ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ጥቅምት 15-21

5ኛ ትምህርት

Oct 26 - Nov 1
የሕጉን መንፈስ መተላለፍሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ነህ. 5:1–5፤ ዘፀ. 21:2–7፤ ሚኪ. 6:8፤ ነህ. 5:7–12፤ ዘዳ. 23:21–23፤ ነህ 5:14–19።


መታሰቢያ ጥቅስ “‘እርሻቸውን፣ የወይንና የወይራ ዘይት ተክል ቦታቸውንና ቤታቸውን በቶሎ መልሱላቸው፤ እንዲሁም የምታስከፍሏቸውን የገንዘቡን፣ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና ዘይት አንድ መቶኛ ዐራጣ መልሱላቸው።’” (ነህምያ 5:11፣ አ.መ.ት.)

እ ስከዛሬ ድረስ እኛ ሰዎች ስለ ሀብት፣ ስለ ድህነት፣ እንዲሁም በሀብታምና በደሃው መካከል ስላለው ልዩነት እና በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሊደረግ ይገባል ከሚል ጥያቄ ጋር እንሟገታለን። በእርግጥ ኢየሱስ “ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤” (ማቴ. 26:11፣ አ.መ.ት ) ብሏል፣ ያ ግን እነርሱን ላለመርዳት ሰበብ ሊሆን አይችልም። በተቃራኒው ቃሉ የራሳችንን ኃላፊነት እንድንወጣ ያዘናል። ይህን ማድረግ ከተሳነን ደግሞ እራሳችንን ክርስቲያን ብሎ መጥራት እንኳን ይቸግረናል።

ኢየሩሳሌምን ለመገንባት ከስደት የተመለሱት ምርኮኞች በችግሮችና በመከራዎች መካከል እንኳን ሆነው ይኸው ጉዳይ ብቅ ማለቱ ያስገርማል፤ ጉዳዩ ደግሞ ድህነትና የድሃው ጉዳይ አልነበረም፣ ነገር ግን አጠያያቂ የነበረው የሃብታሙ ድሃውን መጨቆን ነበር። ይህ ችግር በግዞት ከመወሰዳቸው በፊት ነበረ፤ እናም አሁንም ከስደት ወደ ምድራቸው ሲመለሱም እንደገና አቆጠቆጠ።

በዚህ ሳምንት ይህ ዘመን ያስቆጠረ ርዕሰ ጉዳይ በሌላ አጋጣሚ እንዴት ተከስቶ እንደነበርና ነህምያም ይህን ለመጋፈጥ እንዴት እንደሰራ እንመለከታለን። ይህንንም ስንዳስስ፣ የጭቆና ግፉን የበለጠ አስከፊ እንዲሆን ያደረገው “የህጉ(ን) ፊደል” በማስፈፀም እሳቤ ውስጥ መሆኑ ነበር፣ ይህም ትዕዛዛትና ሕጎች ለመዳረሻው ምክንያቶች እንደሆኑ እንጂ በራሳቸው መጨረሻ መዳረሻ እንደሆኑ እንዳናስብ ልንጠነቀቅ እንደሚገባ ትልቅ ምሳሌን ይተውልናል፤ ይህም መዳረሻ የኢየሱስን ባህሪ ማንጸባረቅ ነው።

የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 22 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጥቅምት 16
Oct 27

የህዝቡ ጩኸት


ነህምያ 5፡1-5ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ላይ ምን እየሆነ ነው ያለው? ህዝቡ እየጨኹ ያሉት ስለ ምንድነው?የአይሁድ ማህበረሰብ በነህምያ መሪነት ስር ከውጭ በሚመጡ ግፊቶች ላይ አንድ የሆኑ ይመስሉ ነበር። ሆኖም ግን ስደትን ለመቃወም እና ከውጭ ጥቃቶች እራሳቸውን ለመጠበቅ በሕዝቡ መሐል ሁሉም ነገር ቀና አልነበረም። በጠላት ላይ ከላይ የሚታይ የተጠናከረና ያበረ ጥላቻ ቢኖርም፣ ማህበረሰቡ ግን በውስጡ የተፈረካከሰ ነበር።

