ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ጥቅምት 8-14

4ኛ ትምህርት

October 19-25
ከተቃርኖ ጋር መጋፈጥሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዕዝራ 4፡1-5፣ 2ቆሮ.6፡ 14፣ዕዝራ5፡1-5፣ሐጌ1፣ዕዝራ4፡6-24፣ ነህምያ4፣ነህ.6፡1-13።


መታሰቢያ ጥቅስ “የአምላካቸው ዓይን ግን በአይሁድ ሽማግሌዎች ላይ ነበረ፤ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ መልሱም በደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ አልከለከሉአቸውም፡፡” ዕዝራ 5፡5

ዕ ዝራ ምዕራፍ 3-6 ቤተመቅደሱ እንደገና ሲገነባ በተለያዩ ዘመናት ያጋጠሙ ተቃውሞዎችን በአንድ ላይ ያስቀመጠበት ነው። ይህን ይዘት ተኮር አወቃቀር መረዳት ዋናው መልዕክት ግልፅ እንዲሆንልን ያደርጋል።

ዕዝራ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሙ የተጠቀሰው በዕዝራ 7፡1 ላይ ነበር። ከክ.ል.በፊት በ457ዓ.ዓ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ነገሮች ተለወጡ፤ እንዲሁም የኢየሩሳሌም ከተማ ከግንቦቿ ጋር መታደስ ጀመረች። ከአስራ ሦሥት ዓመታት በኋላ ነህምያ መጣ (በ444 ዓ.ዓ በአርጤክስስ ተልኮ)፤ የቅጥሩ ግንባታም በመጨረሻ ሊቀጥል ቻለ። ተቃውሞው እጅግ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም ሥራው በ52 ቀናት ውስጥ ተጠናቀቀ (ነህ.6፡15)።

በእግዚአብሔር ሥራ ላይ የሚመጣ ተቃውሞ በዕዝራና ነህምያ መጽሐፎች በስፋት የምናገኘው ኃሳብ ነው። ስለዚህ ቤተመቅደሱንና ከተማይቱን ኢየሩሳሌምን በማደስ ሥራ ላይ የተነሳው ተቃውሞና ስደት አስደናቂ አይደለም። በዛሬዋ ዓለም በየትኛውም አቅጣጫ ብንዞር የእግዚአብሔር ሥራ ተቃውሞ ይደርስበታል። ሰይጣን ግዛቱ እንዳይወሰድበት ስለሚፈራ ወንጌል በፍጥነት እንዳይዳረስ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል። በዕዝራና ነህምያ መጽሐፎች ውስጥ አይሁዶቹ ተቃውሞውን እንዴት አስተናግደውት ይሆን? የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 14 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጥቅምት 9
Oct 20

ተቃውሞው ሲጀመር


ዕዝ 4፡1-5ን ያንብቡ። በዚያ ቀርተው የነበሩት እስራኤላውያን ቤተመቅደሱን ሲገነቡ ሌሎቹ ለመርዳት ሲጠይቋቸው ፈቃደኛ ያልሆኑት ለምን ይመስሎታል?ከላይ ሲታይ ጥያቄው መልካምነት ያለበት ጉርብትናንም የሚያጠናክር ይመስላል፤ ታድያ ለምን አልተቀበሉትም? በአንድ መልኩ መልሱ የሚገኘው በራሱ በጥቅሱ ውስጥ ነው። “ጠላቶቻቸው” ሊረዱአቸው መጡ። ጠላቶቻቸው? እስራኤላውያን ለምን በዚያ መልኩ መልስ እንደሰጡ ያ ብቻውን ትልቅ ፍንጭ ይሰጣል።

