ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ታህሳስ 4-10

12ኛ ትምህርት

October 5 - 11
ከመጥፎ ውሳኔዎች ጋር መጋፈጥሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ነህ. 13፡23-25፤ ዘዳ. 7፡3-4፤ 2ኛ ቆሮ.6፡14፤ ዕዝራ 9 እና 10፤1 ቆሮ. 7፡10-17።


መታሰቢያ ጥቅስ “እንዲህ ስል ፀለይሁ “አምላኬ ሆይ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ሆኖአል፣ በደላችንም እስከ ሰማያት ደርሶአል አምላኬ ሆይ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ለማድረግ ፈራሁ እጅግም ፈራሁ።”(ዕዝራ 9፡6)

እ ስራኤላውያን ካልሆኑ ህዝቦች ጋር በጋብቻ መተሳሰር ልማድ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ዕዝራና ነህምያ መሪዎቹ ሆኑ። ህዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲመሰርት መምራት ስለሚፈልጉ ሁለቱም መሪዎች ይህ ጉዳይ እጅጉን አሳሰባቸው። ከዚህ ቀደም በታሪክ እንዳጋጠማቸው መጥፎ ውጤት ሁሉ አማኞች ያልሆኑና ጣኦት አምላኪዎች በእስራኤላውያን ላይ የሚፈጥሩት መጥፎ ተፅዕኖ እንዳለ በደንብ ተገንዝበዋል። የከነአናውያን ሃይማኖት በእስራኤላውያን ዘንድ ከመንሰራፋታቸው የተነሳ በየኮረብታዎቻቸው በአልንና አሽታሮትን እስከ ማምለክ ደርሰዋል። ከዚህም በላይ አህዛብ የሆኑ የትዳር አጋሮች በእስራኤል ቤተሰቦች ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ እጅግ የከፋ ነበር። በለዓም ሞአባውያን ሴቶቻቸውን ወደ እስራኤል እንዲልኩ ሲመክራቸው እነዚያን ሴቶች ሲከተሉ ከእግዚአብሔር መንገድ ፈቀቅ እንደሚሉ እርግጠኛ ነበር። አሳዛኙ ነገር እርሱ ትክክል ነበር። የትዳር አጋሮች እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን የገዛ ልጆቻቸው እምነት ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። ነህምያና ዕዝራ ስለ እስራኤላውያን የጋብቻ ጉዳይ ምን አደረጉ? ነገሩን ችላ አሉት ወይስ በፅናት ተቃወሙት? በዚህ ሳምንት ሁለቱ መሪዎች ይህንን ጉዳይ በምን መንገድ እንዳስተናገዱት እናያለን። የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለ ሰንበት ይዘጋጁ።

