ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ህዳር 27-ታህሳስ 3

11ኛ ትምህርት

Sep 28 - Oct 4
ወደ ኋላ ያፈገፈገ ሕዝብሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ነህ. 13፡1-19፣ ዘዳ. 23፡3-6፣ ነህ. 13፡10-14፣ ዘሁ. 18፡21-24፣ ነህ. 13፡15-22 ፣ዮሐ. 5፡5-16።


መታሰቢያ ጥቅስ “ሌዋውያኑም ራሳቸውን እንዲያነፁ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፣ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። አምላኬ ሆይ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ እንደ ምህረትህም ብዛት ራራልኝ።” ነህ. 13፡22

በ ምዕራፍ 12ና 13 መካከል ነህምያ ወደ ባቢሎን ተመልሷል። ሄዶ ለምን ያክል ጊዜ እንደቆየ ባናውቅም ሲመለስ ግን (ምናልባትም ከ430-425 ዓ.ዓ አካባቢ) ህዝቡ በእምነታቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው ነበር። ከጣኦት አምላኪዎች ጋር ላለመጋባት፣ ሰንበትን ለመጠበቅና አስራትና ስጦታ በመስጠት ቤተመቅደሱንና አገልጋዮቹን ለመንከባከብ ቃል ቢገቡም (ነህምያ 10) ሶስቱንም ቃሎቻቸውን አጥፈው ነበር።

ነህምያ በተመለሰበት ወቅት ህዝቡ ለእግዚአብሔር በነበራቸው መሰጠት ግድየለሽ ሆነው አገኛቸው። ህዝቡ አስራትንና ስጦታን መመለስን አቁመው የቤተመቅደሱን ክፍሎች ለሌላ አላማ መጠቀም ጀምረው፣ ሰንበትን መጠበቅ አቋርጠው እና በአካባቢያቸው ከነበሩ ሕዝቦች ጋር ወደ መጋባት ተመልሰው ነበር። ከሁሉ የባሰው ደግሞ ህዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር በነበራቸው ግንኙነት ልል እንዲሆኑ ሚናን የተጫወቱት ነህምያ ከመሄዱ በፊት የሾማቸው መሪዎች መሆናቸው ነው። ብዙ ነገሮች ተለዋውጠው ሲያገኛቸው ነህምያ ቢበሳጭ አይገርምም። ሆኖም ሁኔታውን ከመቀበል ይልቅ ለእግዚአብሔር ክብር ሲል ሁኔታውን ለመለወጥ ተንቀሳቀሰ። ለታህሳስ 4 ቀን ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ህዳር 28
Dec 08

የተበላሸ ሃይማኖታዊ አመራር


ነህምያ ምዕራፍ 13 በመካከላቸው ስለነበሩት አሞናውያንና ሞዓባውያን መፃተኞች ያሳሰበውን በመናገር ይጀምራል (ነህ. 13፡1-13)። እነዚህ ቁጥሮች የሚናገሩት ከሌላ ዘር ሆነውም እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ስለማስወጣት ሳይሆን የተለየ እምነት ወይም ጣኦት አምላኪዎችን ስለማስወጣት ነው (ዘዳ. 23፡3-6)። ነህምያ 13፡1-9ን ያንብቡ። ኤልያሴብና ጦቢያ እነማን ነበሩ? ያደረጉት ነገር ትክክል ያልነበረው ለምን ነበር? ነህ. 2፡10፣19፣3፡1፣12፡ 10፣22፣13፡28ን ያንብቡ።ኤልያሴብና ጦቢያ በነህምያ መጽሐፍ ውስጥ በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው። ኤልያሴብ የሀገሪቱ ሊቀካህንና የቤተመቅደሱ ኃላፊ ነበር። ጦቢያ ደግሞ በኢየሩሳሌም የነበረውን የነህምያን ስራ አጥብቆ የሚቃወም ከአሞን የሆነ ጠላት ነበር። በኤልያሴብና በጦቢያ መካከል ወዳጅነት የተፈጠረው በጋብቻ በመዛመዳቸው ነበር።

