ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ጥቅምት 29-ህዳር 5

7ኛ ትምህርት

Nov 9 - 15
ይቅር ባዩ አምላካችንሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ነህ. 9፡1-3፣ ዳን. 9፡4-19፣ ነህ. 9፡4-8፣ ቆላ. 1፡16-17፣ ነህ. 9፡9-38፣ ሮሜ 5፡6-8።


መታሰቢያ ጥቅስ “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።” (ምሳሌ 28፡13)

የ ዳስ ክብረ በዓል እንዳለቀ መሪዎቹ እንደገና ህዝቡን ሰበሰቡ። የደስታው ጊዜ አልቆ ወዳልጨረሱት ጉዳይ ማለትም ስለ ኃጢአታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለመናዘዝ እና ንሰሐ ለመግባት ጊዜው ነበር። እርግጥ ነው አስቀድመው መሪዎቹ መመረራቸውን እና በጥፋታቸው ማዘናቸውን እንዲያቆሙ ነግረዋቸው ነበር። ያ ማለት ግን ማዘንና መናዘዝ አይጠቅሙም ማለት አይደለም። ስለሆነም የደስታ ጊዜያቸውን ስለጨረሱ ትክክለኛ በሆነው ኑዛዜ ውስጥ የማለፊያ ሰአት ነበር።

በዚህ ታሪክ ውስጥ የተገለጸው የክስተቶች ቅደም ተከተል ሁሌም የደስታ እና የሀዘንን ቅደም ተከተል የሚያሳይ ላይሆን ይችላል። ያ ማለት ደግሞ ታቃራኒውን ብቻ ልንከተል ይገባል ማለትም አይደለም። ምንም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ አስቀድመን ኑዛዜን ከዛም የደስታ ጊዜን ማሳለፍን የምንመርጥ ቢሆንም ምናልባትም እግዚአብሔርን በደስታ በማምለክ ልናስቀድም ይገባናል። በሮሜ 2፡4 እንደሚነግረን የእግዚአብሔር መልካምነት ነው ወደ ንሰሃ የሚመራን መልካምነቱ ምስጋና እና ደስታን ያመጣል በዚህም ውስጥ እግዚአብሔር ይቅር ሊለን፣ ሊያነጻን እና ዳግም ሊፈጥረን እንደሚችል እንረዳለን።

ጥቅምት 30
Nov 10

ጾም እና አምልኮ


ነህ. 9፡1-3 ያንብቡ። ለምንድን ነው ሰዎቹ ራሳቸውን ከእንግዶቹ የለዩት?ምንም እንኳን ነህምያ ሰዎቹ ይህንን ወቅት ከደስታ ጋር እንዲያይዙት ጓጉቶ የነበረ ቢሆንም፣ የተሰበሰበውን ሰው ግን ወደ ጾም መምራት ነበረበት። በራሳቸው ላይ አመድን በመነስነስ እንዲሁም ማቅን በመልበስ ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት አዋረዱ። ሌሎቹ ሰዎች በእስራኤላዊያን ኃጥያት ውስጥ የሚጋሩት ነገር ስላልነበር ራሳቸውን አገለሉ። እብራዊያኑ ይቅር ሊባል የሚገባው ሃጥያት የእነሱ እንደሆነ አወቁ ወደ ስደት የመራቸውን የሕዝባቸውን ኃጥያት እውቅና ሰጡ።

በጋራ መጸለያቸውና መናዘዛቸው ስለ ሃጥያታቸው ባህሪ የጠለቀ ግንዛቤ እንደነበራቸው ማሳያ ነው። የቀደሙት አባቶቻቸው ነገሩን አበላሽተው ወደ ስደት እንደመርዋቸው በማሰብ መበሳጨት ይችሉ ነበር ወይም ደግሞ በቀደመው ትውልድ እና በመሪዎቻቸው ምርጫ እና አግዚአብሔርን የመምሰል ባህሪን የማጣታቸውን ነገር እና ይህም ለዚህ እንዳበቃቸው በማሰብ በማማረር ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ጥላቻን እና ቁጭትን ከማናፈስ ይልቅ ራስን ዝቅ በማድረግ እና በመናዘዝ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።