ታህሳስ 5
Dec 15

የነህምያ አፀፋዊ ምላሽ


ነህምያ 13፡23-25ን ያንብቡ። እዚህ ጋ የሆነው ነገር ምንድነው? ነህምያ በዚህ ጉዳይ የመለሰውን ምላሽ በምን መልኩ እንገልፀዋለን?ልጆቹ የአረማይክን(በስደት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረውን ቋንቋ) ወይም ዕብራይስጥ ቋንቋ መናገር ስላልቻሉ የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ማስተዋል አልቻሉም። በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር መገለጥ እውቀት ሊበረዝ ብሎም ከነአካቴው ሊጠፋ ስለሚችል ይህ ትልቅ ችግር ነበር። ፀሐፍት እና ቀሳውስት መልዕክቱን ለህዝቡ የበለጠ ግልፅ ለማድረግ የቶራን መጽሐፍ የሚያብራሩት በአረማይክ ቋንቋ ነበር። ሆኖም ዋና አሳዳጊዎቻቸው የሆኑት እናቶቻቸው ከአሞን፣ ከአሽዶድና ከሞአብ ስለነበሩ ልጆቹ የአባቶቻቸውን ቋንቋ መናገር አለመቻላቸው እምብዛም አያስደንቅም። የምንናገረው ቋንቋ የዛን አገር የተለመዱ የመዝገበ ቃላት ቋንቋዎች ስለምንጠቀም ስለተለያዩ ፅንሰ ኃሳቦች ያሉንን ግንዛቤዎች ያንፀባርቃሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቋንቋዎችን አለማግኘት ማለት የማንነታቸውን መለያ ማጣት ማለት ነው። ስለዚህ ለነህምያ በሀገሪቱ የነበሩ ቤተሰቦች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የነበራቸውን ቁርኝት አልፎም የዕብራውያን ጌታ ከሆነው ህያው አምላክ ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ሲያጡ ማየት ፈፅሞ የማይታሰብ ጉዳይ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚገልፁት ነህምያ ያደረገው ማለትም በአደባባይ ህዝቦችን ማሳፈሩ በወቅቱ እንደ ቅጣት የሚታይ ጉዳይ ነበር። ነህምያ ገሰፃቸው እና ረገማቸው ሲል የቃል ኪዳኑን እርግማን በእነርሱ ላይ መናገሩን እንጂ ስድብና አስነዋሪ ቃላትን እንደተናገረ ልናስብ አይገባም። ዘዳግም 28 ቃል ኪዳኑን በማያከብሩ ላይ ስለሚመጣባቸው እርግማን ይተነትናል። ነህምያ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት መምረጡ የስህተት ተግባራቸውን እና ባልተገባ ምርጫቸው የተነሳ የመጣባቸውን መዘዝ እንዲያስተውሉ ስለፈለገ ነው። ከዚህም በላይ ጥቅሱ “አንዳንዶቹን መታኋቸው ፀጉራቸውንም ነጨሁ” (ነህ. 13፡ 25) ብሎ ሲነግረን ነህምያ በጭካኔ እርምጃ እንደወሰደ ከማሰብ ይልቅ መምታት የተለመደ የአደባባይ ቅጣት እንደነበረ መረዳት አለብን። ይህ አቀጣጥ ደግሞ “አንዳንዶችን” ማለትም ያልተገባ ባህሪን ባንፀባረቁና በመሩ መሪዎች ላይ ነበር። ይህ አይነት እርምጃ በአደባባይ በሰው ፊት የማሳፈር ዘዴ ሆኖ አገልግሎአል። ነህምያ የህዝቡ ምርጫ ወዴት ስቦ እንዳመጣቸውና ምን መዘዝ እንደፈጠረባቸው እንዲያስተውሉ ፈልጓል። በቤተክርስቲያን ውስጥ የምናምነው ነገር የተሳሳተ ተግባር መሆኑን ስንረዳ እንዴት ልናስተናግደው ይገባናል?