መሪዎቹ እና ሀብታሞቹ ለራሳቸው ለሚያጋብሱት ነገር ደሃውን ይጠቀሙበት ነበር፣ ሁኔታው እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ቤተሰቦች እረፍት ለማግኘት ቃተቱ። አንዳንድ ቤተሰቦች እንዳሉት ልጆቻቸውን እንኳን የሚያቀምሷቸው ምግብ በእጃቸው አልነበረም፤ ሌሎቹ ቤተሰቦች ደግሞ በርሃብ ምክንያት ያላቸውን ንብረት(ርስት) ሁሉ በዕዳ ስላስያዙና ምንም ስላልተረፋቸው ጩኸታቸውን ያሰሙ ነበር፤ የቀሩትም ደግሞ ለፋርስ ግብርን ለመክፈል ገንዘብ መበደር ስለሚኖርባቸው በስቃይ ያቃስቱ ነበር፣ ልጆቻቸውም ለባርነት ተሰጥተው ነበር።

በድህነት ያሉ ቤተሰቦች የጎረቤቶቻቸውን ደጅ ለእርዳታ እንዲጠኑ በማድረግ ችግሩን የበለጠ የከፋ እንዲሆን ያደረጉት ረሃብና የግብር ክፍያዎቹ ነበሩ። የፋርስ መንግስት በዓመት 350 ዲናሮችን ለግብር ክፍያ ከይሁዳ ግዛት ይጠይቅ ነበር። (በነህምያ 5፡ 1-5 ላይ Andrews Study Bible ገጽ 598 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ይመልከቱ።) በህግ የተደነገገውን አስገዳጅ የታክስ ምጣኔ ሰው መክፈል የሚያቅተው ከሆነ፣ ያ ቤተሰብ በመጀመሪያ ያለውን ንብረት(ርስት) በመያዣነት ይሰጣል ወይም ገንዘብ ይበደራል። እናም በሚቀጥለው ዓመት ገንዘቡን ማግኘት የማይችል ከሆነ ደግሞ ላለበት ዕዳ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርበታል። ቀጣዩ አማራጭ ስላተከፈለው ዕዳ ሲባል ባሪያ መሆን ነበር። ቀደም ብለው የራሳቸውን መሬት(ርስት) አጥተዋል፤ አሁን ደግሞ ከቤተሰቡ መካከል አንድ ሰው ምን አልባትም ከልጆቹ ውስጥ እዳውን ለመክፈል የአበዳሪው አገልጋይ መሆን ይኖርበታል።

እኛው እራሳችን በወሰንናቸው ውሳኔዎች ምክንያት ድርጊቶቻችን ባመጡት ጦስ እራሳችንን ችግር ውስጥ የምናገኝባቸው ጊዜቶች ይኖራሉ፤ አንዳንድ ጊዜያት ደግሞ ያለጥፋታችን በህመም ወይም በገንዘብ ቀውስ ውስጥ እንወድቃለን። ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ የመንግስት ህጎች የሰዎችን ሕይወት ሲጎዱ ወደከፋም ድህነት ሲጨምሩ የሚያሳይ ነው። በዚህም የድህነት አዘቅት ውስጥ በመያዛቸው ምክንያት የሚያንሰራሩበት መንገድ እንኳን አልነበረም።

በዚያን ጊዜም ቢሆን ልክ እንደዛሬው ሰዎች በኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ ሲቃትቱ ማየት ያስገርማል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ትኩረት መስጠቱ እኛ ከዚህ እውነታ ምን አይነት መልዕክትን እንድንወስድ በማሰብ ነው?