ስለተዛመዱበት መስመር ተፅፎ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም ጦቢያ የአይሁድ ስም ስለነበረው (“እግዚአብሔር መልካም ነው” የሚል ትርጉም ያለው) ከአይሁድ የዘር ግንድ የመጣ እንደሆነ ይገመታል። የሚስቱ ቤተሰቦች ማንነታቸው ባይገለፅም ከአራህ የዘር ግንድ የመጡ ሲሆን ከኤልያሴብ ቤተሰብ ጋር የተዛመዱት እነርሱ እንደሆኑ ይታመናል። በተጨማሪም የነህምያ ሌላኛው ጠላት የሆነው የሆሮናዊው ሳንባላጥ ሴት ልጅ ከኤልያሴብ የልጅ ልጅ ጋር ተጋብታ ነበር። ስለዚህ በነህምያ ላይ የተሸረበው ሴራ እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በምድሪቱ የነበሩት ከፍተኛ ባለስልጣናት አንድ ሆነው ከነህምያ አመራር በተቃራኒ ቆሙ።

አስተዳዳሪው በሌለበት ሊቀ ካህኑ ለአስራትና ስጦታዎች ማስቀመጫነት የተሰራውን ክፍል ለጦቢያ ሰጠ። ለጦቢያ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቋሚ መኖሪያ ሲሰጠው ከሀገሪቱ መሪዎች እንደ አንዱ የሚያስቆጥረው ነበር። በመጨረሻ የነህምያ ጠላቶች ዘመናቸውን ሁሉ ሲፈልጉት የነበሩትን አገኙ፡- ነህምያን አስወግዶ የርሱን ቦታ መውሰድ። ጥሩነቱ ነህምያ ቁጭ ብሎ አለማየቱ ነበር።

በታሪክ ሁሉ ማለትም በጥንታዊቷ እስራኤል የነበሩት አይሁዶች ወይም በአዲስ ኪዳን ዘመን እነርሱን የተከተሏቸው ክርስትያኖች በቀላሉ ወደ ስህተት ሄደዋል? የነርሱን ስህተት እንዳንደግም ምን እናድርግ?

ህዳር 29
Dec 09

በእርሻ የነበሩት ሌዋውያን


ነህምያ 13፡10-14ን ያንብቡ። ነህምያ በዚህ ቦታ መፍትሔ ሊያበጅለት እየሞከረ ያለው ጉዳይ ምን ነበር?ዘማርያኑ፣ የበር ጠባቂዎቹና ሌሎቹ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች የእግዚአብሔር ሥራ ድጋፍ እያገኘ ስላልነበረ ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ በራሳቸው እርሻ መስራት ግድ ሆነባቸው። እጅግ በጥንቃቄ የተዘረጋው የአስራትና የሥጦታ ስርዓት በሙሉ ፈራርሶ ነበር። ነህምያ እንደገና መጀመር ነበረበት። ከክፍሉ ውስጥ ሁሉንም ዕቃ አውጥቶ መወርወሩ በነገሩ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን የሚያሳይ ነበር።