ታህሳስ 6
Dec 16

የነህምያ ዘለፋ


ነህምያ 13፡26-27ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ ከትክክለኛው ጎዳና ሸርተት ስንል ስለሚገጥመን ነገር እንድናውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ስላላቸው ሚና ምን ይነግረናል?ሰለሞን በመረጠው ምርጫ አማካኝነት በኃጢአት አዘቅት ውስጥ ሰጠመ። ሰለሞን ለእስራኤል ነገስታት እግዚአብሔር የሰጠውን ማለትም “ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ” (ዘዳ. 17፡17) የሚለውን ትዕዛዝ ባለመታዘዙ በራሱ ላይ ጥፋት አመጣ። የሰለሞን ህይወት እንደመጥፎ ምሳሌነት የቀረበው ከአንድ በላይ ሚስቶችን ስላገባ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ነህምያ እንደጠቀሰው እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሴቶችን ስለመረጠ ነው። ነህምያ እግዚአብሔርን ከማያምኑ ጋር በጋብቻ በመተሳሰራቸው መገሰፁ ትክክል የነበረው ለምንድነው?ዘፍ. 6፡1-4፣ ዘፍ. 24፡3-4፣ ዘፍ. 28፡1-2፣ ዘዳ. 7፡3-4 እና 2 ቆሮ. 6፡14።ትዕዛዙ አንድ ህዝብ ከሌላው አገር ህዝብ ጋር እንዳይጋባ የሚከለክል ሳይሆን ጣኦት አምልኮን የሚያወግዝ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎችን አግብተዋል። ሙሴ ምድያማዊቷን ሲጳራን አግብቷል፤ ቦኤዝ ሞአባዊትዋን ሩትን አግብቷል። የዚህ ጋብቻ ትዕዛዝ ትኩረቱ የተለየ እምነት ያላቸውን ወይም እምነት የሌላቸውን ሰዎች ስለማግባት ነው። ችግሩ በዕዝራና በነህምያ ጊዜ የነበሩ ህዝቦች እግዚአብሔርን የሚያምኑ ህዝቦችን ለጋብቻ ያለመምረጣቸው ሁኔታ ነበር። ሪቻርድ ኤም ዴቪድሰን Flame of Yahweh (Peabody, mass: Hendrickson Publishers, 2007) በሚለው መጽሐፉ እንደጠቀሰው “ስለ ጋብቻ በኤደን ገነት የታቀደው እቅድ በመንፈሳዊው እምነትና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች የሁለቱ ተጣማሪ አካላት በመተጋገዝ አንድ እንዲሆኑ ይጠይቃል” ገጽ 316። እግዚአብሔርን የማያምኑት ሚስቶች የጣኦት አምልኳቸውን ለመተው እንደተስማሙ ታሪኩ አይነግረንም። በውጤቱም ነህምያ በህዝቡ ምርጫ ከመቆጣት ይልቅ በጣም አዘነ። ምክንያቱም ይህ ለእርሱ የሚያሳየው ለእግዚአብሔር ማሳየት የሚገባቸውን ቁርጥ አቋም ማጣታቸውን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ተመስርተን እንዴት መዝለቅ እንዳለብንና ደስታችንን እንዴት ማብዛት እንዳለብን ሊተገበር የሚችል ቀመርን ይሰጠናል። በተመሳሳይ መልኩ በእኩል ደረጃ ሆኖ በጋብቻ ቀንበር መጠመድ የተሻለ ህይወት እንድንመራና ለእግዚአብሔር መሰጠታችን እንዲጨምር ያደርጋል። ከዚህ ታሪክ ውስጥ ዛሬ እምነታችንንና ቤተሰቦቻችንን መጠበቅ እንድንችል የሚያግዙንን ምን ምን መርሆዎች ልንወስድ እንችላለን?

ታህሳስ 7
Dec 17

ዕዝራ ምላሽ ሰጠ


ዕዝራ 9ን አንብቡ። ዕዝራ ስለ እስራኤላውያን የተቀላቀለ የጋብቻ ሁኔታ ሲሰማ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ዕዝራ 9፡1 እና 2 ላይ እንደሚገልፅልን “ራሳቸውን አልለዩም”። “አልተለዩም” የሚለው ቃል በቀጣዮቹ ቁጥሮች ላይም ተጠቅሷል። ዘሌ. 10፡10፣ 11፡47፣ ዘፀ. 26፡33፣ ዘፍ. 1፡4፣6፣7፣14፣18። የዚህ ቃል አጠቃቀም አማኝ ከማያምን ጋር የሚጋባበትን ሁኔታ የሚገልፅልን በምን መልኩ ነው?ህዝቡ በጋብቻ ስለ መቀላቀል ጉዳይ ለመነጋገር ወደ ዕዝራ ቀረቡ። የተወገዙትን ህዝቦች ዝርዝር የገለፁበት የቋንቋ አገላለፅ ስለ ቶራህ(አምስቱ የሙሴ መጽሐፍት) የነበራቸውን እውቀት ያሳያል። ይህም ዝርዝር ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ነበር። የሚደንቀው የህዝቡ መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ካህናት እና ሌዋውያን የዚህ በደል ተጠያቂዎች ስለነበሩ ዜናውን ለዕዝራ ሹክ ያሉት የመንግስት አመራሮች ነበሩ።