ጥቅምት 17
Oct 28

ከሕጉ መንፈስ በተቃራኒ


ነህምያ 5፡6-8ን ያንብቡ (በተጨማሪም ዘፀ 21፡2-7 ይምለከቱ)። ነህምያ በቁጣ ምላሽ የሰጠው ለምን ነበር?ዛሬ ባለንነበት ዘመን ለማስተዋል ቢከብደንም፣ በቀደመው ዘመን የነበረው ዓለም ባርነትን እንደ ባህላዊ ልማድ አድርጎ ተቀብሎት ነበር። ወላጅ አባት/እናት ባሪያ ሆነዋል ወይም ልጃቸውን ለባርነት ሸጠዋል። ከማህበራዊ ልማድ እና ከሕግ አንፃርም ቢሆን ወላጆች የራሳቸውን ወንድና ሴት ልጆች የመሸጥ መብት ነበራቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር ነጻነትን ሰጪ አምላክ በመሆኑ አበዳሪዎች በስራቸው ያሉ ባሮችን በየሰባት አመቱ ነጻነታቸውን በመስጠት እንዲለቋቸው የሚያዝ ህግ ሰጣቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰዎችን ለዘላለም ባርያ ከመሆን በማላቀቅ በነፃነት እንዲኖሩ ያለውን ፍላጎት ገለፀ።

ማበደር በሕግ ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ወለድን ማስከፈል ግን የተከለከለ ነበር (በአራጣ ማበደርን የሚቃወሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕጎችን በዘፀ. 22:25–27፤ ዘሌዋ. 25:36፣37 ፤ ዘዳ. 23:19ና 20ን ይመልከቱ) ወለድም እንኳን ቢኖረው አበዳሪዎች የሚያስከፍሉት የወለድ መጠን በአካባቢው ከሚኖሩ ሕዝቦች የወለድ ክፍያ አንፃር አነስተኛ ነበር። እንዲከፍሉ የሚጠየቁት በየወሩ አንድ መቶኛውን (1%) ነበር።

በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉ የሜሶፖታምያውያን ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት በዓመት ለብር(silver) ሃምሳ በመቶ (50%) እና ለጥራጥሬ መቶ በመቶ (100%) የወለድ ምጣኔ ይጠየቅ ነበር። በሜሶፖታሚያ ይከፈል ከነበረው አመታዊ የወለድ ምጣኔ ሲወዳደደር በዓመት የአስራ ሁለት በመቶው (12%) ወለድ አነስተኛ ነበር።

ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚገልፀው፣ አበዳሪዎቹ ያደረጉት ትክክል ያልሆነ ነገር ቢኖር ወለድ ማስከፈላቸው ነበር (ነህ. 5፡10)፣ የሚያስገርመው፣ ሕዝቡ በቅሬታቸው ላይ እንኳን ይህንን ሲያነሱት አይታይም፣ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በማህበራዊ ሕጎች ላይና በሕጉ ትዕዛዛት ላይ ተካተው ስለነበረ ነው። ታዲያ ነህምያ “በኃይል የተቆጣው” ለምን ነበር ? በሚገርም ሁኔታ በጉዳዩ ላይ ወዲያው እርምጃ አልወሰደም፤ ነገር ግን ጉዳዩን በጥልቀት ለማሰብ ጊዜ ወሰደ።

ነህምያ ጉዳዩን ትኩረት በመስጠት መከታተሉ እጅግ የሚያስመሰግነው ነው። ምንም አንኳን ነገሩ ሲታይ ሕጉን የማይጥስና በማህበረሰቡ ቅቡል ቢሆንም፣ ደግሞም በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋር ሲወዳደርም “መልካም” ቢባልም፣ ነህምያ የቀረበውን ቅሬታ ችላ አላለውም ነበር። በቀረበው ቅሬታ ላይ ተጥሶ የነበረው የሕጉ መንፈስ ነበር። በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በእርሱ የመደጋገፍ ኃላፊነት ነበረበት። እግዚአብሔር ከተጨቆነው እና ከችግረኛው ጎን ነው፣ እናም በድሃው ላይ የሚፈጸሙትን ክፋቶችና ግፎች ለማሳሰብ ነብያቱን ይልካል። ባለማስተዋልም ቢሆን የሕጉን ፊደል ስንከተል የህጉን መንፈስ የምንጥስባቸው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? (ሚኪ. 6፡8 ይመልክቱ)

