ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ታህሳስ 11-17

13ኛ ትምህርት

October 12-18
በእስራኤል የነበሩ መሪዎችሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- 1 ነገ. 12፡1-16፣ ሐዋ. 15፡7-11፣ ዮሐ. 11፡46-53፣ ነህ. 4፡7-23፣ ዕዝ. 8፡21-23፣31፣32።


መታሰቢያ ጥቅስ “ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ።” (ነህምያ 8፡12)

ዕ ዝራና ነህምያ ለእግዚአብሔር የተሰጡና ጌታ እንዲያደርጉ የጠራቸውን ስራ ለመስራት የቆረጡ ታላላቅ መሪዎች ነበሩ። ለእግዚአብሔር የነበራቸው ፍቅር ታማኝ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ አነሳሳቸው። በእርግጥም የነበራቸው ታማኝነት የጥናታችን ማዕከል ሆኖ ነበር።

በዚህ ሳምንት የዕዝራና የነህምያን ተምሳሌትነት ጨምረን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተምሳሌት የነበሩ መሪዎችን እንመለከታለን። ይህ ማለት ግን ሁሉንም መሪዎች በጥልቀት እንመለከታለን ማለት አይደለም ምክንያቱም ሌሎች ብዙ ልንማርባቸው የምንችላቸው መሪዎች ስላሉ ነው። ሆኖም የምንወስዳቸው ትምህርቶች በማንኛውም ደረጃ ላይ ለሚገኝ መሪ የሚጠቅሙ ናቸው። በዚህ ሰዓት ራስዎን እንደ መሪ አያዩ ይሆናል፤ ነገር ግን ሁላችንም በተወሰኑ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ እናሳድራለን ስለዚህ ትምህርቶቹ ዛሬም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው።

በነዚህ መሪዎች ታሪክ ውስጥ ማዕከል የሆነው ነገር የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉ አስተሳሰባቸውንና ህይወታቸውን ለውጦ መነቃቃትና ተሐድሶን አመጣ። የእግዚአብሔር ቃልና የመመሪያዎቹ ባለ ዕዳዎች ነበሩ። በተመሳሳይ መንገድ ማንም ሆንን ምን በየትኛውም ኃላፊነት ላይ እንሁን እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ክርስትያኖች የህይወታችን ማዕከል የእግዚአብሔር ቃል ሊሆን ይገባዋል። የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለታህሳስ 18 ሰንበት ይዘጋጁ።

ታህሳስ 12
Dec 22

የመሪዎች ተፅዕኖ


በመላው መጽሐፍ ቅዱስ መልካምና መጥፎ አንዳንዴም ሁለቱንም የያዙ የአመራር ተምሳሌቶችን እናገኛለን። ጥሩ ያልሆኑ መሪዎች አንዳንዴ መልካም ነገሮችን ሲፈፅሙ መልካም መሪዎችም አንዳንዴ ክፉ ነገሮችን ሰርተዋል። ደግሞም ሁሉም መሪዎች መልካምንና ክፉን ወይም ትክክለኛውንና የተሳሳተውን ነገር የማድረግ አቅም ያላቸው ሰዎች ናቸው። በራሱ ህይወት ውስጥ እነዚህን ነገሮች ያልተለማመደ ማነው? ችግሩ ግን መሪ ስትሆኑ መልካምም ይሁን ክፉ ትልቅ ተፅዕኖን ታሳድራላችሁ። በራስዎ ቤት፣ የስራ ቦታ ወይም ባሉበት ክበብ ብቻ እንኳን አሉታዊ ተፅዕኖን ማሳደር ራሱ የከፋ ነው። ነገር ግን በመንፈሳዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ በሁለቱም በአመራር ቦታ ላይ ስትሆኑ ተፅዕኖው ይሰፋል። በየትኛውም ኃላፊነት ላይ ቢሆኑ በተለይ እንደ መሪ የቃሉን መርሆዎችና አስተምህሮዎች የማንፀባረቅ አስፈላጊነት እጅግ ወሳኝ ነው። ቀጣዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ። በነዚያ ውስጥ ምን አይነት የአመራር ምሳሌዎችን እናገኛለን? መልካም ከሆኑ ለምን መልካም እንደሆኑ ይግለፁ። መጥፎም ከሆኑ ለምን? ሮብዓም (1 ነገ. 12፡1- 16)ጴጥሮስ (ሐዋ. ሥራ 15፡7-11)ኢዮስያስ (2 ነገ. 23፡1-10)ዲቦራ (መሳ. 4፡1-16)አክአብ (1 ነገ. 21፡1 – 16)በትንሹም ቢሆን ስለ መልካሙና ክፉው አመራር አይነቶች ከነዚህ ታሪኮች ምን ትምህርት እንወስዳለን? ባለንበት በየትኛውም ኃላፊነት ውስጥ የተማርናቸውን መተግበር የምንችለው እንዴት ነው?