“ለባቢሎን ምርኮ የዳረጋቸውን መንስኤ ዕዝራ በሚያጠናበት ጊዜ የተረዳው ነገር ቢኖር እስራኤል ሃይማኖቱን በስፋት እንዲተው ያደረገው ነገር ከአረማውያን ህዝቦች ጋር በመቀላቀሉ ነበር። የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጠብቀው ዙርያቸውን ከከበቡዋቸው ህዝቦች ራሳቸውን ቢለዩ ኖሮ ከአሳዛኝና አንገት ከሚያስደፋ ታሪክ ባመለጡ ነበር። ካለፈው ታሪካቸው ሳይማሩ ታላላቆቹ መሪዎች ሃይማኖታቸውን እንዳይክዱ የሚጠብቃቸውን ህግ ሲተላለፉ ሲያይ ልቡ በውስጡ ተናወጠች።

የትውልድ ሀገራቸውን መሬት እንደገና እንዲረግጡ እግዚአብሔር እድል ስለሰጣቸው ስለ እግዚአብሔር በጎነት እያሰበ ስለ ክፋታቸውና ምስጋና ቢስነታቸው በማዘን የፅድቅን ቁጣ ተቆጣ።” Ellen G. white, prophets and kings p.620 “ተለዩ” የሚለው ቃል ሁለት አካላት እንዳሉ ያመለክታል። እንደውም ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ መሆናቸውን ይገልፃል። ይህንን ሲጠቅሱ ህዝቡ ከሐሰተኛ እምነት ይርቁ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትዕዛዝ ያስተውሉ እንደነበር ገለፁ። ማንም ሰው ተቃራኒ እምነት ከሆኑ የትዳር አጋሮች ጋር መጣመር በጋብቻው ግንኙነት ላይ እና ልጆችን በሚያሳድጉበት ወቅት ምንም ተፅዕኖ አያመጣም ሊል እንደማይችል ተረድተዋል። ጉዳዩ ምን ያክል ከባድ እንደሆነም አስተውለዋል።

ባለፈው ህይወታችን የተሳሳተ ውሳኔን ወስነን የቆየን ቢሆንም በቤታችንና በቤተሰባችን ውስጥ ህያው የሆነ እምነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ታህሳስ 8
Dec 18