ጥቅምት 18
Oct 29

ነህምያ እርምጃ ወሰደ


መገመት እንደምንችለው –“ከገዛ አገራችሁ ሰዎች ላይ እንዴት ዐራጣ ትበላላችሁ” (ነህ. 5:7) የሚለው ለመኳንንቱና ለሹማምንቱ የተነረገው ግሳጼ የተፈለጉትን ውጤቶች ይዞ መምጣት አልቻለም። እናም ነህምያ እዚያ ጋ አላቆመም፣ ነገር ግን በመካከላቸው በጭቆና ስለሚኖሩት መሟገቱን ቀጠለ። ለመኳንንቱና ለሹማምንቱ ለማስረዳት ጥረት አድርጌአለሁ ነገር ግን ጉዳዩን ማስተካከል አልቻሉም፣ በማለት ነገሩን መተው ይችል ነበር። ደግሞም ይጋፈጥ የነበረው በምድሪቱ ከነበሩ ሃብታምና ተሰሚነት ካላቸው ጋር ነበር። ምንም እንኳን በዚህ የመፍትሄ ፍለጋ ውስጥ ብዙ ጠላቶችን ቢያፈራም ለችግሩ መፍትሔ ተገኝቶ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ አልረካም።

ነህምያ 5:7–12ን ያንብቡ። እየሆነ ስላለው ነገር የነህምያ ሙግቶች ምን ነበሩ? ክፋትን እንዲያርሙ ሕዝቡን ለማሳመን የተጠቀመው ምንን ነበር?ነህምያ ታላቅ ስብሰባ ጠራ፤ ይህን ጉዳይ ለመመልከት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በአንድነት መጡ። በዚህ ሁኔታ ጉዳዩ እንዲታይ ያሰበበት ምክንያት፣ ህዝቡ ሁሉ ሲገኙ ምናልባት ግፋቸውን ከዚህ በኋላ ላለመቀጠል መሪዎቹ ሀፍረት እንዲሁም ፍርሃት ይሰማቸው ይሆናል በማለት ነበር።

የነህምያ መነሻ ሃሳብ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በባርነት ላይ ነበር። ነህምያ ከጠራቸው ውስጥ ብዙዎቹ አይሁዶች በሌላ ሀገር ዜጎች ስር ባሪያ ሆነው ያገለግሉ የነበሩ አይሁዶችን ነጻነት ገዝተው አውጥተዋቸው ነበር። እናም አሁን፣ የራሳቸውን ወገን መግዛትና መሸጥ ሊቀበሉት የሚችሉት እንደሆነ መኳንንቱንና ሹማምንቱን ጠየቃቸው። ለራሳቸው ለእስራኤላውያንስ አይሁዳውያንን ገዝተው ነፃ ካወጡ በኋላ በመጨረሻ ለራሳቸው ወገን ባሮች የሚሆኑ ከሆነ ትርጉም ይሰጣቸው ይሆን? መሪዎቹም የቀረበው ማሳመኛ ትክክለኛ መሆኑን ስለተመለከቱ ምንም ምላሽ አላቀረቡም፤ ነህምያም ቀጠለ። “ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን?” (ነህ. 5:9) ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም፤ ነህምያም እራሱ ገንዘብና እህልን ለሕዝቡ እያበደረ እንደነበር አመነ። “ይህን ወለድ እንተውላቸው” (ነህ. 5:10፣አ.መ.ት.) በማለት በዕብራዊ ባልንጀራ ላይ የሚፈጸም ድርጊትን ሕጉ እንደሚከለከል በማረጋገጥ እና በእርሱም አመራር ስር ሕዝቡ እርስ በእርሱ መተሳሰብን ማሳየት እንዳለበት ተናገረ። በሚያስደንቅም ሁኔታ፣ ምላሹ ሙሉ ለሙሉ መስማማትን የሚያሳይ ምላሽ ነበር። መሪዎቹ ለወገኖቻቸው ሁሉንም ነገር ለማስተካከል ተስማሙ።

አንድ ሰው ላይ ክፉ አድርገው ያውቃሉ? ብዞዎቻችን፣ ታማኝ ከሆንን፣ መልሳችን “አዎ” የሚለው ይሆናል ። በሚችሉት መጠን የበደሉትን ሰው ለመካስ፣ አሁን እንኳን እንዳይጥሩ የሚያደርግዎት ምንድነው?

