ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ሕዳር 6 - 12

8ኛ ትምህርት

Nov 16 - 22
እግዚአብሔር እና ቃልኪዳኑሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ነህ. 10:1–29፣ ዘፍ. 4:8–19፣ ዕብ. 13:20፣ ኢያ. 24፣ነህ. 10:30–39፣ ዕብ. 8:1–7።


መታሰቢያ ጥቅስ “‘ከዚህ ሁሉ የተነሳም ጽሁፍ ላይ በማስፈር ግዴታ የምንገባበትን የውል ስምምነት እናደርጋለን፤ መሪዎቻችንም ማኅተሞቻቸውን ያኖሩበታል።’ … እኛም ያምላካችንን ቤት ቸል አንልም።” (ነህ. 9:38፤ 10:39)

መ ጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ኪዳን” ሲናገር ምን ይላል? ለእንዲህ አይነቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኪዳን እጅግ ቀላል መግለጫ የሚሆነው ፣ በእግዚአብሔር እና በሕዝቡ (በእርሱ ሕዝብ) መካከል ሕጋዊ የሆነ ትስስር (ግንኙነት) ማለት ነው። እግዚአብሔር “እኔም አምላካችሁ እናንተም ሕዝቤ ናችሁ።” ያለበት መንገድ ነው። ከዚህ ሌላ በሌሎች ሕዝቦች መካከልም በአብዛኛው በመሪዎችና እነርሱ በሚያስተዳድሯቸው ሎሌዎች መካከል በጽሁፍ የሆኑ በቀደመው ዘመን የነበሩ ኪዳኖችን ልናገኝ እንችላለን።

እነዚህ ኪዳኖች ይፈፀሙ የነበሩበት ምክንያት ለሁለቱም ወገኖች (አካላት) ጠቀሜታ ስለነበራቸው ነው። መሪዎች ለሕዝቡ ማድረግ የሚገባቸውን ያደርጋሉ፤ ሕዝቡም ደግሞ ግብርን ይገብራል። ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ኪዳን ግን ከዚህ ይለያል። እግዚአብሔር ከነበረው ኪዳን የተጠቀመው ምንም ነገር አልነበረም። ሕዝቡ ለኪዳኑ ታማኝ ባልሆኑበት ጊዜ እንኳን ለኪዳኑ ታማኝ ለመሆን ቃል ገባ። ኪዳኖቹ በረከትንና እርግማንን በውስጣቸው በመያዛቸው አስከፊ የሆኑ ነገሮች መፈጠር በሚጀምሩበት ጊዜ እስራኤላውያን ኪዳናቸውን እንዳጠፉ እንዲያስተውሉ ረዷቸው።

በዚህ ሳምንት በነህምያ 10 ላይ እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር አድሰውት ስለነበረው ኪዳን እንመለከታለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ቃል ኪዳን ታሪክና ጥቅም ጠቅለል ባለ መልኩ እንመለከታለን። የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለሕዳር 13 ሰንበት ይዘጋጁ።

ህዳር 7
Nov 17

የኪዳን ምንነት


ነህምያ 10፡1-29ን ያንብቡ። (ደግሞም ነህምያ 9፡36-38ን በማንበብ ያስታውሱ)። ይህንን ኪዳን ያደረጉት እነማን ነበሩ፣ ወዲዚህ ኪዳንስ የገቡት ለምን ነበር?ደግሞም የኪዳኑን ሰነድ የፈረሙት መሪዎች ብቻ ቢሆኑም ጽሁፉ ትኩረት አድርጎ በመጥቀስ ሁሉም “የቀሩት ሕዝብ” ቃል ገቡ “የእግዚአብሔርን ሕግ … ለመታዘዝ በዚህ ርግማንና መሐላ ቃል ገቡ” (ነህ. 10፡28፣29) ይላል። በኪዳኑ ውስጥ ምን ጠቃሚ ነገር ቢገኝ ይሆን ሁሉም ከእግዚአብሔር ጋር ኪዳን ለማድረግ የፈለጉት? ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ ወደ ኋላ ሄደን ከመጀመሪያ ጀምሮ በቃል ኪዳን ፅንሰ ኃሳብ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መረዳት ይኖርብናል።

