ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከመስከረም 24-30

2ኛ ትምህርት

October 5 - 11
ነህምያሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ነህምያ 1-2፤ዘዳ. 7፡9፤ መዝ. 23÷1-6፤ ዘሁ. 23፡19።


መታሰቢያ ጥቅስ “ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥ እንዲህም አልሁ፦ አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ” (ነህ. 1፡4-5)

እ ስካሁን በሁለት ጎራ ያሉ ምርኮኛ ወደ ይሁዳ መመለሳቸው ቢያንስ በከፊልም ቢሆን እግዚአብሔር ለዕብራውያን ዜጎች የገባው ቃል መፈፀሙን ያሳየናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ያዘጋጀው ሌላ ተጨማሪ የተመላሾች ቡድን አለ። በመጨረሻ የሚመለሱት ምርኮኞች አንድን ችግር እንዲያስተካክሉ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። ምንም እንኳን ሁለቱ ቡድኖች እየሩሳሌምን ዳግም ለመገንባትና ቤተመቅደሱን የማጠናቀቅ ስራን ለማከናወን ቢያቅዱም በዙሪያቸው በከበቧቸው ባላንጣ አገሮች ምክንያት የተቀረውን የግንባታ ስራ ማከናወን አልቻሉም። ከበዋቸው የሚገኙ የጎረቤት ህዝቦች እስራኤላውያን ከተማዋንና የከተማዋን ቅጥር እንዲገነቡ አይሹም፤ ምክንያቱም እንደከዚህ ቀደሙ እስራኤል ተመልሳ ኃያል ሀገር እንዳትሆን ስለሰጉ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ህዝቦቹን የጠራው ጥሪውን ለማሳካት በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ ሊተዋቸው አይደለም።

ስለዚህ ፈቃዱን እንዲያከናውንበት እና እቅዱን ይፈፅም ዘንድ አንድን ሰው አዘጋጀ። ይህም ሰው ነህምያ ይባላል። ስለ እርሱና በእግዚአብሔር ሥራ ስላደረገው ነገር እንመለከታለን።

የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለመስከረም 30 ይዘጋጁ።

መስከረም 25
Oct 06

ነህምያ መርዶ ሰማ


የነህምያ መጽሐፍ በተወሰነ መልኩ ከዳንኤል መጽሐፍ አጀማመር ጋር የሚመሳሰል ነገር አለው። (ዳን. 1፡1-2ን ያንብቡ) ይህም መጥፎ ዜና ነው። አዎን ብዙዎች ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው ቀዬ ተመልሰዋል በዛ ስፍራ ግን ነገሮች መልካም ሆነው አልጠበቋቸውም። ነህምያ 1፡1-4ን ያንብቡ። ነህምያ በምንድነው ያዘነው? ለሰማው አሳዛኝ ወሬ የመለሰው ምላሽስ ምን ነበር?አንዳንድ ቀደም ብለው የተማረኩ አይሁዳውያን ከአራቱ አስተዳደራዊ የፋርስ ግዛቶች መካከል ወደ ነበረችውና ነህምያም በቤተመንግስት የንጉሱ ጠጅ አሳላፊ በመሆን ሲያገለግል ወደ ነበረበት ሱሳ ተዛውረው ነበሩ። “ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው አናኒ” የሚለው አገላለፅ የደም ትስስር ያላቸው እንደሆነ አመላካች ነው፤ ምክንያቱም ነህምያ 7፡2 እርሱን እንደ ቤተሰቡ አድርጎ ጠርቶታል። ሆኖም ይህ ሌሎች እስራኤላዊ ወንድሞቹን የሚጠራበት መንገድም ሊሆን ይችላል።

ከአናኒ ጋር የተደረገው ንግግር ዕዝራ ወደ እየሩሳሌም ከተመለሰ ከ13 አመታት በኋላ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ445 ዓ.ዓ. በህዳር ወር አጋማሽና በታህሳስ ወር አጋማሽ መካከል እንደሆነ ይገመታል። አናኒ በእየሩሳሌም ያለው ሁኔታ አደገኛ መሆኑን ገለፀለት። ህዝቦችዋ ዳግም ከተማዋን መገንባት ተስኗቸዋል፤ ጠላት ደግሞ የተከማዋን ቅጥር በማፍረስ ከተማዋ ለጥቃት የተጋለጠችና የወደቀች እንድትሆን አደረገ።

