ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ጥቅምት 22-28

6ኛ ትምህርት

Nov 2 - 8
ቃሉን ማንበብሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት ለመዘጋጀት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። ነህ.8፡1-8፣ ዘዳ.31፡9-13፣ማቴ.17፡5፣ የሐዋርያት ስራ 8፡26-28፣ ነህ.8፡9-12፣ ዘሌ. 23፡39-43።


መታሰቢያ ጥቅስ “የእግዚአብሔርንም ህግ መፅሀፍ አነበቡ፤ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር። ህዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።” (ነህ. 8፡8)

የ ኢየሩሳሌም ቅጥር ተገንብቶ አለቀ። እስራኤላውያንም በነህምያ መሪነት በሩን በመስራት ዋናውን ሥራ አጠናቀቁ። ግንባታው ሲጠናቀቅ በዙሪያቸው የነበሩ ህዝብ “በእግዚአብሔር እንደተከናወነ…”ስላወቁ በመደነቅ ተሞሉ። እጅግ አስከፊ ተቃውሞና ጥላቻ ቢደርስባቸውም እስራኤላወያን ያቀዱትን ከግብ ስላደረሱ የእስራኤል አምላክ ህያው መሆኑን ጠላቶቻቸው ተገነዘቡ።

ከቅጥሩ መጠናቀቅ በኋላ ነህምያ ወንድሙን አናኒን የኢየሩሳሌም ገዥ፣ ሀናንያን ደግሞ የቅጥሩ አለቃ አድርጎ ሾመ። ሁሉቱም ሰዎች የተመረጡት በዘር ሀረጋቸው ሳይሆን በቅንነታቸው፣ በታማኝነታቸው እና ባላቸው ፈርሀ-እግዚአብሄር ነበር (ነህ. 7፡2) ። ቅጥሩ በወርሃ ኤሉል (በ6ኛው ወር) ተጠናቀቀ። (ነህ. 6፡15) የሚቀጥለው ተግባር ምን ይሆን? የሚቀጥሉት የነህምያ መፅሀፍ ምዕራፎች (ነህምያ 8-10) በ7ኛው ወር (በቲሽሪ) የተከናወኑ ክስተቶችን ይገልፃሉ (ነህ. 8፡2) ። በእነዚህ ጥቀሶች ውስጥ የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እንዴት እንደወሰኑ እና በዚያም ሀሴት እንዳደረጉ እንመለከታለን።

*የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 29 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጥቅምት 23
Nov 03

ህዝቡ ተሰበሰቡ


ነህምያ 8፡1 እና 2ን ያንብቡ። የእግዚአብሔር ቃል ለህዝቡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር ይህ ምን ይነግረናል?አይሁዳውያን የቅጥሩን ግንባታ ጨርሰው በኢየሩሳሌም መኖር እንደጀመሩ በ7ኛው ወር ሁሉም በአንድነት በኢየሩሳሌም አደባባይ ተሰበሰቡ። ቲሽሪ ተብሎ የሚጠራው የዓመቱ 7ኛ ወር በእስራኤላውያን ዘንድ ምናልባትም እጅግ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የመለከት በዓል(ለእግዚአብሔር ፍርድ የሚዘጋጁበት፤ የወሩ የመጀመሪያ ቀን)፣ የስርየት ቀን(የፍርድ ቀን፣ የወሩ 10ኛ ቀን) እና የዳስ በዓል(እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶ በምድረ-በዳ የመራቸውን የሚያስቡበት፤ የወሩ 15ኛ ቀን) የሚከበሩበት ነው። ህዝቡ የመለከት በዓል በሚከበርበት በወሩ የመጀመሪያ ቀን ተሰበሰቡ።

መሪዎች ወንዶችንና ሴቶችን ለዚህ የተለየ ስብሰባ የጠሩት የእግዚአብሔርን ህግ በማንበብ ስለ አምላካቸው እና ስለታሪካቸው እንዲማሩ ዕድል ለመስጠት ነበር። ህዝቡ የሙሴን ህግ መጽሐፍ በፊታቸው አምጥቶ እንዲያነብ ዕዝራን ጋበዙት። ለዚህ ተግባር የሚውልምመድረክ አዘጋጁ። ይህ መሪዎቹ በህዝቡ ላይ የጫኑት ግዳጅ አልነበረም። በተቃራኒው ዕዝራን መጽሐፉን እንዲያመጣ የነገሩት “ህዝቡ” ነበሩ። ምናልባትም ዕዝራ ለህዝቡ ያነበበው በሲና ተራራ የተሰጠውን ህግ የያዘውን የሙሴን መጽሐፍ ይሆናል።