እነዚህ ህዝቦች ለምን “ጠላቶች” ተብለው ተጠሩ? 2ኛ ነገስት 17፡24-41 እንደሚገልፀው የሰሜኑ የእስራኤል መንግስት ወደ ሌላ ስፍራ፡ ከፈለሱ በኋላ በሰማሪያና አካባቢው ከሌሎች ሀገሮች ፈልሰው የመጡ ናቸው። የሶሪያው ንጉስ ካህን ልኮ የምድሪቱን አምላክ ማለትም እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው እንዲያስተምራቸው አደረገ። ሆኖም ይህ ሃይማኖት የከነዓናውያንን አማልክት ማምለክንም ይጨምር ነበር። ስለዚህ የቀሩት እስራኤውያን ይህ እምነት ወደ ቤተመቅደሳቸው እንዳይመጣ ፈሩ። ስለዚህ የተሻለውና ብልሁ አማራጭ “እናመሰግናለን ግን አንፈልግም” ማለት ነበር።

ሲጀመርም ለምን ያ ሁሉ በህዝቡ ላይ እንደመጣ ማስታወስ ይኖርብናል። በምርኮ እንዲወሰዱ እና ቤተመቅደሱም እንዲፈርስ ያደረገው አያቶቻቻው በዙሪያቸው ከነበሩ አረማውያን ጋር ያደረጉት ማመቻመች ነበር። ምናልባት እንደሚገመተው ቤተመቅደሱን እንደገና በመስራት ሂደት ውስጥ ሊያደርጉት የማይፈልጉት ነገር ቢኖር በዙሪያቸው ካሉ ህዝብ ጋር መቀራረብ ነበር። በዚህ ጥቅስ ጥያቄውን አለመቀበላቸው ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ሌላ ምን ተመለከታችሁ? (ዕዝራ 4፡4-5)ይህንን የእርዳታ ጥያቄ ለመቀበል በቀላሉ ሊሰጡ የሚችሏቸውን ምክንያቶች ያስቡ። 2ቆሮ.6፡14 በዚህ ረገድ ምን ምክር ይሰጠናል?

ጥቅምት 10
Oct 21

የነቢያቱ ማበረታቻ


እንዳለመታደል ሆኖ በአካባቢው ከነበሩ ህዝቦች በመጣው ተቃውሞ የተነሳ በዕዝራ 4-6 እንደተገለፀው አይሁዳውያኑ በቤተመቅደሱ ለመስራት ፈርተው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ።

ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው ዕዝራ 4፡6-6፡22 በታሪካዊ ቅደም ተከተሉ አልተፃፈም። ስለዚህ ምዕራፍ 4ን ከማየታችን በፊት ምዕራፍ 5ን እንመለከታለን። ዕዝራ5፡1-5ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ሐጌንና ዘካርያስን ወደ አይሁዶች የላከው ለምን ነበር? ትንቢት የመናገራቸው ውጤት ምን ነበር?< አይሁዳውያኑ መገንባታቸውን ያቋረጡት ፈርተው ነበር። እግዚአብሔር ግን ዕቅድ ስለነበረው ቤተመቅደሱንና ከተማይቱን እንደገና እንዲገነቡ ላካቸው። ፈርተው ስለነበር እንዲበረታቱ አንድ ነገር ማድረግ ነበረበት። ስለዚህ ሁለት ነቢያት ጣልቃ እንዲገቡ ጠራቸው። የሰው ተቃውሞ እግዚአብሔርን ሊያስቆመው አይችልም። አይሁዳውያኑ በራሳቸው ተግባር ይህን ተቃውሞ ቢያግዙም እግዚአብሔር ግን አልተዋቸውም ነበር። በነቢያቱ በኩል ሰርቶ ህዝቡ እንዲነቃቃና ወደ ተግባር እንዲገባ አደረገ።