ነህምያ 9፡3 እንደሚለው ህዝቡ ከቀኑ አራተኛው ክፍለ ጊዜ ድረስ የህጉን መጽሐፍ አነበቡ ሌላኛውን አራት ክፍለ ጊዜ ሃጥያታቸውን በመናዘዝ እግዚዘብሔርን አመለኩ።ይሄ ሶስተኛው የቶራው መጽሀፍ ንባብ ነው። ቶራውን ማንበብ ለኑዛዜ ወሳኝ ነገር ነው። ከእግዚአብሔር በሚመጣው እውነት ላይ የተመሰረትን መሆን አለብን ። መጽሀፍ ቅዱሱን ባነበብን ቁጥር እግዚአብሔር ወደ እኛ ይቀርባል መንፈስ ቅዱስም ሊናገረን እና ሊያስተምረን ይችላል። የቃሉ እውነት አስተሳሰባችንን ይቀርጸዋል፣ ያበረታታናል ከፍ ከፍም ያደርገናል። እስራኤላውያንም አዘኑ፣ አለቀሱ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ቅዱስ የሆነ መገኘት ውስጥ መሆን ውበቱን እና መልካምነቱን እንድናይ ያደርገናል። የአለማት ሁሉ ፈጣሪ እኛ ያልተገባንን ሰዎች መምረጡ ምን ያህል ድንቅ እንደሆነ እንድንረዳ ያደርገናል። ስለሆነም ያለ እግዚአብሔር ከእምነት አንጻር ከቀደሙት አባቶቻችን የተለየን አይደለንም። እግዚአብሔር በውስጣችን ሲሰራ ብቻ ነው መሆን የሚገባንን መሆን የምንችለው።

ዳን 9፡ 4-19ን ያንብቡ። በምንም መንገድ ነው ጸሎቱ ዛሬ ባለው ሕይወታችን ሊተገበር የሚችለው? በግላችንም እንደ ቤተክርስትያንም ይህ ምን ሊነግረገን ይችላል?

ህዳር 1
Nov 11

የጸሎቱ መጀመር


ለመጽሐፍ ቅዱሱ መነበብ ሕዝቡ የሰጡት ምላሽ የእግዚአብሔርን መልካምነትና የእስራኤልን አለማመን የሚያስታውስ ረዥም ጸሎት ነበር። እንደውም ምላሹ ከጸሎት ይልቅ ስብከት የመሰለ ነበር ምክንያቱም እያንዳንዱ ጥቅስ ተመሳሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ስፍራ ላይ ይገኛል።

ነህ 9፡4-8 ያንብቡ። በጥቅሱ መጀመሪያ ላይ ዋና ዋናዎቹ ጸሎቱ ያውጠነጠነባቸው አርዕስቶች ምንድናቸው? ለምን?በመጀመሪያው የጸሎቱ ክፍል ሰዎቹ እግዚአብሔርን ይባርካሉ በተለይም ስሙን። በዕብራዊያን ባህል ‹ስም› መጠሪያ ብቻ አልነበረም የማንነትም መገለጫ ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ስም በማመስገን ስሙ ምስጋና የተገባው ስም እንደሆነ እየገለጹ ነበር። ይህ ስም የአለማት ፈጣሪ ስም ነው። ጸሎቱ የሚጀምረው እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪ እና ጠባቂ እንደሆነ በመግለጽ ነው። (ነህ 9፡6 እንዲሁም ቆላ 1፡ 16፣17) “መጠበቅ” የሚለው ቃል እብራዊያን የመጣ ቃል ሲሆን “በሕይወት ማቆየት” የሚልን ትርጉም የያዘ ነው።

የሁሉ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ከልቡ ታማኝነት ውጪ ምንም የተለየ ነገር ያልነበረውን አብረሃምን መረጠ። በብዙ አጋጣሚዎች አብረሃም እምነት ጎድሎት ልናየው እንችላለን ነገር ግን ልጁን እንዲሰጥ በተጠየቀ ሰአት አልተጠራጠረም።(ዘፍ 22 ይመልከቱ) በአንድ ሌሊት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ረዥም ጉዞ ታማኝ መሆንን ተማረ። ‹ልብ› የሚለው ቃል አእምሮን ያሳያል። በሌላ አገላለጽ በአብርሐም ውስጥ ያደገው ታማኝነት በሀሳብ እና በድርጊት የተገለፀ ስለነበር እግዚአብሔርም ወደደለት።

