍቅ ብቻ መሻትን በልባችን አላኖረም፣ ወደራሱ እንዲስበን መንፈስ ቅዱስን ሰደደልን።

እያንዳንዱ መልካምን ነገር ለማድረግ መሻትና፣ ሀጢያትን የማመን ሁኔታ የተከናወነው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። እያንዳንዱ መልካም የመሆን እና ወደ ርህራሄ የማዘንበል እንዲሁም ራስ ወዳድ ያለመሆን ባህሪ ቀድሞውኑ የሚነሳሳው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ምንም እንኳን እኛ ሙሉ በሙሉ ማስተዋል ባይቻለንም መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን ወደ የሱስ ሊስበን ይሰራል (ዮሐ. 16፡7-15)። ነገር ግን የሱስ ራሱ ከስጦታዎቹ ሁሉ የላቀው ስጦታ ነው።

ሰብአዊ ዘር ተስፋ በሚያሳጣ ሁኔታ በሀጢያቱ ጠፍቶ፣ የዘላለም ሞት ቢፈርድበትም፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የመጀመሪያውን ተነሳሽነት ወሰደ። ሉቃስ ሲጽፍ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና” (ሉቃስ 19፡10)። ጳውሎስም ሲያክል “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” (ሮሜ 5፡8)። እግዚአብሔር ለድነታችን ጉዳይ የመጀመሪያውን ተነሳሽነት ወሰደ። ክርስቶስ ክብሩን ትቶ ሰማይን ለቆ የመዋጀት ተልዕኮን ይዞ በሀጢያት ወደጨለመችው አለም መጣ።

ትንሽዬ እርምጃ ወደርሱ ከመቅረባችን በፊት ትልቁን እርምጃ እርሱ ወሰደ። እኛ ሕይወታችንን ለርሱ ከመስጠታችን በፊት በሞቱ በኩል ድነትን ሰጠን። እኛ የእርሱ ጠላቶች ሆነን ሳለን እርሱ ግን የኛ ወዳጅ ሆነ። ጀርባችንን ስናዞርበት እርሱ ግን ፊቱን ወደኛ መለሰ። ለርሱ እምብዛም ግድ የሌለን ስንሆን እርሱ ግን በጥልቀት ስለኛ ግድ ይለዋል።

ሉቃስ 15 ላይ መልካም እረኛ ሆኖ ያለመታከት የጠፋውን በጉን እንደሚፈልግ ተገልጾልናል፣ አንዲት ሴት በቤትዋ ውስጥ የጠፋውን ድሪም በጥድፊያ ስትፈልግ እናያለን፣ የሸመገለው አባት የጠፋውን ልጁን ለመገናኘት ወደርሱ ሲሮጥ እንመለከታለን። ኤለን ጂ ኋይት ልናሰላስል የሚገባንን ይህንን አስደናቂ አባባል ትናገራለች “ታላቁ የድነት እቅድ የታሰበው አለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ነው። ለሰው ልጅ ቤዛ ለመሆን የሚወሰደውን አስደናቂ ሀላፊነት ለመውሰድ ክርስቶስ ብቻውን አልቆመም። በሰማያዊው ምክር ቤት አለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን በአባቱ ዘንድ ያለው ክርስቶስ የኃጢያተኞችን ስፍራ በመውሰድ እና በእርሱ ላይ የሚጣለውን የፍርድ ቅጣት በመውሰድ ለመሰቃየት አብ አባትና ልጁ በአንድነት ቃል ተገባቡ” –The Advert Review and Sabbith Herald, November 15, 1898.

ለጥቂት ጊዜ እስቲ አስቡ። አስደናቂ እድል እና የሚገርም ሀላፊነት የተሰጠን ነን። ከክርስቶስ ጋር በመተባበር የእርሱን ተልዕኮ በመደገፍ ዘላለማዊው ደስታም ተሰጥቶናል። በዚህ ሩብ ዓመት የምንማረው ትምህርት እንግዲህ ይሄ ነው። የኮኔክቲከስ ተወላጅ የሆኑት አሜሪካዊ የአገሬው ተወላጅ ማርክ ፊንሊይ የዚህ ሰንበት ትምህርት ደራሲ አለማቀፍ እውቅና ያላቸው ወንጌላዊ፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2005-2010 ድረስ የጀነራል ኮንፍራንስ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ። ከሙሉ ጊዜ ስራቸው ጡረታ ከወጡ በኋላ የጀነራል ኮንፍረንስ ፕሬዚዳንት ረዳት ሆኑ። ፓስተር ፊንሊይ እና ባለቤታቸው ኤርነስቲን ሦስት ልጆች እና አምስት የልጅ ልጆች አሏቸው።

በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ

3ኛ ሩብ ዓመት

ከሰኔ 20 - መስከረም 15 (2012/13) ዓ.ም.

አዘጋጅ፡ ፓ/ር ማርክ ፊንሊይ (Thd,phd)

ትርጉም: ብሩክ ፈለቀ

እና

ኤፍሬም ኤርምያስ