“ቤተመቅደሱ የደረሰበት ንቀት ብቻ ሳይሆን ስጦታዎቹም አላግባብ ውለው ነበር። ይህም ህዝቡ መለገሱን እንዲያቋርጥ አደረገው። ግለታቸውን አጥተው አስራታቸውን ለመመለስ ችላ አሉ። የእግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤት እጦት ሲያጋጥመው ዘማሪዎቹና ሌሎቹ የቤተ መቅደሱ ሠራተኞች በቂ ድጋፍ ስላላገኙ የእግዚአብሔርን ሥራ ትተው ሌላ ሥራ ለመስራት ሄዱ።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ነቢያትና ነገስታት፣ ገፅ.670 ይሁዳ ሁሉ እንደገና በአንድነት ተሰብስቦ የፈራረሰውን እንደገና ሲጠግኑ ማየት ያስደንቃል። ህዝቡ ነህምያ ያደረገው ሁሉ ለህዝቡ ጥቅም እንደሆነ ስለገባቸው ከጦቢያና ከኤልያሴብ በተቃራኒ በነህምያ በኩል ቆሙ። በተጨማሪም ነህምያ የዕቃ ቤት ኃላፊነቶችን ቀናና ታማኝ ለነበሩት ሰጠ። ኃላፊነታቸውም አስራትና ስጦታዎችን መሰብሰብ የተሰበሰቡትን በጥንቃቄ መጠበቅና ለሚገባቸው ደግሞ በተገቢ ሁኔታ ማከፋፈል ነበር። በሌላ አማርኛ ነህምያ መጥቶ የአመራሩን ብልሹ አሠራር በመጥረጊያ ጠራረገ።

ነህምያ በቤተመቅደሱ አሠራር ውስጥ አዳዲስ ታማኝ ሃላፊዎችን ቢሾምም ሊቀካህኑ ኤልያሴብ ከአሮን የዘር ግንድ የተሰጠው ስለነበር ስልጣኑን አላጣም ነበር። የሊቀ ካህኑ ኃላፊነቶች መሆን በሚገባቸው ሥራዎች ላይ ነህምያ ሌሎችን በመሾሙ የኤልያሴብ ሥራ ተገድቦ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁንም ሊቀ ካህን ነበር። ነህምያ “አምላኬ ሆይ ስለዚህ አስበኝ፤ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ።” (ነህ. 13፡14) ብሎ ፀልዮአል። በዚያ ፀሎት ውስጥ ከሰው መሆኑን የሚያሳይ ምን ነገር ነበር?

ህዳር 30
Dec 10

አስራቶችና ስጦታዎች


ነህምያ የቤተመቅደስ አገልግሎቶችን ሲያድስ አስራቶችና ስጦታዎች የሚሰበሰቡትንና የሚከፋፈሉበትን ሥርዓትም አድሶ ነበር።

ነህምያ 18፡21-24ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች አስራቶችና ስጦታዎች ለቤተመቅደስ አገልግሎቶች ብቻ ሳይሆን ለዛሬም ቢሆን ስላላቸው አስፈላጊነት ምን ይነግሩናል?አስራቶችና ስጦታዎች ካልተሰበሰቡ ቤተመቅደሱ ስራውን ሊያከናውን አይችልም። አስራት መመለስ ሲቀር የቤተ መቅደሱ አገልግሎቶች ፈራረሱ፤ የአምልኮ ስርዓቱ በሙሉም በስጋት ውስጥ ወደቀ። የቤተመቅደሱ አገልጋዮች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ሌላ ስራ ለመፈለግ ሲሄዱ ቤተመቅደሱን መንከባከብ ላይ ሊያተኩሩ አልቻሉም። በውጤቱም ለእግዚአብሔር ይደረግ የነበረው አምልኮ ቀነሰ። “የአስራት ስርዓት ቀላል በመሆኑ ማራኪ ነበር። ከሀብታሙም ከደሃውም ተመጣጣኝ ነገር ይጠበቃል። የርሱን ንብረት እንድንጠቀምበት በሰጠን ልክ እኛም አስራት ልንመልስ ይገባናል።”