ሐጌ 1ን ያንብቡ። ለነርሱ የተሰጠው መልዕክት ምን ነበር? ለራሳችን ከዚህ ምን ትምህርት መውሰድ እንችላለን?“ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ የችግሩን ጊዜ ለመጋፈጥ የተነሱ ነበሩ። ልብን በሚቀሰቅሱ ምስክርነቶች የችግራቸውን መንስኤ ለሕዝቡ የገለጡ መልዕክተኞች ነበሩ። ነቢያቱ ሕዝቡ በዚያ ወቅት ያጋጠማቸው እጦት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማስቀደም ሲኖርባቸው ችላ በማለታቸው እንደሆነ ተናገሩ። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አክብረው ቢሆን ኖሮ፣ የርሱን ቤት ግንባታ የመጀመሪያ ስራቸው በማድረግ ክብር ሰጥተውት ቢሆን ኖሮ መገኘቱንና በረከቱን ይጋብዙ ነበር።” ኤለን ጂ.ኋይት፣ ፕሮፌትስ ኤንድ ኪንግስ፣ በእንግሊዝኛው ገፅ 573-574

ጥቅምት 11
Oct 22

ሥራ ማቆም


በኢየሩሳሌም የነበረው ሥራ እንዲቆም “ጠላቶቻቸው” በዕዝራ 4፡6-24 ላይ ምን አደረጉ?“የምድሪቱ ሰዎች” አይሁዶችን በመክሰስ መጀመሪያ ለዳርዮስ (ዕዝራ 5 እና 6) ከዚያም ለጠረክሲስ እና አርጤክስስ ደብዳቤ ፃፉ። በኢየሩሳሌም ይካሄድ የነበረውን ሥራ ለማስቆም አቅማቸው የቻለውን ሁሉ እያደረጉ ነበር።

በዙሪያ የነበሩት ሕዝቦች ከተማይቱ እንደገና ከተገነባች ንጉሱ ሊያስተዳድራት እንደማይችል ምክንያቱም ቦታው ከበፊትም ጀምሮ የአመፅና የችግር ነው የሚል ስሞታን አቀረቡ። በሚያሳዝን ሁኔታ ንጉስ አርጤክስስ አይሁዳውያን እየገነቡ ያሉት ነፃነታቸውን ለማግኘት እንደሆነ ወደማመን ስላዘነበለ ነገሩን ተቀበለው። ሥራው እንዲቋረጥ ትዕዛዝ አስተላለፈ፤ ሕዝቡም የከተማይቱን ግንባታ እንዳይቀጥል ወታደር ላከ። ይህ የኃይል እርምጃ የእግዚአብሔር ሥራ እንዲቋረጥ አደረገ። ዕዝራ 4፡23-24ን ያንብቡ። አይሁዳውያኑ ግንባታውን ያቆሙት ለምን ነበር? እግዚአብሔር ከተማይቱ እንድትገነባ እንደፈለገ አያውቁም ነበር? ታዲያ ምን አጋጠማቸው?አይሁዳውያኑ እግዚአብሔር ያችን ከተማና ቤተመቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ እንደጠራቸው እንደሚያውቁ ግልፅ ነው። ነገር ግን ጠንካራ ተቃውሞ ስለገጠማቸው ፍርሃት ያዛቸው። ምናልባትም “አሁን ጊዜው ላይሆን ይችላል” ወይም “እግዚአብሔር በእውነት ይህንን እንድናደርግ ከፈለገ መንገዱን ይከፍትልን ነበር” የሚሉ ሰበቦችን ደርድረው ይሆናል።

እግዚአብሔር እንድናደርግ እንደጠራን ያመንነውን ነገር ስናደርግ በመንገዳችን ተቃውሞ ሲገጥመን የእግዚአብሔርን ምሪት መጠራጠርና ጥያቄ ውስጥ መክተት ይቀናናል። በቀላሉ ራሳችንን እንደተሳሳትን ልናሳምን እንችላለን። ፍርሃት አእምሯችንን ሽባ ያደርግና በእግዚአብሔር ኃይል ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በረዳተ ቢስነትና በተስፋ መቁረጥ ላይ እናተኩራለን። እርስዎስ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞት ያውቃል? እግዚአብሔር አንድ ነገር እንዲያደርጉ እንደጠራዎት አምነው ነገሮች ከባድ ሲሆኑ ግን ጥርጥር ውስጥ ገብተው ያውቃሉ? (ለምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስን ያስቡ) ከእሱ ልምምድ ምን ተማራችሁ?