ጥቅምት 19
Oct 30

መሐላ


ነህ. 5:12፣13ን ያንብቡ። ነህምያ በስምምነቱ መሠረት ከነርሱ የሚጠበቀውን በማይወጡት ላይ ለምን እርግማንን አወጀ?ምንም እንኳን መሪዎቹ የወረሱትን ለመመለስና ለባለቤቱ ለመስጠት ቢስማሙም፣ ነህምያ በቃላቸው ብቻ አምኖ ሊቀባለቸው አልወደደም። የበለጠን ማረጋገጫ ፈለገ፤ እናም በካህናቱ ፊት መሓላ እንዲምሉ አደረጋቸው። ይህም ድርጊት ምን አልባት ቆየት ብሎ ስምምነቱን ለማየት ቢፈልግ ቃለ ጉባኤው ሕጋዊ ተገቢነት እንዲኖረው ያደርጋል።

ታዲያ ለምንድነው እርግማንን መጨመር ያስፈለገው? ነህምያ ተምሳሌታዊ በሆነ ድርጊት የልብሱን ዘርፎች በውስጣቸው አንድ ነገር እንደያዙ አድርጎ በመሰብሰብ እና የማጣትን ነገር እንዲያሳይ ደግሞ መልሶ በማራገፍ ተምሳሌታዊ የሆነን ድርጊት አሳየ። እናም፣ ከዚህ መሓላ በተቃራኒ የሚሄዱ ሁሉንም ነገር እንደዚሁ ያጣሉ ማለት ነው። ለሕጎች ወይም ስርዓቶች ክብደት ለመስጠት እርግማን መጨመር የተለመደ ነበር። ሰዎችም ሕግን ከመጣስ ጋር በተያያዘ እርግማን የተቀመጠ ከሆነ ሕጉን ላለመታዘዝ ያላቸው ድፍረት አነስ ያለ ይሆን ነበር። ነህምያም የተነሳው ጉዳይ እጅግ አስፈላጊ እንደነበር በእርግጥም ስለተሰማው የነገሩን ስኬታማ የመሆን እድል ከፍ ለማድረግ ጠንከር ያለን ድርጊት መፈጸም ነበረበት።

ከዚህ በታች የተቀመጡት በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ጥቅሶች መሓላ በህዝቡ መካከል የተቀደሰ ነገር እንደነበር ምን ይነግሩናል? (ዘኁ. 30:2፤ ዘዳ. 23:21–23፤ መክ. 5:4፣5፤ ዘሌዋ. 19:12፤ ዘፍ. 26:31)።በመጨረሻም፣ ንግግር እግዚአብሔር ለሰብዐዊ ዘር ያጎናጸፈው ትልቅ ተጽዕኖ ያለው ስጦታ ነው፤ እንስሳት ካላቸው ተፈጥሮ ይልቅ ፍጹም ልዩነትን የሚፈጥር ሆኖም ይቀመጣል። እናም በምናወጣቸው ቃላት ውስጥ ኃይል አለ፣ እንዳውም የሕይወትና የሞት ኃይል። ስለሆነም ለምንናገረው ነገር፣ ልንከውነው ለምንገባው ቃል፣ እንዲሁም እንፈጽማቸዋለን ብለን ከአንደበታችን ለምናወጣቸው ቃላት ጥንቃቄን ልናደርግ ያስፈልጋል።