የዕዝራ እርምጃ


ዕዝራ 10ን ያንብቡ። ዕዝራና መሪዎቹ በጋብቻ የመቀላቀልን ሂደት እንዴት አድርገው አስቀሩ?የተሰበሰበው ጉባኤ በሞላ በአንድነት ባዕዳን ሚስቶቻቸውን ወደ ስፍራቸው ለመስደድ ወሰኑ። በሚያስደንቅ ሁኔታ በዕዝራ 10፡15 ላይ ከተጠቀሱት አራት ሰዎች በስተቀር ሌሎቹ ተጋቢዎች በእቅዱ ተስማሙ። አይሁዳውያን ሴት የትዳር አጋራቸውን ወደ ቀድሞ ስፍራቸው እንዲሄዱ ለማድረግ ቃል ገቡ እቅዱም እስኪፈፀም ሶስት ወራትን ወሰደ። በስተመጨረሻ 111 አይሁዳዊ ወንዶች ሚስቶቻውን ሰደዱ (ዕዝራ 10፡18-43)። የመጨረሻው ቁጥር ላይ እንደሚገልፅልን (ዕዝራ 10፡44) ባዕዳን ሚስቶች ካገቡት ውስጥ አንዳንዶቹ ልጆችን ወልደው ነበር። እናትና ልጆችን ከቤተሰብ ነጥሎ መስደድ ለኛ ተገቢነት ያለው ወይም ትክክለኛ ውሳኔ አይመስልም። ቢሆንም ግን ማስታወስ የሚገባን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በአይሁድ ህዝብ ላይ ስራውን ለመስራት እነርሱም ከእርሱ ጋር በመተባበር የተነሱበት ወቅት ስለነበር ነው። ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን መከተል ደግሞ ትልቅ የለውጥ እርምጃን መውሰድን ይጠይቃል። በዕዝራ 10፡11 እና 19 ላይ “ተለዩ” (badal) እና “ገለል በሉ” (yatza) የተባሉት ቃላት በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የትዳር ፍቺን ለመግለፅ አልተጠቀመበትም። ዕዝራ ለፍቺ ይጠቀሙ የነበረውን የቋንቋ አገላለፅ ቢያውቅም እዚህ ጋር ግን ሊጠቀመው አልወደደም። ዕዝራ ግልፅ አድርጎ ያስቀመጠው የቶራን መፅሐፍ ትዕዛዝ የሻረ እስከ ሆነ ድረስ ጋብቻውን እንደ ትክክለኛ ጋብቻ መቁጠር አልፈለገም። በሌላ አገላለፅ ከህጉ ተቃራኒ በመሆኑ ጋብቻው ተሰርዟል። ታዲያ ቀጣዩ ሂደት ያልፀደቀውን ጋብቻ ማፍረስ ነው። ሆኖም እነዚህ ሚስቶችና ልጆቻቸው ምን እንደገጠማቸው እና በማህበረሰቡ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖን እንዳመጣ የተነገረን መረጃ የለም። በዛን ጊዜ በነበረው ባህል መሰረት የቀድሞ ባሎች የቀድሞ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ሲልኩ የመንከባከብ ኃላፊነት ነበረባቸው። ሚስቶችም ወደ አባቶቻቸው ቤት ተመልሰው ይገባሉ።

ከጊዜያት በኋላ አንዳንድ አይሁዳውያን በድጋሚ ባዕዳንን ማግባት ጀመሩ፤ ምናልባትም አንዳንዶች ቀድመው ወድደዋቸው ወደነበሩት ሚስቶቻቸው ተመለሱ። የመጣው መፍትሔ አጭር ዕድሜ ብቻ የኖረው በሰው ልጅ ደካማ ተፈጥሮና ለእግዚአብሔር ያለን መሰጠት በየጊዜው ከፍና ዝቅ ስለሚል ነው። ራሳችንን እንደ ጠንካራ አማኝ የምንቆጥር ሰዎች እንኳን ከእርሱ ጋር በነበረን ጉዞ ለእርሱ መሰጠት ከሚገባን በታች የወረደ ህይወት ኖረን እንደነበር ልንቀበል ይገባል። የሚያሳዝነው የሰው ዘር እግዚአብሔርን በማስቀደም ትግል ውስጥ ይኖራል። እርስዎ “ለእግዚአብሔር ያነሰ መሰጠት” ባሳዩበት ወቅት የእርስዎ የሕይወት ተሞክሮ ምን ይመስል ነበር? ከነዚያ የሕይወት ተሞክሮዎች ምን ትምህርት ወሰዱ?