ኪዳኑ እግዚአብሔር ከኃጢአተኛው ሰብዓዊ ዘር ጋር ከነበረው ትስስር ጋር ስለሚያያዝ አስፈላጊ ነበር፣ ይህም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው ያለውን ከልብ የሆነ ፍላጎት ያሳያል። ሰዎችም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት እንዲገልፁ መንገዱን ከፍቶላቸዋል።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመፍጠር ታሪክ ስለ መጀመሪያዎቹ ሰብአዊ ፍጡራን መፈጠር የሚገልፅ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል እንዲሁም እርስ በእርሳቸው ስለነበራቸው ግንኙነት ጭምር የሚናገር ነው። ሆኖም ግን ኃጢአት በመካከል ገባ፤ እናም የነበሩትን ግንኙነቶች (ትስስሮች) ሰበራቸው። ኃጢያት የመፍጠር ተቃራኒ፣ ተቃርኖውም ደግሞ አለመኖርን (ሞትን) የሚያስከትል ነው።

እናም፣ ቀስ በቀስ የአዳም የዘር ሀረግ ለሁለት ተከፈለ፣ ቃየል ክፉን መረጠ (ዘፍ. 4፡8-19)፣ ሴት ደግሞ እግዚአብሔርን መረጠ (ዘፍ. 5:3-24)። የቃየል የዘር ሀረግ የተደመደመው ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ በሆነው በላሜሕ ሲሆን፣ ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት ልማድን የጀመረውም እርሱ ነበር። ታማኝ ከሆነው ከሴት ትውልድ ትይዩ በቃየል በኩል አመጸኝነትና በቀል ነበር ። የሴት ትውልድም ሲዘረዘር፣ የዚህ የዘር ሀረግ ሰባተኛ ትውልድ ሄኖክ ሲሆን፣ እርሱም “አረማመዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” (ዘፍ 5፡24)፣ እናም ወደ ሰማይ ተወሰደ።

አሳዛኙ ነገር፣ ዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ከመተባበር ይልቅ ከክፉ ጋር ተጣበቀ፣ በትውልድ ሀረጉ ውስጥም ታማኝ የሆኑት ቁጥራቸው አናሳ እየሆነ መጣ፣ እናም ትንሽ ቢቀጥል እግዚአብአብሔር የተስፋውን ዘር በመላክ ሰብአዊ ፍጡርን ለማዳን ቃሉን ሊፈጽምበት የሚችል አንድ ቤተሰብ እንኳን ባልቀረም ነበር። በዚያ ሁኔታ ግን፣ በውሃ ጥፋት እግዚአብሔር ጣልቃ ገባ። የውሃ ጥፋቱ ፣ሰፊ ጥፋትን ፣ የበለጠ የሕይወት ጥፋትን ያስከተለ ቢሆንም ፈጣሪ ያስወገደው ሰዎች እራሳቸው ቀድመው አፈራርሰው የጨረሱትን ነገር ነበር (ዘፍ. 6፡11-13)።

የኃጢአትን የማጥፋት ኃይል እውነታ በግል በምን መልኩ ተሰምቶዎት ያውቃል? ኃጢያትን ማሸነፍ የሚችለው ብቸኛ ሃይል ምን ይሆን፣ ለዚህ ሃይል ራሳችንን ማስረከብ የምንችለውስ እንዴት ነው?

ህዳር 8
Nov 18

ኪዳኖች በታሪክ ውስጥ


ከውሃ ጥፋት በኋላ፣ እግዚአብሔር ከኖህና ከእርሱ በኋላ ከኖሩት ጋር እንደገና ጀመረ። ከእነርሱም ጋር ደግም ወዳጅነት እንዲኖረው ፈቀደ፣ የዚህ ግንኙነትም ማዕከል የነበረው የኪዳን ጽንሰ ሀሳብ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የገባቸውን ሰባት ዋና ዋና ኪዳኖችን ያሳየናል።
1ኛው ቃል ኪዳን - አዳም (ዘፍጥረት 1 – 3)
2ኛው ቃል ኪዳን - ኖህ (ዘፍጥረት 6-9 )
3ኛው ቃል ኪዳን - አብረሃም (ዘፍጥረት 12፡1- 3)
4ኛው ቃል ኪዳን - ሙሴ እና የእስራኤል ሕዝብ (የሲና ወይም የሙሴ ኪዳን በመባል የሚታወቀው ኪዳን፣ ዘፀአት 19 – 24)
5ኛው ቃል ኪዳን - ፊንሐስ (ዘኁልቅ 25፡10 – 13)
6ኛው ቃል ኪዳን - ዳዊት (2 ሳሙኤል 7፡5 – 16)
7ኛው ኪዳን - አዲስ ኪዳን (ኤርምያስ 31፡31–34)

የሚቀጥሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። “ዘላለማዊ ኪዳን ” ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? (ዘፍ 9፡16፣ 17፡7፣ ኢሳ. 55:3፣ ዕብ. 13:20)።መጽሐፍ ቅዱስ “ዘላለማዊ ኪዳን” የሚለውን ቃል አስራ ስድስት ጊዜ ያክል በውስጡ አካትቷል። ከእነዚህ ውስጥም፣ አስራ ሦስቱ ከአብረሐም፣ከእስራኤል ጋር በሲና እና ከዳዊት ጋር ከተገቡ ኪዳኖች ጋር በተያያዘ ተገልፀው እናገኛቸዋለን። ከላይ የተጠቀሱት ኪዳኖች ደግሞ፣ የተለያየ ይዘት ቢኖራቸውም ሁሉም ስለ “ዘላለማዊ ኪዳን” የሚናገሩት ነገር አለ። የዘላለማዊ ወንጌል በመጀመሪያ በዘፍጥረት 3፡15 ተነግሮ በሂደት ደግሞ በሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ እንደተገለፀው፣ ስለ ዘላለማዊ ኪዳንም ተመሳሳዩን ነገር እንመለከታለን። ሁሉም በተከታታይ የመጡ ኪዳኖች በድነት ዕቅድ ውስጥ በሙላት የተገለፀውን ዘላለማዊ የፍቅር ኪዳን ለማብራራትና የበለጠ በጥልቀት ማስተዋል እንድንችል ለማድረግ ጥቅም ላይ ውለዋል። አዲሱ እና አሮጌው(ብሉይ) ኪዳኖች ብዙውን ጊዜ ተለያይተው ቢነገሩም ፣ የያዙት ግን ተመሳሳይ የሆኑ ሀሳቦችን ነው።

1.ቅድስና፡ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ።” (ኤር. 31፡33፣ ከዕብ. 8፡10 ጋር ያስተያዩት)። 2.እርቅ፡ “እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (ኤር. 31፡ 33፣ ዕብ. 8፡10)።

3.ተልዕኮ፡ “ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣ ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም” (ኤር. 31፡34፣ ዕብ. 8፡11) 4.ጽድቅ፡ “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም።” (ኤር. 31፡34፤ ዕብ. 8፡12።)

ህዳር 9
Nov 19

ኪዳናዊ አወቃቀር


የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኝዎች እንደሚስማሙት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ኪዳኖች ተመሳሳይነት ያለው የአወቃቀር ስርዓት አላቸው፤ ይህ የኪዳን ይዘት በጥንት ሂታይቶች እንኳን ሲተገበር ይስተዋል ነበር። ይህም፣ እግዚአብሔር ሰዎችን በባህላቸው፣ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ያገኛቸው ነበር ማለት ነው። በጥንቷ እስራኤል ዘመን ይዘወተሩ በነበሩት ኪዳኖች የሚከተሉት ክፍሎች ይካተቱባቸው ነበር፡ መግቢያ (የእግዚአብሔር ማንነት)፤ ታሪካዊ ማብራሪያ (ያለፈው ጊዜ የታሪክ ትስስር ይብራራል)፤ የሕግ ድንጋጌዎች፤ በረከቶችና መርገሞች፤ ምስክሮች፣ ልዩ መመሪያ ወይም የኪዳን ምልክት። እናም፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን በተመሳሳይ መልኩና በሚያውቁት መንገድ ወደነርሱ ለመድረስ መሞከሩ የሚያስገርም አይደለም።