የምንናገራቸው ቃላትም ከድርጊቶቻችን ጋር የተስማሙ ሊሆኑ ይገባል። ቃላቶቻቸው ክርስቲያናዊ፣ ድርጊታቸው ግን የተገላቢጦሽ በሆኑ ሰዎች ምክንያት ምን ያህል ሰዎች ለክርስትና ጀርባቸውን ሰጥተው ይሆን? እስኪ ከአንደበታችሁ የሚወጡ ቃላት በሌሎች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያሰላስሉ። ምን መናገር እንዳለብን፣ መቼ መናገር እንዳለብን ፣ እና እንዴት መናገር እንዳለብን እጅግ ልንጠነቀቅ እንደሚገባ ልንማር የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 20
Oct 31

የነህምያ ምሳሌነት


ነህምያ 5:14–19ን ያንብቡ። ነህምያ ከሕዝቡ “ለአለቃ የተመደቡለትን (ክፍያዎች)” (ነህ. 5:18) ላለመቀበሉ ምን አይነት ማሳመኛዎችን ሰጠ?ነህምያ በእነዚህ ቁጥሮች ላይ የተገለፁትን ኃሳቦች ይሁዳን ለ12 ዓመታት ካስተዳደረ በኋላ ወደ ንጉስ አርጤክስስ ቤተ-መንግስት ተመልሶ ጽፏቸው ሊሆን ይችላል። አገረ ገዢዎች ከሚያስገብሩት ማህበረሰብ ግብርን እንዲቀበሉ ስልጣን ያላቸው ቢሆንም ነህምያ ይህንን መብት ጠይቆ አያውቅም፣ ይልቁንም የራሱን ወጪ ይችል የነበረው በራሱ ነበር። የራሱን ወጭ በራሱ መክፈል ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ለእርሱ ቤተሰብ እንዲሁም በእርሱ ዙሪያ ያሉት ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ከእርሱ ያገኙ ነበር።

ዘሩባቤል፣ በስም የምናውቀው የመጀመሪያው አገረ ገዥ ነው። ነህምያ “የቀደሙት መሪዎች” ሲል ምናልባትም በዘሩባቤልና በእርሱ መካከል አስተዳድረው ያለፉትን አገረ ገዦች መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። እናም የአስተዳዳር ዘመኑን ሲጨርስ ብዙ ገንዘብን ከራሱ ወጪ አድርጎ ሊሆን ይችላል። የተቀመጠበት የክብር ቦታ ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው ብልጽግና ይልቅ ምናልባትም ሃብቱን አጥቷል። ነህምያ ባለፀጋ ነበር፤ ለዛም ነው ለብዙዎች የዕለት ጉርሳቸውን ያቀርብ የነበረው፣ እና ለሌሎች ብዙ በመስጠት ለጋስ ነበር (ነህ. 5:17፣18)።

ምንም እንኳ አብረሀም በአካባቢው ይኖሩ በነበሩ ሕዝቦች በምርኮ የተወሰዱትን ሰዎች ነጻ አውጥቶ ከተመለሰ በኋላ ካከናወነው ነገር ጋር ተመሳሳይ ባይሆንም (ዘፍ. 14ን ይመልከቱ)፣ ነህምያ በዚህ ቦታ ላይ ያደረገው ነገር ተመሳሳይ የሆነን አስፈላጊ መርህ ይገልጽልናል። ነህምያ 5፡19ን ያንብቡ። በዚህ ስፍራ ላይ ነህምያ እያለ ያለው ምንድነው? ከወንጌልስ አንፃር እንዴት እናስተውለዋለን?በነህምያ ውስጥ የተመለከትነው፣ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ሥራ ከራሱ የግል ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ በማስቀደም ምሳሌ መሆን የሚችልን ሰው ነው። ያለንበት ሁኔታ ምንም ቢሆን ምን ይህ ለእያንዳንዳችን የሚሆን መልካም የሆነ ትምህርት አለው። ለጌታ መስራት ብዙም ዋጋን የማያስከፍል ከሆነ ቀላል ሊሆን ይችላል ።

ፊሊ. 2:3-8ን ያንብቡ። በዚህ ስፍራ የተገለፁት ዓይነት እራስን የመካድ መርሆች፣ዛሬ በእኛ ሕይወት ውስጥ መገለጥ የሚችሉት እንዴት ነው?