ነህምያ ሰማርያውያን በከተማይቱ ቅጥር ላይ ስላደረሱት ጥፋት ጭምጭምታ ሰምቶ ሊሆን ቢችልም እስከዚህ ጊዜ ድረስ እርግጠኛ መረጃን አላገኘም ነበር።በተጨማሪም ንጉስ አርጤክስስ ከወንዙ ማዶ አቤቱታ ሲያቀርቡ የነበሩ ሰዎችን በመስማት ከምርኮ ተመልሰው ኢየሩሳሌምን ይገነቡ የነበሩትን በማስቆም ቅስማቸው እንዲሰበር አደረገ(ዕዝራ 4)። ምንም እንኳን ቤተ መቅደሱ ዳግም ቢገነባም አገልግሎት ላይ አልዋለም፤ ምክንያቱም በቤተመቅደሱ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች በእየሩሳሌም ኑሯቸውን ማድረግ ስላልቻሉ ነበር። የሰማው ወሬ ወደ ውስጡ ዘልቆ ስለገባ ጉዳዩ ነህምያን ክፉኛ አሳዘነው። አይሁድ እግዚአብሔርን ለማስከበር ተመልሰው ቢመጡም ያንን ማድረግ ግን አልቻሉም። በተቃራኒው ግን ጠላቶቻቸውንና ጨቋኞቻቸውን ስለፈሩ የእግዚአብሔርን ቤትና ቅድስቲቱን ከተማ ችላ አሉ።

ስለዚህ ነህምያ በፍጥነት ወደ አምላኩ ፊቱን መለሰ። የይሁዳ ሰዎች እምነት የላቸውም በማለት አላጣጣላቸውም ወይንም ደግሞ ሁኔታው እንዲሁ መሆን ስላለበት ነው ብሎም አልተቀበለም። ነገር ግን በጉልበቱ ተንበርክኮ መፀለይና መጾም ጀመረ። መጥፎ ዜና በሰማ ጊዜ ነህምያ አነባ፣ ጾመና ፀለየ። ይህ በከባድ መከራ ውስጥ ወደ ጌታ በምን መንገድ መቅረብ እንዳለብን ምን ይነግረናል?

መስከረም 26
Oct 07

የነህምያ ፀሎት


በነህምያ 1፡5-11 ላይ የሚገኘውን የነህምያን ፀሎት ያንብቡ። የፀሎቱ ይዘት ሆነው የቀረቡ ምን ምን ነገሮች አሉ? በፀሎቱ ላይ ራሱን ልክ እንደሌሎቹ ጥፋተኛ ያደረገው ለምንድነው?1.እግዚአብሔር ታላቅና የምህረት አምላክ (ነህ.1፡5) 2.ስማኝ (ነህ.1፡6) 3.የኃጢአት ኑዛዜ (ነህ. 1፡6-7) 4.ቃልኪዳንህን አስብ (ነህ. 1፡8-9) 5. እኛን ተቤዥተሀል (ነህ. 1፡10) 6. ስማኝ (ነህ 1፡11) የነህምያ ፀሎት የእግዚአብሔርን ታላቅነት የገለፀ፣ የእነርሱን ኃጢአተኝነት የጠቀሰ እና እርዳታን ሽቶ በመጮኽ የተደመደመ የፀሎት አካሄድ ነው። ይህ ፀሎት በዳን. 9 ላይ ዳንኤል ከፀለየው ፀሎት ጋር በብዙ መልክ የሚመሳሰል ሲሆን ነህምያ ከዚህ ቀደም ዳንኤል የፀለየውን ፀሎት የሚያውቅም ይመስላል። ነህምያ ለእርዳታ በመጮህ ፀሎቱን አለመጀመሩ እሙን ነው ከዛ ይልቅ ግን ስለ እግዚአብሔር ታላቅነትና አስደናቂነት ገለፀ። እግዚአብሄር ቃልኪዳን የሚጠብቅና ለሚወዱት ደግሞ ምህረትን እንደሚያደርግ ተናገረ። እግዚአብሔር ታማኝና አሁንም የማይለወጥ አምላክ እንደሆነ እያስታወሰው ነው።

