ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ጥቅምት 1-7

3ኛ ትምህርት

October 12-18
የእግዚአብሔር ጥሪሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዕዝራ 7፡10፣ ነህ.1፡1-11፣ ዳን.9፡ 24-27፣ ዳንኤል 8፣ሮሜ 8፡28-29፣ ሮሜ 9፣ ዘፀዓት 3፣4።


መታሰቢያ ጥቅስ “በኢየሩሳሌም የሚገኘው የእግዚአብሔር ቤት በዚህ ሁኔታ እንዲከበር ይህን በንጉሱ ልብ ያኖረ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ብሩክ ይሁን።” (ዕዝራ 7፡27)

በ ውኑ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ለተለየ አላማ ይጠራል? ለአንድ ኃላፊነት ብቁ ከመሆን አንፃር አንዱ ከአንዱ ሊበልጥ የሚችልባቸው መለኪያዎች ይኖሩ ይሆን? እነዚያ መለኪያዎች በሰው አይንና በእግዚአብሔር ዓይን ሲታዩ ይለያዩ ይሆን? ምናልባት ብዙዎቻችን ለመጨረሻዎቹ ሁለት ጥያቄዎች መልሳችን አዎን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜያት እግዚአብሔር በትምህርት ወይም በልምምድ ውስጥ ለአንድ የተለየ ኃላፊነት ሲያለማምደን በሌሎቹ ጊዜያት ደግሞ ፈቃደኛና ትሁት ስለሆንን ብቻ ለአገልግሎት ይመርጠናል።

በኛ ህይወት ውስጥ የእግዚአብሔር አላማ (ጥሪ) ምን እንደሆነ ማወቅ ግን ብዙ ጊዜ ቀላል አይደለም፤ ልክ ነው? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ለተለየ ኃላፊነት እግዚአብሔር በመረጣቸው ሰዎች ታሪኮች የተሞላ ነው።

በአስደናቂ ሁኔታ ዕዝራና ነህምያ በእግዚአብሔር ለተለየ ኃላፊነት ተጠርተው ነበር፤ ይኸውም የፈራረሰውን እንደገና ለመገንባት ነበር። ሆኖም መልሶ መገንባት በዚህ ረገድ የተለያዩ ኃላፊነቶችን በውስጡ የያዘ ነበረ።

የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ በመምራት ቤተመቅደሱንና ከተማይቱን እንደገና መገንባት ይጠበቅባቸው ነበር። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ለህዝቡ ስለ እግዚአብሔር ማስተማርና ከሁሉ በላይ ደግሞ ከርሱ ጋር የጠለቀ ግንኙነት እንዲያደርጉ መምራት ነበረባቸው። ስለ እግዚአብሔር ጥሪና ስለተመረጡት እንመለከታለን። ለጥቅምት 8 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 2
Oct 13

የዕዝራና የነህምያ አጠራር


ዕዝራ በተለያዩ ምክንያቶች ተመረጠ ልንል እንችላለን፡ 1) ለመሄድ ፈቃደኛ ነበር 2) መሪ ነበር እንዲሁም 3) የተካነ ፀሐፊና መምህር ነበር። ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችንም እናገኝ ይሆናል። ነገር ግን ዕዝራ ለምን ይህ ኃላፊነት እንደተሰጠው በጥሩ ሁኔታ የሚገልፅ አንድ ጥቅስ አለ።

ዕዝራ 7፡10 ስለ ዕዝራ ምን ይናገራል? ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ህግ” ለመፈለግና ለማድረግ ልቡን ያዘጋጀው እንዴት ይሆን?ቃል “ አዘጋጀ ፣ ሰጠ ፣ ጠነከረ ፣ ፀና እንዲሁም ተከለለ” የሚል ትርጓሜ ያለው ነው። ስለዚህ የዚህ ዓረፍተ ነገር ትክክለኛ ትርጉም ዕዝራ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን አፀና ወይም ተሰጥቶ ነበር የሚል ትርጉምን ይዟል።

ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ ዕዝራ ለእግዚአብሔር ራስን መስጠት የሚለውን ኃሳብ በተግባር እያሳየ ለ13 ዓመታት በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቃል አስተማረ። በነዚያ አስራ ሶስት ዓመታት ውስጥ ምንም ልዩነት እንዳላመጣ ተሰምቶት ይሆናል። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ግንቦቹ ካለቁ በኋላ ህዝቡ ማንም አስገድዷቸው ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ ስብሰባ (ጉባኤ) ጠሩ። ከዕዝራ ሲሰሙ የቆዩት የእግዚአብሔር ቃል ስር ሰዶ ነበር።

ነህምያ ለምን ተመረጠ? ነህምያ 1፡1-11ን ያንብቡ።ነህምያ ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ልቡ የቀና ነበር። በኢየሩሳሌም ተጀምሮ የነበረው ሥራ እንደቆመ ሲረዳ ተረበሸ። ነህምያ ለዚህ ጉዳይ ግለቱ ነበረው፤ ልክ እንደ ዕዝራ ደግሞ ለስራው ፈቃደኛ ሆኗል። እግዚአብሔር ፀሎታቸውንና ምኞታቸውን ሰማላቸው። አንዳንድ ጊዜ አንድን ነገር ከወደድነው ከእግዚአብሔር አይደለም ማለት ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚሰጠን መስራት የማንፈልጋቸውን ከባድ ኃላፊነቶች ብቻ ነው ብለን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር የምንራመድ ከሆነ የምንወደውን ለማድረግ የሚኖረን ፍላጎት በአብዛኛው ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ለእርሱ የምናደርገውን ነገር በግለት እንድናደርገው ይፈልጋል። እግዚአብሔር እርስዎ የሚወዱትን እንዲያደርጉ እየጠራዎት እንደሆነ ተሰምቶት ያውቃል። ከሆነ እንዴት?

ጥቅምት 3
Oct 14

የትንቢቱ ጊዜ (መጠበቅ)


በመጀመሪያው ትምህርት እግዚአብሔር እንዴት ዘሩባቤልን (538 ዓ.ዓ) እና ዕዝራን (957 ዓ.ዓ) ለተለየ አገልግሎት እንደጠራቸው አጠናን። በሁለተኛው ትምህርት እግዚአብሔር ነህምያን የጠራበትን ሁኔታ ተመለከትን (444 ዓ.ዓ)። እነዚህ አጠራሮች እግዚአብሔር የወደፊቱን የሚያውቅ ከመሆኑ እውነታ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ለምሳሌ ዘሩባቤል በኤርሚያስ የተነገረው የ70 ዓመት የምርኮ ጊዜ በመድረሱ የተወሰነ ኃላፊነት እንዲወጣ እግዚአብሔር አነሳሳው።

ዕዝራ ለአገልግሎት የተጠራው በየትኛው ዓ.ዓ ነበር? ንጉስ አርጤክስስ አዋጅን ካሳወጀበት (ትዕዛዝ ካወጣበት) ዓመት ጋር ተመሳሳይ ዓመት ነበር። ያ ዓመት በትንቢት ያለው ወሳኝ ቦታ ምንድን ነው? ዳንኤል 9፡24-27ን ያንብቡ።ዳን. 9፡25 “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዢው መሲህ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባኤና ስልሳ ሁለት ሱባኤ ይሆናል።” ብሎ ይናገራል። የዚህ ትንቢት የመጨረሻው ሳምንት በቁጥር 27 ላይ ተገልጿል። አንድ ሳምንት ሰባት ቀናትን ስለሚይዝ በትንቢት የተገለፀ አንድ ሳምንት 7 ዓመታትን ይወክላል (ዘሁ. 14፡34፣ ሕዝ. 4፡6)። ስለዚህ ይህ ትንቢት ስለ 70 ሳምንታት ማለትም ስለ 490 ዓመታት ነው የሚናገረው።

ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ “የሰባው ሱባኤ (ሳምንት) ትንቢት የሚጀምረው መቼ ነው?” የሚለው ነው። ጥቅሱ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን አዋጅ ከሚወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው ይላል። የአይሁድ ህዝብ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያዙ (የሚፈቅዱ) ሶስት አዋጆች ወጥተው ነበር። ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ የመታደስ (የመመለስ) ትዕዛዝን አስተላልፈው ነበር። ሆኖም ኢየሩሳሌም ከተማን የተመለከተ ትዕዛዝን የያዘውና ከትዕዛዙ ጋር ተያይዞ እግዚአብሔር ጣልቃ ስለመግባቱ የተመሰገነው ንጉስ አርጤክስስ ባወጣው አዋጅ ነው።

ስለዚህ የሰባ ሱባኤውን (ሳምንቱን) ትንቢት መቁጠር የምንጀምረው በዕዝራ 7፡ 7-26 እንደተጠቀሰው በንጉስ አርጤክስስ ግዛት 7ኛ ዓመት ከክ.ል በፊት በ457 ዓ.ዓ ይሆናል ማለት ነው። በተጨማሪም 457 ዓ.ዓ በዳንኤል 8፡14 የተጠቀሰው የ2300ው ቀናት ትንቢትም መጀመሪያ ስለሆነ ይህ አዋጅ ለሁለቱም ትንቢቶች መነሻ ሆኖ ያገለግላል። (የነገውን ጥናት ይመልከቱ)።

ሰባው ሳምንታት በ34 ዓ.ም ማለትም የወንጌል ሥራው አድጎ ወደ አሕዛብ በሰፋበት (ቀደምቷ ቤተክርስትያን ብዙ ስደት ያጋጠማትና እስጢፋኖስም ተወግሮ የሞተበት ዓመት) ዓመት አበቃ። የመጨረሻው ሳምንት አጋማሽ ማለትም 31 ዓ.ም ደግሞ ኢየሱስ የተሰቀለበት ዓመት ነበር። የዳንኤል 9፡24-27ን ትንቢት ለራስዎ ይመርምሩ። እጅግ አስደናቂ በሆነ ትክክለኝነት የኢየሱስን አገልግሎት ጊዜ የገለጠው እንዴት ነበር? እንደዚህ አይነት ትንቢት እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?

ጥቅምት 4
Oct 15

ሰባው ሱባኤው 2300ው ቀናት


በዳንኤል 9፡24 ላይ “ሰባ ሱባኤ ተቀጥሮአል” በሚለው ውስጥ “ተቀጥሮአል” የሚለው ቃል ቀጥታ ትርጉሙ “ተቆርጧል” የሚል ነው። “ተቀጥሮአል” የሚለውን ቃል በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ባናገኘውም በአይሁድ ፅሁፎች ውስጥ እናገኘዋለን። ትርጉሙም ረዘም ካለ ነገር ላይ “ተቆርጧል” የሚል ነው። ዳንኤል 8 የ2300 ዓመታቱን ትንቢት ቢናገርም ከመቼ እንደሚጀምር ግን አልተናገረም። በመቀጠል በዳንኤል 9፣ 490 ዓመታት ስለመቆረጣቸው ሲናገር ሊቆረጡ የሚችሉት ቀደም ባለው ምዕራፍ ከተናገረው ከ2300ው ትንቢታዊ ዓመታት ብቻ ነው። ይህ ጊዜ ከሌላ ረዘም ካለ የጊዜ ትንቢት ካልሆነ ከምን “ሊቆረጥ” ይችላል? ዳንኤል 8ን ያንብቡ። ከራዕዩ ውስጥ ያልተብራራው ክፍል የትኛው ነበር (ዳን.8፡14፣26 ይመልከቱ)?ምሽትና ጠዋት ትንቢት በአንድ ላይ ለመሔዳቸው ብዙ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል።

