ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከመስከረም 17-23

1ኛ ትምህርት

Sep 28 - Oct 4
ዘሩባቤልና ዕዝራ፡- ታሪኩን ግልፅ ማድረግሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት፡ ኤር. 25፡11-12፣ዳን.9፡1-2፣ ዕዝራ 4፡1-7፣ ኢሳ.55፡8-9ንና ዕዝራ 7፡1-28ን ያንብቡ።


መታሰቢያ ጥቅስ “የፋርስ ንጉስ ቂሮስ እንዲህ ይላል፡- የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግስታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሰራለት ዘንድ አዝዞኛል።” ዕዝራ 1፡2

በ ኤርምያስ ትንቢቶች ውስጥ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ለ70 አመታት በባቢሎን ከተማረኩ በኋላ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ተናግሯል። ይህ መመለስ ተግባራዊ እንዲሆን ንጉስ ቂሮስ የእግዚአብሔር መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። በእግዚአብሔር የተቀባው ቂሮስ (ኢሳ. 45፡1) በ538 ዓ.ዓ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ቤተመቅደሱን እንዲገነቡ ትዕዛዝ አወጣ።

ኢየሩሳሌም “እንደገና ትገንባ” እንዲሁም የቤተመቅደሱ “መሰረቱ ይጣል” ያለው ግን ቂሮስ ሳይሆን እግዚአብሔር ነበር (ኢሳ. 44፡28)። ኢየሩሳሌም እንደገና እንደምትሰራ ዋስትናው እግዚአብሔር ሲሆን ቤተመቅደሱ እንዲገነባ ፍቃድ እንዲሰጥ የቂሮስን ልብ አነሳሳው።

ለጌታ ሥራ የእርሱ ሕዝብ መልካም ምላሽ ሲሰጡ ማየት የሚያበረታታ ነው። “ከዚያም እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሳሳው የይሁዳና የብንያም ቤተሰብ አለቆች እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ለመስራት ተዘጋጁ።” (ዕዝራ 1፡5) በዚህ ቦታ ለእግዚአብሔር ብርቱና ድንቅ ተግባራት ቀና ምላሽ የሰጡ ሰዎችን ምሳሌነት እናገኛለን። ብቃታችን የእግዚአብሔርን ማንነት፣ እርሱ ያደረገውንና ለህዝቡ ሲል በፍቅር ጣልቃ መግባቱን ከማወቅ የሚመጣ ነው። ለመስከረም 24 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

መስከረም 18
Sep 29

የምርኮኞቹ የመጀመሪያ መመለስ


ኤርሚያስ 25፡11-12ንና 29፡10ን እንዲሁም ዳንኤል 9፡1-2ን ያንብቡ። ምርኮኞቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለሱት መቼ ነበር? ይህ የየትኛው ትንቢት ፍፃሜ ነበር?በኤርሚያስ የተነገረው የ70 ዓመት ትንቢት ፍፃሜ እንዲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከምርኮ እንዲመለሱ እንዲፈቀድ እግዚአብሔር ቂሮስን አነሳሳው። ኤርሚያስ የይሁዳ ምድር ለ70 ዓመታት ባዶ እንደምትሆን ፅፎ ነበር (ይህ ከ606/605 እስከ 537/536 ዓ.ዓ ከክ.ል.በፊት ተከስቷል)። ከዚያ በኋላ ግን ምርኮኞቹ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በሩን እንደሚከፍት ተፅፏል። ዳንኤል የኤርምያስን ትንቢቶች ሲያጠና የመመለሻው ተስፋ ቃል የሚፈፀምበት ጊዜ እንደደረሰ አስተዋለ።

በዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ ዳንኤል 70ው ዓመታት እያለቁ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ለውጥ ባለመታየቱና አዲሱ የፋርስ አገዛዝ ወደ ስልጣን በመምጣቱ የተነሳ ሲጨነቅ እንመለከተዋለን። ምህረትን ለማግኘትና ተስፋውም እንዲፈፀም በእግዚአብሔር ፊት አለቀሰ። በዚያው ምዕራፍ ደግሞ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር እያየ እንደሆነና ወደፊት የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ፣ ፅድቅን ለማምጣት እና መስዋዕትን ለማስቀረት ለህዝቡ ስለሚሞተው ነፃ አውጪ በመንገር መተማመኛ ሰጠው (ዳን. 9፡24-27)። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር “ዳንኤል ሆይ፣ አትጨነቅ። እውነተኛው አዳኝ (ኢየሱስ) ስለሚመጣ እንደዚሁ ለእናንተም አሁን አዳኝ (ነፃ አውጪ) እልክላችኋለሁ።” እያለው ነበር።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ እግዚአብሔር የፋርሱን ንጉስ ቂሮስን ልብ በማነሳሳት ምርኮኞቹ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ አስተላለፈ። እግዚአብሔር ለቃሉ ሁልጊዜም ታማኝ አምላክ ነው (ዳንኤል 10 ላይ እግዚአብሔር የሕዝቡ ንብረት በሃገራቸው እንዲጠበቅ እንዴት ጣልቃ እንደገባ ይመልከቱ)። ዕዝራ ምዕራፍ 1 ንጉስ ቂሮስ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና የጌታን ቤት እንዲሰሩ ነፃ እንዲለቀቁ ያወጣውን አዋጅ ይዟል። አዋጁ ከክ.ል. በፊት ከ539-6 - 537 ዓ.ዓ ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። ቂሮስ የፈቀደላቸው እንዲመለሱ ብቻ ሳይሆን ስጦታን እንዲሁም ናቡከደነፆር ዘርፎ ያመጣቸውን የቤተመቅደሱን ዕቃዎች ይዘው እንዲመለሱም ጭምር ነበር። ይህ ክስተት ከብዙ ዓመታት በፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ሲወጡ የግብፅ ሰዎች ስጦታን እንዲሰጧቸው እግዚአብሔር ልባቸውን ያነሳሳበትን ታሪክ ያስታውሰናል።

የመጀመሪያው ተመላሽ ቡድን 50,000 ሰዎችን የያዘ ሲሆን ይህ ደግሞ ሴቶችንና ህፃናትን ያካተተ እንደነበር ይገመታል። ልክ እንደ ተፃፉት የተፈፀሙ ከሌሎች ታሪካዊ ትንቢቶች የትኞቹን ያስታውሳሉ? ከነርሱ ተነስተን እግዚአብሔር የወደፊቱን እንደሚያውቅና እርሱ ለኛ የገባውን ቃል እንደሚፈፅምልን መተማመን የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 19
Sep 30

ነገስታቱና ታሪኮቹ በአጭሩ


የመጀመሪያዎቹ ተመላሾች የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ መልሶ የመገንባት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። በቤተመቅደሱ ግንባታ ላይ ስለተጋረጡት ፈተናዎች ቆየት ብለን በሌሎቹ ትምህርቶች እንመለከታለን። አሁን ግን ቤተመቅደሱ ለረዥም ጊዜ ሲገነባ እንዲሁም ኢየሩሳሌም እንደገና እየተገነባች በነበረችበት ወቅት ስለተቀያየሩት የፋርስ ነገስታት እንመለከታለን።