የመጀመሪያዎቹ የፀሎቱ ሀረጎች የሚያውጠነጥኑት እግዚያብሔር 1ኛ ፈጣሪ 2ኛ ጠባቂ እና 3ኛ ቃሉን የሚጠብቅ በመሆኑ ላይ ነው። ሰዎቹ አስቀድመው እግዚያብሔር ማን እንደነበር በማስታወስ ጀመሩ ይህም የፈጠረን ታማኙ አምላክ ፣ የሚያቆየን እና ሁሌም የገባልንን ቃል የሚጠብቅ እርሱ ነው። ይህንን በአእምሮአችን ማስቀመጥ በትክክለኛው አስተሳሰብ አእምሮአችንን ከመምራቱ ባሻገር እና የራቀ ሲመስለን እና በግድድሮሻችን ግድ የሌለው ሲመስለን እንዲሁም በከባድ ሁኔታ ውስጥ እንኳን እንድናምነው ይረዳናል።

እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው የሚለው አስተምህሮ ለእምነታችን ቁልፍ የሆነው ለምንድን ነው? የህይወታችንን 1/7 ኛውን በየሳምንቱ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን መሆኑን እያስታወስን እንድንኖር ከታዘዝንበት ከዚህ ትምህርት የተሻለ ምን ትምህርት ይኖር ይሆን?

ህዳር 2
Nov 12

ከበፊት የተገኘ ትምህርት


ነህምያ 9፡9-22ን ያንብቡ። ይህኛው የፀሎቱ ክፍል ከመጀመሪያው የፀሎቱ ክፍል የሚለየው በምንድን ነው?ፀሎቱ እግዚአብሔርን ስለታማኝነቱ ከማመስገን ወደ እስራኤላውያን አለመታመንና የበረሃ ውስጥ ልምምድ ይሻገራል። እግዚአብሔር ለእስራኤላዊያን የሰጠውን የተለያየ ነገር ይዘረዝራል። ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ የአባቶች ምላሽ ለዚህ ስጦታ ኩራት፣ መንቻካነትና እግዚአብሔር ከፀጋው ብዛት የተነሳ ያደረጋቸውን አለመቀበል ነበሩ። መውደቃችንንና ለእግዚአብሄር እውነተኛ መሰጠት ማጣታችንን ማወቅ ለመናዘዝና ለንስሀ ወሳኝ ደረጃዎች ናቸው። ምንም እንኳ እነዚህ ፅሁፎች በጥንት ዘመን ስለነበሩ ሰዎች ቢናገሩም እያንዳንዳችን ይህ ችግር እንዳለብን የሚካድ አይደለም።

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ወንጌል ለእኛም ለእነሱም የሚመጣው። ሀጢያታችንን መናዘዛችን አያድነንም የሚያድነን የክርስቶስ በእኛ ምትክ ዋጋ መክፈል ነው። መናዘዝ ከንስሀ ጋር በክርስቶስ ስለመዳናችን እውቅና የምንሰጥበት ዋና መግለጫ ነው። “በንስሀና በእምነት ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ስንቀበል አምላክ ሀጢያታችንን ይቅር ሊለንና በህጉ የተቀመጠውን ቅጣት ሊያነሳልን ይችላል። ያኔ ሀጢያተኛው በእግዚያብሔር ፊት ንጹህ ሆኖ ይቆማል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከአባቱ እና ከልጁ ጋር ህብረት ይኖረዋል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የተመረጡ መልእክቶች ፣ መጽሀፍ 3፣ ገፅ 191