1ኛ ሁለቱም የጊዜ ትንቢቶች ናቸው፤ 2) “ራዕይ” ና “ማስተዋል” የሚሉት ቃላት የተያያዙ በመሆናቸው (ዳን.8፡26 እና 9፡23ን ይመልከቱ) 3) የሁለቱም ትንቢቶች ትርጉሞች በገብርኤል የተነገሩ መሆናቸው (ዳን. 8፡16 እና 9፡21ን ይመልከቱ) 4) በዳንኤል 8 ውስጥ ያልተብራራው የራዕዩ ብቸኛ ክፍል በ14ኛው ቁጥር የሚገኘው የ2300ው ምሽትና ጠዋት ጉዳይ ነበር 5) ዳንኤል 8 ራዕዩንና ከፊል ትርጓሜን የያዘ ሲሆን ዳንኤል 9 ግን ትርጓሜን ብቻ ይዟል። በተለይም ከራዕዩ ውስጥ ዳንኤል ያላስተዋለውና (ዳን.8.27) በዳንኤል ምዕራፍ 8 ላይ ያልተተረጎመው የዳንኤል 8፡14ቱ የ2300ው ቀናት ትንቢት ብቻ ነበር።

በዕዝራ መጽሐፍ የተሰጠን መረጃ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተተነበየውን ትንቢት ክፍተት ማለትም ትንቢታዊ ጊዜውን ከመቼ መጀመር እንዳለብን በተለይም ኢየሱስ በእኛ ፋንታ ሆኖ የሚያካሂደውን አገልግሎት በተመለከተ መረጃን ያሟላል። የሰባው ሱባኤና የ2300 ቀናቱ ትንቢት ይዘት በምስል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ጥቅምት 5
Oct 16

የእግዚአብሔር አመራረጥ


እግዚአብሔር እኛ አንድ ነገር እንድንፈፅም ስለመምረጡ ብዙ ይባላል። ብዙዎች ስለዚያ ምርጫ የተለያየ አመለካከት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለእኛ መመረጥ ምን ይናገራል? ሮሜ 8፡28-29ን ያንብቡ። እግዚአብሔር የጠራን ወደ ምንድን ነው? የመረጠንስ ለምንድነው?ይህ ገፅ በተለይ እግዚአብሔር ለሰዎች ያለው አላማ የልጁን መልክ እንዲመስሉ መሆኑን ይገልፃል። እዚህ ጋ እኛ ለመዳን ወይም ለመጥፋት መምረጥ የማንችል ወይም ምርጫ የሌለን ነን እያለ አይደለም። በሌላ አነጋገር መመረጣችን እኛ እንድንለወጥ ነው። ተለውጠን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስን የምናንፀባርቅ ልንሆን ይገባናል። ይህ መለወጥ ጳውሎስ በቀጣዮቹ ቁጥሮች (ሮሜ 8፡30) እግዚአብሔር የጠራቸውን አፀደቃቸው እንዲሁም አከበራቸው (ቀደሳቸው) በሚል ተስፋ ተሰጥቷል። ስለዚህ እኛ ራሳችንን እንድንለውጥ ሳይሆን በእርሱ ኃይል ሊለውጠን ቃል ገብቷል።

ሮሜ 9ን ያንብቡ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የእግዚአብሔር ምን አይነቱ አጠራር (አመራረጥ) ነው የተገለፀው?በሮሜ 9 ጳውሎስ የእግዚአብሔር አመራረጥ ለተለየ ኃላፊነት እንደሆነ ያብራራል። እስራኤላውያን ስለ እግዚአብሔር መልካሙን ዜና ለዓለም ለማዳረስ ተመርጠው ነበር። “ያዕቆብን ወደድኩ ኤሳውን ጠላሁ።” (ሮሜ 9፡13) የሚለው ጥቅስ በአብዛኛው በስህተት ተስተውሎ እግዚአብሔር ከሁለቱ ወንድማማቾች አንዱን ብቻ እንደወደደ ይታሰባል። ሆኖም በዚህ ምዕራፍ አውድ መሰረት ጳውሎስ እያለ ያለው ያዕቆብ እንደተመረጠና ኤሳው ደግሞ እንዳልተመረጠ ነው። ያዕቆብ የተመረጠው ለምን ነበር? የእስራኤል ሕዝብ አባት ለመሆን ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሁለት አይነት አመራረጦች አሉት።