ጥቅምት 12
Oct 23

ነህምያ እርምጃ ወሰደ (444 ዓ.ዓ)


ነህምያ 4ን ያንብቡ። በነህምያ እየተመሩ አይሁዳውያኑ ተቃውሞውን ለማሸነፍ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር እንደሚጠብቃቸው በማመን ቁጭ ከማለት ይልቅ ለውጊያ ራሳቸውን ማዘጋጀታው አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?ጀምረው ካቋረጡ በኋላ ህዝቡ እንደገና መስራት ጀመሩ። አይሁዶቹ ፀለዩ፤ ነህምያም ጠባቂዎችን አቆመ። ህዝቡ በቀንና በማታ በፈረቃ እየተቀያየሩ ለማንኛውም ጥቃት በተጠንቀቅ ቆሙ። በአጥሩ ዙሪያ ያሉትን ሰዎችም መሳሪያ በማስታጠቅ ነህምያ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለመዋጋት ዝግጁ እንዲሆኑ አደረገ። በተጨማሪም አገልጋዮቹን ለሁለት በመክፈል ግማሹ እንዲሠራና ግማሹ ደግሞ መሳሪያ ይዞ እንዲጠብቅ አደረገ። ግንቡን እየገነቡ የነበሩት ለጥቃት ቅርብ ስለነበሩ የተለየ ከለላ ይደረግላቸው ነበር።

እያንዳንዱ ግንበኛ በአንድ እጁ ሰይፍ ይዞ በሌላው እጁ ደግሞ በግንቡ ላይ ጡብን ይጨምር ነበር። ተቃውሞውን ለመጋፈጥ ዝግጁ ነበሩ። ከነርሱ የሚጠበቀውን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ደግሞ የቀረውን ሞላ። ነህምያ በእግዚአብሔር ጥበቃ ላይ የነበረው እምነት የሚያነቃቃ ነው። ሆኖም እጁን አጣምሮ ቁጭ ብሎ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንዲያደርግ አልጠበቀም። አቅማቸው በቻለው ሁሉ ዝግጁ ሆኑ።

“አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ” (ነህ.4፡14) የሚለውና “አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።” (ነህ.4፡20) የሚለው ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ አነቃቂ አረፍተ ነገሮች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።

በቀጣይነት በመጣባቸው ተቃውሞ ምክንያት አይሁዳውያኑ ግንባታውን ሊያቋርጡ ይችሉ ነበር። ነገር ግን አሁን በፍርሃት ከመሸነፍ ይልቅ እግዚአብሔር ለእነርሱ እንደሚዋጋ የገባውን የተስፋ ቃል አጥብቀው ያዙ። ስለ እግዚአብሔር ስም፣ ስለ እምነታችን ወይም እግዚአብሔር እንድናደርግ ስለጠራን ነገር ተቃውሞ ሲገጥመን ሁልጊዜም ቢሆን “እግዚአብሔር ስለ እኛ እንደሚዋጋልን” ልናስታውስ ይገባናል። በመጨረሻ አይሁዳውያኑ በሚሰሩት ሥራ እግዚአብሔር ከጎናቸው እንደሆነ ተረዱ፤ ይህም ወደ ፊት ለመቀጠል ብርታትን ሰጣቸው።

እያደረግን ያለነው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሆነ ማወቅ የሚጠቅመን ለምንድነው? ስለዚህ ወሳኙ ጥያቄ፡- እያደረግኩ ያለሁት ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን የማውቀው እንዴት ነው? የሚል ይሆናል።