ታህሳስ 9
Dec 19

ጋብቻ ዛሬ


በዕዝራና ነህምያ ስለ ተቀላቀለ ጋብቻ ባየነው መሰረት እግዚአብሔር ጋብቻን በትኩረት እንደሚያይ ግልፅ ሆኖልናል፤ እኛም እንዲሁ ልንሆን ይገባናል። ስለምናገባው የህይወት አጋራችን በአንክሮ ልንፀልይ በውሳኔዎቻን ላይም እግዚአብሔርን ልናካትት ይገባናል። እግዚአብሔር በሰጠን መርሆዎች ታማኞች ለመሆን ልንወስን ይገባናል ይህም ከሃዘንና ምስቅልቅል ካለ ህይወት ይታደገናል። ክርስቲያኖች ያላመኑ የትዳር አጋሮች ሲኖሯቸው ሁኔታውን ጳውሎስ በምን መንገድ እንዳስተናገደ እስቲ ይመልከቱ። 1ኛ ቆሮ. 7፡10-17ን በትኩረት ያንብቡ። ዛሬ በማይመች አካሄድ የሚጠመድ ጋብቻን በተመለከተ ምን ማድረግ ይገባናል?ከተለያዩ እምነቶች ስለሚደረግ ጋብቻ ሁኔታ ጥልቅ የሆነ ትዕዛዝና ማብራሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባናገኝም አማኝ የሆነን ሰው ከማታምን የትዳር አጋሩ መለያየት ከጥቅሱ ኃሳብ ጋር የሚቃረን ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔ ነው። የዕዝራና ነህምያ ጉዳይ ግን የአንድ ጊዜ ክስተት ሲሆን የእግዚአብሔርም ፈቃድ ነበር(ዕዝራ.10፡11)። ምክንያቱም እስራኤል ወደፊት እንደ ማህበረሰብ እግዚአብሔርን የማምለኩ ጉዳይ አደጋ ላይ ስለነበር ነው። ህያው አምላኩን እንደሚያመልክ ህዝብ ያላቸውን ማንነት እያጡ ነበር።

አይሁዳውያን በግብፅ ምድር መንቀሳቀስ በማይችሉበት ሁኔታ ሰፍረው በነበሩበት ወቅት የገዛ መሪዎቻቸው በጋብቻ መቀላቀልን ፈቀዱላቸው ወዲያውም ያህዌን ከባዕድ እንስት ጣኦት ጋር የቀላቀለ እምነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ። ከዚህም በተጨማሪ የመሲሁ የዘር ግንድ መስመር አደጋ ላይ ሆነ። ስለዚህ ይህ የአንድ ወቅት ክስተት ብቻውን ያመነና ያላመነ በአንድ ጋብቻ በሚኖሩበት ጊዜ ጋብቻውን ለማፍረስ እንደ መፍትሄ ኃሳብ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም። ይህ ጥቅስ በጋብቻ በሚመች አካሄድ ስለተጣመሩ ሰዎች እግዚአብሔር ትልቅ ስፍራን እንደሚሰጥ ይገልፃል። ለእግዚአብሔር እንድንሰጥ ከማያደፋፍረን ሰው ጋር በጋብቻ ስንጣመር ሰይጣን ይደሰታል። ምክንያቱም ሁለቱ ተጣማሪዎች ተመሳሳይ መሰጠት ካላቸው አንዱ ብቻ ታማኝ ከሆነበት ጋብቻ ይልቅ የእግዚአብሔርን የተልዕኮ ስራ በኃይል እንደሚሰሩ ያውቃልና።

ከማያምን ሰው ጋር በማይመች አካሄድ እንዳንጠመድ መጽሐፍ ቅዱሳችን በግልፅ እየመከረንም (2 ቆሮ. 6፡14) ከዚህ በተቃራኒ ለሄዱትም ፀጋ ሲበዛላቸው ተመልክተናል። እግዚአብሔር ያላመኑ ሰዎችን ያገቡትን ለእርሱና ለትዳር አጋራቸው ታማኞች ሆነው እንዲዘልቁ ያበረታታቸዋል። እግዚአብሔር ከእርሱ ፈቃድ የሚፃረር ምርጫን ስንመርጥ እንኳን አይጥለንም፤ ለእርዳታ ስንማፀነውም ይረዳናል። ይህ ማለት ግን ያሻንን ሁሉ አድርገን እግዚአብሔር እንዲባርከን መጠበቅ አለብን ማለት አይደለም ይልቁኑም በትህትና ልብ እርሱን ስንፈልግ ሁልጊዜም ያደምጠናል። ያለ እግዚአብሔር ፀጋ ለማናችንም ተስፋ የለንም ምክንያቱም ሁላችንም ኃጢያተኞች ነን።