ታህሳስ 13
Dec 23

በእግዚአብሔር አይን ክፉ


ከዚህ በመቀጠል የተጠቀሱትን ጥቅሶች ይመልከቱ። እነዚህ ጥቅሶች ስለነዚህ መሪዎችና በሚመሯቸው ሰዎች ላይ ስለነበራቸው ተፅዕኖ ምን ይነግሩናል? 1 ነገስት 15፡26፣342 ነገስት 13፡1 - 3ዮሐንስ 11፡ 46 - 53በየትኛውም ደረጃ መሪ ለሆንን የኛ አመራር ሰዎችን በመንፈስ ከፍ ወይም ዝቅ ሊያደርግ እንደሚችል ማሰብ ያስደነግጣል። በዚህ ቦታ በተጠቀሱት በሁሉም ደግሞ ተፅዕኗቸው በአስገራሚ ሁኔታ አሉታዊ ነበር።

በተለይም ደግሞ ባህሪያችንና ለክርስቶስ ያለን መሰጠት በምናገኛቸው ላይ ልዩነትን ይፈጥራል። መንፈሳዊ መሪዎች ራሳቸው ጌታን የሚፈልጉ ከሆኑ ወደ ጌታ ካልሆኑም ወደ ክፉው ይመራሉ። ከላይ ካየናቸው በተቃራኒ ዕዝራና ነህምያ ከእግዚአብሔር ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራቸው አይካድም። በነዚህ መጽሐፎች የተጠቀሱት ፆምና ፀሎቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ታላላቅ መሪዎች ከፆሟቸው ጾሞች በቁጥር ይበልጣሉ። ምንም እንኳን ሁሉም ፍፁም ባይሆን በነርሱ አመራር ዘመን ሀገሪቱ ከእግዚአብሔር ጋር እየተራመደች ነበር። የህይወታቸው አቅጣጫ ወደ እግዚአብሔር ነበር። በሌላ በኩል በዕዝራና ነህምያ ተፅዕኖ ያልተነኩ (ያልተለወጡ) ሰዎች መኖራቸው የሌላ የማንም ሳይሆን የራሳችን እምነት በዋናነት በእኛ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የሚያስረግጥ ነው። ደግሞም ኢየሱስን በስጋ ዓይን ለማየት፣ ሲያስተምር ለመስማትና ተዓምራት ሲያደርግ ለማየትና ስለ ስለታደሉትና በመጨረሻ ስለገፈተሩት ሰዎች ያስቡ። አዎን በህይወታን በምንም አይነት ኃላፊነት ላይ ብንሆን መልካም ወይም ክፉ ተፅዕኖ የማሳደር ሚና አለን። ነገር ግን በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፊት እያንዳንዱ ሰው ስለራሱ መልስ ይሰጣል።

በእርስዎ የተፅዕኖ ክበብ ውስጥ ስላሉት ሰዎች ያስቡ። ተፅዕኖዎን የበለጠ ወደ መልካም ማዘንበል የሚችሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ታህሳስ 14
Dec 24