ፀሎቱ የተለየ ቅርፅን ይዞ የቀረበ ነው (ከላይ እንደተገለፀው) ቁጥር 8 ላይ ትኩረት አድርጎ ነህምያ የእግዚአብሔር ቃልኪዳን ላይ አነጣጥሮ ጥያቄውን አቀረበ። ነህምያም አለ ‹‹አስብ›› በሌላ አገላለፅ ላንተ ታማኞች ካልሆንን እንደምትበታትነን አምላክ ሆይ አስብ ነገር ግን መልሰህ እንደምታመጣንና ሁሉንም ነገር እንደምታድስልን ቃል ገብተህልናል። የመጀመሪያው ነገር ሆኖ ስላለፈ ሌላውና ቀጣይ ነገር ሊሆን ይገባል ምክንያቱም ወዳንተ ተመልሰናልና። እግዚአብሔር በቃልኪዳኑ እርሱን ለመያዝ በምናሳየው ፈቃደኝነት ይደሰታል። የተስፋ ቃሎቹን አምነን ጮክ ባለ ድምፅ ለእርሱ እንድንነግረው ይሻል። እርሱ ለኛ ቃል የገባልንን ጉዳይ ቃል አውጥተን ስንናገር በተለይ ነገሮች በሙሉ ተስፋ የለሽ በሆኑበት ወቅት የተስፋ ቃሎቹ እጅጉን ያበረቱናል።

በአሁን ሰአት እግዚአብሔርን የሙጥኝ የምትሉበት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳኖች የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ቃል ኪዳኖች ተስፋ ሳንቆርጥ የሙጥኝ ብለን የመያዛችን አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? (በነበሩ በቃል ኪዳኖቹ ላይ ተስፋ ካጡ ምን ይቀርዎታል?)

መስከረም 27
Oct 08

ነህምያ ተናገረ


ነህምያ 1፡11 እንደሚነግረን ነህምያ የንጉሱ ጠጅ አሳላፊ ነበር። ለእኛ የዚህ ስራ አስፈላጊነት እምብዛም እንደ ሆነ እናስብ ይሆናል፤ ነገር ግን ጠጅ አሳላፊዎች ሁልጊዜ ከንጉሱ ጋር የመቅረብ እድል ስለነበራቸው ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ጠጅ አሳላፊዎች የተጠመቀው መጠጥ ንጉሱን እንዳያሳምም ወይንም እንዳይገድል ንጉሱን ለመከላከል ቀድመው ይቀምሳሉ። ሄሮደተስ እንደጠቀሰው ፐርሺያውያን ለጠጅ አሳላፊዎች ትልቅ ክብር አላቸው፤ እንደ ትልቅ ባለስልጣንም ይታያሉ።

ለምሳሌ የሶርያውያን ንጉስ ጠጅ አሳላፊ የነበረው ኢሳርሃዶን በመንግስት አገዛዙ ውስጥም የዋና ሚኒስቴር ቦታን የያዘ ሰው ነበር። ስለዚህ ነህምያም በአገዛዙ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን የያዘ ሰው ነው ወደ ንጉሱ ለመጠጋት ካለው እድል አኳያ እግዚአብሔር አይሁዳውያን ስላሉበት ከባድ ሁኔታ ለንጉሱ ሲናገር እንዲያግዘው ተማፀነ። ነህምያ 2፡1-8ን ያንብቡ። በነህምያ ጾምና ፀሎት ምክንያት ምን ውጤት መጣ?ኒሳን በተባለው ወር በግምት ሚያዚያ ወር 444 ከክ.ል.በፊት አካባቢ ፀሎቱ ምላሽን አገኘ። ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ የሚያውክ ዜና ነህምያ ጆሮ ከደረሰ አራት ወራት አልፈዋል። በነዚህ አራት ወራት ውስጥ ነህምያ ሲጾምና ሲጸልይ በነበረበት ወቅት እያንዳንዱ ቀን ሲያልፍ እግዚአብሔር ፀሎቱን ያልመለሰ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጊዜ ሁልጊዜ ፍፁም ነው። እግዚአብሔር ንጉሱ ነህምያን እንዲሰማና ጥሩ ምላሽ ይሰጠው ዘንድ እያዘጋጀው ነበር።