ዘዳ. 31፡9-13ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በዚህ ቦታ ለህዝቡ የተናገረው ምን ነበር? እኛስ ከዚህ ምን ትምሀርት ልንወስድ እንችላለን?በዘዳ 31፡9-13 ላይ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች በዳስ በዓል ጊዜ በአንድነት ሰብስበው የህጉን መጽሐፍ እንዲያነቡ ነገራቸው። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንም ይጠቅሳል፤ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ልጆች፤ በቤታቸው የሚኖር መፃተኛም ጭምር! በነህምያ 8፡1 ላይ ህዝቡ “እንደ አንድ ሰው” ተሰበሰቡ ይላል።

በአማኞች መካከል ሊኖር ስለሚገባው አንድነት ይህ ምን ያስተምረናል?

ጥቅምት 24
Nov 04

ህጉን ማንበብና መስማት


ዕዝራ በህዝቡ ፊት ይነበብ ዘንድ “ህጉን አመጣው”። ምን ነበር ያነበበላቸው? ግማሽ ቀን ሙሉ አስርቱ ትዕዛዛትን እየደጋገመ ይሆን? የህጉ መጽሐፍ የሚለው አገላለፅ ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያለውን በዕብራይስጡ ቶራ ተብሎ የሚጠራውን አምስቱን የሙሴ መፃህፍት ይወክላል። ስለዚህ “ህጉ” ተብሎ የተጠቀሰው ከተነበበው የተወሰነውን ክፍል ሲሆን “መመሪያ” ተብሎ ቢተረጎም በሙላት የሚገልፀው ይሆናል። ግባችንን ሳንስት መሄድ በሚገባን መንገድ እንድንጓዝ የሚያስችሉን የእግዚአብሔር መመሪያዎች ናቸው።

ዕዝራ ሲያነብ ሳለ ህዝቡ ከፍጥረት አንስቶ እስከ ኢያሱ ዘመን ድረስ ያለውን ታሪካቸውን አዳመጡ። በታሪኮች፣ በመዝሙራት፣ በግጥሞች፣ በበረከቶችና በህግጋቱ አማካኝነት እግዚአብሔርን ለመከተል የነበራቸውን ተግዳሮት እና እግዚአብሔር ለእነርሱ የነበረውን ታማኝነት አስታወሱ። ቶራው “ህጉን” ቢጨምርም ከህጉ ባለፈ ብዙ ነገሮችንም ይዟል። የእግዚአብሔርን ህዝብ ታሪክ እንዲሁም የተገለጠውን የእግዚአብሔር ምሪት አቅፎ ይይዛል።በውጤቱም ለማህበረሰቡ ማንነትንና መሠረትን ሰጥቷቸዋል።

ነህምያ 8፡3፣ ዘዳግም4፡1፣ 6፡3-4፣ ኢያሱ 1፡9፣ መዝሙር 1፡2፣ ምሳሌ 19፡20፣ ሕዝቅኤል 37፡4 እና ማቴ.17፡5ን ያንብቡ።ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ምን ይነግሩናል?ህዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፍላጎት ያደረባቸው ዕዝራ ከ13 ዓመት በፊት ወደኢየሩሳሌም ከመጣ አንስቶ ቃሉን እያነበበና እያስተማረ ስለነበር ይሆናል። ለእግዚአብሔር ሥራ ራሱን የሰጠ እና ለውጥ ለማምጣት ቆርጦ የተነሳ ሰው ነበር። ከዕዝራ አንደበት የሰሙት የእግዚአብሔር ቃል በተደጋጋሚ ሲሰሙት ህያው እንደሆነ ህዝቡ አስተዋሉ። ስለሆነም ከእግዚአብሄር ለመስማት ይፈልጉ ስለነበር ለመስማትና ሰምቶም ለማስተዋል ውሳኔ አደረጉ። በዚህ አጋጣሚም ወደ ቶራው የቀረቡት በአክብሮትና ለመማር ፈቃደኛ በሆነ መንፈስ ነበር። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ጠልቆ መግባት እግዚአብሔርን በህይወታችን የበለጠ እንድንፈልገው ያደርገናል።

ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለዎት ግንኙነት እንዴት ነው? እንደምታምኑት በአንደበታችሁ ብትናገሩም በኑሮአችሁ ውስጥ እንዴት ይገለፃል? የሚያስተምረውን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ናችሁ? መጽሐፍ ቅዱስን ባትታዘዙ በህይወታችሁ ምን ለውጥ ይኖር ነበር?