ጥንካሬና ማበረታቻ


ነህምያ 4፡7-23ን ያንብቡ። የነህምያ ጥንካሬ የታየው በምን መልኩ ነው? ይህን ብርታት የሰጠው ምንድነው?ነህምያ አይሁድን ካስፈራሩት የህዝቡ ጠላቶች በተቃራኒ ቆመ፤ ሕዝቡን ለጦርነት በማዘጋጀትም ምላሽ ሰጠ። ነህምያ “እሺ ጌታ ሆይ ሁሉንም አንተ አድርገው” ብሎ አልተቀመጠም። በተቃራኒው ሕዝቡ ከነርሱ የሚጠበቀውን እንዲያደርጉ አደረገ። ቅጥሩን እየሰሩ ሰይፍንና ሌሎች መሳሪያዎችን አነሱ (ያዙ)። በነህምያ ምሪት ስር የነበሩት አይሁዳውያን ከመፍራት ይልቅ በድፍረት ራሳቸውን ለመከላከል የጦር መሳሪያን ያዙ። ነህምያ ህዝቡን አበረታታ፣ እምነት ጣለባቸው፣ አብሯቸው ሠራ እናም የሚሰሩትን ኃላፊነት ሠጣቸው። ኃላፊነት እንደ መስጠቱ ደግሞ ሥራውን እንዲሰሩ አስታጠቃቸው። ሆኖም ነህምያ ህዝቡ ማድረግ ያለባቸውን ነግሯቸው ከዚያ በቤቱ አልተደበቀም። ከጎናቸው ሆኖ መደረግ ያለበትን ከባድ ስራ ሁሉ አደረገ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ብቻ ሲዋጋ ህዝቡ ቆሞ ብቻ እንዲያይ የተናገረባቸው ጊዜያት እንዳሉ ሁሉ “ለሥራ (ለጦርነት) ተዘጋጁ እኔም ድል እሠጣችኋለሁ” ያለበትም ሌሎች ብዙ ምሳሌዎች አሉ። የእግዚአብሔርን በረከትና ማሻገር መመልከት ከፈለግን ከኛ የሚጠበቀውን እናድርግ። “ለእግዚአብሔር ሥራ የነበረው መሰጠትና በእግዚአብሔር መታመኑ ነህምያ በጠላቶቹ ቁጥጥር ውስጥ እንዳይወድቅ ረዳው። ሰነፍ የሆነ ሰው በፈተና ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ ይወድቃል፤ ከፍ ያለና የማይነቃነቅ አላማ ባለው ሰው ህይወት ውስጥ ክፉው ሊያገኝ የሚችለው ጥቂት ስፍራ ብቻ ነው። በየጊዜው የሚያድግ ወደፊት የሚቀጥል ሰው እምነት አይደክምም፤ ምክንያቱም የማያልቀው ፍቅር ለራሱ መልካም የሆነውን በዚያ ሰው ለማከናወን ከላይ፣ ከታችና ከጎኑ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። የእግዚአብሔር እውነተኛ አገልጋዮች በፀጋው ዙፋን ሁልጊዜ ስለሚተማመኑ በማይነቃነቅ ግለት ይሰራሉ።” ኤለን ጂ.ኋይት ነቢያትና ነገስታት በእንግሊዘኛው፣ ገፅ 660።

በመጨረሻ ነህምያ ጥንካሬውን ያገኘው ስለ እግዚአብሔር መኖርና ስለ ኃይሉ ስለተረዳ ነበር። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው እግዚአብሔርን ማወቁ እምነቱን በተግባር እንዲገልፅ ረዳው። አውዱ የተለየ ቢሆንም በነህምያ ውስጥ ያየነው ነገር “ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ፤ እኔም ስራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል። (ያዕቆብ 2፡18) የሚለውን የሚያንፀባርቀው እንዴት ነው?

ታህሳስ 15
Dec 25

ዓላማና ግለት


ቀጣዮቹ ጥቅሶች በዕዝራና ነህምያ ህይወት ውስጥ እየመራ ስላለው ነገር ምን ያስተምሩናል? (ነህ. 2፡1-10፣ ዕዝራ 7፡8-10)በሚያደርጉት ሁሉ ዕዝራና ነህምያ የእግዚአብሔር ፈቃድ በህዝቡ ህይወት ውስጥ እንዲከናወን ይፈልጉ ነበር። አዎ ህዝቡ አጥፍቷል፤ ለዚያም ተቀጥቷል። እግዚአብሔር ግን እንደሚመለሱ ለገባው ቃል ታማኝ ስለነበረ ህዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲመለሱ መንገዱን ከፈተላቸው፤ ታማኝ ከሆኑም ያሰበላቸውን ግብ ለመፈፀም ተዘጋጀ። እናም እግዚአብሔር በጥበቡ እንደ ሙሴ አይነት ሁለት የተሰጡ ሰዎች ልክ የሙሴን ትውልድ እንደተጠቀመ ለዚህ መታደስም ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ መረጣቸው።