ጥቅምት 13
Oct 24

“ታላቅ ሥራ”ን ማከናወን


ነህምያ 6፡1-13ን ያንብቡ። ነህምያ በኢየሩሳሌም እያከናወነ የነበረውን ሥራ እንደ “ታላቅ ሥራ” የቆጠረው ለምን ነበር (ነህምያ 6፡3)? በዚህ ቦታ እሱን ለማስቆም የተሞከረው በምን መልኩ ነበር?ምዕራፍ 6 በነህምያ ህይወት ላይ የተሞከሩትን ብዙ ሙከራዎች ይገልፃል። በስብሰባ አሳበው ሳንባላጥና ጌሳም ነህምያን ለማግኘት በተደጋጋሚ ደብዳቤ ይፅፉለት ነበር። ሆኖም ስብሰባው በጠላት ክልል ውስጥ በሚገኘው በኦኖ ሜዳ ላይ ስለነበረ የግብዣው እውነተኛ አላማ ግልፅ ነበር። ሳንባላጥ፣ ጦቢያና ጌሳም ቅጥሩ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅና በሮቹ እስኪዘጉ ድረስ አጋጣሚዎችን ይፈልጉ ነበር።

አይሁዶቹ የፋርስ ንጉስን ከለላ አግኝተው ስለነበረ ጠላቶቻቸው ፊት ለፊት አጥቅተው ሊያሸንፏቸው አይችሉም። ነገር ግን መሪያቸውን ማስወገድ ቢችሉ ሥራውን ማጓተት ምናልባትም አይሁዳውያኑን ለዘላለም ማስቆም ይችሉ ነበር። ሙከራቸውን አላቋረጡም፤ ነህምያ መልስ ባይሰጥም ሙከራቸውን ቀጠሉ። በእያንዳንዱ እርምጃ ተቃውሞ ሲያጋጥመው ለነህምያ እጅግ አሰልቺ ሆኖበት ይሆናል። “ትልቅ ስራን እየሰራሁ ነኝ።” (ነህምያ 6፡3) በማለት ይመልስላቸው ነበር። በዓለማዊ መለኪያ ቢሆን የንጉሱ ጠጅ አሳላፊ ሆኖ ንጉሱን በማማከር ይሠራ የነበረው ሥራ በዚያች ምድር እጅግ ትልቅ ሥራ ነበር። ነገር ግን እምብዛም አስፈላጊ ያልሆነችንና የፈራረሰችን ከተማ እየገነባ? ትልቅ ስራ ብሎ የጠራው ይሄንን ነው? ነህምያ ለእግዚአብሔር የሚሰራውን ሥራ “ትልቅ” አድርጎ ቆጥሮታል፤ ከዚያም በላይ ምክንያቱ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ስም የሚሰጠው ክብር በአደጋ ውስጥ እንደሆነ በመረዳቱ ነበር።

እግዚአብሔር የቤተመቅደሱን ስነ-ስርዓት ሲያቋቁም የክህነት አገልግሎትንም አስጀምሯል። በሰዎች አእምሮ ውስጥ ቤተመቅደሱ ቅዱስና የተለየ ቦታ እንዲሆን በቤተመቅደሱ ውስጥ የሚካሄዱትን ነገሮች እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸው ካህናት ብቻ ነበሩ። ሰው በራሱ የእግዚአብሔርን ቅድስና ማየት ስለሚከብደው እስራኤላውያን ወደ እርሱ መገኛ በአክብሮት እንዲቀርቡ ማሳያን ሰጣቸው።

ነህምያ የቤተመቅደሱ አደባባይ ለሁሉም የተፈቀደ ውስጠኛ ክፍሎቹ ግን እንዳልተፈቀዱ ያውቅ ነበር። ሸማያ በራሱ አፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ ሲል ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ውጪ የሆነን ነገር በመጠየቅ ሐሰተኛ ነቢይና ከሃዲ መሆኑን በራሱ አጋለጠ።

ዛሬ እኛ ያለምንም ምድራዊ ቤተመቅደስ የእግዚአብሔርን ቅድስና የምናስብባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ከኛ ኃጢአተኛነት አንፃር የእግዚአብሔርን ቅድስና ማስተዋላችን ወደ መስቀሉ የሚመራን እንዴት ነው?