በተመሳሳይ የእግዚአብሔር መልካምነት ሀጢያታችንን እንድንናዘዝ እና ንስሀ እንድንገባ ሲያደርገን እኛም ደግሞ በአግዚያብሔር ሀይል ሀጢያታችንን ለመተው ቆራጥ መሆን አለብን። መደምደሚያው እስራኤል ልበ ደንዳና የነበረ ሲሆን እግዚአብሔር ግን አፍቃሪ ነው። ህዝቡ እግዚአብሔር ለእስራኤላዊያን ያደረገውን ዞር ብለው ሲመልከቱ ለእነሱም እንደዛው እንደሚጠነቀቅላቸው አሰቡ። ሁሌም እግዚአብሔር በታሪካቸው ውስጥ ያደረገውን ማስታወስ የሚጠቅማቸው ለዚህ ነበር። ሲረሱ ነበር ችግር ውስጥ የሚገቡት።

ወደኋላ መለስ ብላችሁ እግዚአብሔር በህይወታችሁ እየሰራ እንደነበር እርግጠኛ የነበራችሁበትን ጊዜ አስታወሱ። በቀጣይ ችግር ሲያጋጥምዎ ከዚያ መፅናናትን ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ስለወደፊቱ ተስፋ ስትቆርጡ፣ የተተዋችሁ ሲመስላችሁ እና ስትፈሩ እንዴት ነው በእግዚአብሔር መልካምነት መታመንን መማር የምትችሉት?

ህዳር 3
Nov 13

ህጉ እና ነቢያት


ነህምያ 9፡ 23-31። ከእግዚአብሔር ታላቅ መልካምነት አንፃር እስራኤላውያን እንዴት ነው የተገለፁት?ቀጣዩ የፀሎቱ ወይም የስብከቱ ክፍል የሚያተኩረው እግዚአብሔር የተሰጣቸውን በከነዓን የነበረው ህይወት ላይ ነበር። መሬት፣ ከተማ እና የወይን እርሻ ለመጠቀም ዝግጁ የነበረ ተሰጣቸው ሆኖም እንደተገባቸው ነገር ቆጠሩት። የቁጥር 25 መጨረሻ ‹በሉ፣ ጠገቡ ወፈሩም› በማለት ይነግረናል። መወፈር የሚለው አገላለጽ በመጸሀፍ ቅዱስ ውሰጥ ጥቂት ስፍራ ብቻ የሚገኝ አገላለጽ ነው። (ዘዳ 32፡15 እና ኤር 5፡28) እና በእያንዳንዱ አገላለጽ አሉታዊ ትርጉም ነበር የነበረው።

በታላቅ መልካምነቱ ሊደሰቱ ሲችሉ ደስታቸው የነበረው በእግዚአብሄር ሳይሆን በነበራቸው ነገር ነበር። የሁሉ ነገር መኖር ከእግዚአብሔር ጋር ተጠጋግቶ መራመድን ወይም መኖርን አያመጣም። አብዛኛውን ጊዜ ያ ወይም ይህ ቢኖረኝ ደስተኛ እሆናለሁ እንላለን። እንዳለመታደል ሆኖ፣ እስራኤላዊያን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ነገር ነበራቸው ከዛ ነገር ያገኙት ደስታ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን መሰጠት ቀነሰው። አብዛኛውን ግዜ ከሰጪው ይልቅ በስጦታው ላይ እናተኩራለን። ይህ ክፉ መታለል ነው።

ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር በሰጠን ነገሮች ልንደሰት አይገባም ማለት አይደለም። በስጦታዎቹ እንድንደሰት ይፈልጋል። ነገር ግን ይህ ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ዋስትና አይደለም። እንደውም ካልተጠነቀቅን እነዚህ ነገሮች እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ።

በዚህ ምዕራፍ መሪዎቹ ለእግዚአብሔር እንዴት ታማኞች እንዳልነበሩ ተናዘዙ። ታሪክ ወደኋላ ሄደው ሲያዩ እንደ ህዝብ የተላለፉትን ነጥለው አወቁ ሁለት ነገሮች በመደጋገማቸው ምክንያት ወሳኝ እንደሆኑ ጎልተው ወጥተዋል። 1. እስራኤል የእግዚአብሔርን ህግ ተወ 2. ነብያቱን እሳደዱ