እንደነዚህ አይነት ታላላቅ መሪዎች ግብ አላቸው። እያንዳንዱን ተግባራቸውን የሚያንቀሳቅስ የሕይወት አላማ አላቸው። ዕዝራና ነህምያ በህይወታቸው አላማ ነበራቸው ብለን መናገር እንችላለን። የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲደርስ የሚፈልጉት ቦታ አለ፤ ያንን ግብ ለመድረስ ደግሞ ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው ተጠቀሙ። ዕዝራ ይህንን ያሳካው ቃሉን በማጥናትና ለህዝቡም ቃሉን በማስተማር ነበር። ነህምያ ህዝቡ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉና ለእግዚአብሔር በድፍረት እንዲቆሙ አበረታታቸው። ሁለቱም ኢየሩሳሌም ታድሳ ማየት ይፈልጋሉ መታደሱ ግን ቁሳዊ ብቻ እንዲሆን አልፈለጉም። በነዋሪዎቹ ህይወት መንፈሳዊ መነቃቃትና ተሃድሶ ማየት ፈልገዋል። ሲያርሙ፣ ሲገስፁና የተወሰነ ተግባር እንዲፈፀም ሲፈልጉ የነበረው በዚህ ምክንያት ነው። ታላላቅ መሪዎች ከተለመደውና ከሚታሰበው ከፍ ባለ ነገር ያምናሉ። ዕዝራና ነህምያ በአፍቃሪ፣ ኃያልና ተዓምር አድራጊ አምላክ የሚያምኑና ሁሉም ሰው ከእርሱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዲኖረው የሚፈልጉ ነበሩ። ከነህምያ ምዕራፍ አንድ ስንጀምር ነህምያ ለእግዚአብሔር ነገር የነበረው መሰጠትና በህዝቡም ዘንድ ስለነበረው ውድቀት የተሰማውን ሐዘን ማየት ያስደንቃል።

በምዕራፍ 1 እስራኤላውያን በይሁዳ እየገጠማቸው ስለነበረው ከባድ ነገር ሲሰማ አለቀሰ። በጉልበቱ ተንበርክኮ እግዚአብሔር ያለውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ቃል ገባ። ነህምያ በአለም ላይ ልዩነትን ማምጣት በሚለው ኃሳብ የተመራ ይመስላል። የተግባር ሰው ለእግዚአብሔር የሚሰራ ሰው ነበር። ነህምያ ልዩነት ለመፍጠር የመረጠው ከፍተኛ ደሞዝን ወይም ከፍተኛ ስልጣንን ለማግኘት ብሎ አልነበረም (ሁለቱንም በፋርስ አግኝቷቸው የነበረ ቢሆንም)። ነገር ግን በእያንዳንዱ እርምጃ ተቃውሞ እየገጠመው ብዙም ሐብታም ወዳልሆነችው ይሁዳ ሄደ። ምንም አይነት ተግዳሮቶች ቢገጥሙት በእምነት ወጣ።

ታህሳስ 16
Dec 26

ራስን ማዋረድና ፅናት


ዕዝራ 8፡21-23፣31፣32ን ያንብቡ። እርስዎ ዕዝራ ንጉሡን ለመጠየቅ ማፈሩን እንደ ሞኝነት ይቆጥሩታል ወይስ እንደ ጀግንነት? ዕዝራና ህዝቡ ራሳቸውን ያዋረዱት እንዴት ነበር?በእርግጥ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነህምያ የንጉሡን ጥበቃ ተቀብሏል። በዕዝራ አጋጣሚ ውስጥ ግን እግዚአብሔር ራሱን በተሻለ የሚገልፀው ከንጉሡ ምንም ነገር ባይጠይቁ እንደሆነ አምኗል። ስለዚህ ወደ ይሁዳ በሰላም ሲደርሱ እግዚአብሔር እንደጠበቃቸው ይረዳሉ፤ ምስጋናም ይሰጣሉ። ምናልባት በአንዳንድ ሁኔታዎች በሰዎች ላይ እጅግ እንታመንና እግዚአብሔር ግን ራሱን እንዲገልፅ በበቂ ሁኔታ አንታመንበትም። በዚህ ሁኔታ ዕዝራ እግዚአብሔር ሥራውን እንዲሰራ በመፍቀድ እግዚአብሔር ኃያል አምላክ መሆኑን ለንጉሱ አረጋገጠለት።