መጀመሪያ እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ለድነት ይመርጠንና ኢየሱስን ወደ መምሰል እንድንለወጥ ይፈልግብናል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የተለያዩ ሰዎችን ለተለያዩ ኃላፊነቶች ይመርጣል። ለመዳን አስቀድመን የተወሰንን መሆናችንን ማወቃችን የሚያበረታታን እንዴት ነው? ያ ማለት ግን ምርጫችን እግዚአብሔር የሰጠንን ድነት ሊያሳጣን አይችልም ማለት ያልሆነው ለምንድነው?

ጥቅምት 6
Oct 17

የኛ ኃላፊነት


በእግዚአብሔር ከተጠራን ልክ እርሱ የሚሰጠንን መዳን ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል ምርጫ እንዳለን ሁሉ አሁንም የመቀበልና ያለመቀበል ነፃ ምርጫ አለን። በተለየ ኃላፊነት ላይ አስቀምጦን ቢሆን እንኳን የእርሱን ፈቃድ ላለመከተል መምረጥ እንችላለን። አዎን፣ ልክ እርሱን እንድንመስል እንደሚጠራን ሁሉ ለእርሱ የተለዩ ነገሮችን እንድናደርግ ይፈልጋል። የእግዚአብሔር እኛ ለተለየ ኃላፊነት መምረጥ የእርሱ ማዳን ዕቅድ ክፍል ነው። እንድናደርግ የጠራንን ስናደርግ እርሱ የሰጠን ድነት በህይወታችን እውነታ መሆኑን እንገልፃለን።

ንጉስ ሳኦል የንግስና ቦታ ተሰጥቶት ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ሳኦል የተሰጠው ኃላፊነት ቢኖርም ልቡን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር አልሰጠም ነበር። አንድ ሰው ለእግዚአብሔር አንድን የተለየን ነገር እንዲያደርግ መጠራቱ ያ ሰው በእግዚአብሔር መንገድ እንደሚሄድ ማረጋገጫ አይሆንም። ወሳኙ ነፃ ምርጫችን ነው፤ እናም የእግዚአብሔርን ምሪት ካልተከተልን ሁሉንም ልናጣ እንችላለን።

ዘፀዓት 3 እና 4ን ያንብቡ። እግዚአብሔር አንድን ሰው ለአንድ ስራ ሲጠራው ምን ሊሆን እንደሚችል ይህ የሚያስተምረን እንዴት ነው?ሰበብ እንዳበዛው እንደ ሙሴ ሊሆን ይችላል። ሙሴ በመጨረሻ ሄደ፤ ነገር ግን ለመውጣት ሳይታገል ግን አልቀረም። ብቁ እንዳልሆነ፣ ተራ ሰው እንደሆነና ጠቃሚ ኃላፊነት ይዞም እንዳልነበረ በማስታወስ ተቃወመ። ታድያ ፈርኦን እንዴት ይሰማዋል? አይሁዳውያኑም እርሱን እንደማያምኑት፣ እንደማይሰሙትና ከንቱ ልፋትም እንደሚሆን በማሰብ ተጨንቆ ነበር። በተጨማሪም “ኮልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” በማለት ችሎታ የሌለው መሆኑን በመናገር የማይገባው መሆኑን አሳወቀ።

በመጨረሻ እግዚአብሔር ሌላ ሰው እንዲልክ ጠየቀው። ሆኖም የሙሴን ታሪክ ስናስብ ሙሴ እንከን ቢኖርበትም እንዴት ኃይለኛ መሪ መሆን እንደቻለ እንረዳለን። እግዚአብሔር እንዲያደርግ የጠራውን በታማኝነት የፈፀመ ሰው ነበር። እግዚአብሔር እንድናደርግ እንደሚያስችለን እያወቅን ላለማድረግ የምንሰጣቸው ምክንያቶች ምንድናቸው?