ጥቅምት 25
Nov 05

ማንበብና ቃሉን መተርጎም


ነህምያ 8፡4-8ን ያንብቡ። ህጉ የተነበበው እንዴት ነበር?በንባቡ ጊዜ ከዕዝራ አጠገብ በሁለት ረድፍ የቆሙ 26 ሰዎች ነበሩ። የመጀመሪያዎቹ 13ቱ (ነህምያ 8፡4) የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ሲያግዙ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ህዝቡ ንባቡን እንዲያስተውሉ የሚያግዙ ነበሩ። በአደባባዩ ውስጥ ይህ ስርዓት እንዴት እንደሚተገበር መረጃ የለንም። ነገር ግን በማንበቡ በኩል የሚያግዙት ሰዎች ምናልባት ቶራውን በመሸከም (የዕብራይስጥ የብራና መዛግብት ከባድና የሚጠቀለሉ ነበሩ) እንዲሁም እየተቀያየሩ በማንበብ ሚናቸውን ይወጡ ይሆናል። ከንጋት እስከ ቀትር ድረስ ያነቡ ስለነበር በአደባባዩ የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ለመድረስ መንገድ ቀይሰው ይሆናል።

“ህዝቡ የሚነበበውን እንዲያስተውሉ ያደርጉ ነበር” የሚለው ሀረግ ቃሉን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ መተርጎምን ወይም ትርጉምን የማብራራት ሂደትን ሊወክል ይችላል። በዚህ ምሳሌ ምናልባት ሁለቱንም ይገልፃል። ህዝቡ ብዙ ዓመታት ከኖሩበት ከባቢሎን መመለሳቸው ሲሆን በዚያም ይነገር የነበረው የአረማይክ ቋንቋ ነበር። ስለዚህም የዕብራይስጥ ንባብን ለማስተዋል ለብዙዎቹ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ቀላል አይሆንም። በተጨማሪም አንባቢያን ሰለ መጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ከሚሰጡ መጽሐፍትም ሊጠቀሙ ይችላሉ። ስብከት እና ማብራሪያ ቃሉ ህያው እንዲሆን በማድረግ አድማጮች በህይወታቸው እንዲተገብሩት ይረዳል።

የሐዋርያት ሥራ 8፡26-28ን ያንብቡ። በዚህ ምዕራፍ በኢየሩሳሌም ይካሄድ ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ምን ሂደት እናገኛለን? ከዚህ ምን እንማራለን? እንደ ፕሮቴስታንትነታችን እያንዳንዱ ግለሰብ የእግዚአብሔርን ቃል ለራሱ ማወቅ እንዳለበት እንዲሁም የትኛውም ስልጣን ያለው ሌላ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ የሚሰጠውን ማብራሪያ በጭፍን መቀበል እንደሌለብን እንረዳለን። ሆኖም የቃሉን ትርጉም በሚገልጡ ሰዎች ያልተባረከ ማን ይሆን? እያንዳንዳችን የምናምነውን በትክክል ማወቅ ቢገባንም ከሌሎች አስተማሪዎች በኩል ከሚመጣ ብርሀን ተጠቃሚ አንሆንም ማለት ግን አይደለም።

ጥቅምት 26
Nov 06

የሕዝቡ ምላሽ


ዕዝራ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የዕብራይስጡን ቶራ ሲከፍት ህዝቡ ተነስተው ቆሙ። ዕዝራ ማንበቡን ከመጀመሩ በፊት እግዚአብሔርን ይባርክ ነበር። ካነበበ በኋላም ሕዝቡ እጃቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው “አሜን አሜን” እያሉ መለሱ(ነህ. 8፡6)። ከዚያም በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።

ነህምያ 8፡9-12ን ያንብቡ። መሪዎቹ እንዳያለቅሱ” የነገሩዋቸው ለምን ነበር? ህዝቡ “እንዳያዝኑ እና“ሕዝቡ ከባቢሎን በተመለሱባቸው በኋለኞቹ ዘመናት የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብ ስለ መተላለፋቸው አለቀሱ። “አታልቅሱ…ሂዱ፤ የሰባውንም ብሉ፤ ጣፋጩንም ጠጡ፤ላልተዘጋጀላቸውም ዕድል ፈንታቸውን ስደዱ፤ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችሁ ነውና” (ነህ. 8፡9-10)” የሚሉ የፀጋ ቃላት ተነገሩ።”Ellen G White, The Ministry of Healing, p.281