ጠጅ አሳላፊዎች ከስራ ሃላፊነታቸው አርፈው የሌላ አገር ገዥ እንዲሆኑ ማድረግ ያልተለመደ ተግባር ነበር። እግዚአብሔር በነህምያ በኩል ተናግሮ ንጉስ አርጤክስስን በማስደነቁ ነህምያ የይሁዳ አገረ ገዥ እንዲሆን ተሾመ። የንግስቲቱ ስም በዚህ ስፍራ ላይ መጠቀሱ የንጉሱ የቅርብ ሰዎች ብቻ የተገኙበት ዝግጅት መሆኑን ያሳየናል ምክንያቱም መደበኛ በሆኑ ዝግጅቶች ሁሉ ንግስቶች ስለማይገኙ ነበር። ንጉሡ ስለኢየሩሳሌም ቀደም ብሎ የሚያስበውን ኃሳብ ለማስቀየር ስለፈለገ ነህምያ ወዲያውኑ እየሩሳሌምን አልጠቀሰም ይልቅ በግሉ ስለሚያሳስበው ነገር ስሜትን በሚነካ መልኩ ተማፅንዖን አቀረበ። ከዛም ቦታውን በጠቀሰበት ሰዓት ንጉሱ በነህምያ ሃሳብ ተረቶ ነበር።

ነህምያ በችሎት ፊት የነበረውን ስፍራና ዳንኤል በባቢሎን የነበረውን ስፍራ ስናነፃፅር ምን ተመሳሳይ ነገሮችን እናያለን? ንጉሱ ለነህምያ የሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ስለ ነህምያ ባህርይ ምን ያስገነዝበናል?

መስከረም 28
Oct 09

ነህምያ ተላከ


ንጉሱ ደብዳቤውን በነህምያ አስይዞ ከወንዙ ባሻገር በሚገኘው ግዛት ለሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለሆሮናዊው ሰንበላጥና ለአሞናዊው ጦቢያ፣ ነህምያ ያሰበውን እንዲፈፅም መንገድ እንዲጠርጉ ላከ። በተጨማሪም ንጉሱ የርሱ ደን ጠባቂ የሆነው አሳፍ የከተማውን ቅጥሮችና የቤተ መቅደሱን ደጃፎች መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገውን ጣውላ እንዲሰጠው(እንዲያቀርብለት) አዘዘ።

ነህምያ 2፡9-10ን ያንብቡ። እነዚህ ቁጥሮች ነህምያና በአጠቃላይ አይሁዳውያኑ ሊገጥማቸው ስለነበረው ተቃውሞ ምን ይነግሩናል?ነህምያ ከክ.ል.በ. በ445/444 ዓ.ዓ አካባቢ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ነህምያ ምንም አይነት የተግባር እርምጃ ሳይወስድ ገና ጥያቄው ወደ አገረ ገዢው እንደደረሰ ነበር ተቃውሞ የተቀሰቀሰው። ጦቢያ “ጌታ መልካም ነው” የሚል ትርጉም ያለው የአይሁዳውያን ስም ቢሆንም (የልጁ ዮሃናን ስም የአይሁድ ስም ሆኖ ትርጉሙም “ጌታ የፀጋ አምላክ ነው” ማለት ቢሆንም) የአሞንን ግዛት ያስተዳድር ነበር። ስለዚህ ኢየሩሳሌም የተከበበችው በባላንጣዎችዋ ነበር፡- ሰንባላጥ በሰሜን በኩል የሰማሪያ ገዢ፣ ጦቢያ ደግሞ በምስራቅ በኩል የአሞን ገዢ፣ ጌሴም በደቡብ በኩል ኤዶምንና ሞዓብን ጨምሮ የአረብ ገዢ (ነህ. 2፡18-19)። የሚያሳዝነው ግን በዛ አካባቢ የነበሩ አመራሮች ሁሉ ነህምያ ለተጨቆኑት “ደህንነት” በማሰቡ አገለሉት። ፌዘኞች እነርሱ የሚያስጨንቋቸው መልካም ሲሆንላቸው ማየት አያስደስታቸውም።