ከዕዝራና ነህምያ ታሪኮች ጀርባ ያሉትን ታሪኮች ማወቃችን ለመልዕክቶቻቸው ጥልቅ መረዳት እንዲኖረን ያስችለናል። ዕዝራ 4፡1-7ን ያንብቡ። በቤተመቅደሱ ግንባታ ላይ ተቃውሞ እየደረሰ በነበረበት ወቅት እየገዙ የነበሩት ነገስታት እነማን ነበሩ?ከዕዝራና ነህምያ መጽሐፍት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የፋርስ ነገስታት ዝርዝር እንደሚከተለው ነው። የፋርስን መንግስት ካቋቋመውና በክ.ል.በፊት በ539 ዓ.ዓ ባቢሎንን ከወረረው ከቂሮስ ይጀምራል። ቂሮስ 2ኛ “ታላቁ” (ከክ.ል በፊት 559-530ዓ.ዓ) ካምቢሰስ 2ኛ (ከክ.ል በፊት 530-522 ዓ.ዓ) ዳርዮስ 1ኛ (ከክ.ል በፊት 522-486 ዓ.ዓ) ጠረክሲስ 1ኛ (ከክ.ል በፊት 486-465 ዓ.ዓ) አርጤክስስ 1ኛ (ከክ.ል በፊት 465-424 ዓ.ዓ) እነዚህን መጽሐፍት ስናጠና በዕዝራ መጽሐፍ ውስጥ እነዚህ ነገስታት በተቀመጡበት ቅደም ተከተል አለመቀመጣቸውን ማስተዋል ተገቢ ነው። ለምሳሌ ዕዝራ 4፡6-24 የተፃፈው ከምዕራፍ 5 በፊት ነው (ይህም በቤተመቅደሱ ግንባታ ላይ የተደረገውን የተቃውሞ ታሪክ ይቀጥላል)። ስለዚህ በዕዝራ ምዕራፍ 4 ላይ ለንጉስ ጠረክሲስ 1ኛና ለአርጤክስስ 1ኛ የተፃፉት ደብዳቤዎች በምዕራፍ 5 እና 6 ከተፈጠሩት ክስተቶች በኋላ የተፃፉ ናቸው።

ይህ የቅደም ተከተል መዛነፍ አንባቢዎችን ግራ ያጋባል፤ በነዚህ መጽሐፎች ዙሪያ ለዘመናት ሰዎች ለተፈጠሩባቸው ግራ መጋባቶች ይህ መዛነፍ እንደ ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው። በዚህ ሶስት ወር ትምህርታችንን ስንቀጥል ቅደም ተከተላቸውን ማወቅ የዕዝራና የነህምያ መልዕክቶችን በተሻለ ለመረዳት ይጠቅመናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለእርስዎ ግራ ያጋቡ ነገሮችን ምን ያክል ጊዜ አግኝተዋል? የማይገቡን ነገሮች ሲያጋጥሙን እንኳን በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይ መተማመን የምንችለው እንዴት ነው? ያንን ማድረግ የሚጠቅመን ለምንድነው? (ኢሳ. 55፡8-9ን ያንብቡ)።

መስከረም 20
Oct 01

የምርኮኞቹ ሁለተኛ መመለስ


በዕዝራ 7፡1-10ና 8፡1-14 ላይ ንጉስ አርጤክስስ 1ኛ ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ ሲፈቅድ የሚያሳዩ ሲሆኑ ለመመለስ የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲወስድ ተፈቀደለት (ይህ በ457 ዓ.ዓ ተከሰተ)። በንጉሱና በዕዝራ መካከል ስለነበረው ግንኙነት ወይም ዕዝራ በፍርድ ቤት ስለ መስራቱ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም።

ዕዝራ ምዕራፍ 8 የተመለሱት ቤተሰቦችን መሪዎች ከካህናቱ ጀምሮ የነገስታት ዘር ካለባቸው ይቀጥልና በመጨረሻ በሰፊው የአይሁድ ህዝብ ይጨርሳል። የአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ማስታወሻ በሚመስል መልኩ አስራ ሁለት ቤተሰቦች ተጠቅሰዋል። ምዕራፉ 1500 አባ-ወራዎችን የጠቀሰ ሲሆን ሴቶችና ህፃናት ሲጨመሩ ከ5000 እስከ 6000 ይደርሳሉ ተብሎ ይገመታል። ይህ ደግሞ በመጀመሪያ ከዘሩባቤልና ኢያሱ ጋር ከተመለሱት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ያነሰ ቁጥር ነው። ዕዝራ 7፡1-10ን ያንብቡ። ስለ ዕዝራ ምን ይነግረናል?ዕዝራ በክህነት ማዕረግ የህግ መምህር ነበር። እንደ ካህን የእስራኤል ሕዝብ የመጀመሪያው ካህን የነበረውና የሙሴ ወንድም ከነበረው አሮን ዘር ነው። በዕዝራ መጽሐፍና በአይሁድ ትውፊቶች ውስጥ ስለ ዕዝራ ከተፃፈው በመነሳት የዕዝራ ስም ዛሬም ድረስ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ነው። ዕዝራ በንጉስ አርጤክስስ ሸንጎ እንደ ፀሐፊነት ያገለግል ወይም አያገልግል ባይታወቅም ዕዝራ እንደ ፀሐፊ መገለፁ ቀደም ብሎ የነበረው ኃላፊነት ወይም ይሁዳ ከደረሰ በኋላ መወጣት (ማውጣት) የጀመረው ኃላፊነት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ንጉሱ ዕዝራን እንዲህ ወደ ይሁዳ የሚመለሱትን እንዲመራ መምረጡ ከዚያ ቀደም ብሎ ከንጉሱ ጋር በቅርበት ሰርቶ እንደነበር ፍንጭ ይሰጣል።