ጥቅምት 7
Oct 18


ተጨማሪ ሀሳብ


ከነቢያትና ነገስታት (በእንግሊዝኛው ገፅ 697-699) የሰባው ሱባኤ ትንቢትና ታሪካዊ አፈፃፀሙን በተመለከተ በጥንቃቄ ያንብቡ። “ክርስቶስ የሚመጣበት ጊዜ፣ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱ፣ ሞቱና የወንጌል ለአህዛብ መሰጠት በግልፅ ተተንብየው ነበር። በኢየሱስ ተልዕኮ ውስጥ እነዚህ ትንቢቶችን መረዳትና መፈፀማቸውን ማወቅ ለአይሁዳውያን የተሰጠ ዕድል ነበር። ክርስቶስ የትንቢት ጥናትን አስፈላጊነት በተመለከተ ለደቀመዛሙርቱ በተደጋጋሚ ነግሯቸዋል። በዳንኤል የተሰጡትን የጊዜ ትንቢቶች በተመለከተ” አንባቢው ያስተውል።” (ማቴ. 24፡15) በማለት ተናግሯል።

ከትንሳኤው በኋላ ለደቀመዛሙርቱ በነቢያት ሁሉ”ስለ እርሱ የተፃፉትን”(ሉቃስ 24፡27) ገልፆላቸው ነበር። አዳኙ በነቢያቱ ሁሉ ሲናገር ነበር።”በነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ” ስለ ክርስቶስ ስቃይና ከዚያም ስለሚከተለው ክብር አስቀድመው መስክረዋል።” 1ጴጥ.1፡11።” ኤለን ኋይት፣ የዘመናት ምኞት ገፅ 222 (በአማርኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች
1.እርስዎ ማድረግ የሚወዱትን ነገር እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ሊጠራ ይችላል በሚለው ኃሳብ ላይ ያሰላስሉ። ስለምንወደው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያደረግን እንደሆነ ለማወቅ የትኞቹን መርሆዎች እንከተል?

2.የዮናስን ታሪክ ያንብቡና ዮናስ ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ የሰጠበትን መንገድ ያስታውሱ። ከርሱ ልምምድ ምን አይነት ትምህርቶችን መውሰድ እንችላለን? እንዲሁም ዮናስና ጳውሎስ በጌታ ሲጠሩ የመለሱትን ምላሽ ያነፃፅሩ (ሐዋ. 9፡1-20ን ይመልከቱ።) በሁለቱ መካከል የነበሩ ዋና ዋና ልዩነቶች ምን ነበሩ?

3.”የይሁዳ ታሪክ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረ መሆን ሲችል በታቃራኒው በአስከፊ ሁኔታ የተደመደመ ሕይወትን ያመለክታል። ይሁዳ ወደ ኢየሩሳሌም ከተደረገው የመጨረሻ ጉዞ በፊት ሞቶ ቢሆን ኖሮ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ መሆን እንደሚገባውና ቀድሞ በመሞቱም ትልቅ እጦት እንደደረሰ ተደርጎ ሲታወስ ይኖር ነበር።” ኤለን ጂ.ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገፅ 754 (በአማርኛው)። ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ያስቡ። የርሱ ጥሪ ኢየሱስን ”ለመካድ” ነበር” እንደዚያ ከሆነ ለእርሱ እንዴት ፍትሐዊ ይሆን ነበር? ይሁዳንና የነበሩትን ዕድሎች በመጨረሻ ካደረገው አንፃር እንዴት እንረዳዋለን? በህይወታችን የምርጫ ነፃነት ስላለው ኃይል በተመለከተ ከእርሱ ታሪክ ምን ትምህርቶችን እንወስዳለን?