በሌላ አገላለፅ እንደ እግዚአብሔር ህዝብም ሆነ በግል ለማደግ የእግዚአብሔር ህግ እና ነብያት ወሳኝ እንደነበሩ ተረዱ። የፀሎቱ መደምደሚያ የሚያተኩረው ሰው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ማድረግ ከቻለ ሊኖርበት እንደሚገባና (ነህምያ 9፡ 29 በቀጥታ ከዘሌዋውያን 8፡15 የተወሰደ) በነቢያቱ ሲናገር የነበረው መንፈስ ቅዱስ እንደነበር በመግለጽ ነው። እግዚአብሔር ህግጋቱን የሰጠን ለተትረፈረፈ ህይወት ሲሆን ነብያቱን የላከው ደግሞ እውነቱን እንድንረዳ ነበር። በእነዚህ ስጦታዎች ምን ማድረግ አለብን የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።

ህዳር 4
Nov 14

ምስጋና እና ተማፅኖ


ነህ 9፡32-38 ያንብቡ። የኑዛዜ ጸሎቱ መደምደሚያ ዋና ሃሳብ ምንድን ነው?በድጋሚ ጸሎቱ እግዚአብሔርን ስለማንነቱ ወደ ማመስገን ይመለሳል። ታላቅ፣ ሁሉን ቻይ አስደናቂ ቃሉን የሚጠብቅ እና ምህረቱን የሚያጸና። እግዚአብሔር ለእነርሱ ስላደረገው መልካምነት በቅንነት እውቅና እየሰጡ ያለ ይመስላል። በምዕራፍ 10 ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በሚመስል መልኩ ልመናቸውን ያቀርባሉ። ተማጽኗቸው ምንድን ነው?

‹አሁንም አምላካችን ሆይ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ ከአሦር ነገስታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ እና በነገስታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነብያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ።› ነህ 9፡32

ማህበረሰቡ በአከባቢው ለነበሩት ነገስታት መገበር ነበረባቸው በየአቅጣጫው የሚመጣው ጫና እሰራኤልን እያስጨነቀ ነበር ይህም እጅግ አታክቷቸው ነበር። ተከታትሎ የሚመጣውን መከራ መሸከም ነበረባቸው። ከዚህም የተነሳ ፋታ ለማግኘት ይመኙ ነበር። የሕዝባቸውን አለመታመን ከዘረዘሩ በኋላ በሚያስገርም ሁኔታ ራሳቸውን ባሪያዎች ብለው ነበር የሚጠሩት በእርግጥም ባሪያዎች የሚፈጽሙት ጌቶቻቸው ያዘዟቸውን ነው።

ይህን ቃል መጠቀማቸው የሚያሳየው ቀደምት አባቶቻቸው ባልታዘዙት መንገድ አምላካቸውን መታዘዝ እንዳለባቸው መረዳታቸውን ነው። ለአምላካቸው እና ለሰጣቸው ትእዛዝ ታማኝ የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልጽ ነው። እናም እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች በጉዳያቸው ጣልቃ እንዲገባላቸው እየጠየቁት ነው።

ዕዝራ እና ነህምያ የነበሩበት ማህበረሰብ ያሉበትን ሁኔታ <<ፅኑ መከራ>> (ነህ 9፡ 37) በማለት በግብጽ ከደረሰባቸው መከራ (ነህ 9፡9) ጋር በማነፃፀር ገልፀውታል። በፀሎታቸው እግዚአብሔር በግብጽ መከራቸውን ሳይንቅ በመመልከቱ አመሰገኑት። ሕዝቡ እግዚአብሔር ከዚህ ቀደም ጣልቃ እንደገባ እንዲገባላቸው እየጠየቁት ነበር። ምንም እንኳን ያልተገባቸው መሆናቸውን ቢያውቁም ምክንያቱም ነገስታትም፣ ልዑሎቹም፣ ካህናትም ፣ ነብያትም ማናቸውም ታማኝ አልነበሩም። ስለሆነም የተማመኑት በራሳቸው እና በቀደምት አባቶቻቸው ስራ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ጸጋ፣ ምህረት እና በነገራቸው ጣልቃ እንደሚገባላቸው በነበራቸው ተስፋ ብቻ ነበር።

ሮሜ 5፡6-8 ያንብቡ። ይህ ጥቅስ እንዴት ነው አስራኤላዊያን እግዚአብሔርን ሲጠይቁት የነበረውን የሚያሳየው? እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ሲጠይቁት ከነበረው እና ጳውሎስ በሮሜ ከሚናገረው ምን አይነት አጽናኝ ነገር እናገኛለን?