ለምሳሌ፣ ሙሉ የዘዳግም መፅሐፍ የተጻፈው በኪዳን መልክ ነው፣ ምክንያቱም ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከአምላካቸው ጋር አዲስ ኪዳን እንዲፈጽሙ ጥሪ እያደረገ ስለነበር ነው። ኪዳኑንም በሚከተለው መልኩ ገልጾት ነበር፡ (1) መግቢያ (ዘዳ. 1፡ 1 – 5)፤ (2) ታሪካዊ ማብራሪያ (ዘዳ. 1፡6 - 4፡43 ) ፤ (3) የሕግ ድንጋጌዎች (ዘዳ. 4:44–26:19)፤ (4) በረከቶችና መርገሞች (ዘዳ. 27 – 30)፤ (5) ምስክሮች (ዘዳ. 30፡19፤ እና በመጨረሻም፣ (6) ልዩ መመሪያና ጥቅም (ዘዳ. 31፡9 – 13)። ኢያሱ 24ን ያንብቡ። በዚህ ምዕራፍስ ውስጥ እንዴት ነው የዚሁ አይነት ኪዳን አወቃቀር የተገለፀው?በኢያሱም ዘመን ኪዳኑ በታደሰበት ጊዜ የተከናወነው ይኸው ነበር። ሲጀምር፣ እግዚአብሔር እራሱን “የእስራኤል አምላክ፣ እግዚአብሔር” (ኢያ. 24፡2) በማለት የገለጠበት ሁኔታ መግቢያ ሆነ። ከዚያም ኢያሱ እግዚአብሔር በቀደመው ዘመን ለእነርሱ ምን አድርጎላቸው እንደነበር እንዲያስታውሱ ለሕዝቡ የተናገረበት ሰፋ ያለ የታሪክ ማብራሪያ ይከተላል (ኢያ. 24፡2 – 13)። ከዚህ ታሪክ በኋላ፣ የሕግ ድንጋጌዎች ተዘርዝረዋል (ኢያ. 24፡14፣15 ፣23)፣ በረከቶችና መርገሞች ተጠቅሰዋል (24፡19፣20)፣ ምስክሮችም ተለይተዋል (ኢያ. 24፡22፣27)፣ የተለየ ጥቅምም ተጠቅሷል (ኢያ. 24፡25፣26)። ስለዚህ በዚህ ስፍራም፣ መሰረታዊ በሆነ የኪዳን አቀራረብ ቅርጽ ከእስራኤል ጋር ኪዳንን መፈጸም ጥቅም ላይ ውሏል ማለት ነው። እግዚአብሔር በቀደመው ዘመን ብቻ ህዝቡን መምራቱ እንዳለ ሆኖ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ከእነርሱም የሚጠበቅ ነገር ነበር።

ኢያሱ 24:15ን ያንብቡ። በዚህ ስፍራ ለራሳችን በዚህ ዘመን ልንተገብረው የሚገባ ምን መርህ አለ?

ህዳር 10
Nov 20

የሕዝቡ ድርሻ


ነህምያ 10፡30–39 ያንብቡ። እስራኤላውያን የታደሰው ኪዳን አካል በመሆን እንፈጽማለን ብለው ቃል የገቧቸው አራት ነገሮች ምን ነበሩ?ሕዝቡ የሚከተለውን ቃል ገብተው ነበር፡
1. ከእስራኤል ውጪ የሆነ ጋብቻ ላለመፈፀም ( ሰውን ወደ ጣዖት አምልኮ የሚመራ የጋብቻ ትስስር ውስጥ ላለመግባት)፤
2. እውነተኛ የሰንበት አጠባበቅ (በንግድ ግብይት ምክንያት የሚመጣ አለመታዘዝ አይኖርም)፤
3. የእዳ ስረዛ እና በየሰባት አመቱ ለድሆች ቸርነትን ማድረግና ነፃነታቸውን መስጠት፤
4. ቤተመቅደሱን፣ በውስጡ ያሉ አገልግሎቶችንና አገልጋዮችን በገንዘብ መደገፍ፤ ይህም የሚሆነው የዕህል በኩራት በማምጣት፣ የበኩር ልጅን በመስጠትና አስራትን በመመለስ ነበር። እነዚህ ነገሮች እውነተኛው አምልኮ እንዲቀጥል እገዛ ያደርጋሉ።

የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቃልኪዳኖች ከሌሎች ጋር ከሚኖሩ ግንኙነቶች(ትዳርና ዕዳ ስረዛ) ጋር እና፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከሚኖር ግንኙነት(ሰንበት) ጋር የሚያያዙ ሲሆኑ የመጨረሻው ደግሞ (ነህ. 10፡32–39) ከቤተመቅደሱ ስርዓት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ህጎች ይናገራል።

የማህበረሰቡ አላማ ለኪዳኑ የተሰጡ መሆናቸውን ማሳየት ሲሆን ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመገንባት በተግባር የሚታዪ ነገሮችን ማከናወን ነበረባቸው። ምንም እንኳን ኪዳኑን ፍፁም በሆነ መልኩ ሁልጊዜ መጠበቅ ባይችሉም፣ ትክክለኛ ባህሪና እውነተኛ ልማድ መጪው ጊዜ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ አስተውለው ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በትክክለኛው መንገድ ላይ እንዲገኝ ከተፈለገ፣ ሊደርሱበት ካሰቡት ግብ ጋር ተስማሚ (ገጣሚ) የሆኑ ልማዶችና ባህሎችን ማቋቋም ይኖርባቸው ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር አካሔዳቸውን ለማድረግ ከፈለጉ፣ ሰንበት አስፈላጊ እንደሆነ መቀበል እና ለቤተ መቅደሱ ጥንቃቄ ማድረግ በዚህኛው አቅጣጫ ወደፊት ለመጓዝ የሚያግዙ መልካም ነገሮች ነበሩ።

የሚያሳዝነው፣ በነህምያ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፎች እንደተቀመጠው የገቡትን ቃልኪዳን መጠበቅ አልቻሉም። ሆኖም፣ ምንም እንኳን አብዛኛው ሰው መጠበቅ ባይችልም ፣ የተወሰኑ ወይም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ማከናወን ችለው ነበር። ከእግዚአብሔር እርዳታ ጋር እና ትኩረታችንን ደግሞ እርሱ ላይ በማድረግ፣ ትክክለኛ ባህሪን ማጎልበት እና ትክክለኛውንም መንገድ መያዝ እንችላለን። “ፈቃዳችሁን በትክክል በመጠቀም ውስጥ በሕይወታችሁ ሁለንተናዊ የሆነ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ፈቃዳችሁን ለክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ስታስረክቡ ከገዥዎች እና ከኃይላት ሁሉ በላይ ከሆነው ኃይል ጋር ሕብረት እንዲኖራችሁ አደረጋችሁ ማለት ነው። ፀንታችሁ እንድትቆሙ የሚያደርገውን ጥንካሬ ከላይ ታገኛላችሁ፣ እናም ደግሞ ዕለት ዕለት እራሳችሁን ለእግዚአብሔር በማስረከብ የአዲስ ሕይወት ልምምድን ትኖራላችሁ፣ እንዳውም በእምነት የሆነ ሕይወትን ትለማመዳላችሁ።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ፣ ገፅ. 48። በዚህ ስፍራ ላይ የተፃፈውን እንዳንለማመደው ወደኋላ የሚስበን ምንድን ነው?

ህዳር 11
Nov 21

ቤተመቅደሱ


ነህምያ 10፡32–39ን እንደገና ይመልከቱ። “እኛም የአምላካችንን ቤት ቸል አንልም” በሚል ነህ 10፡39 ላይ እንደሚታየው፣ ከቤተመቅደሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት ለእስራኤላውያን አስፈላጊ የሆኑት ለምን ነበር? (በተጨማሪም ዕብ. 8፡ 1–7 ይመልከቱ) ቤተመቅደሱ በአጠቃላይ ለእምነት አስፈላጊ የነበረው እንዴት ነው?እስራኤላውያን ለቤተመቅደሱ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር። ምንም እንኳ በነገስታቱ የግብር ጫና የነበረባቸው በቁጥርም አነስተኛ የሆኑ ሰዎች የተሰበሰቡበት ማህበረሰብ ቢሆኑም እንኳ፣ ቤተመቅደሱ በትንሹ እንዲያንሰራራ ሳይሆን የሚታይ እድገት (ለውጥ) እንዲኖረው በማሰብ ከሚያገኙት ከጥቂቱ ለመስጠት ወስነው ነበር። እናም ህጉ ከሚያዘውና፣ ከተስማሙበት በላይ በየዓመቱ አንድ ሦሥተኛ ሰቅል (የእስራኤላውያን የመገበያያ ገንዘብ) ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ለመስጠት ፈቅደው ነበር። ሕዝቡ ያስፈልጋል ከተባለውም በላይ የበለጠ ነገር ማከናወን እንዳለበት አስተውሎ ነበር። በተጨማሪም፣ ያለ ቅንጅት ስራው እንደሚበላሽ ተገንዝበው ስለነበር መሰዊያው ላይ ለሚነደው እንጨት አንድን ቤተሰብ በኃላፊነት መድበው ነበር።