የነህምያ በሰራዊት ታጅቦ “ኢየሩሳሌም መግባት ወሳኝ በሆነ አላማ መምጣቱን የሚያሳይ ቢሆንም ይህ ክስተት በከተማ አቅራቢያ የሚገኙና በአይሁድ ሕዝብ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ጥቃት በማድረስና በመሳደብ በየጊዜው ይገልፁ የነበሩ ጎሳዎችን ቅናት አነሳሳ። በነዚያ ክፉ ተግባራት ውስጥ የተሳተፉትም የጎሳዎቹ ዋነኛ መሪ የነበሩት ሆሮናዊው ሰንበላጥ፣ አሞናዊው ጦቢያ እና አረባዊው ጌሴም ነበሩ። እነዚህ መሪዎች በቅድሚያ የነህምያን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ አይን በማየት ስራውና እቅዱ እንዲከሽፍ ያላቸውን አቅም ሁሉ ተጠቅመው ከፍተኛ ጥረት አደረጉ” -Ellen G. white, prophets and kings, p.635።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈፀም በእግዚአብሔር የተጠሩ ስለገጠማቸው ተግዳሮት የሚገልፁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምን ምን ታሪኮች አሉ? በሰንበት ቀን ምላሽዎን ይዘው ይቅረቡ።

መስከረም 29
Oct 10

ነህምያ ለስራው ራሱን አዘጋጀ


እግዚአብሔር ለዚህ ኃላፊነት ነህምያን መጥራቱና የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላቱ ፈፅሞ የሚያጠራጥር አይደለም። በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እውቀት ታጥቆ እና በእርሱ ጥሪ እርግጠኛ ሆኖ ጉዞውን ቀጠለ። ነገር ግን አስቀድሞ በመጠንቀቅ እና በፀሎት ቆየ። በሌላ አባባል ምንም እንኳን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ ቢያውቅም ይህ እውቀቱ የሚያደርገውን ነገር እንዳያደርግ አላስገደደውም። ነህምያ 2፡11-20ን አንብቡ። ቅጥሩን የመገንባት ፕሮጀክቱን ለማዘጋጀት ነህምያ ምን አደረገ?የአመራር ትምህርቶች፡- 1ኛ ትምህርት፡- ነህምያ እቅዱ ምን እንደነበር ለማንም አልተናገረም። “ለእየሩሳሌም አደርገው ዘንድ እግዚአብሔር በልቤ ያኖረውን ነገር ለማንም አልነገርኩም” (ነህ. 2፡12)። ጉዳዩን የደበቀው ከጠላቶቹ ብቻ ሳይሆን ከአይሁድ መሪዎችም ጭምር ነበር። 2ኛ ትምህርት፡- ነህምያ ምንም ነገር ከማቅረቡ በፊት አስፈላጊ የሆነውን የቤት ስራና የስራ እቅድ አስቀድሞ ሰርቷል።

3ኛ ትምህርት፡ ስለ ስራው በሚናገርበት ጊዜ ነህምያ አስቀድሞ እግዚአብሔር ህዝቡን ከዚያ በፊት እንዴት እንደመራ በመጥቀስ በማስከተልም ንጉሱ የተናገረውን ቃል ይናገር ነበር። ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ ከመጠየቁ አስቀድሞ አበረታታቸው። ሊመጣ ያለው ተቃውሞ ቢኖርም ከተማዋን ለመገንባት አይሁዳውያኑ በቀናነት ምላሽ መስጠታቸው ተአምር አይደለም። እግዚአብሔር በነህምያ ጾምና ፀሎት ያዘጋጀው ንጉሱን ብቻ ሳይሆን የአይሁድ ህዝብም በድፍረትና በኃይል ምላሽ እንዲሰጡም አዘጋጅቷቸዋል።