በዕዝራ 7፡6ና 10 ውስጥ ዕዝራ “ችሎታ ያለው” እና “እራሱን የሰጠ” ፀሐፊ ወይም መምህር ተብሎ ተገልጿል። “ችሎታ ያለው” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ በንግግርና በማስተዋል የቀለጠፈ የሚል አንድምታ ያለው ነው። ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በተመለከተ ባለው ዕውቀትና መረዳት እጅግ የታወቀ ባለ ፈጣን አእምሮ ነበር። በተጨማሪም ንጉሱ እስራኤላውያኑን ወደ ይሁዳ መርቶ እንዲወስድ ዕዝራን መምረጡ ስለ ዕዝራ ጥንካሬና የመምራት አቅም ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው።

ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ሕግ” በመፈለግ ልቡን ያዘጋጀ ነበር የሚለውን ልብ ይበሉ (ዕዝራ 7፡10)። ይህን በእኛ ሕይወት እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን?

መስከረም 21
Oct 02

የአርጤክስስ ትዕዛዝ


ዕዝራ 7፡11-28ን ያንብቡ። የንጉሱ ትዕዛዝ ምን ምን ነገሮችን ይዞ ነበር? እነዚህ መመሪያዎች ለእስራኤል ሕዝብ የሚጠቅሙት እንዴት ነበር?የአርጤክስስ ትዕዛዝ የቂሮስን የመጀመሪያ ትዕዛዝ ይመስላል። ንጉሱ ፈቃደኛ የሆኑት ሁሉ በተለይም ከካህናት የዘር ግንድ የሆኑት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲጓዙ አዟል። ምንም እንኳን የሙራሹ ታሪካዊ ሰነድ እንደዘገበው ብዙዎቹ አይሁዶች በፋርስ ቢቀሩም (በአስቴር ታሪክ ውስጥ እንደተገለፀው) በቅድመ አያቶቻቸው ሃገር አዲስ ህይወት ለመጀመር አሰፍስፈው ሲጠብቁ የነበሩ ነበሩ። ንጉሱ በአብዛኛው በኤፍራጥስ አካባቢ ላሉት ገንዘብ ያዦች ትዕዛዝ ሰጠ። ገንዘብ ያዦቹ ከተማይቱን ለማደስና “የጌታን ቤት ለማስዋብ” (ዕዝራ 7፡27) የሚያስፈልገውን ሁሉ ያዘጋጃሉ(ያሟላሉ)።

እንደዚሁም ንጉሱ የፍርድ ስርዓትን በማቋቋም የእግዚአብሔርና የሀገሪቱ ህግ እንዲከበር እንዲያደርግ ለዕዝራ ኃላፊነትን ሰጠው። ይህ ትዕዛዝ የሚፈጥረው ስርአትና አደረጃጀት በማንኛውም ማህበረሰብ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ንጉሱ ዕዝራና እስራኤላውያን እናት ሀገራቸውን እንዲያድሱ ሁኔታዎችን ቀላል አደረገላቸው።

ንጉሱ ከተማይቱ እንደገና እንድትሰራና ቤተመቅደሱ እንዲገነባ መወሰኑ በዕዝራ አምላክ ማመኑን ያረጋግጥ ይሆን? አርጤክስስ እግዚአብሔርን “መኖሪያው በኢየሩሳሌም የሆነው የእስራኤል አምላክ” (ዕዝራ 7፡15) ብሎ ነው የጠራው። ንጉሱ የእስራኤልን አምላክ የገለፀበት መንገድ የሚያሳየው በስጦታዎች እንደሚደሰት እንደ አንድ ሌላ አምላክ እንደሚያየው ነው። ይህ የዚያ አካባቢ አምላክ በእርሱና በልጆቹ ላይ እንዲቆጣ አልፈለገም (ዕዝ. 7፡23)።