የምርት በኩራቶች፣ የበኩር ልጆች፣ እና አስራቶችና የፈቃድ ስጦታዎች ለቤተመቅደሱ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆኑ የሚቀርቡትም የካህናቱና የሌዋውያኑን አገልግሎት እንዲደግፉ ነው። የሁሉም ነገር አንድ አስረኛ ወደ ሌዋውያኑ የሚሄድ ሲሆን፣ የበኩር ልጆችም በገንዘብ ሲዋጁ ገንዘቡ ለሌዋውያኑ በተጨማሪነት ይገባል። ለሌዋውያኑ የተፈቀደው አንድ አስረኛ አስራት ይወጣለትና ወደ ካህናቱ ይላካል። ቤተመቅደሱ ለእስራኤል ሕዝብ የልብ ምት በመሆን አገልግሎት ነበረው ማለት ይቻላል። ለእምነታቸው እጅግ ማዕከል ከመሆኑ የተነሳ ናቡከደነፆር ቤተመቅደሱን በማውደም ነዋየ ቅዱሳቱን ሲወስድ ጥልቅ ሐዘን ተሰማቸው።

ቤተመቅደሱን በሚገባ ማስተዳደር በተቻለበት ዘመን፣ ሕዝቡ የተነቃቃ መንፈሳዊ ሕይወትን እንዲያገኝ አስችሎ ነበር፣ ምክንያቱም ሕዝቡን ለኃጢአት በሽታ የመጨረሻ (ብቸኛ) መፍትሔ ወደሆነው በግ ሞት ያመላክታቸው ስለነበር ነው። ኢየሱስም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ያ መፍትሔ ተሰጠ (ሮሜ. 5፡ 5–10)። በበለጠ ሁኔታ ደግሞ፣ አመታዊ አገልግሎት በሆነውም የስርየት ቀን አማካኝነት፣ እግዚአብሔር በመጨረሻ ክፋትንና ኃጢያትን ለዘላለም እንደሚያስወግድ ሕዝቡ ይማሩ ነበር።

በሌላ አነጋገር፣ ለሕዝቡ የድነትን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ለመግለጽ መቅደሱ እንደ መግለጫ ስርአትነት አገልግሏል። የቤተ መቅደሱን አገልግሎት በመመልከት የምናገኛቸው ትምህርቶች በጣም ሰፊና አስፈላጊ ሲሆኑ ስለ እግዚአብሔር ባህሪም ትልቅን ምስል ይሰጡናል፣ የድነት ዕቅድንም የበለጠ ግልፅ እንዲሆንልን ይረዱናል። “ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ’ የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኀጢያተኞችም ዋና እኔ ነኝ።”(1 ጢሞ. 1፡15)። የጳውሎስ ተስፋ ምን ነበር፣ እኛም የራሳችን ተስፋ ልናደርገው የምንችለው እንዴት ነው?

ህዳር 12
Nov 22


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ. ኋይት “ራስን ቀድሶ መስጠት” ከገፅ 43–48, ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ ያንብቡ።