ህዳር 5
Nov 15


ተጨማሪ ሀሳብ


ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ ከሚለው መጽሐፍ ‹ኑዛዜ› የሚለውን ምዕራፍ ያንብቡ። በነህ. 9፡25 ዕብራዊያኑ እንዴት አባቶቻቸው ‹ራሳቸውን በእግዚአብሔር መልካምነት እንዳዝናኑ› ይናገራሉ። ስርወ ቃሉ ከኤደን ጋር ተመሳሳይ ነው። ልክ ‹ኤደን ገነት› ዘፍ. 2፡15 እንደሚለው ምናልባትም ኤደናዊ የሚለው ቃል ግስ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ትክክለኛው ትርጉም የሚሆነው ‹ራሳቸውን ኤደናዊ አደረጉ› የሚለው ነበር ።

ከኤደን የተሻለ ወንጌል መመለስ እንደመሆኑ የሚገልጽ ኃሳብ የለም። እግዚአብሔር ዕብራውያንን ያስነሳው እና ወደ ቀደመው አለም መስቀለኛ መንገድ ያመጣቸው በወደቀችው አለም የኤደንን የተቀራረበ ምስል ለመፍጠር ነበር። ኢሳ 51፡3 ‹ እግዚአብሔርም ፅዮንን ያጽናናል በእርሷም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል ምድረበዳዋንም እንደ ኤደን በረሃዋንም እንደ እግዚአብሔር ገነት ያደርጋል፣ ደስታና ተድላ የምስጋናና የዝማሬ ድምጽ ይገኝባታል።›

በቁሳዊ በረከት በዚህ በወደቀ አለም በገባላቸው ቃል መሰረት ተባርከው ነበር ይህም የኤደንን በረከት ማስታወሻ ነበር። ያም መልካም ነበር። እንዲደሰቱበት ነበር የተሰጣቸው። እግዚአብሔር አለምን የፈጠረው በትክክል የሰው ልጅ እንዲደሰትበት ነው። በእግዚአብሔር የተባረኩት እስራኤላዊያን ተደስተውበት ነበር። ሀጢያታቸው የነበረው ራሳቸውን ኤደናዊ በማድረጋቸው ሳይሆን የእግዚአብሔርን መልካምነት በመርሳታቸው ነው። ሕዝቅኤል 23፡35 በመልካምነቱ ግን ሲደሰቱ ነበር። በረከቶቹ በራሳቸው መደምደሚያ ሆኑባቸው ለመደምደሚያው መነሻ ሊሆኑላቸው ሲገባ። ይህም በአካባቢያቸው ላሉ የእግዚአብሔርን ማንነት መግለጥ ነበር።
የመወያያ ጥያቄዎች
1.የሱስ “በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው። የዚህም አለም ሀሳብ እና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል የማያፈራም ይሆናል።” ማቲዎስ 13፡22 የዚህም አለም ሀሳብ እና የባለጠግነት መታለል ሲል ምን ማለቱ ነው? ይሄ በዚህ ሳምንት ካጠናነው የኑዛዜ ፀሎት ጋር እንዴት ይገናኛል?

2.በድጋሚ የተፈጥሮን ቀኖና አስቡበት። በነህምያ 9 ወዲያውኑ ስለ እግዚአብሔር ፈጣሪነት እና አፅንቶ አቋሚነት እንደሚጸልዩ ያስተውሉ ይሄ ቀኖና ለእምነታችን መሰረት ስለመሆኑ ምን ይነግረናል?

3.በውስጣችን ባለው ኃጢያተኝነት የተነሳ ስለ ኃጢያታችን እውቅና በመስጠት መካከል እና ሰይጣን በኃጢያተኝነታችን ተስፋ እንድንቆርጥ እና እምነታችንን እንድንተው እንዳያደርገን ባለው መካከል ሚዛኑን እንዴት ማግኘት እንችላለን?