“እግዚአብሔር አስራትን ሲጠይቅ ከምስጋና ወይም ከልግስና ስጦታ ጋር አላያያዘውም። ለእግዚአብሔር በምናደርገው ሁሉ የምስጋና ልብ ሊኖረን ቢገባንም አስራት የምንመልሰው እግዚአብሔር ስላዘዘን ነው። አስራት የእግዚአብሔር ነው፤ እርሱም እንድንመልስለት ይጠይቀናል” ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች እንዲህ ያምናሉ (2ኛ ዕትም) ገፅ. 304 በእስራኤላውያኑ ቤተመቅደስ እንደሆነው ያለ አባላት አስራቶችና ስጦታዎች ቤተክርስትያናችን ለመቀጠል ትቸገራለች። ጊዜያቸውን ጥራት ላለው አገልግሎት፣ ዕቅድና የቤተክርስትያን አስተዳደርን ለመፈፀም የሚከፈላቸው ሰዎች ከሌሉ ቤተክርስትያን አትኖርም። ለእግዚአብሔር የሚሰጠው አምልኮም ጥራቱ ይቀንሳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያለ አስራትና ስጦታዎች የወንጌል ሥራ ለመኖር አይችልም።

በተጨማሪም አስራትን የምንመልሰው እግዚአብሔር ያንን ስርዓት በቃሉ ውስጥ ስላቋቋመው ነው። እግዚአብሔር ለምን አንድን ስርዓት እንዳቋቋመ መግለፅ የማይጠበቅበት ጊዜያት አሉ። በርሱ አመራር ስር ሆነን እንድንታመነው ይፈልጋል። አገልግሎቱ እንዴት እንደሚከወን ልናውቅ ይገባናል ከዚያ በኋላ ግን በእጁ አሳልፈን ልንሰጠው ይገባናል።

አስራት ለመንፈሳዊ ህይወታችን የሚጠቅመን በርሱ ለመታመናችንም መለኪያ የሚሆነው ለምንድነው?

ታህሳስ 1
Dec 11

በሰንበት ወይን መጥመቅ


ነህምያ 13፡15-16ን ያንብቡ። ነህምያ በዚህ ቦታ ስለምን እየተናገረ ነው?በቁጥር አናሳ ከሆኑት ውስጥ ሆኖ ለእግዚአብሔር መቆም ቀላል አይደለም። እግዚአብሔር ሰንበት ማንም ሥራ የማይሰራባት የተቀደሰች ቀን ትሁን ስላለ ይህ ትዕዛዝ በኢየሩሳሌም ተግባራዊ እንዲሆን ነህምያ ተንቀሳቀሰ። ይህንን ውሳኔ መያዝ እንዳለበት የሞራል ግዴታ ተሰማው ከዚያም ወደ ተግባር ገባ። ሰንበት በፍጥረት ሳምንት መጨረሻ የተቀመጠችው ሰዎች በሌላ ቀን ለእንጀራቸው ሮጠው ከሚገኙት በተለየ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በመውሰድ እንዲታደሱ የተሰጠች ልዩ ቀን ስለሆነች ነው።

“እስራኤላውያን ሰንበትን ከጠበቁት ይልቅ ሰንበት እስራኤላውያንን ጠብቋቿል” ተብሎ ይነገራል። ነጥቡ ሰባተኛው ቀን ሰንበት በእግዚአብሔር ፀጋ ሊጠብቋትና በርሷ የሚገኘውን አካላዊና መንፈሳዊ ጥቅም ለማጣጣም ለሚሹ ሁሉ እምነታቸው ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጓ ነው።

ነህምያ 13፡17-22ን ያንብቡ። ነህምያ በሰንበት እየተካሄደ የነበረውን “መግዛትና መሸጥ” ለማስቆም ምን አደረገ?ነህምያ የአይሁድ ገዢ ስለነበር የርሱ ሥራ ህግን ማስፈፀም እንደሆነ ተረዳ። የአይሁድ ህጎች ደግሞ በእግዚአብሔር ህግ ላይ የተመሰረቱ ስለነበሩ ሰንበትን ጨምሮ በአጠቃላይ የህጉ አስፈፃሚ ሆነ። በአይሁድ የተከበሩ የነበሩት ሰዎች ሊቀካህኑ ሲያጠፋ ተቃውመውት ቢሆን ኖሮ ነህምያ ራሱን በዚህ ቦታ ላያገኘው ይችል ነበር። ምናልባት ገዢዎቹና የተከበሩቱ ቀደም ብሎ ነህምያ ለድሆች መመለስ ያለባቸውን ስላስመለሳቸው ቅር ተሰኝተውበት ኤልያሴብና ጦቢያ ነገሮችን ሲያበላሹ አይተው ምንም ተቃውሞ አልሰነዘሩ ይሆናል።