ጥቅምት 14
Oct 25


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ.ኋት በእንግሊዝኛው “ነቢያትና ነገስታት” ከሚለው መፅሐፏ ውስጥ ከገፅ 635-660 “የቅጥሩ ግንበኞች”ተግሳፅ” እና “የአሕዛብ ሴራ” የሚሉትን ምዕራፎች ያንብቡ።

“በነህምያ ዘመን የቅጥሩ ሠራተኞች ከግልፅ ጠላቶችና ከአስመሳይ ወዳጆች የገጠማቸው ተቃውሞና ተስፋ ማስቆረጥ ዛሬ ለእግዚአብሔር የሚሰሩት ከሚያጋጥማቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። ክርስትያኖች ከጠላቶቻቸው በሚሰነዘር ንዴት፣ ዛቻና ጭካኔ ብቻ ሳይሆን በወዳጆቻቸውና ረዳቶቻቸው በኩል በሚመጣ ስንፍና፣ ማስመሰል፣ ቸልተኝነትና ክህደትም ጭምር ይፈተናሉ።” ኤለን ጂ.ኋይት፣ (በእንግሊዝኛው) ነቢያትና ነገስታት ገፅ. 644 “ለእግዚአብሔር ሥራ የነበረው መሰጠትና በእግዚአብሔር መታመኑ ነህምያ ጠላቶቹ እጅ ውስጥ እንዳይወድቅ ረዳው። ሰነፍ የሆነ ሰው በፈተና ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ ይወድቃል፤ ከፍ ያለና የማይነቃነቅ አላማ ባለው ሰው ህይወት ውስጥ ክፉው ትንሽ ስፍራ ብቻ ነው ሊያገኝ የሚችለው። በየጊዜው ወደፊት የሚቀጥል ሰው እምነት አይደክምም፤ ምክንያቱም የማያልቀው ፍቅር ለራሱ መልካም የሆነውን በዚያ ሰው ለማከናወን ከላይ፣ ከታችና ከጎኑ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። የእግዚአብሔር እውነተኛ አገልጋዮች በፀጋው ዙፋን ሁልጊዜ ስለሚተማመኑ በማይነቃነቅ ግለት ይሠራሉ።” ገፅ 660
የመወያያ ጥያቄዎች
1.ራስዎን በዘሩባቤል፣ በኢያሱና በሌሎቹ መሪዎች ቦታ ያስቀመጡና እነዚያ ሰዎች ለመርዳት ጥያቄያቸውን ይዘው ሲመጡ የነበረውን ሁኔታ ያስቡ። ዛሬ ላይ ወደኋላ ስንመለከት ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ትክክል እንደነበሩ መመልከት እንችላለን። አድቬንቲስት እንደመሆናችን ከእኛ እምነት ውጪ ከሆኑ ሰዎች ጋር መቼ መተባበርና መቼ ደግሞ አለመተባበር እንዳለብን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ትክክሉንና ስህተት የሆነውን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በምን መስፈርት እንሂድ?

2.በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁሉ በእምነታችን ከአለም ጋር የመደራደርን አደገኝነት እንመለከታለን። በእርግጥም የጥንታዊቱ እስራኤል ታሪክ በባቢሎን እስከተማረኩበት ጊዜ የነበረው ታሪክ የዚህ ማመቻመች (መደራደር) ማሳያ ነው። በተመሳሳይ ደግሞ ሰዎች እንዲህ አይነቱን አደጋ ለማስወገድ ብለው ወደ ፅንፈኝነት ሲሄዱ ምን ይፈጠራል? ኢየሱስ ራሱ ሰንበት ሽረሃል ተብሎ ሲከሰስ (ዮሐንስ 9፡14-16) ከሳሾቹ ወደ ሌላ ፅንፍ የመሄድ ምሳሌ አይሆኑንም?ትክክለኛውን ሚዛን እንዴት ማግኘት እንችላለን?