ሕዝቡ የእግዚአብሄርን ቃል ባደመጡ ጊዜ ኃጢዓተኝነታቸው ዘልቆ ስለተሰማቸው ማልቀስ ጀመሩ። እግዚአብሔር ራሱን ሲገልጥልን እና የፍቅሩን፣ የመልካምነቱን፣ የምህረቱን እና የታማኝነቱን ሙላት ማስተዋል ስንጀመር የእኛ ጉድለቶችና ወድቀቶች በፊታችን ይመጣሉ። የእግዚአብሔርን ቅድስና በቃሉ መነፅር መመልከት የራሳችንን አስከፊ ሁኔታ በአዲስ ብርሀን እንድናየው ያደርጋል። የእስራኤል ሕዝብ ይህንን ሲያስተውሉ በለቅሶ እና በሀዘን ቢሞሉም “የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላቸው” ስለሆነ በሀዘን መቀመጥ አልነበረባቸውም። በሌላ አነጋገር ምንም እንኳን በውድቀት ውስጥ ቢሆኑም በእግዚአብሔር ሀይል መታመን ይችሉ ነበር።

ቀኑ ልዩ ቀን፣ ቅዱስ ቀን የመለከት በዓል ሲሆን አጫጭር የመለከት ድምፆች ለእግዚአብሔር የፍርድ ቀን(በዚሁ ወር 10ኛው ቀን የሚከበረው የስርየት ቀን) “የልብ” ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያሳስቡበት ነበር። የመለከቱ ድምፅ በእግዚአብሄር ፊት ቆመው እንዲናዘዙ ያመለክታል። ቀኑ ህዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የተዘጋጀ በመሆኑ ማልቀሳቸውና ማዘናቸው የሚጠበቅ ነው። መሪዎቻቸው ግን አንዴ ከተናዘዙ በኋላ እግዚአብሔር እንደሰማቸው እና በእግዚአብሔር ይቅርታ የሚደሰቱበት ጊዜ እንደሆነ አስታወሷቸው።

ለኃጢዓት ችግር መፍትሄ የክርስቶስ መሰቀል ብቻ መሆኑ ስለ ኃጢዓት አስከፊነት ምን ይነግረናል? ምን ተስፋስ ይሰጠናል?

ጥቅምት 27
Nov 07

የእግዚአብሔር ደስታ


“የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችሁ ነውና”(ነህ. 8፡10) የሚለው ጥቅስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ደስ እንድንሰኝ እና ህይወትን እንድናጣጥም እንደሆነ ያስታውሰናል። በጣም አስፈላጊ የሆነው ነጥብ ይህ ደስታ ማንኛውም ዓይነት ደስታ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከማወቅ እና ፍቅሩን ከመረዳት የሚመነጭ ደስታ ነው። በእግዚአብሔር መልካምነት ሀሴት ማድረግ እንዲሁም ለእኛ በሚያደርግልን መደሰትን ዘወትር ልንለማመደው ይገባል። በተጨማሪም በእግዚአብሔር ደስ መሰኘት በፊታችን የሚመጡ ግድድሮሾችን እንድንጋፈጥ ኃይል ይሰጠናል።

ነህምያ 8፡13-18ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ምን ተከሰተ? በጊዜው ስለነበሩት ህዝብ እና መሪዎቻቸው ምን ይነግረናል?በቀጣዩ ቀን የሕዝቡ መሪዎች ከእግዚአብሔር መፅሀፍ የበለጠ ለመማር ወደ ዕዝራ መጡ። በመሪዎች ዘንድ የነበረው ተነሳሽነት ህዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመምራት ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል። እነርሱ እግዚአብሔርን ካልፈለጉ እና ከእርሱም ዕውቀትን ካላገኙ ህዝቡን በትክክለኛው ጎዳና መምራት እንደማይችሉ አስተውለው ነበር።