ነህ. 2፡19-20ን ያንብቡ። ስለ ነህምያ እምነት እነዚህ ቁጥሮች ምን ይነግሩናል? ዘዳ. 7፡9፤መዝ. 23፡1-6፤ዘሁ. 23፡19 የመሳሰሉት አስደናቂ ጥቅሶች ነህምያን እንዴት አግዘውት ይሆን?> ንግግሮቻችን ማን እንደነበርንና ከልባችን ምን እንደምናምን ይገልፃሉ። ነህምያ ልብን ከፍ የሚያደርጉ ቃላትን ተናገረ። ሰዎች ቢያሾፉበት እንኳን በሚናገረው ንግግር ሁሉ ስለ እግዚአብሔር በመጥቀስ እርሱን አከበረ። ምንም እንኳን ጠላቶቹ በእነርሱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ቢያውቅም ቃላትን አልሰነጠቀም ስለ እግዚአብሔርም ከመናገር አልተቆጠበም። ከአያሌ አመታት በፊት ዮሴፍ በግብፅ እንደነበር ነህምያ እግዚአብሔርን በማያምኑ ህዝቦች መካከል ስለ አምላኩ ለመናገር አልፈራም።

መስከረም 30
Oct 11


ተጨማሪ ሀሳብ


“የእድል ሰው” pp.628-623, Prophets and Kings (ነቢያትና ነገስታት) በማንበብ አሰላስሉ። ነህምያ የፀሎት ሰው ነበር። “ነህምያ ለህዝቡ ሲል ልቡን በአምላኩ ፊት ያፈስ ነበር። ነገር ግን አሁን በሚፀልይበት ጊዜ ቅዱስ የሆነው አላማ አእምሮውን ወረሰው። የንጉሱን ይሁንታ ካገኘና ተግባሩን ለመፈፀም አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ማሟላት ከቻለ እርሱ ራሱ የእየሩሳሌምን ቅጥር ለማደስና የእስራኤል ህዝብን ጥንካሬ ለመመለስ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አሰበ።

እግዚአብሔር በንጉሱ ፊት ሞገስን እንዲሰጠውና እቅዱ እንዲሰምር ጠየቀ። “በዚህ ሰው ፊት ሞገስን አድርግለት፣ ዛሬ ለባሪያህ መከናወንን ስጠው” ብሎ ፀለየ። ለንጉሱ ጥያቄውን የሚያቀርብበትን አመቺ ጊዜ ለማግኘት አራት ወራትን ጠበቀ” -Ellen G. white,Prophets and Kings, pp.629-630።


የመወያያ ጥያቄዎች
1.ለረቡዕ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን በእግዚአብሔር የተጠሩ ሰዎች ሁሉ ከባድ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል ማለት ምን ማለት ነው? በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ይህ መሆኑስ ምን የሚሰጠን ትርጉም አለው? የተሻለው ጥያቄ ሊሆን የሚችለው፡የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈፀም የተጠራ ሰው ሆኖ ምንም ተቃውሞ ያልገጠመው በምሳሌነት የምናቀርበው ሰው በእርግጥ አለን? ለዚህ የምንሰጠው መልስ እግዚአብሔር ልንፈፅመው እንደጠራን ስናምንና የእርሱን ፈቃድ ስንፈፅም ጠንካራ መሰናክሎች ሲገጥሙን ፈፅሞ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን ምን ያስተምረናል?

2.ነህ. 2፡18ን ያንብቡ። የግል ምስክርነት ስላለው ኃይል ምን ይነግረናል? ነህምያ ከአይሁድ ወገኖቹ ላገኘው ቀና ምላሽ ይህ ምን ያክል አስፈላጊ ነገር ነበር? 3.ዕዝራም ይሁን ነህምያ ያለ ንጉሱ እገዛ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም። በሌላ አባባል እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች እግዚአብሔርን ከማያምኑ የፖለቲካ ባለስልጣናት ጋር አብረው ሰሩ። እንደ ቤተክርስትያን መቼና እንዴት ከፖለቲካ ሀይላት ጋር መስራት እንዳለብን ከዚህ የምንወስደው ትምህርት ምንድነው? ቤተክርስትያን ይህንን ስታደርግ መጠንቀቅ ያለባት ለምንድነው?

4.በጥናት ክፍልዎ የነህምያን ፀሎት ይመልከቱ (ነህ. 1፡1-11)። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ጥልቅ ይሆን ዘንድ ይህ ምን ትምህርት ይሰጠናል? ይህ ራስን ስለማስረከብ፣ ስለኑዛዜ እና የተስፋ ቃሉን ስለመጠማጠም ምን ያስተምረናል?