በተጨማሪም በ457 ዓ.ዓ ግብፃውያን በፋርስ ላይ ያመፁበት አመት መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል፤ ስለዚህ እነዚህ የንጉሱ ተግባራት በአይሁድ ሕዝብ ዘንድ አመኔታን ለማግኘት የተደረጉ ይመስላሉ። እንዳለመታደል ሆኖ ንጉሱ ከዕዝራና ነህምያ ጋር ቅርርብ ቢኖረውም ያ ግን በእግዚአብሔር እንዲያምን አላደረገውም። ቢያንስ በጥቅሶቹ ውስጥ ከአማኞቹ አንዱ ስለመሆኑ የሚገልፅ ነገር የለም። ይህም ማለት እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈፀም ያላመኑ (ያልተለወጡ) ሰዎችንም ጭምር ሊጠቀም ይችላል ማለት ነው። በዚህ ቦታ እንዳየነው በብዙ ስቃይና ህመም ውስጥ እንኳን እግዚአብሔር በአለም ላይ ሉአላዊ በመሆኑ ላይ መተማመን የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 22
Oct 03

የትምህርት ጥቅም


ዕዝራ 7፡6 እና 10ን ያንብቡ። እዘኒህ ጥቅሶች ስለ ትክክለኛው የሃይማኖት ትምህርት ጥቅም ምን ይነግሩናል?ዕዝራ ሙሉ ልቡን ለእግዚአብሔር መስጠቱና ቃሉን ለማጥናት ለመተግበርና ለማስተማር ቁርጥ ውሳኔን ማድረጉ በእስራኤል ከፍ ላለ አገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን አደረገው (ዕዝራ 7፡6፣10)። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል የእግዚአብሔርን ህግ ለማጥናት፣ ለመተግበርና ለማስተማር ራሱን እንደሰጠ ይናገራል።

በዚህ ዙሪያ ኤለን ኋይት ጠቃሚ መረጃን ትሰጣለች ‹‹ከአሮን የዘር ግንድ የመጣው ዕዝራ የክህነት ትምህርትን ወስዷል። በተጨማሪም በሜዶና ፋርስ የሚገኙ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቆጣሪዎችና የጠቢባን ፅሁፎችን አንብቧል። ሆኖም በነበረበት መንፈሳዊ አቋም አልረካም። ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ በሙሉ በህብረት ለመሆንና መለኮታዊውን ኃሳብ ለመፈፀም የሚያስችለውን ጥበብ ለማግኘት ይናፍቅ ነበር።

ስለዚህ “የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈለግ ልቡን አዘጋጀ።” (ዕዝራ 7፡10)። ይህም በነቢያቱና በነገስታቱ እንደተፃፈው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ታሪክ በማጥናት እንዲጠመድ አደረገው። የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊና ሥነ-ቃላዊ ይዘት ያላቸውን መጽሐፍት በመመርመር እግዚአብሔር ኢየሩሳሌም እንድትጠፋና ህዝቦቿም በአረማዊያን ምድር እንዲማረኩ ለምን እንደ ፈቀደ ምክንያቱን ለማወቅ ሞከረ።” Prophets and kings, P.608 “ዕዝራ ቅዱሳት መጽሐፍቱን በሚያባዛበትና ዕድሜውን በሙሉ መጽሐፍቱ ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደርግ በነበረው ጥረት ሰዎች ቅዱሳት መጽሐፍቱን የማጥናት ፍላጎታቸው እንዲነሳሳ ለማድረግ በቀጣይነት መስራቱ ተፅፏል። ያገኛቸውን የህጉን ቅጂዎች ሁሉ ሰብስቦ እንደገና እንዲፃፉና እንዲሰራጩ አደረገ። ንፁሁ ቃል ተባዝቶ በሰዎች እጅ ሲገባ በገንዘብ የማይለካን እውቀት ሰጠ።” ገፅ. 609

