ዕዝራ እና ነህምያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2019

የዕዝራና የነህምያ ወንጌል

መግቢያመደበኛ እትምይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

አዘጋጅ፡ ጂሪ ሞስካላ (Thd,phd)

ትርጉም: በበረከት እና ብሩክ ፈለቀ

በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመየዕዝራና የነህምያ ወንጌል

ዕዝራና ነህምያ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲበለፅግ የእግዚአብሔርም ስም በዓለም ሁሉ የታወቀና የተከበረ እንዲሆን ከልብ የተመኙ፣ በመንፈስ የተመሩ፣ በቃላቸው የሚገኙና እግዚአብሔርን ያስቀደሙ መሪዎች ነበሩ። ህይወታቸው እግዚአብሔር ለእርሱ በተሰጡና ታማኝ አገልጋይ መሪዎቹ ውስጥ ሊሰራ የሚችለውን ያሳየ ነው። ወደ ኃጢአት ባዘነበለ ተፈጥሯችን፣ በለመድናቸው ልማዶችና በወረስናቸው እንከኖች ምክንያት እውነተኛና ዘላቂ ለውጦችን ማምጣት የምንችለው የሚለውጠውን የእግዚአብሔር ቃል በማጥናትና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ብቻ ነው። አማኞች “በኃይልና በጉልበት ሳይሆን በመንፈሱ” (ዘካርያስ 4፡6) እንዲሁም ተስፋውን በእምነት በመጠማጠም (ዕንባቆም 2፡4) የሚኖሩ ሲሆኑ ህይወት ያለው መንፈሳዊ ህይወት ሊኖራቸው ይችላል።

የዚህ ሩብ ዓመት ትምህርት የተመሰቃቀለ ህይወትን ያስቃኘናል። መልካም ነገር ለማድረግ ስንነሳ ወዲያው እንቅፋቶች ይመጡና ተቃውሞ ይነሳል። ወዳጆቻችን እንኳን በግልፅም ይሁን በሚስጥር ሊቃወሙንና በሂደትም ጠላቶቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። በመልካሙ ላይ የሚመጡ እንቅፋቶችና ተቃውሞዎች ሰይጣን ህያው መሆኑንና ኃጢአትም እውነት መሆኑን ያስረዳሉ። ሰይጣን ከኛ ይበልጥ ብርቱ ስለሆነ በሰውኛ (በራሳችን ኃይል) ልንዋጋው አንችልም። ድልን ሊያጎናፅፈን፣ አስተሳሰባችንን ሊቀይርና ሚዛናዊ ህይወትን መኖር የሚያስችለን እግዚአብሔር ብቻ ነው። በህይወታችን ያሉ ተስፋ መቁረጦች ለለውጥ የተከፈቱ ዕድሎች ናቸው። ተስፋ መቁረጦች በዋናዎቹ ላይ ትኩረት እንድናደርግ በማስቻል በእግዚአብሔር ኃይል እያንዳንዱን ችግር በድል ስናልፍ መንፈሳዊ ዕድገታችንን ያፋጥኑልናል።

የዕዝራም ሆነ የነህምያ መጽሐፍ መልካም አጨራረስ የላቸውም። ኃጢአት በቀላሉና በፍጥነት የሚሰራጭ ክፉ ነው። ትልቁ ተግዳሮት ከውጭ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተገለጠውን የርሱን ፈቃድ ላለመከተል ሲያፈገፍጉ ነው። ለጌታ ታማኝ መሆንና እርሱን በመከተል መፅናት ወይም አለመፅናት የእግዚአብሔር ቤተክርስትያን የምትፈተነው ፈተና ነው። ዕዝራ በትክክል እንደተረዳው ብቸኛው ኃይል የሚገኘው ቃሉን በትጋት በመመርመር፣ በማስተዋልና በመተግበር ነው። የሰባው ሱባኤና የ2300ው ምሽትና ጠዋት ትንቢቶች የሚጀምሩበት ጊዜው እውን ይሆን ዘንድ (በ457 ዓ.ዓ የጀመረው) ዕዝራ ከሌሎች እስራኤላውያን ጋራ በመሆን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ጥበቃ ለማድረግ እንዲሁም ለቤተመቅደሱ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ንጉስ አርጤክስስ 1ኛን ተጠቀመው(ዕዝራ 7፡11-28)። በነዚህ በሁለት መጽሐፎች የተቀመጡት ነገሮች ሁሉም በታሪካዊ ቅደም ተከተላቸው አለመቀመጣቸውን እንዲሁም አንዳንዶቹ ከይዘታቸው አንፃር መቀመጣቸውን ልብ እንበል።

ወደፊት እንደምንመለከተው የዕዝራና የነህምያ ግድድሮሽ ቤተመቅደሱን መልሶ መገንባት ሳይሆን (ዕዝራ ከመምጣቱ ከ50 ዓመታት በፊት በ515 ተጠናቆ ነበር) የኢየሩሳሌም ከተማን መገንባት አስተዳደሯን ስርዓት ማስያዝና ራሷን በራሷ ማስተዳደር እንድትችል ማድረግ ነበር። እነዚህ ሁሉ ደግሞ ለመሲሁ መምጣት ቀስ በቀስ መንገድ የሚጠርጉ ነበሩ። በዚህ ሩብ ዓመት የእግዚአብሔርን ቃል ስናጠና እግዚአብሔር ልባችንን ነክቶ፣ አስተሳሰባችንን በመለወጥ በየቀኑ በታማኝነት እርሱን እንድንከተለው በማስቻል ይባርከን!

ጂሪ ሞስካላ (Thd,phd) በአንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የስነ መለኮት የትምህርት ክፍል ዲንና የብሉይ ኪዳን ጥናት ፕሮፌሰር ናቸው። ይህን የትምህርት ክፍል የተቀላቀሉት በ1999 እ.ኤ.አ ሲሆን ከዚያ በፊት በቼክ ሪፐብሊክ በተለያዩ ኃላፊነቶች (ፓስተር፣ አስተዳዳሪ፣ አስተማሪና ርዕስ መምህር በመሆን) አገልግለዋል። የተለያዩ የሥነ መለኮት ጥናት ማህበሮች ውስጥ አባል ሲሆኑ በቼክና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብዙ ፅሁፎችንና መጽሐፎችን አበርክተዋል። በተጨማሪም በዮርዳኖስ ቴል ጃሉል የሥነ ምድር ጥናት ሥራዎች ላይም ተሳትፈዋል።

4ኛ ሩብ ዓመት

ከመስከረም 17 - ታህሳስ 17, 2012 ዓ.ም.