ዘሌዋውያን 23፡39-43ን ያንብቡ። እስራኤላውያን እንዲፈፅሙት የተነገራቸው ምን ነበር? ለምን?በነህምያ 8፡15 ላይ ያለው ጥቅስ ተግባራቸውን “እንደተፃፈው” ይፈፅሙ እንደነበር መጥቀሱን ልብ ይበሉ። ብዙ አስርት ዓመታት በባርነት ውስጥ የአለመታዘዝን ውጤት ስለተማሩ የእግዚአብሔርን ቃል ምን ያህል ለመታዘዝ እንደሚፈልጉ እንረዳለን። በዘሌዋውያን ላይ በዓሉን እንዲያከብሩ እና “በእግዚአብሔር በአምላካቸው ፊት ሰባት ቀን ደስ እንዲሰኙ” ተነግሮአቸውም ነበር። በሌላ አነጋገር የእግዚብሔርን ምህረት፣ ፀጋና ማዳኑን ባስታወሱ ጊዜ እግዚአብሔር ለእነርሱ ስላደረገው ነገር ደስ መሰኘት ይገባቸው ነበር።

የእስራኤል በዓላት በሙሉ በሚወክሉት በኢየሱስ ሰለተሰጠን ነገር አስቡ። በአስቸጋሪ እና በስቃይ ጊዜያት እንኳን በጌታ ደስ መሰኘትን እንዴት ልንማር እንችላለን? ይልቁንም በእነዚህ ጊዜያት መደሰት ያለብን ለምንድን ነው?

ጥቅምት 28
Nov 08


ተጨማሪ ሀሳብ


Ellen G. White `Instructed in the Law of God,` pp.661-668, in Prophets and Kings. “አሁን በተስፋው ላይ ያላቸውን እምነት ሊያሳዩ ይገባል። እግዚአብሔር ንስሐቸውን ተቀብሏል፤ በኃጢዓት ይቅርታ እርግጠኝነት እና ዳግም የእግዚአብሔር ፊት በእነርሱ ላይ በመሆኑ ደስ ሊሰኙ ያስፈልጋል። . . . እውነተኛ የሆነ ንስሀ በህይወት ውስጥ ዘላቂ ደስታን ያጎናፅፋል።

አንድ ሀጢዓተኛ እራሱን ለመንፈስ ቅዱስ ተፅእኖ አሳልፎ ሲሰጥ ልብን ከሚመረምረው ከታላቁ እግዚአብሔር ቅድስና ጋር የእራሱን ጥፋተኝነት እና በኃጢዓት መቆሸሽ አነፃፅሮ ይመለከታል። እንደ ህግ ተላላፊ የተኮነነ መሆኑን ይረዳል። ነገር ግን ከዚህ የተነሳ በሀዘን መዋጥ የለበትም። ምክንያቱም እርግጥ የሆነ ይቅርታን አግኝቷል።

ኃጢዓቱን ይቅር ስለመባሉ እንዲሁም ስለ ይቅር ባይ ሰማያዊ አባቱ ደስ ሊሰኝ ይገባል። ንስሐ የገባን ኃጢዓተኛ ቁስል ማከም፣ ከኃጢዓት ማንፃትና በፅድቅ ልብሽ መሸፈን የእግዚአብሔር ክብር ነው።” Ellen G. White, Prophets and Kings, P.668


የመወያያ ጥያቄዎች
1.“የእግዚአብሔርን ደስታ” (ነህ. 8፡10) ኃይላችሁ አድርጋችሁ የምትለማመዱት በምን ዓይነት ሁኔታዎች ነው? ይህም ማለት የእግዚአብሔርን ኃይል እና ይቅርታ በህይወታችን ለመለማመድ ማድረግ የሚገባን ድርጊት ይኖር ይሆን? መልስዎ አዎን ከሆነ ምንድን ነው?

2.ለኃጢዓታችን በማዘን እና በጌታ በመደሰት መካከል ትክክለኛውን ሚዛን እንዴት እናገኛለን?እርስ በእርሳቸው የተቃረኑ አይደለምን? ህግ እና ወንጌል በአንድነት ለዚህ መልስ እንዴት ይሆኑናል?(ሮሜ 3፡1924ን ይመልከቱ)

3.በነህምያ 8፡10 ላይ ነህምያ “ሂዱ፤የሰባውንም ብሉ፤ጣፋጩንም ጠጡ፤ ዕድል ፈንታ ለሌላቸውም ስደዱ፤ የእግዚአብሔርም ደስታ ሀይላችሁ ነውና አትዘኑ” ያለውን ያንብቡ። “ለጌታ የተቀደሰ ቀን ስለሆነ” የሰባውን መብላት፣ ጣፋጩን መጠጣት እና ዕድል ፈንታ ለሌለውም መስደድ አለብን? በጌታ ደስ ስለምንሰኝበት መንገድ ምን ያስተምረናል? “የተቀደሰ” የሚለው ቃል በዚህ ዐውድ ምን ትርጉም አለው?