ታህሳስ 10
Dec 20


ተጨማሪ ሀሳብ


Ellen G.white “Reformation” pp.669-678 in Prophet and Kings. “እግዚአብሔር ላስቀመጠው ተግባር መጠመድ የእውነተኛ ሃይማኖት ወሳኝ ድርሻ ነው። ሰዎች የእርሱን ፈቃድ ለመተግበር ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው እንደ መሳሪያነታቸው ስራውን ለመስራት ሊጓጉ ይገባል። በትክክለኛው ጊዜ የሚደረግ ፈጣን የሆነ የውሳኔ ተግባር የክብር ሽልማትን ያስገኛል መዘግየትና ችላ ማለት ግን ውድቀትንና እግዚአብሔርን አለማክበርን ያመጣል። መሪዎች ለእውነት ቅንአት ከሌላቸው ቸልተኞች እና አላማ ቢስ ከሆኑ ቤተክርስትያንም ቸልተኛ፣ ሰነፍ እና ተድላን ብቻ የምትወድ ትሆናለች። ነገር ግን እግዚአብሔርና እግዚአብሔርን ብቻ ለማገልገል በቅዱስ አላማ ከተሞሉ ህዝቦች አንድነት ያላቸው፣ ባለ ተስፋዎችና ጉጉት የሚታይባቸው ይሆናሉ።”

“የእግዚአብሔር ቃል በሁለት በኩል የተሳለ ስለት ነው ተቃራኒ የሆነውን ነገር ይመታል። ሐጢያትና ቅድስና ጎን ለጎን ተቀምጠዋል ስለዚህ አንዱን ትተን ሌላውን እንቀበላለን። የሰንበላጥና ጦቢያ ጥላቻ ሐሰተኝነት እና ክህደትን የተረኩልን እነዚህ ገጾች የዕዝራንና ነህምያን ጥበበኝነት፣ መሰጠት እና ራስን መስዋዕት ስለማድረግ ይገልፁልናል። እኛም እንደ ምርጫችን ከሁለት አንዱን ወስደን በመተግበር ነፃነት ተሰጥቶናል። እርሱን በመታዘዝ ከምናገኘው በረከት በተቃራኒም ህጉን ስንተላለፍ ስለሚመጣብን አስፈሪ ውጤት አይተናል። እኛ ራሳችን አንዱን ምርጫ በመምረጥ ሌላውን በመተው መወሰን ይገባናል።” -ellen G.white, prophets and kings, p.676.


የመወያያ ጥያቄዎች
1.ታሪኮቹን በምናነብበት ጊዜ በመጀመሪያ ህዝቦቹ በእግዚአብሔር የተሰጡ እንዳልነበሩ አድርጎ ይነግረናል ለዚያም ነው ባዕዳን ሚስቶችን የመረጡት። ነገር ግን ዕዝራ በውሳኔያቸው አልተዋቸውም ነገር ግን ለውጥን ያመጡ ዘንድ እንዲታረሙ ገሰፃቸው። ታዲያ ለውጡ በእርግጥ መጣ? ባህሪያቸውን በመለወጥ ውስጣቸው ተለወጠ ለእግዚአብሔር ያላቸው መሰጠት በእርግጥ አደገ? ብዙዎች እንዳልተለወጡ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለን? የልብ ለውጥ ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ ከእነርሱ ስህተት የምንማረው ወሳኝ ነገር ምንድነው?
2.ባልተገባ ጋብቻ ውስጥ ሆነው በብዙ ችግር ለሚዳክሩ የቤተክርስቲያናችን ሰዎች በምን አይነት መልኩ እርዳታችንን ልንለግሳቸው እንችላለን?
3.የእግዚአብሔር መርሆዎች ዘላለማዊና ፍፁም ቢሆኑም ባህሎች ግን በየጊዜው ይለያያሉ። እነኚህን ልዩነቶች በአዕምሮአችን ይዘን የእግዚአብሔርን መርሆች ለህይወታችንና ለሁኔታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?