ጥቅምት 21
Nov 01


ተጨማሪ ሀሳብ


Ellen G. White, “A Rebuke Against Extortion,” pp. 646-652, in Prophets and Kings. “ነህምያ ይህንን አይነት አስከፊ ጭቆና በሰማ ጊዜ፣ ውስጡ በንዴት ተሞልቶ ነበር። ‘ጩኸታቸውንና እነዚህን አቤቱታዎች ከሰማሁ በኋላ’ ይላል ‘እጅግ ተቆጣሁ’። በጭቆና የማስከፈልን ልማድ በማስቀረት በኩል እንዲሳካለት ከፈለገ ስለ ፍትህ የማይለወጥ አቋም መውሰድ እንዳለበት በሚገባ አስተውሎ ነበር። በተለየ ሃይልና ቁርጠኝነት ለወገኖቹ ዕረፍትን ለማምጣት ሳይታክት ሰራ። —Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 648.

“ኢየሱስ ስለ መኃላ መመሪያን ሲያስቀምጥ አስፈላጊ እንዳልሆነ ተናግሮ ነበር። የንግግር ሕግ እውነት ሊሆን እንደሚገባ አስተማረ። “ቃላችሁ ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’፤ አይደለም፣ ከሆነም ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነው… (በአ.መ.ት)” —Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, p. 67

“እነዚህ ቃላት እርባናቢስና ስሜትን በመኅላ ለመግለፅ ጥቅም ላይ የሚውሉ፣ ትርጉም አልባና ንቀትን መነሻቸው ያደረጉ ንግግሮችን ሁሉ ይነቅፋሉ። አሁን ባለው ማህበረሰብና በቢዝነሱ ዓለም ውስጥ ያሉትን የይምሰል ውዳሴዎችን፣ እውነትን ለመሸፋፈን የሚደረጉትን፣ የሽንገላ ቃላትን፣ ግነቶችን፣ የንግድ ላይ ማታለሎችን ሁሉ ያወግዛል። እነዚህ ቃላቶች ያልሆነው ሆኖ ለመቅረብ የሚሞክርን፣ ወይም በአንደበቱ የሚወጡ ቃላት በልቡ ያለን እውነተኛ ሃሳብ የማያሳዩ ከሆነ፣ ማንም እውነተኛ ሊባል እንደማይችል ያስተምራሉ። —Page 68.


የመወያያ ጥያቄዎች
1.የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስግብግብነትን እንዴት ማስወገድ ይችላሉ? ይህንን ለማስወገድ እግዚአብሔር ምን ሰጥቷል? እነዚህን ጥቅሶች ያንብቧቸው፡ ኢሳ. 58፡3-12 እና ሚክ. 6፡6-8።

2.እራስ ወዳድነት ለምነድነው የችግሮቻችን ሁሉ ዋና ማጠንጠኛ የሚሆነው፣ በተለይ ከገንዘብ ጋርና ከእርስበርስ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ሲሆን?

3.በንግግር ስጦታ ላይ እና የምንናገራቸው ቃላት ምን ያህል ኃይል እንዳላቸው በማሰብ ጊዜ ይውሰዱ። ዮሐንስ 1፡1-2 ኢየሱስን “ቃል” ብሎ ሲጠራው ምን ማለቱ ነው? ይህም ስለምንናገራቸው ቃላት እና የሚይዙት ትርጉም ምን ያህል ጠቃሚ እነደሆኑ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?

4.ኢየሱስ ከሁለት ሺህ አመታት በፊት ድሆች ሁልጊዜም በመካከላችን እንደሚኖሩ መናገሩ አስገራሚ ነው። እነርሱንም በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንድንረዳ ተነግሮናል። እነዚህ ሁለት ሃሳቦች አንድ ላይ በመሆን ክርስቲያኖችን ከእነሱ በታች በድህነት ላሉት እንዲሰሩ ሊያነሳሷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?