ነህምያ መጀመሪያ የተከበሩትን ከገሰፀ በኋላ በሮቹ እንዲዘጉና ጠባቂዎች እንዲቆሙ አደረገ። የገበያ ቦታው ከከተማ ውስጥ ወደውጭ ሲሸጋገር የበለጠ ጠንካራ እርምጃን በመውሰድ በቀጣዩ ሰንበት ነጋዴዎቹ ከመጡ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠነቀቃቸው። ከዚያ በኋላ ነጋዴዎቹ ያልተመለሱት ነህምያ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ቢሆን ነው።

ታህሳስ 2
Dec 12

አባቶቻችሁ ይህን አላደረጉምን?


ነህምያ ለሰንበት የነበረው ቅናት አስደናቂ ነው። ነህምያ ሰንበት በትክክል እንድትጠበቅ ከነበረው ፍላጎት የተነሳ ከሌላ ሀገሮች የመጡ ነጋዴዎች ላይ እጁን እንደሚያነሳባቸው አስጠነቀቀ። በሌላ አማርኛ በሌላ ሰንበት እንደገና በከተማው ውስጥ ወይም በበሮቹ ቢያገኛቸው ራሱ ሊቀጣቸው ይችል ነበር ማለት ነው። እንደ አስተዳዳሪ ይህ ትዕዛዝ እንዲጠበቅ ለማድረግ ህጋዊ ኃላፊነቶች ነበሩት። “ነህምያ ኃላፊነቶቻቸውን ችላ ስላሉ በድፍረት ተጋፈጣቸው። “ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድነው? የሰንበትን ቀን ታረክሳላችሁን? አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚህ ከተማ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተም ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ።” ከዚያም የኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ እንዲዘጉ እና ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ ተዘግተው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጠ። የኢየሩሳሌም ሹማምንት ከሾሟቸው ይልቅ የእርሱ አገልጋዮች ላይ ስለተማመነ የርሱ ትዕዛዝ መፈፀሙን እንዲያረጋግጡ አገልጋዮቹን በበሩ ሾማቸው።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ነቢያትና ነገስታት ገፅ. 671-672

ነህምያ ስለ ሰንበት መርከስና አጠባበቁን በተመለከተ ስለተጣሱት ነገሮች የሰጠው ማስጠንቀቂያ በዘመናት ሁሉ እስከ ኢየሱስ ዘመን ጭምር ሲስተጋባ የቆየ መልዕክት ነው። ይህንን የምናውቀው ኢየሱስ ከሐይማኖት መሪዎች ጋር ሰንበትን በትክክል መጠበቅን በተመለከተ ሲከራከር ስለነበረ ነው።

ማቴዎስ 12፡1-8፣ ማርቆስ 3፡1-6፣ ሉቃስ 6፡6-11 እና ዮሐንስ 5፡5-16ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ የተነሳው ጉዳይ ምን ነበር? የጥንታዊ እስራኤልን ታሪክ ማስተዋል ያ ግጭት እንዴት እንደተነሳ ለማብራራት የሚጠቅመን እንዴት ነው?እነዚህ መሪዎች በተሳሳተ መንገድ ላይ ሆነው እንኳን ሰንበት እንዳትረክስ ከነበራቸው ቅናትና ማጥበቅ የተነሳ “የሰንበት ጌታ” የሆነውን ኢየሱስን እንኳን ሽረሃል ብለው እስከ መክሰስ ደረሱ። መልካም ነገርም (ማርም) እጅግ ሲበዛ ይመራል እንደሚባለው ብዙዎቹ ሰዎች ስለ ህጉ እጅግ ጠንቃቆች ቢሆኑም የህጉን “ዋና ነገሮች” ማለትም “ፍትህ፣ ምህረትና እምነትን” (ማቴ. 23፡23) ረሱ።