ዕዝራ የአረማውያኑን አደራረግ ቢያጠናም ትክክል እንዳልነበሩ አውቋል። ስለዚህ እውነቱን የእውነት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃልና “ከእግዚአብሔር ሕግ” ለማወቅ መረመረ። በአለማዊ ዩኒቨርሲቲዎች ከተማራቸው ብዙዎቹን ነገሮች ከአእምሮው ማውጣት ነበረበት፤ ምክንያቱም ስህተት ስለነበሩ ነው። ደግሞስ “የአስማተኞቹና የኮከብ ቆጣሪዎቹ” ጽሑፎች ምን ያክል ይጠቅሙት ነበር? እኛስ ዛሬ ከዓለም ከተማርናቸው ትምህርቶች አእምሯችንን ማላቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 23
Oct 04


ተጨማሪ ሀሳብ


“ካህኑና ፀሐፊው ዕዝራ ገፅ.607-617 የሚለውን “ነቢያትና ነገስታት” ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ ያንብቡ። የዕዝራ ትጋት ላይ ያሰላስሉ፡- “ሰዎችን ስለ ሰማያዊ ህጎች በማስተማር ዕዝራ የእግዚአብሔር አፍ ሆነ። በቀሩት እድሜዎቹ በሜዶንና ፋርስ ንጉስ ሸንጎ ቢሆን ወይም በኢሩሳሌም ዋና ስራው ማስተማር ሆነ። ያወቃቸውን እውነቶች ለሌሎች ሲያካፍል የመስራት አቅሙ ጨመረ። የሃይማኖትና የትጋት ሰው ሆነ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ማወቅ በዕለት ተዕለት ህይወታችን የማስከበር ኃይል እንዳለው ለዓለም የእግዚአብሔር ምስክር ነበር።” Ellen G.White, Prophets and kings, P.609

“ዛሬ ሊከናወን በሚገባው የተሐድሶ ሥራ ውስጥ በኃጢአት ጉዳይ የማይደራደሩና እግዚአብሔርን ከማስከበር ወደኋላ የማይሉ እንደ ዕዝራና ነህምያ ያሉ ሰዎች ያስፈልጋሉ። የሥራው ሸክም ያረፈባቸው ሰዎች ክፋት ሲሠራ እያዩ አርፈው አይቀመጡም፤ ክፉውንም በውሸት ልግስና ካባ አይሸፍኑም። እግዚአብሔር የሰው ተከታይ እንዳልሆነና ለጥቂቶች የሚመጣው ስቃይ ለብዙዎች ደግሞ ምህረትን እንደሚያመጣ ያስታውሳሉ። በተጨማሪም ክፉውን በሚገስፀው ውስጥ የክርስቶስ መንፈስ እንደሚገለጥም ያስታውሳሉ።” ገፅ 675


የመወያያ ጥያቄዎች
1.አዎን ከጌታ ብዙ የተስፋ ቃሎችን ተቀብለን ይሆናል። በተመሳሳይ ደግሞ እግዚአብሔር አስገድዶን ምንም ነገር አያደርግም። እርሱ ለኛ የሰጠው የተስፋ ቃል እንዳይፈፀም በህይወታችን ምን አይነት ምርጫዎችን ልንመርጥ እንችላለን?

2.የዳንኤል 9፡1-23ን ፀሎት ያንብቡ። በዚህ ቦታ በእርስዎ ልምምድ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምን መርሆዎችን እናገኛለን? ማለትም ዳንኤል ምን እያደረገ ነበር፣ አመለካከቱ ምን ይመስል ነበር፣ እየጠየቀ የነበረውስ ምን ነበር? በዛ ቦታ ዛሬ በኛ ህይወት ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምን ሌላ ነገር እንመለከታለን?

3.በሐሙስ ጥናታችን ኤለን ኋይት የእግዚአብሔር ቃል በዕዝራ ህይወት ውስጥ ምን ያክል ማዕከል እንደነበረና እርሱም ቃሉን ለሌሎች ለማዳረስ ምን ያክል እንደተጋ የፃፈችውን አንብበናል።የእግዚአብሔር ቃል በህይወታችንና በቤተክርስትያናችን ሊኖረው ስለሚገባው ቦታ ምን ትምህርት እናገኛለን?