ሆኖም ዕዝራ በመሰለኝ አልተንቀሳቀሰም። ህዝቡን ሁሉ ጠራና በጉዳዩ ላይ ፆመው ፀለዩ። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ ሳይወስዱ ጉዟቸውን አልጀመሩም። በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን አዋርደው ከለላ እንዲያደርግላቸውና ከለላውም የኃይሉ ምልክት እንዲሆን ጠየቁ፤ እግዚአብሔርም መለሰ። ነህምያ 5፡14-19ን ያንብቡ። ነህምያ ራሱን ያዋረደው እንዴት ነበር?እውነተኛ መሪዎች እራሳቸውን ለማዋረድ የሚፈቅዱና አገልጋይ ሊሆኑ ይገባል። ብቁ መሪዎች ክብርን ለማግኘት “ማዕረግ” አይፈልጉም። ነህምያ በሩ ክፍት የሆነና ለህዝቡ በልግስና የሰጠ መሪ ነበር። በእግዚአብሔር ማመኑን በተግባር አሳየ፤ ለእግዚአብሔር የነበረው አስደናቂ መሰጠት ለህዝቡ አርአያ የሆነ ነበር። ጠንካራ ስብዕና የነበረውና የተበላሸ ባህሪ ያልነበረው ቢሆንም ራሱን ከሌሎች ከፍ አድርጎ አላስቀመጠም። በጊዜው በአይሁድ ህዝብ ከፍተኛው ማዕረግ ላይ የነበረ ቢሆንም ያልተኮፈሰ ነበር። በዚህ መንድ ኢየሱስ ሰዎችን ለመምራት የተሻለው መንድ ማገልገል እንደሆነ ያስተማረውን በተግባር ገልጧል። ኢየሱስ አድርጎታል፣ እኛም በየትኛውም ማዕረግ ላይ ብንሆን ተመሳሳዩን ልናደርግ ይገባናል።

“ተቀምጦ አሥራ ሁለቱን ጠርቶ፡- ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው።” ማርቆስ 9፡35 እነዚህ የክርስቶስ ቃላት በእግዚአብሔር አይን እውነተኛ መሪ መሆን ማለት እንዴት እንደሆነ ምን ያስተምሩናል?

ታህሳስ 17
Dec 27


ተጨማሪ ሀሳብ


“ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ” ከሚለው መጽሐፍ ስለ ፀሎት የተፃፈውን ያንብቡ። “ከምርኮ የተመለሱት በዘሩባቤል፣ ዕዝራና ነህምያ አመራር የሠሩት የተሐድሶ ሥራ በምድር ታሪክ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ሊመጣ የሚገባውን መንፈሳዊ ተሐድሶ የሚያሳይ ነው። የእስራኤል ሕዝብ ለጠላት ጥቃት የተጋለጡ ደካሞች ቢሆኑም በእነርሱ ውስጥ ግን ጌታንና ህጉን ማወቅ ተጠብቆ እንዲቆይ እግዚአብሔር ሠራ። የእውነተኛው አምልኮና የተቀደሱት መልዕክቶች (እሴቶች) ጠባቂዎች ነበሩ።

ቤተመቅደሱንና የከተማይቱን ቅጥር መልሰው ሲገነቡ የተለያዩ ልምምዶችንና ጠንካራ ተቃውሞዎችን መጋፈጥ ነበረባቸው። የዚህ ሥራ መሪዎች ከባድ ሸክም ቢሸከሙም በማይነቃነቅ ልበ ሙሉነት፣ በተዋረደ መንፈስና እውነቱ ድል እንዲነሳ እግዚአብሔር እንደሚሰራ ጠንካራ እምነት በመያዝ ወደፊት ቀጠሉ። ልክ እንደ ንጉስ ሕዝቅያስ ነህምያም “ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፤ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፤….. ትዕዛዛቱን ጠበቀ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።” (2ነገ 18፡ 6-7)” ኤለን ጂ.ኋይት፣ ነቢያትና ነገስታት በእንግሊዝኛው ገፅ.677።


የመወያያ ጥያቄዎች
1.መሪዎቻችንን ለምንድነው? ለመደገፍ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ያለብን
2.የአገልጋዩ አመራር ዘዴ ከባድ፣ ብዙ ሥራ የሚጠይቅና በተመሳሳይ ደግሞ መልካም ውጤት ያለው የሆነው ለምንድነው? የቤተ ክርስትያን መሪም ቢሆን የአገልጋይ ልብ ሊኖረው የሚገባው ለምንድነው?
3.በመጽሐፉ መጀመሪያ መጨረሻና እንዲሁም መሐል ላይ ነህምያ ይፀልይ ነበር። ዕዝራና ነህምያ ሁለቱም የፀሎት ሰዎች ነበሩ። በዕዝራና ነህምያ መጽሐፍት ውስጥ “ፀሎት” እና “ፀለየ” የሚሉት ቃላት ምን ያክል ጊዜ እንደተጠቀሱ ይቁጠሩ። እነዚህ መሪዎች በቀጣይነት ሲፀልዩ ነበሩ። ያ ስለ እኛ የፀሎት ህይወት ምን ሊነግረን ይገባል?
4.“ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፤ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፤ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትዕዛዛቱን ጠበቀ።” (2ነገ.18፡6)። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር መጣበቅ የሚችለው እንዴት ነው? ከእግዚአብሔር ጋር መጣበቅ ትዕዛዛቱን ከመጠበቅ ጋር የሚያያዘውስ እንዴት ነው?