ከሰንበት ጋር የተያያዘ ቢሆን ወይም በሌላ አስፈላጊ ጉዳይ እንደ ግለሰብ እና እንደ ቤተክርስትያን እነዚህ ሰዎች የሰሩትን ስህተት ደግመን እንዳንሰራ መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ታህሳስ 3
Dec 13


ተጨማሪ ሀሳብ


ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ ከገፅ 115-126 “በጌታ ደስ እንዲለን” የሚለውን ምዕራፍ ያንብቡ። “የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ፣ ማስጠንቀቂያዎቹን፣ በዚህ ኃጢአት ምክንያት ቀደምቷ እስራኤል ላይ ስለወረደው አስፈሪ ፍርድ ሲያስታውሳቸው ልቦናቸው ተነሳስቶ የተሐድሶ ስራ ስለጀመረ የእግዚአብሔር ቁጣ ተከልክሎ በረከቱ ተላከ።”

ከቤተመቅደሱ አመራሮች መካከል ያገቧቸውን አህዛብ ሚስቶች ላለመለየት ጥያቄ ያቀረቡ ነበሩ። ነገር ግን በማዕረግ ወይም በስልጣን ላይ ስለነበሩ አልተደላላቸውም፤ ሁሉም በእኩል ተቀጡ። ከካህናቱ ወይም ከመሪዎቹ መካከል ከጣኦት አምላኪዎች ጋር አልለያይም ቢል ከእግዚአብሔር ሥራ ይወገድ ነበር። የአስቸጋሪውን የሳንባላጥን ሴት ልጅ ያገባው የሊቀ ካህኑ የልጅ ልጅ ከሥራው መወገድ ብቻ ሳይሆን ከመላው እስራኤልም በቅፅበት እንዲወጣ ነበር የተደረገው። ነህምያም “አምላኬ ሆይ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንን ቃልኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው” ብሎ ፀለየ።” ኤለን ጂ. ኋይት ነቢያትና ነገስታት ከሚለው መጽሐፍ በእንግሊዝኛው ገፅ 673-674


የመወያያ ጥያቄዎች
1.ከላይ የተጠቀሰውን የኤለን ኋይት አነጋገር ያንብቡ። በክፍላችሁ ነህምያ ስላደረገው ነገር ምንም ልዩነት ሳያደርግ ሚስቶቻቸውን እጅግ የሚወዱ የሚመስሉት ሁሉ ላይ ስላደረገው ነገር ተነጋገሩ። ነህምያ ግትር እንደሆነና አንዳንዶቹን መተው ነበረበት ብላችሁ ታስባላችሁ? ለምን? ከዚሁ ሳንወጣ ቤተክርስትያን የስነ ምግባር እርምጃን ስትወስድ የእግዚአብሔርን መመሪያ ሳታቃልል በአፍቃሪነትና በመረዳት መንፈስ መተግበር የምትችለው እንዴት ነው?

2.አለመስረቅ፣ አለመመኘት ወይም አለመዋሸት ህግ አጥባቂነት እንዳልሆኑት ሁሉ ሰባተኛው ቀን ሰንበትን መጠበቅም ህግ አጥባቂነት እንዳልሆነ ብናውቅም ህጉን መጠበቅ በህግ ከመዳን ጋር አንድ እንዳይሆንብን መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? መስቀሉንና ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገውን ነገር ሁልጊዜ ማሰብ ህግን ጠብቆ ለመዳን በማሰብ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ የሚጠብቀን እንዴት ነው?

3.በተመሳሳይ ደግሞ ነህምያ እንደተጋፈጠው ቀስ በቀስ ከሚሆን መንሸራተትና ማመቻመች መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?