“የምድራዊው ቤተመቅደስ አገልግሎት ሁለት የአገልግሎት አይነቶች (ክፍሎች) ነበሩት፤ ካህናቱ የየዕለት አገለግሎትን በቅዱሱ ክፍል ይከውኑ ነበር፣ በአመት አንድ ጊዜ ደግሞ ሊቀ-ካህናቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የተለየ የስርየት ሥራን ያከናውናል፣ መቅደሱንም ያነፃዋል። ቀን በቀን ንስሀ የሚገባ ኃጢአተኛ ያመጣውን የኅጢያት መስዋዕት ወደ ድንኳኑ መግቢያ በር ያመጣና፣ ለመሰዋት የቀረበው እንስሳ ጭንቅላት ላይ እጁን በመጫን ኅጢያቱን ሁሉ ይናዘዛል፣ ይህም ኃጢአቱ ከእርሱ ወደሚሰዋው ንፁህ መስዋዕት የሚተላለፍ መሆኑን ለማሳየት ነው። ከዛም እንስሳው ይታረዳል።

‘ደም ሳይፈስ፣’ ሐዋርያው ሲናገር ‘የኀጢያት ስረየት የለም’። ” “የፍጡር ሕይወት በደም ውስጥ ነው” (ዘሌ. 17፡11)። የተጣሰው የእግዚአብሔር ሕግ የሕጉን ተላላፊ ሕይወት ይጠይቃል። ደሙ ስለ ኃጢአተኛው በቅጣት መልክ የቀረበውን ሕይወቱን ይወክላል፣ የእርሱ በደል እንስሳው እንዲታረድ አደረገ፣ ደሙም በካህኑ ይያዝና ወደ ቅዱሱ ክፍል ይገባል፣ በመጋረጃውም ላይ ይረጫል፣ ይህም ኀጢያተኛው የተላለፈውን ሕግ በውስጡ ከያዘው ታቦት አጠገብ በሚገኘው መጋረጃ ላይ ሆነ ማለት ነው። በዚህ ስርዓት መሰረት ምሳሌያዊ በሆነ መልኩ በደሙ አማካኝነት ኀጢያቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ይተላለፍ ነበር። በአንዳንድ አገልግሎቶች ደሙ ወደ ቅዱሱ ክፍል እንዲገባ አይደረግም ነበር፣ ስጋው ግን ሙሴ የአሮንን ልጆች ባዘዘው መሰረት በካህኑ መበላት ነበረበት፣ እንዲህም ብሎ ነበር፣ “ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢያት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ተሰጥቷል … ” (ዘሌዋውያን 10:17) ሁለቱም ስርዓቶች ኃጢአት ከበደለኛው ወደ ቤተመቅደሱ መሸጋገሩን በምሳሌ የሚያሳዩ ናቸው። Ellen G. White, The Great Controversy, p. 418.


የመወያያ ጥያቄዎች
1.ምንም ያህል ከልብዎና በቅንነት ሊጠብቋቸው ቢሞክሩም እንኳን ፣ቃል ገብተው ነገር ግን ስላልፈፀሟቸው (ስላፈረሷቸው፣ ስላልጠበቋቸው) ቃልኪዳኖች ያስቡ። ከዚህ ልምምድዎ ምን መማር ቻሉ፣ ደግሞስ ወደፊት ተመሳሳይ የሆነ ስህተትን እንዳይሰሩ ምን ያህል አገዘዎት?

2.ኪዳን ማለት ግንኙነትን በሕግ ማዕቀፍ ማዋቀር ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኪዳን ዘወትር ብናፈርሰውም ፣እኛ ምንም ያህል ለራሳችን ድርሻ ታማኝ ባንሆንም፣ እርሱ ግን የራሱን ድርሻ በታማኝነት ሁልጊዜም ይጠብቃል። ይህን የእግዚአብሔር መልካምነት እና ታማኝነት መረዳት ሰዎች ክእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲመሰርቱ ምን ያህል ይረዳቸዋል፣ እኛም መኖር እንደሚገባን ለመኖር ይህ እንዴት ያግዘናል?

3.ምን ያህል ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ታማኝነትና በተሰጠን አዲስ ኪዳን ውስጥ ለተቀበልናቸው ቃል ኪዳኖች ታማኝ እንዳልነበርን እናሰላስል። እናም፣ የድነትን ዕቅድ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ መስዋዕትነት አማካኝነት ያገኘነውን የምህረት (የይቅርታ) ቃል፣ በእርሱም ደም አዲሱን ኪዳን ስለ እኛ ስለማተሙ (ሉቃ. 22፡20፣ዕብ. 8፡13፣ 9፡ 15) ፣ ማስተዋላችን ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድነው?